Saturday, 20 June 2015 10:51

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በፋሽስት ለተፈጸመባት ግፍና ጭፍጨፋ ካሣ ልትጠይቅ ይገባታል!

Written by  በዲ/ን ኒቆዲሞስ
Rate this item
(4 votes)

ኢጣሊያ ምሥራቅ አፍሪካ ጠቅላይ ግዛት
የፕሮቶኮል መዝገብ ቁጥር 9325
አዲስ አበባ ግንቦት 24/1937 ዓ.ም.

ጥብቅ ምስጢር፡- ለጄኔራል ማሌቲ- ደብረ ብርሃን፣
ለክቡር ምክትል ገዥ ኤታማጆር- አዲስ አበባ፣
ለፖለቲካ ጉዳይ ዋና አዛዥ- አዲስ አበባ፣
ለጦር ፍርድ ቤት- አዲስ አበባ፣
ለካራቢኜራዎች ዋና አዛዥ- አዲስ አበባ፡፡
ቁጥር 26609- የደብረ ሊባኖስ ጉዳይ ሙሉ ሓላፊነቱ የእርስዎ እንደሆነ አረጋግጬያለሁ፡፡ የደብረ ሊባኖስ ገዳም መነኮሳትና ዲያቆናት ሁሉም አንድ ሣይቀር በጥይት እንድትፈጇቸው አዝዣለሁ፡፡ ትእዛዝህን በአስቸኳይ አስፈፅሜያለሁ በሚል ቃል እንድታረጋግጥልኝ ይሁን!
ማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒ


ክፍል-፩
ለዛሬው ጽሑፌ መነሻ የሆኑኝ ሁለት ዐበይት ምክንያቶች ናቸው፡፡ የመጀመሪያው በዚህ ዓመት በአሜሪካዊው ምሁር በፕ/ር ኢያን ካምፔል፤ ‹‹The Massacre at Debre Libanos Ethiopia 1937:- The Story of One of Fascism’s Most Shocking Atrocities›› በሚል ርእስ የተጻፈው መጽሐፍ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የኒው ዮርክ ታይምስ ከሁለት ሳምንት በፊት የአርመን ኦርቶዶክስ ቤ/ን ከመቶ ዓመት በፊት ቱርካውያን በአርመን ክርስቲያኖችና አብያተ ክርስቲያናት ላይ ላደረሱት ግፍና መከራ የአርመን ቤተክርስቲያን መሪና መንፈሳዊ አባት የሆኑት አቡነ አራህም I የቱርክ መንግሥት ለቤተ ክርስቲያኒቱ ተገቢውን ካሣ እንዲከፍል የጠየቁበትና ያሳሰቡበት ሰበር ዜና ነው፡፡
 ከሰሞኑ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ላይ ሰፊ ምርምርና ጥናት በማድረግ የሚታወቁት አሜሪካዊው ምሁር ፕ/ር ኢያን ካምፔል፤ የፋሽስት መንግሥት በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በተለይም ደግሞ በደብረ ሊባኖስ ገዳም መነኮሳትና አገልጋዮች ላይ ያደረሰውን ዘግናኝ ጭፍጨፋና እልቂት፣ መከራና ሥቃይ በተመለከተ የሚተርከውን መጽሐፍ በቁጭትና በኀዘን ውስጥ ሆኜ ነው ያነበብኩት፡፡
መጽሐፉ የፋሽስት መንግሥትን የጭካኔና የአውሬነት ጥግ በሥዕላዊ ቃላት የሚከስት፣ የሚገልጽ ድንቅ ሥራ ነው ብል እምብዛም ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡ በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረውን መሰሉ የሆነውን የሰው ልጅን ለሚወድና ለሚያከብር፣ ሰብአዊነት፣ ፍቅርና ርኅራኄ ምን ማለት መሆኑን ለተረዳ ሰው ለሆነ ሰው ሁሉ ፋሽስት በሰው ልጆች፣ በወገኖቻችን ላይ ያደረሰው ግፍና ጭካኔ፣ ጭፍጨፋና እልቂት ልብን በኀዘን ጦር የሚወጋ፣ ሰው የመሆን ታላቅ ክብርን በትልቅ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡
እኚህ ምሁር አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስግዶም የተባሉ ወጣት ኤርትራውያን በፋሽስቱ ጄኔራል በማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒ ላይ በቀድሞው ገነት ልዑል በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ካደረጉት የግድያ ሙከራ ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ የታወጀው ግድያና ጭፍጨፋ፣ እልቂትና ፍጅት ወደ ደብረ ሊባኖስም ዘልቆ በርካታ መነኮሳት፣ ካህናት፣ ዲያቆናትና ምእመናን በግፍ ማለቃቸውን፣ ተጨባጭ ከሆኑ መረጃዎች፣ ታሪካዊ ሰነዶችና ፎቶግራፎች ጋር አጠናክረው ፋሽስት በገዳሙ ላይ ያደረሰውን ውድመትና እልቂት፣ ኢ-ሰብአዊ የሆነ ግፍና ጭፍጨፋ በሚገባ ተርከውታል፡፡
ምሁሩ በጊዜው ከዚያ አሰቃቂ እልቂት የተረፉትን አባቶች ቃለ መጠይቅ በማድረግ፣ በደብረ ሊባኖስ ገዳም በሚገኙ መነኮሳትና አገልጋዮች ላይ ፋሽስቱ ሞሶሎኒ ለጦር ባልደረቦቹ ያስተላለፈውን የግድያ ዕርምጃ የሚያረጋግጡ የቴሌግራም መልእክቶችንና ምስጢራዊ የሆኑ ሰነዶችን በመመርመር፣ ለበርካታ ዓመታት ጥናት ያደረጉበትን ይህን መጽሐፋቸውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ለንባብ አብቅቶታል፡፡
ኢትዮጵያም ሆነ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በፋሽስት ኢጣሊያ የደረሰባቸውን ግፍና መከራ፣ እልቂትና ጭፍጨፋ መላው ዓለም ያውቀው ዘንድ ይህን መጽሐፍ ያበረከቱልን ፕ/ር ኢያን ካምፔል ባለውለታችን ናቸውና ልናመስግናቸውና ለሥራቸውም የሚገባውን እውቅና ልንሰጣቸው ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስም ለእኚህ ምሁር የሚገባውን ክብርና ዕውቅናም ቢሰጣቸው መልካምና ተገቢም ይመስለኛል፡፡
በዛሬው ጽሑፌ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በፋሽስት ስለደረሰባት ግፍና መከራ፣ በአገልጋዮቿና በመእምናኖቿ ላይ ስለደረሰው አሰቃቂ ጭፍጨፋና እልቂት የኢጣሊያን መንግሥት ይቅርታ በመጠየቅ ተገቢውን ካሣ ሊከፍላት ይገባል!›› ያልኩበትን ምክንያት ከታሪክ ድርሳናትና መዛግብቶች በመፈተሽ በጥቂቱ ለማብራራት ልሞክር፡፡
የኢትዮጵያ ቤ/ን ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ስለ ሰው ልጆች ከፈጣሪው ስለ ተቸረው ነጻነት ከመናገርና ከማስተማር ባሻገርም ነፍሳቸውን ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ነጻነት ክቡር መሥዋዕት አድርገው ያቀረቡ ፍቅርንና እውነትን፣ የነጻነትን ክብርና ልእልና በደማቸው ጽፈው የተረኩና ለዚህ ክፉና ጨካኝ ዓለም በተግባር አሣይተው ያለፉ አባቶች ያለፉባትና ያሉባት ሐዋርያዊት ቤ/ን ናት፡፡
እንደ ሰማዕታቱ አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤል ያሉ እውነተኛ፣ ኢትዮጵያዊ መንፈሳዊ አባቶችና የወንጌል አርበኞች “ቤተ ክርስቲያናችን በሮማ ካቶሊክ ሥር አታድርም፣ በሕይወት ቆመን እያለን ቤተ ክርስቲያናችንና ሕዝባችንን ቅኝ ለማድረግ የቋመጣችሁለት ይህ የዘመናት ሕልማችሁ ዕውን አይሆንም፤ አገራችንም ሆነ ሕዝባችን ለፈጣሪ እንጂ ለእናንተ ፈጽሞ አይገዛም፣ ከፈጣሪ የተቸረንን የአገራችንን፣ የቤተ ክርስቲያናችንንና የሕዝባችንን ነጻነትና ልዑላዓዊነትም ለእናንተ ለጨካኞችና ለአውሬዎች አሳልፈን አንሰጥም” በማለታቸው ነበር- እምነታቸውን፣ ቃላቸውን እንደጠበቁ፣ እንዳከበሩ በፋሽሽት መትረየስ በአደባባይ ተደብድበው እንዲገደሉ፣ እንዲረሸኑ የተደረጉት፡፡
የጨካኞቹና የአውሬዎቹ የፋሽስት የሞት አበጋዞች ማስፈራራትና መደለያ መንፈሳዊ ጽናታቸውን ፈጽሞ ሳይበግረው ሞትን በፍቅር ድል ነሥተው ዘላለማዊነት የተጎናጸፉ እነዚህ አባቶቻችን፤ ‹‹ኢትዮጵያዬ ብረሳሽ ቀኜ ትርሣኝ፣ ምላሴ ከትናጋዬ ይጣበቅ!›› በሚል ጽኑ የመኻላ ቃል ታስረው፣ ‹‹እግዝእትነ ማርያም ስሚዕ ኀዘና ወብካያ ለአገሪትነ ኢትዮጵያ!›› ብለው እንባቸውን በጽድቅ ለሚፈርድ አምላክ ወደ ሰማይ ረጭተው፣ በጸሎታቸው ተማፅነው፣ ቃል ኪዳናቸውን ሣያረክሱ፣ ቃላቸውን ሳያጥፉ፣ እትብታቸው የተቀበረባትን እናት ምድራቸውን በደማቸው ቀድሰውና በመስቀላቸው ባርከው፣ በእንባቸውና በደማቸው ነጻነታቸውን አውጀው ወደሚናፍቁት አምላካቸው በሰማዕትነት በክብር የሄዱት፡፡
የኢትዮጵያ ታላቅ ባለውለታ የነበሩትና የኢጣሊያን ፋሽስት ጭካኔና ግፍ ለዓለም ሁሉ በማጋለጥ ከኢትዮጵያውያን ጎን የቆሙት ሲሊቪያ ፓንክረስት፤ የፋሽስቱ መሪ ቤኒቶ ሞሶሊኒ በሃይማኖት አባቶች ላይ እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ሊያሸማቅቅ እንደሚችልና ጭፍጨፋውም ውጤታማ እንደሆነ በወቅቱ ለምስራቅ አፍሪካ ለቅኝ ግዛት ሚ/ሩ ለግራዚያኒ ያስተላለፈውን ምስጢራዊ የቴሌግራም መልእክት Ethiopia and Eritrea በሚለው መጽሐፋቸው እንዲህ ጠቅሰውታል፡-
… The execution of Abune Petros, one of the four Ethiopian bishops, has terrified the leaders and the public. The work of repression against armed groups dispersed in the forest continues. All prisoners have been shot. Inexorable reprisals have been effected against the populations guilty, if not complicity, at least of lack of favourable attitude. A telegram of March 1, 1937.
‹‹በአቡነ ጴጥሮስ ላይ የተወሰደው የግድያ ዕርምጃ ብዙዎችን እንዲፈሩና እንዲሸማቀቁ አድርጓል፤ ይህ ዓይነቱ እርምጃ ለኢጣሊያን እንዳይገዛ ሕዝቡን በሚያነሣሡና በዱር በገደል በአርበኝነት በተሰማሩት ፋኖዎችም ላይ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል . . . ፡፡››
የታሪክ ድርሳናትን ስንፈትሽ በተለያዩ ጊዜያት ኢትዮጵያን ቅኝ ለመያዝ፣ ሕዝቦቿን ለመግዛት የመጡ አውሮጳውያን ወራሪዎችና የአረብ ተስፋፊዎች ሁሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ ቀዳሚ ዒላማ ልትሆን የቻለችባቸው ራሱን የቻለ ምክንያት አለው።  ይኸውም ቤ/ቱ በኢትዮጵያ ነጻነትና ልዑላዊነት ላይ ያላት ጠንካራና የማይለወጥ፣ የማያወላውል ጽኑ አቋም ነው፡፡ ዳንኤል ሮፕስ የተባለ ፈረንሳዊ ጋዜጠኛ እ.ኤ.አ. ፲፱፻፷፫ ‹‹አክሌዥያ›› በሚባል በፓሪስ ከተማ ለሚታተም ጋዜጣ፡- ‹‹የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን ታውቃላችሁን?›› በሚል ርዕስ ባሰፈረው ሰፊ ሐተታም እንዲህ ሲል ምስክርነቱን ሰጥቶ ነበር፡-
ኢትዮጵያ ወራሪዎች ምድርዋን በግፍ የያዙባት መሆኑን ታሪክ ያወሳል፤ ነገር ግን ሃይማኖቷ ኃይሏና የእንቅስቃሴዋ መሳሪያ ሆኖ በመገኘቱ ነጻነቷን መልሳ አግኝታለች፡፡ በማዕከላዊው ክፍለ ዘመን ‹‹የካህን የዮሐንስ ግዛት›› በአረመኔው ዓለም ተከቦ የክርስቲያን ምሽግ ሆነዋል እየተባለ ስለ ኢትዮጵያ ይነገር የነበረው ሁሉ ፍጹም ልበ-ወለድ ታሪክ አይደለም፡፡ ከሁለት ሺሕ ሜትር በላይ ከፍታ ያለውን ደጋማና ለምለም መሬት ቁልቁል የሚያዩት ቀይ፣ ጥቁርና ሰርጥነት ያላቸው የእሳተ ገሞራ ውጤት ባሕርይ ያላቸው ጠረጴዛ መሰል ተራራዎች የጊዜን ውሽንፍር እንዳሳለፉትና የባሕር ዓሣም ሳይበገርና ሳይላላ ማዕበሉን እንደሚያሳልፍ ክርስቲያኒቷ ኢትዮጵያም በታሪክ ውስጥ ጠንካራ ስፍራዋን ይዛና አስከብራ ቆይታለች …፡፡ በማለት ጽፏል፡፡
ይህን ቤተ ክርስቲያኒቱ በኢትዮጵያ ልዑላዊነትና በሕዝቦቿ ነጻነት ላይ ያላትን የማያወላውል ጽኑ አቋም በሚገባ የሚያውቁ አውሮጳውያን ቅኝ ገዢዎች፣ ወራሪዎችና ተስፋፊዎችም በተለያዩ ዘመናት ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማፍረስና ቢቻላቸውም በራሳቸው ግዛትና ቁጥጥር ሥር ለማድረግ ያልቆፈሩት ጉድጓድ፣ ያልወጡት ተራራ የለም ማለት ይቀላል። አልተሳካላቸውም እንጂ፤ ይህ ሙከራቸው ደግሞ መልኩንና ይዘቱን ቀይሮ እስካሁንም ድረስ የዘለቀ ነው ማለትም ይቻላል፡፡
የኢትዮጵያ ቤ/ን በውጭ አገራት ወራሪዎችና ቅኝ ገዢዎች ዘንድ ጥርሳቸው እንዲነኩስባትና በተለያዩ ዘመናት ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ያጋጠማቸውን ወረራ፣ የቅኝ ግዛት መስፋፋት በማውገዝና በመቋቋም ረገድ ያደረገችውን ተጋድሎና የከፈለችውን ክቡር መሥዋዕትነት ከታሪክ ድርሳናትና መዛግብት እየፈተሽኩ ሁሉንም ለመተረክ የዚህ ጋዜጣ ገጽም ሆነ ጊዜው አይፈቅድልኝም። ግና ወደተነሣሁበት መደምደሚያ የሚያደርሰኝንና በኢትዮጵያ የዘመናዊ የታሪክ ዘመናት በቅርብ ዓመታት የተከሰቱትን የአውሮጳውያን ወረራዎችና ቅኝ ገዢ ተስፋፊዎች ሕልማቸውን በማምከን ቤተ ክርስቲያኒቱ የነበራትን ተሣትፎና ዐቢይ ሚና ብቻ በመዳሰስ የዛሬውን የመጀመሪያ ክፍል መጣጥፌን ልቋጭ፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ክብሯንና ዝናዋን በዓለም አቀፍ እንዲናኝ ካደረጉት ታሪካዊ ክስተቶች መካከል የዐድዋው ድል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ከጦርነት ዘመቻው ዝግጅትና፣ ከዘመቻውና ድሉ ድረስ ቤተ ክርስቲያኒቱ ያልነበረችበት፣ ያልተሳተፈችበት አጋጣሚ አልነበረም፡፡ ይህ ደግሞ ትናንትና በአገር ወሰንና ድንበር ተከልሎ የሆነ ብቻ አይደለም፡፡ ከታሪክ እንደምንማረው ለአብነት ያህል ለመጥቀስም አክሱማዊው ንጉሥ ዐፄ ካሌብ ከአንድ ሺ አምስት ዓመታት በፊት በየመን ግፍ፣ መከራና ስደት ካጸኑባቸው ሰዎች ነጻ ሊያወጣቸው በመቶ የሚቆጠሩ ጦር መርከቦችንና ወታደሮችን ይዞ በየመን ያሉ ክርስቲያኖችን ለመታደግ ዘምቶ እንደነበር ታሪካችን ይነግረናል፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለሰው ልጆች ኹሉ ከፈጣሪ በተሰጠ ነጻነት፣ በእውነት፣ በፍትሕ ላይ ያላት ጽኑ የሆነ አቋም ስለ ነጻነታቸው፣ ስለ ፍትሕና ስለ ሰው ልጆች እኩልነት በሚታገሉና በሚጋደሉ የዓለም ሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተሰማ፣ ትልቅ ክብርና ዝና ያለው ነው፡፡ በተለይም ደግሞ አውሮጳውያን ቅኝ ገዢዎችንና ተስፋፊዎችን በእጅጉ ያደናገጠውና ያሳፈረው በዓድዋው ጦርነትና አንጸባራቂ ድል ላይ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከዘመቻው ጀምሮ እስከ ጦር ግንባር ድረስ የነበራትን ተሣትፎ ከአፍሪካ እስከ ላቲን አሜሪካ፣ ካረቢያና ጃሜይካና ደቡብ አፍሪካ ድረስ የተሰማና ጥቁር ሕዝቦችን ያኮራ ነበር፡፡
ይህ የቤተ ክርስቲያኒቱ ክብርና ዝና በመላው አፍሪካ፣ አሜሪካና አውሮጳ ድረስ ተሻግሮ ጥቁር ሕዝቦችን ለነጻነታቸው፣ ለመብታቸው፣ ለሰብአዊነታቸውና ለክብራቸው ዘብ እንዲቆሙ አነሳስቷቸው እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ፡፡ ይህ በዓለም ሁሉ የተሰማው የቤተ ክርስቲያኒቱ በዐድዋ ዘመቻ የነበራት ውሎና ለሰው ልጆች ነጻነት ያደረገችው ተጋድሎ ለአፍሪካ፣ ለጥቁር ሕዝቦች ወኔና ትልቅ መነሳሳት ሆኗቸው እንደነበር የሚመሰክሩ ታላላቅ የዓለማችን የነጻነት ታጋዮችና የአገር መሪዎች አሉ፡፡
ይህን የታሪክ ሐቅ አስመልክቶ በአንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እ.ኤ.አ በ2010 ዓ.ም. የክብር ዶክትሬት የተሠጣቸው የነጻነት ታጋይና የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት  ታቦ እምቤኪ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለአፍሪካ በተለይም ደግሞ ለደቡብ አፍሪካውያን የነፃነት ትግልና ተጋድሎ ትልቅ ኩራትና መነቃቃትን የፈጠረች መሆኗን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ልደት አዳራሽ ባደረጉት ንግግራቸው ከታሪክ በማጣቀስ እንዲህ ገልጸውት ነበር፡-
...The Ethiopian Church would the authentic African church serve as a repository of the aspirations of all Africans for freedom and respect for their cultures, their identity and their dignity. It was therefore not by accident that the independent African churches I have mentioned called themselves the Ethiopian Church ….
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እውነተኛ የአፍሪካ ቤተክርስቲያንና ለአፍሪካውያን በሙሉ ነፃነታቸው፣ ባህላቸው፣ ልዑላዊነታቸው፣ ማንነታቸውና ሰብአዊነታቸው እንዲከበር ላላቸው ህልም እንደማከማቻ ቦታ ሆና ታገለግላለች ብለው ያምኑ ነበር፡፡ ታዲያ በዚህ እውነታ እና ታሪካዊ ሐቅ ላይ ተመስርተው ነበር እነዚህ የጠቀስናቸው ቤተ ክርስቲያናት እራሳቸውን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብለው የሰየሙት፡፡
እንግዲህ ይህ ቤተ ክርስቲያኒቱ በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ፣ በመላው ጥቁር ሕዝቦችና በአጠቃላይም ነጻነታቸውን በሚያፈቅሩና በሚያከብሩ የሰው ልጆች መካከል ያላት አኩሪ ታሪክ፣ ገድልና መልካም የሆነ ምስክርነት በኋላ ዘመን አፍሪካን እንደ ቅርጫ ሥጋ ለመቀራመት ለመጡ አውሮጳውያን እንደ እግር እሳት ነበር ያንገበገባቸው፡፡
እናም ይህን ለጥቁር ሕዝቦችና አፍሪካውያን መመኪያ የሆነ ታሪክ በማጠልሸት፣ ቅርሱንና ታሪኩን ከመሠረቱ በመናድ፣ በሃይማኖቱ ጽኑ የሆነውንና ለነጻነቱ ቀናዒ የሆነውን ሕዝብ ለመበቀል ሲል ፋሽስት የበቀል በትሩን በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ አነሳ። በቀጣይ ጽሑፌ በሰፊው የምዳስሰው የደብረ ሊባኖሱ ጭፍጨፋና እልቂትም የዚሁ በቀል ትልቅ ማሳያ ነው፡፡    
ሰላም!


Read 2233 times