Saturday, 27 June 2015 09:33

ባይተዋርነት የላሳቸው የባይተዋርነት ልቦለዶች

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(1 Vote)

ደጃዝማች ግርማቸው ተክለሀዋርያት (ከደጃዝማችነቱም በላይ ደራሲ ናቸው) የግብርና ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ነው፡፡ ደጋግመው የሚያዩት አንድ ሰራተኛ አለ፡፡ ቢሮዋቸው ሆነው በመስኮት ያዩታል፣ ከሥራ ሲወጡ ያዩታል፣ ወደ ሥራ ሲገቡ ያዩታል፡፡ ሰው ሁሉ ቢሮው በተከተተበት ሰዓት ሰማይ - ጠቀስ ቁመቱን ይዞ ግቢው ውስጥ ይንጎራደዳል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የግብርና ሰራተኛ ሁሉ የሚፈራውን የቢሮዋቸውን አንፃር እሱ ደፍሮ ይንጎራደድበታል፡፡
“ሥራ የለውም?” በማለት ልቦናቸው ውስጥ ያንጎራድዱት ጀመር፡፡ አውጥተው አልጠየቁም። ብቻ በስራ መካከል “አለ? የለም?” በሚል ቀና ብለው በአይናቸው ይፈልጉታል፡፡ ከእርዝመትና ከቅጥነት ብዛት ተቆልምሞ ያዩታል፡፡
“ይሄን ጀልጋጋ ምን ፈረደብኝ” ሳይሉ አልቀሩም።
አንድ ቀን ይሄ ሰው ቢሮአቸውን ከፍቶ ገባ፡፡ እንደተቆለመመ ሲያዩት ገረማቸው፡፡
“ምን ነበር?” አሉት ዝም ስላለ፡፡
“ክቡር ሆይ፣ የፃፍኩት መፅሐፍ አለ”
ደጃዝማቹ ገረማቸው፡፡ ትክ ብለው አዩትና፡-
“ኧከከከከ … ባለሙያ ኖርሃልና-- ግሩም! ግሩም!” አሉ፡፡
“ታዲያ ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?”
“ለማሳተሚያ ገንዘብ አጥቼ ተቀምጧል፡፡”
“እና …”
“ማሳተሚያውን እርስዎ …”
“ቆይ ቆይ እስቲ፡፡ መጀመሪያ ላንብበውና የሚቀጥለው በሚቀጥለው ይሆናል፡፡”
አመጣላቸው …
… አነበቡት፡፡ ግራ ገባቸው፡፡ መያዣ መጨበጫ የለውም፡፡ ከአንዱ ወዳንዱ ይዘላል፡፡ ገፀ ባህሪው ተለዋዋጭ ነው፡፡ አንድ ወር ሙሉ ከታገሉት በኋላ ደራሲውን አስጠሩት፡፡ ተቆልምሞ ፊታቸው ቆመ፡፡
“ለመሆኑ የመፅሐፍህን ርዕስ ምን አልከው?” ሲሉ ጠየቁት፡፡
 እየተኩራራ፡- “መቼ ነው የምሞተው?” አላቸው፡፡
ደጃዝማች ግልፍ አላቸው፡-
“አሁን ባንተ ቤት እየኖርክ ነው፣ ጀልጋጋ! ውጣ ከዚህ፣ ጥፋ ከፉቴ!!” ብለው አባረሩት፡፡
አንዳንዴ …. እንደዛሬ ሁሉ በምናብ ቀበጥ ያደረገኝ ቀን ይሄንን ጀልጋጋ በሐሳቤ አመናትላለሁ። ምን ፅፎ ይሆን? በእርግጥ የፃፈው አይረባም ነበር? ወይስ ደጃዝማቹ ተለምዷዊውን የአፃፃፍ ስልት ሙጥኝ በማለታቸው ሳይረዱት ቀሩ? ደግሞም’ኮ “ርዕሱ” ወጣ ያለ ነው፡፡ “መቼ ነው የምሞተው?” ከግለሰብ መብሰክሰኪያነት አልፎ ለመፅሐፍ ርዕስ እና ጭብጥ  ይሆናል? ሲሆንስ እንዴት ነው? …
… የመፅሐፉ ርዕስ ብቻ ሳይሆን የሰውየው ፀባይም ያልተለመደ ነው፡፡ ህግና ደንብ የሚገዛው አይመስልም፤ ሲፈልግ የሚሰራ ካልፈለገ የሚተው አይነት ነው፡፡ ከቅርብ አለቃው እስከ ሚኒስትሩ ድረስ ከእነመኖራቸው መርሳት እንዴት ተቻለው? ግሳፄያቸው ሳያስበረግገው፣ ማስጠንቀቂያቸው ሳያባንነው እንዴት ቀረ? መስሪያ ቤት የሚያሳየው ጸባዩ የክት ነው? ኑሮውስ እንዴት ነው? ቤት ንብረቱ? ወዳጅ ጎረቤቱ? …
…አንድ ቆጭባራ ሰው የሚሰጠንን ቆጭባራ (Absurd) ሥራ ያጣን ሆኖ ይሰማኛል፡፡ በተለይ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወዲህ የመጡ ደራሲያን ሥራቸው “ግርንቢጥ” የሆነው ከህይወታቸው በመቀዳቱ እንደሆነ ተረጋግጧል፡፡ ኢዩጂን ኢኦኔስኮ፣ ሳሙኤል ቤኬት፣ ፍራንዝ ካፍካ፣ አልበርት ካሙ … ከቆጭባራ ህይወታቸው ቆጭባራ ሥራ ያፈለቁ ቆጭባራ ደራሲዎች ናቸው፡፡
ኢዩጂን ኢኦኔስኮ “Rhinoceros” (አውራሪስ) የተሰኘ የሙሉ ሰዓት ድራማ አለው፡፡ በዚህ ድራማ ውስጥ ሰዎች ሁሉ ወደ አውራሪስነት ተለውጠው አንድ ቤተሰብ ብቻ ሰው እንደሆነ ይቀራል፡፡ የድራማው ግጭት እንደ ብዙሃኑ አውራሪስ እንሁን፣ አንሁን ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ኢኦኔስኮ የብዙሃን ተፅዕኖ እንዲያርፍበት የማይፈቅድ፣ ብቻውን “ሰው” ሆኖ ለመቀጠል የወሰነ አይነት ሰው ነው፡፡ አኗኗሩ ፍፁም ብቸኝነት የተጠናወተው ከመሆኑ የተነሣ እንደ ድራማው “ሰው ሁሉ አውራሪስ ሆኖ አልቋል ብሎ የደመደመ ይመስላል” ይሉታል፡፡
የእኛ “ጀልጋጋ” እንዲህ የወሰነ ነበር ይሆን?
ሌላው “ቆጭባራ” ደራሲ ሳሙኤል ቤኬት ነው። ከጓደኞቹ  ጋር ሲኒማ አይቶ ሲመለስ ስለሲኒማው እያወራና እየተከራከረ ነበር፡፡ አንድ እንግዳ የሆነ ሰው ተቀላቅሏቸው ክርክሩን አሳብሮ ገባ፡፡ ከዚያም ጩቤ አውጥቶ ቤኬትን ወጋው፡፡ እሞት አፋፍ ደርሶ ከተመለሰ በኋላ ያንን እንግዳ ሰው የታሰረበት ድረስ ሄዶ ጠየቀው። “ለምን ወጋኸኝ?”
“ለምን እንደወጋሁህ እኔም አላውቀው” ሲል መለሰለት፡፡
ቤኬት ይሄን መነሻ አድርጎ “ቆጭባራ” ህይወትና “ቆጭባራ” ድርሰት ጀመረ፡፡ የመጀመሪያና ብቸኛ ልቦለዱ “Molloy” በዋና ገፀባህሪው ሥም የተሰየመ ነው፡፡ ሞሎይ ቁርጥ ቤኬትን ነው የሚሉ ሀያሲያን አሉ፡፡ አንዳንዶቹ አጋማሹን ከራሱ ቀድቷል ይላሉ። Edith Kern `Moran – Molloy the hero as Author” በሚል ርዕስ ዋናው ገፀባህርይ እና ደራሲው የሚመሳሰሉበትን ነጥብ ተንትና አስረድታለች፡፡
የእኛስ “ጀልጋጋ” ጨው አልባ ህይወቱን ስለቀዳ ይሆን ለደጃዝማች ግርማቸው አልጣፍጥ ያላቸው?
ሌላኛው ፈረንሳዊ ደራሲ አልበርት ካሙ እንዲሁ ግራ የሆነ ጠባይ ነበረው፡፡ ዘሩ ከፈለቀበት ፈረንሳይ ይልቅ ለተወለደባት አልጄሪያ በማድላት ከቅኝ ግዛትነት እንድትላቀቅ ይታገል ነበር፡፡ በዚህም ተከስሶ እስከመታሰር ደርሷል፡፡
ካሙ ይሄ ገጠመኙ ከውስጡ ሳይጠፋ እስከ ህይወቴ ፍፃሜ ቆይቷል፡፡ ደጋግሞም በተለያዩ ሥራዎቹ ውስጥ አንፀባርቆታል። በተለይ “The Stranger” እና “Outsider” ተብሎ ከፈረንሳይኛ ወደ እንግሊዘኛ በተመለሰ ስራው ላይ በሽሙጥ አንፀባርቆታል፡፡ ዋና ገፀባህሪው ሜርሳልት ስለአንድ ጎረቤቱ የሚተርክበት ቦታ አለ፡፡ ያ ጎረቤቱ ለስምንት አመታት ያልተለየው ውሻ አለው፡፡ እንግዲህ የፈረንሳይንና የአልጄሪያን ግንኙነት የሚመሰጥረው በዚህ ሽማግሌና ውሻው ግንኙነት ነው። ሚፍታ ዘለቀ ከተረጎመው ከዚህ ልቦለድ (“ባይተዋሩ”) ላይ ያንን ቦታ እንጥቀስ፡-
“…ሽማግሌው ጎረቤቱ ሳልማኖን አገኘሁት። ከውሻው ጋር ነው፡፡ ለስምንት አመታት አልተነጣጠሉም። የስፓኔል ዝርያ የሆነው አጫጭር እግሮች ያሉት ውሻው የቆዳ በሽታ አለበት፡፡ ፀጉሮቹን እንዳለ አርግፎ ቆዳውን በቡኒ የደም ቋጠሮ የሸፈነ ለምፅ የሚመስል ማንጌ የሚባል በሽታ መሰለኝ፡፡ በአንዲ ትንሽ ክፍል ለረጅም ጊዜ አብረው በመኖራቸው አንደኛው ሌላኛውን መምሰል ጀምሯል። ሽማግሌው ሳልማኖ ፊቱ ላይ ቀያይ የደም ቋጠሮዎች ሲኖሩት የተጥመለመለና ብን ያለ ቢጫ ፀጉር አለው፡፡ ውሻው ልክ እንደጌታው፣ አንገትና እግሮቹን ወደፊት ያሰገገና ለምቦጩን የጣለ ነው፡፡ ከአንድ ዝርያ የተገኙ ቢመስሉም አንዱ ሌላኛውን አምርሮ ይጠላል፡፡ በየዕለቱ ሁለት ጊዜ ቀን አምስትና ምሽት አስራ አንድ ሰዓት ንፋስ ለመቀበል ይወጣሉ፤ በስምንት ዓመት ውስጥ አንድም ቀን መንገድ ቀይረው አያውቁም። በሩደሊዮን አውራ ጎዳና ውሻው የታሰረበትን ገመድ እየመነጨቀ፣ ሳልማኖ ደግሞ ወደራሱ እየጎተተ ልታዩዋቸው ትችላላችሁ፡፡ እንዲህ ሲሆን ሽማግሌው ሲያንባርቅና ውሻውን ሲደበድበው ይታያል፡፡ ይሄኔ ውሻው እየለገመ ወደኋላ ይቀራል፡፡ ጎታች ሽማግሌው ይሆናል፡፡ ውሻው እንደገና ረስቶት ጎተታና ምንጨቃውን ሲጀምር ማንባረቁና ዱላው ይከተላል፡፡ ይህ ሲሆን እግረኛው መንገድ ላይ ይቆሙና ውሻው በፍርሃት፣ ሽማግሌው፣ በጥላቻ ይፋጠጣሉ፡፡ ሁሌም እንዲህ ነው የሚኖሩት። ውሻው መሽናት ሲፈልግ ሽማግሌው በቂ ጊዜ ሳይሰጠው ስለሚጎትተው ሽንቱን መንገድ ላይ እያንጠባጠበ ያልፋል …”
(ባይተዋሩ ከገፅ 27-28)
  ፈረንሳይና አልጄሪያ ለአልበርት ካሙ እንደ ሽማግሌውና ውሻው ናቸው፡፡ እየተጓተቱ፤ አልጄሪያ ለመመንጨቅ እየሞከረች፣ ፈረንሳይ እየቀጣችና እየተቆጣች አብረው አርጅተዋል፡፡ የሽማግሌውና የውሻው መጨረሻ የሁለቱ አገሮች መዳረሻ እንደሆነ ካሙ ያምናል፡፡ ውሻው ይጠፋል፣ ሽማግሌው ይናውዛል፡፡ ፀቡና መጓተቱ ሱስ ሆኖበት፣ ሌሊት ሌሎች ውሾ በጮሁ ቁጥር እየባተተ ቀሪ ህይወቱን ይገፋል፡፡
የእኛ “ጀልጋጋ” እንዴት ያለ መመስጠር፣ በእንዴት ያለ ሁኔታ ስራው ውስጥ አስገብቶ ነበር ይሆን?….
….ላልታተመ፣ እንደውም የት እንደገባ ለማይታወቅ መፅሐፍ (ምንም በምናብ ቀበጥ ቢያደርገኝ) ይሄን ያህል በሀሳብ መመናተል ተገቢ ነው? አይመስለኝም! ምክንያቱ ደግሞ ግልፅ ነው። የእኛ አንባቢዎች ወጣ ያሉ የጥበብ ስራዎችን በትከሻ ግፊያ ከማሽቀንጠር ጋብ ብለው ሲያቀርቡ ስለማይታይ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- የዳንኤል ታዬ “ቅዠት” ከዚሁ ዘርፍ የሚመደብ ሥራ ቢሆንም ከአሥር አመታት በላይ የገበያ ደጅ እንዲጠና ተገድዶ ነበር። የዳዊት ፀጋዬ “ነጥቡ”ም እንደዚያው ከመገፍተሩ አልፎ ለደራሲው ስድብ አትርፎለት አልፏል፡፡ አሁን ደግሞ …
….አሁን ደግሞ የአልበርት ካሙ “The stranger” (Outsider) “ባይተዋሩ” በሚል ርዕስ በሚፍታ ዘለቀ ተተርጉሞ ቀርቦልናል፡፡ የካሙ ፍልስፍና መተርጎሚያ እና ማስተንተኛ የሆነው ይሄ ትልቅ ሥራ፤ እኛ ዘንድ ለመቀላቀል ሳይችል ቀርቶ ደጅ እንዲጠና የተፈረደበት ይመለስላል፡፡ የካሙ ሥራዎች በአማርኛ ተፈልገው አለመገኘታቸው ነውር ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከዚያ በላይ ነውራችን ደግሞ ተተርጉሞ ሲቀርብ ፊት መንሳታችን ነው። የአንድ ቋንቋ ሥነ-ፅሑፍ አንገቱን መድፋት የሚገባው ይሄኔ ነው፡፡ እንኳን ሥም ያለው ብዙ የተባለለትና ከፍ ከፍ የተደረገ ደራሲ ቀርቶ ጀማሪውንም ቢሆን በቋንቋችን ጠልፈን የኛ ማድረግ የተገባ ነበር፡፡ ነገር ግን…፡፡  

Read 1712 times