Saturday, 27 June 2015 09:29

ዝነኛ ዓለማቀፍ ሆቴሎች ወደ አፍሪካ እየተመሙ ነው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

በዓለም ዝምና ዝናቸው የገነነ፣ ምርጥ ባለ 5 እና 4 ኮከብ ሆቴሎች ቢኖሩም በአፍሪካ ስለሌሉ ብዙም አይታወቁም፡፡ በአፍሪካ የሌሉት ደግሞ በአጋጣሚ አይደለም - ሆን ብለው ነው፡፡ እንግዲህ የሆቴል ቢዝነስ ትርፍ ላይ ያተኮረ አይደል! አብዛኛው የአፍሪካ ህዝብ ድሃ ስለሆነ ሆቴሎቹ ቢሰሩም ተጠቃሚ አይኖራቸውም በማለት ነው፡፡
አሁን ግን ሁኔታዎች እየተለወጡ ነው፡፡ ብዙ የአሜሪካና የአውሮፓ አገሮች ኢኮኖሚያቸው ክፉኛ ዳሽቆ ከዚያ ማጥ ውስጥ ለመውጣት ሲዳክሩ፣ ብዙ የአፍሪካ አገሮች የለውጥና የዕድገት ጎዳናውን ተያይዘውታል። ጥቂት አገሮችም በዘመናት ከሚታወቁበት ድህነት አፈትልከው መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ ቀን ቆርጠዋል፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ ታዋቂዎቹ የዓለም ሆቴሎች ፊታቸውን ወደ አፍሪካ ያዞሩት፡፡ ካርልሰን ሬዚዶር፣ ስታር ውድ፣ ማንጋሊስ፣ ሮታና፣ ሉቨር ሆቴል ግሩፕ በሚሉ በሚታወቁና ሌሎችም ወደ አፍሪካ እየተመሙ ነው፡፡
መቀመጫውን ሌጎስ ናይጄሪያ ያደረገው ደብሊው ሆስፒታሊቲ ግሩፕ የተሰኘ አማካሪ ድርጅት ይፋ ባደረገው የዘንድሮ ዓመት ሪፖርት፤ ወደ አፍሪካ ለመግባት እየተወዳደሩ ያሉትን 10 ከፍተኛ ሆቴሎች ዝርዝር አውጥቷል፡፡ በአፍሪካ 7,250 ክፍሎች ያላቸው አዳዲስ ሆቴሎችን ለመገንባት ዝግጅቱን ጨርሶ ፉክክሩን እየመራ ያለው ሂልተን ሆቴል ሲሆን ከዚህ ውስጥ 18 በመቶዎቹ ባለፈው ዓመት የተጀመሩ ናቸው ተብሏል፡፡   
6,953 ክፍሎች ያላቸውን 32 አዲስ ሆቴሎች በመገንባት አፍሪካን ለማልማት 2ኛ ሆኖ እየገሰገሰ ያለው ካርልሰን ሬዚዶር ነው፡፡ በ3ኛ ደረጃ እየተከተለ ያለው ደግሞ ማርዮት ነው፡፡ 6, 412 ክፍሎ ያላቸውን 36 አዳዲስ ሆቴሎች ሊጀምር ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ 22 በመቶዎቹ ባለፈው ዓመት የተጀመሩ ናቸው።
በአዳዲስ ሆቴሎች ግንባታ ደግሞ 36 ሆቴሎችን በመገንባት ላይ የሚገኘው ማሪዮት ቀዳሚ ነው። 32 እና 29 አዳዲስ ሆቴሎች በመገንባት ካርሊሰን ሬዚዶር 2ኛ፣ ሂልተን 3ኛ በመሆን ይከተላሉ፡፡ ወደ አፍሪካ ገበያ ከገቡትና በመግባት ላይ ካሉት ሆቴሎች መካከል በአዳዲስ ሆቴሎች ግንባታና በክፍሎች ብዛት የመጀመሪያዎቹን 10 ምርጥ ሆቴሎች ከዚህ በታች ይመልከቱ፡፡

Read 1649 times