Saturday, 13 June 2015 15:34

የማሸነፍ አባዜ!

Written by  ወጋየሁ ማዴቦ
Rate this item
(5 votes)

…ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፌ፣ ብዙ አንስቼ ብዙ ጥዬ፣ ብዙ አዝኜ ተደስቼ ... ከተጠለልኩበት የሽንፈት ድንኳን፣ ከሱስና ከተስፋ መቁረጥ መንደር፣ የዓለምን ጨለማ ዕኩለ ሌሊቱ ላይ ሆኜ በምዳክርበት ወቅት ላይ ነው፡፡ አዎ… የዛሬ ሶስት ዓመት ለሥራ ደብረ ማርቆስ ሄጄ፣ ከከተማው ትልቅ አደባባይ ወረድ ብሎ ካሉት ሱቆች አንዱ በር ላይ ቆሜ ሰው ስጠብቅ የሰማሁት ድምጽ … ህይወት አጎናፀፈኝ ሠላም...ተስፋ…ብርሃን…ደስታ…ፍቅር ድል…አያሌ ነገሮችን  ወደ ሕይወቴ ይዞ መጥቶ ነበር፡፡
“ይ…ቅ…ር…ታ…!” ከመላዕክቶች መንግስት የተላከች የምትመስል ወጣት እንደ ወፍ ስታዜም ሰማሁዋት፡፡
“ይቅርታ…ወንድሜ!” ብላኝ ወደ ኋላ አጣምርያቸው የነበሩትን እጆቼን ስትነካቸው እንደ ሰመመን ይታወቀኝ ነበር፡፡ ቢራቢሮዎች ሲበሩ፣ አበቦች ሲወዛወዙ የሰማሁ መሰለኝ፡፡ ከዚያም የሆነ እሳት የሚተፉ የሰው ጣቶች ነኩኝ፡፡ ከደረቀው ገላ አንገቴ ብቻ ትንሽ ወደ ኋላ መዞር ተሳካለት፡፡
በፍርሃት የታጀቡ ግን የሚያበሩ አይኖች…እንደ ዋዛ ሸብ ካደረገችው ሻሽ ሥር ሾልኮ የወጣውን ሉጫ ፀጉር የተሸከመ ረዥም አንገት…ታየኝ፡፡ ፊቴ ድቅን ያለችው እማዬ መስላኝ ነበር፤ እናቴ፡፡
“እጆችህን አጣምረህ ቆመህ ስትተክዝ ስላየሁህ ነው…በእናትህ እጆችህን አላቃቸው…”
ሠምቻታለሁ፤ ግን ማላቀቅ አልቻልኩም፡፡
“አባዬና እማዬ ከተለያዩ በኋላ አባቴ ሁሌ አሁን አንተ እንደቆምከው እጆቹን ወደ ኋላ አጣምሮ፣ ቆሞ ሲተክዝና ሲያዝን እያየሁ ነው ያደግሁት…ወንድ ልጅ እንደሱ ሲቆም አልወድም” ሠምቻታለሁ…ግን …፡፡
“እጆችህን አላቃቸው በፈጠረህ…”
አልቻልኩም… ፡፡
እሷ ዞራ ባታላቅቃቸው ኖሮ፣ እጆቼ እስከ ዛሬ እንደተጣመሩ ይቀሩ ነበር፡፡ እኔም ደብረማርቆስ አደባባይ ሥር ደርቄ ቀርቼ ነበር፡፡
 ነፍስ…ዘራችብኝ፡፡
“ወንድ ልጅ አንገቱን አይደፋም! አይዞህ! እሺ?”
“እሺ” አልኳት፡፡
ፈገግ አለች፡፡ የእማዬ ጓሮ የቡና አበባዎች ትዝ አሉኝ፡፡ እንደ ቡና አበባ የፈኩ ጥርሶች፡፡ ይህች ልጅ…ከእናቴ ጋር ምን አላት?
ማርቲን በዚህ ሁኔታ ነበር የተዋወቅኋት፡፡
ማርቲ ሚሊዮን ጥሩ ነገሮች አሏት፡፡ እሷን የምወድበት ሚሊዮን ምክንያቶች አሉኝ ማለት ነው። ሚሊዮን መልካም ነገሮች ያሏትን ልጅ ማን ነው የማይወደው?
ማርቲ እንደ “ፍቅር እስከ መቃብር”ዋ ሰብለወንጌል ናት…ንፁህ ጨዋና አፍቃሪ ናት። አትዋሽም አትደብቅም…እንደ ህጻን ልጅ ትጠነቀቅልኛለች…እንደ እናቴ ትሳሳልኛለች፡፡
ማርቲን የምወድበት ሚሊዮን ምክንያቶች አሉኝ…ነገር ግን አንዲት ኢምንት የሆነች እንከን አላት፤ እኔ የማልወድላት፡፡ ግን አንድ እና ሚሊዮን እንዴት ይነጻፀራል? አንድ ሆና ብቻዋን ከሚሊዮን በተቃራኒ የቆመች ደንቃራ አለቻት፡፡ ማርቲ ካላሸነፈች መኖር አትችልም፡፡ እንዴት ሁሌ ማሸነፍ ይቻላል?
የማርቲ የህልውና መሰረት ማሸነፍ ብቻ ነው። የማታሸንፍ ከመሰላት አትገጥምም፤ የተሸነፈች ከመሰላት ደግሞ ያንን ሁኔታ ለመቀልበስ የማትምሰው ጉድጓድ የለም፡፡  
በአንድ የተረገመ ቀን በጣም የምወደው ጓደኛዬ ለሥራ የሚሆን ገንዘብ እንዳበድረው አበክሮ ተማፀነኝ፡፡ ፍቅረኛዬ እንደመሆንዋ የሁለታችን የሆነውን ነገር ግን ለብቻዬ ሠርቼ ያጠራቀምኩትን ገንዘብ “ላበድረው ወይስ አላበድረው?” እያልኩ ከራሴ ጋር ተወዛገብኩ፡፡
ጉዳዩን ለማርቲ ባማክራትና አይቻልም ብትለኝ፣ ገንዘቡን ለባልንጀራዬ ማበደር የማይታሰብ ሊሆን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከምወደው ጓደኛዬ ጋር ያቀያይመኛል፡፡ ስለዚህ ማርቲ ሳታውቅ “ቶሎ እመልሳለሁ” የሚለውን የሕይወት ዘመን ባልንጀራዬን ቃል አምኜ፣ ገንዘባችንን አንስቼ ለጓደኛዬ አበደርኩት፡፡ ቶሎ … ማለት መቼ ይሆን?
ሳምንት…ወር…መንፈቅ…ዓመት…?
ባልንጀራዬ ግን ገንዘቡን እንደሰጠሁት ቶሎ በሚለው ቃል ምትክ…የቤት መኪናውን ከነሙሉ ውክልናው በሬ ላይ አቁሞት ወዳልነገረኝ መንገድ ሄደ፡፡
ማርቲ አበደች! እሷ ሠርግ ይደገስ ስትል፣ እኔ የቤት መኪና እንግዛ ብያት ሳንግባባ ቀርተን ስለነበር ግጥምጥሞሹ እሳት አቀጣጠለ፡፡ መኪናውን የገዛሁ ነበር የመሰላት፡፡ ምን ብዬ ልንገራት? ነገሮቹ ሁሉ በእኔ ከሃዲነትና እምቢ ባይነት ተደመደሙ። እሷ ካመረረች ቤተሰብ፣ ጓደኛ፣ ካህን … ማንም አይመልሳትም፡፡ ይህን እያወቅሁ በፈፀምኩት ስህተት ጥላኝ ሄደች…ወደ ጨለማዬ መልሳኝ፡፡
አርባዎቹን ያለፈ ወንድ የማይችላቸው ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡ ዋናው ማልቀስ ይመስለኛል። ሁለተኛው አምባጓሮ፡፡ ሶስተኛው መለመን፡፡ እኔ ግን ሁሉንም ቻልኩበት…በተለይ ማልቀስና መለመኑን፡፡ የእሷን ልብ ግን ማራራት አልቻልኩም። ጭራሽ ቤቷን ቀየረች፤ ስልኳን ጠረቀመች…የፌስ ቡክ ገጿን ዘጋች…ኢ-ሜይል አትመልስም፡፡ እምጥ ትግባ ስምጥ የሚያውቅ ጠፋ፡፡ ስሟንና መልኳን ጭምር የቀየረች ሁሉ መስሎኝ ነበር፡፡
የኔ ፀሐይና የኔ ጨረቃ ላይመለሱ የጠለቁ በመሠለኝ ጨለማ ውስጥ ያላሰብኩት ነገር ተከሰተ፡፡
ይህችን ጦሰኛ መኪና እየነዳሁ ሳለ፣ ቃሊቲ ከመንገድ ትራንስፖርት መሥሪያ ቤት ዝቅ ብሎ የዋናው አስፋልት ዳር ይዛ ስትራመድ የነበረችው ሃና፤ የኔ መኪና ውሃ እንዳይረጭባት ፈርታ ስትጠነቀቅ፣ የመንገዱ ጠርዝ አንሸራቷት አንድ እግሯ ዝቅ ብሎ ካለው ጭቃ ውስጥ ገብቶ፣ ከፍ ካለው ደረቅ ቦታ በቆመችበት፣ በሌላኛው እግሯ ሚዟኗን ለመጠበቅ ስትውተረተርና ቦርሳዋን ጥላ በፍርሃት ስትወራጭ አየኋት…
በዚያች ቅጽበት ከመኪናው ዘሎ ወርዶ፣ እሷን ጐትቶ ከጭቃ ውስጥ የሚያወጣ ሰው መንገድ ዘጋ ይባላል? ከኋላዬ የነበረው የከባድ መኪና ጡሩንባ የምሬት ነበር፡፡ በኔ በኩል የነበረውን ረዳት፤ “እናንተ ቦሌ መንገድ ላይ ስለማታሽከረክሩ ለሀገር መሪ ቆማችሁ አታውቁም አይፈረድባችሁም!” አልኩትና ዳር ወጣሁለት፡፡ የሀናን ቦርሳ ማንሳት አለብኝ…መኪና ውስጥ አስገብቼ ላስቀምጣት ይገባኛል…ጭቃ የነካ እግሯንና ጫማዋን ማጠብ አለብኝ…ብዙ ሥራ ነበረብኝ፡፡
ረዳቱ እያሾፈ፤ “የየት ሀገር መሪ ናት?” አለኝ፡፡
“የነፍሴ መሪ” ስል ኮስተር ብዬ መለስኩለት፡፡
“ሕይወት ይቀጥላል…” የሚለውን አባባል መጀመሪያ የተናገረው ማን ይሆን?
ከማርታ ጋር ስንተዋወቅ የሚነገር ታሪክ አልነበረኝም፡፡
ቢኖር እንኳን ለማርታ ሰብዕና፣ ለእሷ ንፁህ ሕይወት የሚመጥን ታሪክ አልነበረኝምና…ምንም አልነገርኳትም፡፡
ለሀና ግን በየቀኑ የሚነገር የማርታ ታሪክ ነበረኝ። እሷም ሆንብላ እየነካካች ታስቀባጥረኛለች፡፡ እኔም ማውራቴን አላቆምም ግን ሁሌም መቋጫዋ አንድ ነው፡፡ “አሁን የኔ ነህ፤ ማንም ወንድ አስፋልት ዳር ላይ የማያውቃትን ሴት ጭቃ እግር አያጥብላትም፤ ካንተ በስተቀር፤ አንተ ደግሞ የኔ የሀና ፍቅረኛ ነህ፡፡”
አራት ነጥብ!!
*   *   *
አንድ እሁድ ተሲያት በኋላ በዚህችው ጦሰኛ መኪና ሰው ቀጥሮን ወደ ቄራ እየሄድን ነበር፡፡ መሃል ላይ “ዛሬ እኮ ማርታን አየሁዋት” አለችኝ ሃና ድንገት፡፡
ክው ብዬ ደነገጥኩኝ፡፡  ግን ምን አስደነገጠኝ?
“ታውቂያታለሽ እንዴ?”
“አዎን!”
“እንዴት?”
“ዝርዝሩ ምን ያደርግልሃል………?”
“ያደርግልኛል”
“በእኔ ቦታ ያለች ማንኛዋም ሴት ማርታን ለማወቅ የማትፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም…”
“ለምን?”
“ትፈራታለህ……ስሟ ያስፈራሀል…….. ኧረ መንፈሷ ሁሉ …. እሷንማ ማወቅ ነበረብኝ”
ቄራ ብሎም ካፌ ደርሰን በረንዳው ላይ ተቀመጥን፡፡
“የቱ ጋ ነበር ያየሻት?”
“ቦሌ….ኖክ ያለውን ዜብራ ስታቋርጥ……”
“አየችን…?”
“ዜብራውን ስታቋርጥ በድንዋ ነበር የሚራመደው፤ አይታሃለች…”
ሃናን ትኩር ብዬ አየሁዋት…….የሆነ ነገር ልትናገር አፏ ላይ ነበር፡፡
“ምንድነው? ሃኒ…” አልኳት፡፡
“ምላሴን አወጣሁባት” አለችኝ፡፡
ክው አልኩኝ… ጭንቅላቴን የተመታሁ ያህል አዞረኝ፡፡
“ምነው! ምነው ሃኒ….ምን አደረኩሽ በእናትሽ…?”
“ሶሪ ጌታዬ…ዊርድ ነገር ነው ያደረኩት….አም ሪሊ ሶሪ…….”
“አይይይ ሃኒ…….ማርታን አታውቃያትም ማለት ነው”
“ምን ለማለት ፈልገህ ነው?” አፈጠጠችብኝ፡፡
“ኡ.. ፍ.. ፍ.. ፍ.. ፍ.. ፍ…” በረዥሙ ተነፈስኩኝ።
“ትፈራታለህ አይደል?” ሃና ጠየቀችኝ፡፡
“እኔ’ጃ ስሜቱ…..በቃላት አይገለጽም”
ሃናን ከፋት…ሃና ምስኪን ናት፡፡
ከወራት ስቃይ በኋላ እስዋን ያገኘኋት ዕለት ነበር ጥሩ እንቅልፍ የወሰደኝ፡፡ እሷን ማጣት አልፈልግም። ፈራኋት፡፡ እንደዚያ ሲከፋት አይቻት አላውቅም። የሃናን ፊት ለመሸሽ ስሞክር አንድ ላዳ ታክሲ ወደ ካፌው በረንዳ ተጠግቶ ሲቆም ተመለከትኩ፡፡ ከቆመው ታክሲ ውስጥም አንዲት ሴት ስትወርድ እኔና ሃና እኩል አየናት፡፡
ገባኦን ላይ እያሱ ጠላቶቹን እየተዋጋ ሲመሽበት፣ አምላኩን ለምኖ ፀሐይ ቆማለት ነበር…ይህንን ታሪክ አንድ ሰባኪ “ፀሐይ ሳትሆን ምድር ናት የቆመችው” ያለው ትዝ አለኝ፡፡ ቄራ ብሎም ካፌ አካባቢ ምድር ቆማ ነበር፡፡
የኔ ልብ ቆሟል…የሃና ቁጣ ቆሟል….የማርታ አይን እሳት ይረጫል… ያለቀሰች ትመስላለች፡፡ ቀጥ ብላ እኛ ወደተቀመጥንበት መጣች፡፡ ሲቃ ነገር ያዳመጥኩ ይመስለኛል….ፊቷን ደግሜ አላየሁትም…ትንፍሽ አላልኩም…አልተንቀሳቀስኩም፡፡ በንዴት የጦፈች ሴት፣ በሲቃ የታፈነ ድምጽ ግን ሰምቻለሁ። እሱም በቀረው ዘመኔ ሁሉ የማልረሳው የማርታ ድምጽ ነበር፡፡
“አ ባ ቢ…የመኪናውን ቁልፍ ስጠኝኝኝኝ…” ያኔ ያለቀሠች ይመስለኛል……ከመቀመጫዬ ሳልንቀሳቀስ፣ ከበድን አካሌ ላይ ደርቆ የነበረውን ቁልፍ የያዘውን እጄን ሙሴ በበትሩ ደገፈው መሠለኝ…ወደ ማርታ ተዘረጋላት…..ወሰደችው፡፡
ፊቷን የማይበት አቅም አልነበረኝም…ግን አይኖቿ ላይ የእንባ ዘለላዎች ስለመኖራቸው እርግጠኛ ነኝ፡፡
ማርታ ሙሉ ክብ ዞራ የመኪናዋን አፍንጫ ወደ መስቀለኛው ስታንቀሳቅሰው ምድር ተንቀሳቀሰች። የሰዎችና የመኪኖች ድምጽ መሰማት ተጀመረ፡፡ ማርታ እንዲህ ናት፡፡
…ካላሸነፈች መኖር አትችልም!!
የማሸነፍ አባዜ ተጠናውቷታል፡፡
ሃናም ተነስታ እየተጣደፈች ማርታ የመጣችበት ታክሲ ውስጥ ገባች፡፡ ሁሉም ካላሸነፉ መኖር አይችሉም እንዴ……….?

Read 2614 times