Saturday, 13 June 2015 14:28

እነማን በብዛት ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ?

Written by 
Rate this item
(7 votes)

       ጆቫጎ የተሰኘው አለማቀፍ የመንገደኞች የሆቴል ቀጠሮ አስያዥ ድረገጽ ከውጭ አገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ፣ ወደ ውጭ አገራት የሚጓዙና በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ መንገደኞችን በተመለከተ የሰራውን ጥናት ይፋ ማድረጉን ሜል ኤንድ ጋርዲያን ከትናንት በስቲያ ዘገበ፡፡በውጭ አገራት የሚኖሩ ትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ አለማቀፍ መንገደኞች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚጓዙ የጠቆመው ጥናቱ፣ ወደ ኢትዮጵያ በርካታ መንገደኞች የሚመጡባቸው ቀዳሚዎቹ አምስት አገራት አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ደቡብ አፍሪካና ኬንያ ናቸው ብሏል፡፡  ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ጎብኝዎች ቁጥር ባለፉት አምስት አመታት ከፍተኛ እንደነበር የገለጸው ጥናቱ፣ እ.ኤ.አ በ2010 በድረ ገጹ አማካይነት በኢትዮጵያ የሆቴል ቀጠሮ ያስያዙ መንገደኞች 468 ሺህ እንደነበሩና ይህ ቁጥር በ2013 ወደ 681 ሺህ ከፍ ማለቱን ገልጾ፣ ቁጥሩ እስከ 2017 ከ1.2 ሚሊዮን በላይ እንደሚደርስ ያለውን ግምት አስቀምጧል፡፡ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት በድረገጹ አማካይነት የሆቴል ቀጠሮ ካስያዙ መንገደኞች፣ በከፍተኛ ርቀት ላይ የተገኘው የጃፓኗ ቶክዮ ከተማ መንገደኛ እንደነበርና ቀጠሮውን ያስያዘው በ10ሺህ 89
ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ ሆኖ እንደነበር ጠቁሟል፡፡ በድረገጹ በኩል ቀጠሮ አስይዘው ወደተለያዩ አገራት የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን መንደገኞችን በተመለከተም፣ ኢትዮጵያውያን መንገደኞች በብዛት የሚሄዱባቸው አገራት ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ አይቬሪኮስት፣ ጅቡቲና የተባበሩት አረብ ኢሜሬትስ ናቸው ብሏል ጥናቱ፡፡
በአገር ውስጥ የሚደረገውን የመንገደኞች ዝውውር በተመለከተም፣ አዲስ አበባ ከአገሪቱ ከተሞች በአገር ውስጥ መንገደኞች መዳረሻነት ቀዳሚነቱን መያዟንና ከመንገደኞቹ መካከል 13 በመቶ ሽፋን እንዳላት የገለጸው ጥናቱ፤ ጎንደር በ10 በመቶ፣ ላሊበላ በ9 በመቶ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን እንደያዙ ጠቁሟል፡፡ ከሃገር ውስጥ ጎብኝዎች 6 በመቶ የሚሆኑት ሃዋሳን ምርጫቸው አድርገዋል  ብሏል፡፡ ወደ ሌሎች የአገሪቱ ከተሞች በመጓዝ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች 60 በመቶውን ሲይዙ፣ የሃዋሳ ነዋሪዎች 2 በመቶ፣ የተቀሩት የአገሪቱ ከተሞች ደግሞ 38 በመቶውን ድርሻ ይይዛሉ ተብሏል፡፡

Read 3979 times