Saturday, 13 June 2015 15:43

‹‹ማሂ ድንግሏ››

Written by  ህይወት እምሻው
Rate this item
(3 votes)

ልጃገረድነት ሰልችቶኛል፡፡ ቦይፍሬንድ አምሮኛል፡፡
‹‹የኔ ፍቅር››  መባል፣ ‹‹የኔ ቆንጆ›› ተብሎ መጠራት አሰኝቶኛል፡፡
እስከዛሬ ድረስ ‹‹ትምህርቴን በስርአት ለመከታተል››፣ ‹‹ከአልባሌ ቦታ ለመራቅ››፣ ‹‹መቅደም ያለበትን ለማስቀደም››፤ የከጀሉኝን በአልገባኝም እየሸወድኩ፣ የጠየቁኝን እምቢ እያልኩ፣ ስንት የተቀበረ የወንድ ፈንጂ በጥንቃቄ አልፌ፤ ልጃገረድ ሆኜ ቆይቻለሁ፡፡
ኮሌጅ ከገባሁ ጊዜ አንስቶ ግን ከካልኩለስ በላይ ይሄ እየከበደኝ መጣ፡፡ አብሶ ሶስተኛ አመት ስደርስ። አብሶ 21 አመት ሲሞላኝ፡፡ አብሶ ጓደኞቼ ሁሉ ወሬያቸው በ ‹‹እንትና ደውሎልኝ›› ፣ በ‹‹ እንትና ቴክስት ልኮልኝ››፣ በ‹‹እንትና ስሞኝ›› ሲጀምርና ሲያልቅ፤ እኔ ደግሞ ከወሬው መገለል ስጀምር፡፡
እኔ ስልክ የሚደውልልኝ ታላቅ ወንድሜ ብቻ ነው፡፡ ቴክስት የሚደርሰኝ ከ8100 ብቻ ነው፡፡
ተስሜ የማውቀው አስራ አንደኛ ክፍል እያለን አሳስቶ (ለአራት ወራት) በቀመሰኝ ዮናታን ብቻ ነው፡፡
እነሆ! ድንግል መሆኔን ያወቁት የቅርብ ጓደኞቼ የቀልዶች መጀመሪያ ካደረጉኝ ቆዩ፡፡
‹‹አንቺ ልጅ አረ ተይ...?! ኮርማ አምጥተን እናስጠቃሽ እንዴ..!.›› ‹‹ቱሪዝም ኮሚሽን ስላንቺ ያውቃል...? ከድንቃድንቅ ቅርሶች መሃል አስመዝግበው ያስጎብኙሽ እንጂ!››
‹‹የሆነ አራት መአዘን የመስታወት ሳጥን ውስጥ አስቀምጠው ሊመረምሩሽ እንዳይመጡ...››
ልጃገረድነት ሰልችቶኛል፡፡ ቦይፍሬንድ አምሮኛል፡፡ ‹‹የኔ ፍቅር›› መባል፣ ‹‹የኔ ቆንጆ›› ተብሎ መጠራት አሰኝቶኛል፡፡
ግን ቦይፍሬንድ እንዴት እንደሚገኝ፣ ልጃገረድነት እንዴት እንደሚሰጥ፣ የኔ ፍቅር ለመባል በየት በኩል እንደሚኬድ አጥርቼ ስለማላውቅ፣ ጓደኞቼ ሲወጡና ሲገቡ ማጥናት፣ አንዳንዴም ጥያቄ መጠየቅ፣ አንዳንዴም ዝም ብለው ሲያወሩ ከዝባዝንኬው ፍሬ ነገር መልቀም ያዝኩ፡፡
ልክ ክፍል ውስጥ ገብቼ ደብተሬ ላይ ዋና ዋናውን እንደምፅፈው፤ ከአፋቸው የሚወጡ ነገሮችን ጆሮዎቼን አፋቸው ስር እንደ ባልዲ ደቅኜ መቅዳት ጀመርኩ፡፡
ብዙ ጊዜ የሚጠቅመኝን ነገር የምታወራው ግን ሰምሃል ነበረች፡፡
ሰምሃል እንደ ኤቲኤም ማሽን ለወንዶች ሃያ አራት ሰአት ክፍት ናት፡፡ በተለይ የሚስጥር ኮድዋን ለሚያውቁ፡፡
‹‹የሴቶች ቫያግራ ገንዘብ ነው ›› የምትለው ነገር አላት፡፡ ገንዘብ ካገኘች እንደ ህዝብ ስልክ ማውራት ትጀምራለች፡፡ አውርታም የተጠየቀችውን ታደርጋለች፡፡
አንድ ቀን ዶርም ለብቻችን ስንሆን ድፍረት አጠራቀምኩና፤ ‹‹ ስሚ ሰምሃል...›› አልኳት ‹‹እ...››
‹‹እንዳትስቂ ግን›› ‹‹በምን እስቃለሁ...?›› ‹‹በምጠይቅሽ ነገር›› ‹‹ምንድነው...የሚያስቅ ነው.?..››
‹‹ኦፋ! አትሳቂ አልኩሽ አይደል..?.›› ‹‹እሺ.. ጠይቂኝ›› የእግር ጥፍሮችዋን አይን የሚያደነቁር ቀይ ቀለም እየቀባች ነው፡፡ ጎንበስ ብሎ ለሞከረ ከአውሮፕላን ይታይ ይመስለኛል፡፡
‹‹እ...ቦይፍሬንድ...ቦይፍሬንድ እንዴት ነው የሚያዘው...ማለቴ...መጀመሪያ ምን ማድረግ ነው ያለብኝ...?››
አልሳቀችም፡፡ ገረመኝ፡፡ ‹‹ማሂዬ! የኔ ቆንጆ....ልብስ እንዴት ነው የሚገዛው...?›› አለችኝ ቀለም ቅቡን ትታ ወደኔ እያየች፡፡ ‹‹እ..?››
‹‹ልብስ ስትገዢ ምንድነው የምታደርጊው...?›› ‹‹እለካለኋ!›› ‹‹እኮ...ወንድም እንደዛ ነው...ገበያ ትወጫለሽ....፣ ያማረሽን ታነሲያለሽ...ትለኪዋለሽ....ካልጠበበ...ወይ ካልሰፋ...በልክሽ የሆነውን በአቅምሽ ትገዣለሽ....››
ብዙ ጊዜ የምትለው ነገር አይጥመኝም ነበር፤ ይሄ ግን ልክ መሰለኝ፡፡
በልክ መግዛት፡፡ በአቅም መግዛት፡፡
ግን ልኬ ማነው...? አቅሜስ ምን ያህል ነው...? ወንድን ‹‹መለካት››ስ ምን ማለት ነው...? ስንት ምሳ ተጋብዤ እመርጣለሁ?
ስንት ከንፈር ቀምሼ አውቃለሁ?
ከስንቱ ጋር ተኝቼ እወስናለሁ...?
ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎች ነበሩኝ ግን፤
ልጃገረድነት ሰልችቶኛል፡፡ ቦይፍሬንድ አምሮኛል፡፡
‹‹የኔ ፍቅር›› መባል፣ ‹‹የኔ ቆንጆ›› ተብሎ መጠራት አሰኝቶኛል፡፡
ስለዚህ በፈራ -ተባ ቦይፍሬንድ ገበያ ወጣሁ፡፡
ምን ያደርጋል! የምሄድበት ቦታ ሁሉ የኖህ መርከብ ይመስል ካለ ጥንድ ብቻውን የቆመ ሰው ግን አጣሁ፡፡
አልፎ አልፎ ብቻውን የቆመ ባገኝም፤ ለምሳሌ አንዱ መላጣ እና ሾጣጣ ጭንቅላታም ይሆንና ‹‹አሁን ይሄ መላጣ ሌላ ፊት አያሰራም!?›› እያልኩ ስስቅ የቦይፍሬንድ ግዢውን እረሳለሁ፡፡
እንዲህ እንዲህ እያልኩ አቃቂር ሳወጣ ውዬ ባዶ እጄን እመለሳለሁ፡፡
-----
ሙከራ አንድ!
ከእለታት በአንዱ ቀን በሰምሃል አያያዥነት ከአብስራ ጋር ተዋወቅሁ፡፡
ለነገሩ በፊትም አውቀው ነበር፡፡ ‹‹ጓደኝነታችን›› ሲጠነክር እና በግ ተራ እየተቀጣጠርን መገናኘት ስንጀምር የነገሩን አቅጣጫ በመገመት ለሚመጣው መዘጋጀት ጀመርኩ፡፡ የዚያን ጊዜ ነው ሰምሃል የአብስራም እንደኔ ‹‹ልዩና አስደናቂ ወጣት›› እንደሆነ የነገረችኝ፡፡ ጎበዝ የማትስ ዲፓርትመንት ተማሪ ስለነበር ‹‹በሂደቱ ላይ›› ችግር ቢፈጠር መላ መምታት አይከብደውም ብዬ ብዙ አልከፋኝም፡፡
ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ተከራይቶ የሚኖርበት ቤት ወስዶ ‹‹የሚያሳብድ ሙዚቃ›› ሊያሰማኝ እንደሚፈልግ ሲነግረኝ በጠዋት ወጥቼ የውስጥ ሱሪ ገዛሁ፡፡ ቀይ፣ ባለ አበባ፣ የመቀመጫዬን  አንድ አራተኛ ብቻ የሚሸፍን “ሻፋዳ” የውስጥ ሱሪ፡፡
እንደ ጎበዝ ተማሪ ባህሪዬ፤ ከዚያ በፊት በነበሩት ቀናት ግን ሰምሃልና ሌሎቹ ባሉበት የቅድመ ዝግጅት ጥያቄዬን ልምድ ላካበቱት አቅርቤ ነበር፡፡
‹‹ያማል?›› ‹‹አዎ ግን አሪፍ ህመም ነው››
‹‹ካደረግኩ በኋላ ወዲያው መቆምና መራመድ እችላለሁ?›› (ከህብረት ሳቅ በኋላ) ‹‹እንዴ! ስልክ እንጨት የምትውጪ መሰለሽ እንዴ?!›› ሰምሃል ናት፡፡
‹‹ከሱሬ ጋር ካላደረግሽ...ቆመሽ ትሄጃለሽ...›› ሁሉም ጮህ ብለው ሳቁ፡፡ ‹‹ሱሬ ደግሞ ማነው?›› ሌላ የማላውቀው ነገር ከጣሪያ በላይ ሲያስቅ እኔ ግን መጠየቅ እየሰለቸኝ ጠየቅኩ፡፡ ‹‹ሱሬ ቲቪኤስ ነዋ! ሱሬን አታውቂውም?›› ሰምሃል ተሽቀዳድማ፡፡ ‹‹ሱሬ ማ?››
‹‹ሱሬ ቲቪኤስ!›› እንደገና ሳቁ፡፡ ‹‹ምንድነው ደሞ ቲቪኤስ?›› እያመመኝ ጠየቅኩ፡፡
ሶስቱም በአንድ ጊዜ እንዳጠኑት ሁሉ እኩል ‹‹ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪ!›› አሉና እንደገና ሳቁ፡፡
አፍሬም ስቄም ዝም ብዬ ትንሽ እንደቆየሁ ማክዳ ‹‹ለመጀመሪያ እንኳን ባለማርያም ጣቱን ያድርግልሽ›› አለች ከቅድሙ የተረፈ ይሆን አዲስ  ያላወቅኩትን ሳቅ ሳታቆም፡:
ስቄ ዝም አልኩ፡፡
‹‹ባይ ዘ ዌይ...ክብሩ እንደዛ ነው አሉ›› (ያው እንደምትገምቱት ሰምሃል ናት ይሄን ያለችው) ‹‹ክብሩ..? ክብሩ ሳይኮሎጂ!?›› ማክዳ ተሸቀዳድማ ጠየቀች
‹‹ያ!...ሰኒ አብራው አድራ ስትመጣ እንዴት ነበር ስላት ምን ብትለኝ ጥሩ ነው?›› ‹‹ምን አለች?››
‹‹እሱ ኮንዶም ሲያመጣ እኔ ደግሞ ማይክሮስኮፕ ይዤ መሄድ ነበረብኝ!››
እኔ የሌለሁበት ሌላ የሕብረት ሳቅ፡፡ ልጃገረድነት ሰልችቶኛል፡፡ ቦይፍሬንድ አምሮኛል፡፡
‹‹የኔ ፍቅር›› መባል፣ ‹‹የኔ ቆንጆ›› ተብሎ መጠራት አሰኝቶኛል፡፡ ከእነዚህ ልጆች ሳቅ መደመር አምሮኛል፡፡
የአብስራ፤ ከላይ ጣራዋን፣ ከታች ወለሏን በማዳበሪያ ኮርኒስ የተለበጠች፣ ከትንሽነቷ ብዛት በስፋት ልኬት ልትጠራ የማይገባት ቤቱ ይዞኝ ሄደ፡፡ ፍራሽና ቴፕ ብቻ ነው ያላት፡፡
‹‹ሙዚቃ ልንሰማ..ሃሃ...ያልተበላ ብላ!›› አልኩ በሆዴ፡፡
ፍራሹ ላይ ተጣበን ተቀመጠን፡፡
ካሁን ካሁን ወጣብኝ፣ ካሁን ካሁን ሴት አደረገኝ፣ ካሁን ካሁን --- ብዬ ስጠብቅ በላዬ ላይ ተንጠራርቶ ቴፑ ውስጥ የሆነ ሲዲ ከተተ፡፡
‹‹ግርማ ይፍራሸዋን መስማት አለብሽ...!ስሚ የምር ሙዚቃ›› አለና ጎታታ የፒያኖ ሙዚቃ ከፈተልኝ፡፡
ዝም ብዬ አየዋለሁ፡፡ በግርማ ይፍራሸዋ ም..ስ...ጥ ብሏል፡፡ በቁሙ ምስጥ ይብላውና!
---------
ሙከራ ሁለት!
ሰምሃል ያጣበሰችኝ ሚኪ እየሳመኝ ነው፡፡ ሲስም እንደ ዮናታን አይደለም፡፡ ዮናታን ሲስመኝ ምላሱን የሚያደርግበት ቦታ ጠፍቶት አፌ ውስጥ ይዘፈዝፈው ነበር፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ጥርሴን ይልስበት ነበር፡፡ እንደዛ እንደዛ ሲደርግ ሊያስመልሰኝ ይደርስ ነበር፡፡
መሳም ለካ እንዲህ ነው!
‹‹ጎበዝ ነህ..መሳም›› አልኩት የትንፋሽ መሰብሰቢያ እረፍት ስንወስድ ፈገግ አለና ዝም አለ፡፡
‹‹እንዴት...የት ተማርከው በናትህ?›› ‹‹መሳም ስሜት እንጂ ሳይንስ የለውም...››
እንደገና መሳሳም ጀመርን፡፡ ዮናታን እግዜር ይይለት፡፡
ሲስመኝ ሲስመኝ...ሲስመኝ...ነገራችን ከሰሜን ወደ ደቡብ ቢዘልቅ ተመኘሁ፡፡
ባየው አይወርድም፡፡ ባየው አይወርድም፡፡
ከንፈሬን ሙጭጭ ብሎ ቀረ፡፡
የትራንስፖርት ወጪ ያለበት ይመስል ሰሜን ላይ ሙጭጭ አለ፡፡
አቅበጠበጠኝ፡፡ እጁን በእጄ ይዤ ወደ ደቡብ ተጓዝኩ፡፡
ዋናው ከተማ ላይ ከተመ፡፡ ጎሽ!...
በድንገት ግን ባልጠበቅኩት ፍጥነት ዋና ከተማውን ማተራመስ ጀመረ፡፡
ተናወጥኩ፡፡ ደነገጥኩ፡፡
እሱ ሲቸኩል እኔ አዘገምኩ፡፡
እሱ ሲፈላ እኔ ቀዘቀዝኩ፡፡ ‹‹ተው!›› አልኩና ሸሸሁ፡፡
‹‹ምነው....?›› ድምፁ የሱ አይመስልም (ድምፃቸውም ይቀየራል እንዴ?) ‹‹ሚኪ...ቨርጂን ነኝ...›› ‹‹አውቃለሁ...››
‹<፣እንዴት..? ...ማለት እንዴት አወቅክ?››
‹‹እነ ሃይላብ ሲያወሩ ሰምቼ ነው..ሰምሃል ነግራው...ነገረችኝ ብሎ ነገረኝ...›› ‹‹ምኑን...?>>
‹‹ያው ቨርጂን እንደሆንሽ እና ‹‹ዲስቨርጅ›› መደረግ እንደምትፈልጊ...››
ራሴ ዞረ፡፡
‹‹ዲስቨርጅ መደረግ እንደምትፈልጊ›› በሚለው አባባል ራሴ ዞረ፡፡
ልክ እንደሚፈለጥ ኮብል ስቶን፣ እንደሚፈታ ሳይመልቲኒየስ ኤኩዌዥን፣ እንደሚተረተር ቱባ ክር መታየቴ ራሴን አዞረው፡፡
የሰዎች በኔ ጉዳይ ተወያይቶ መወሰን፣ ሴራው፣ ቅንብሩ፣ ድርድሩ አዞረኝ፡፡
ሽሽት አልኩ፡፡
ራሴን ለመታረድ ያቀረብኩ ገራገር በግ የሆንኩ መስሎ ተሰማኝና ሽሽት አልኩ፡፡
‹‹ምን ሆነሻል?›› ‹‹ምንም..ሬዲ አይደለሁም...እንሂድ....››
ሙከራ ሶስት አልነበረም፡፡
ከሚኪ በኋላ የተረዳሁት ነገር ከተጨማሪ ሙከራ አቀበኝ፡፡
ልጃገረድነት ሰልችቶኛል፡፡ ቦይፍሬንድ አምሮኛል፡፡ ‹‹የኔ ፍቅር›› መባል፣ ‹‹የኔ ቆንጆ›› ተብሎ መጠራት አሰኝቶኛል፡፡
ግን፤
ይሄን ሁሉ ስሞክር የነበረው በመገፋቴ እንጂ በመፈለጌ አልነበረም፡፡ ይሄን ሁሉ ስሞክር የነበረው ተገፍትሬ እንጂ ተራምጄ አልነበረም፡፡
ይህን ሁሉ ስሞክር የነበረው በይ በይ ተብዬ እንጂ በይ በይ ብሎኝ አይደለም፡፡
ነገም ይሆን የዛሬ አመት፣ የዛሬ አምስት አመት፣ የዛሬ አስር አመት (ወይኔ ጉዴ! እዛስ ባልደረስኩ!)
ድንግልናዬን ማስወሰድ ሳይሆን መስጠት ነው የምፈልገው፡፡ ድንግልናዬን መገላገል ሳይሆን አሽሞንሙኜ መሸኘት ነው የምሻው፡፡
ድንግልናዬን ማስገርሰስ ሳይሆን መጋራት ነው የምመኘው፡፡
Top of Form
Unlike - Comment - Share
Bottom of Form

Read 6442 times