Saturday, 06 June 2015 14:11

‹‹ዲሞ›› ጨዋታ አይቆጡም ‹‹ጌታ››

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(1 Vote)

አሌክሲስ ዲ. ቶኮቪሌ በ1945 ዓ.ም (እኤአ) ግድም፤ ‹‹How Democracy affects the relation of masters and servants›› በሚል ርዕስ አንድ መጣጥፍ ፅፎ ነበር፡፡ እኔም በዚህ መጣጥፍ፤ ይህንኑ የቶኮቪሌ ፅሁፍ መሠረት አድርጌ፤ የሐሳብ ‹‹ቶኒክ›› ሊሆኑ የሚችሉ አንዳንድ ነገሮችን ለማንሳት እሞክራለሁ - እንዳሰብኩት ከተሳካልኝ፡፡ ቶኮቪሌ ‹‹masters and servants›› ሲል ያፈራቸውን ቃላት፤ እኔ ‹‹ጌታ›› እና ‹‹ሎሌ›› በሚል ልተረጉማቸው ብሞክርም፤ በፍቺ ቀጣሪ እና ተቀጣሪ ወይም አዛዥ እና ታዛዥ ወይም መሪ እና ተመሪ ወዘተ የሚሉ ሐሳቦችን እንዲይዝ እፈልጋለሁ፡፡
እስከ ዛሬ ድረስ፤ ሐብታም ወይም ድሀ የሚባሉ ሰዎች የሌሉበት፤ ‹‹ጌታ›› እና ‹‹ሎሌ›› የሚል ማህበራዊ ክፍፍል የማይታይበት ሐገር በታሪክ አልታየም፡፡ ስለዚህ የዴሞክራሲ መኖር እንደዚህ ዓይነት መደቦችን አያጠፋቸውም፡፡ ነገር ግን፤ በሁለቱ መደቦች መካከል ያለውን የእርስ በርስ ግንኙነት ባህርይ እንዲለወጥ ማድረጉ አይቀርም፡፡ እናም፤ በዲሞክራሲያዊ ስርዐት ውስጥ የ‹‹ጌታ›› እና ‹‹ሎሌ›› ግንኙት ምን እንደሚመስል ለማየት፤ የቶኮቪሌን መጣጥፍ መሠረት በማድረግ ትንሽ ፍተሻ አደርጋለሁ፡፡
ቶኮቪሌ እንዲህ ሲል ይጀምራል፡- ‹‹በአንድ ወቅት፤ አውሮፓን ለረጅም ጊዜ ሲጎብኝ የቆየ አንድ አሜሪካዊ እንዲህ ብሎኝ ነበር፤ ‹የእንግሊዛውያን የሠራተኛ አያያዝ የማያፈናፍን እና ፍፁም የበላይነት የሚንፀባረቅበት ነው፡፡ ለእኛ ለአሜሪካውያን እንዲህ ያለ ነገር እንግዳ እና አስገራሚ ጉዳይ ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ ፈረንሳውያን ሠራተኞቻቸውን ቤተሰባዊ መንፈስን በተላበሰ ወይም ትህትናን በተሞላበት አኳኋን ሲይዟቸው እንመለከታለን። ይህም ለእኛ ለአሜሪካውያን ግራ አጋቢ ነው፡፡ የፈረንሳውያን ቀጣሪዎች የሠራተኞች አያያዝ፤ ለማዘዝ የፈራ ሰው ሁኔታ ይንፀባረቅበታል፡፡ በፈረንሳውያን ዘንድ የጌታ እና የሎሌ ድንበር በግልፅ የተሰመረ አይደለም›› ይላል፡፡
ቶኮቪሌ አያይዞ፤ ‹‹ይህ አስተያየት ትክክል ይመስለኛል›› ካለ በኋላ፤ ‹‹እኔም ብዙ ጊዜ እንዲህ ዓይነት አስተያየት መስጠቴን አስታውሳለሁ፡፡ በኔ አመለካከት በእንግሊዝ የጌታ እና የሎሌ ግንኙነት ድንበር ጠበቅ ያለ ሲሆን፤ በተቃራኒው በፈረንሳይ ውስጥ ዘና ያለ ነገር ይታያል፡፡ እንደኔ ገጠመኞች፤ ‹ጌታ› እጅግ ከፍ ብሎ ወይም ዝቅ ብሎ የሚታይባቸው፤ እንደ ፈረንሳይ እና እንግሊዝ ያለ ሐገር አይቼ አላውቅም›› በማለት አትቷል፡፡
‹‹ታዲያ በኒህ በሁለት ፅንፎች መካከል የተቀመጠች አንዲት ሐገር አለች፡፡ እሷም አሜሪካ ነች፡፡ የሦስቱን ሐገራት ሁኔታ የተመለከተ ሰው ከፍ ብሎ ከተገለፀው ነገር የተለየ ግንዛቤ ሊይዝ አይችልም›› የሚለው ቶኮቪሌ፤ ‹‹ታዲያ የእነዚህ ነገሮች መንስዔ ምንድን ነው?›› የሚል ጥያቄ አንስቶ፤ መልስ ለማግኘት ነገሩን በዝርዝር ማየት አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ ማብራሪያውን ይቀጥላል፡፡
ግን የቶኮቪሌን ማብራሪያ ከማየታችን በፊት፤ ከሦስት እና ከአራት አስርታት በፊት፤ የእኛን ሐገር ‹‹የጌታ›› እና ‹‹ሎሌ›› ግንኙነት ምን እንደሚመስል ለማሳየት ‹‹አደፍርስ›› በተሰኘው የዳኛቸው ወርቁ ልቦለድ የሚገኙ ሁለት ገፀ ባህርያት የሚያደርጉትን ውይይት አንስቻለሁ። ተረኩ፤ በዲሞክራሲያዊ ስርዐት ውስጥ የ‹‹masters›› እና የ‹‹servants››ግንኙነት ምን እንደሚመስል ለማሳየት ያግዛል፡፡ ወይዘሮ አሰጋሽ፤ ቸግሮት እህል ሊበደር የመጣ አንድ ጭሰኛ ጋር ይነጋገራሉ፡፡ ‹‹በመንገድ ስንገናኝ ሸረር ብሎ መንገድ አለቀቀልኝም፤ አግዘኝ ብለው እምቢ አለ›› በሚል ቂም ይዘውበታል፡፡ እናም ነገር እያሳቀሉ እንዲህ ይሉታል፤
‹‹[እግዚአብሔር] የበደሉትን ሰዎች እግሮች ተንበርክኮ ያጥባል - እንደፈለጋችሁ - እንደምላዳችሁ - እንደ ስሜታችሁ ኑሩ የሚል ይመስላል ለብልሃቱ። አንድ ቀን የሱን ትልቅነት የሱን ወሰን የለሽነት፤ የሱን አይመረመሬነት ዘንጋ ያልን ጊዜ ድራሻችንን ሊያጠፋ። ሊያመጣው ውርጅብኙን፡፡ ሥልጣናችሁን በደንብ አልተጠቀማችሁበትም - ለክብሬ የሚገባኝን አላቀረባችሁልኝም- ….ስለዚህ እኔም የምሰራውን አውቃለሁ ሊለን… ተጓባቢውን ጎረምሳ፣ ጥጋብ የነፋውን፣ በዱላ የሚመላጎደውን ዱለኛ፤ ለባለርስቱ፣ ለባላባቱ የማይታዘዘውን ገበሬ፤ አንገቱን ሰብረው ጭራውን እንደ ውሻ እንዲሸጉብ እስኪያደርጉት ድረስ - ሊለን! ሊያመጣው የጭቃ ጅራፉን……›› እያሉ፤ ያስፈራሩታል፣ ያንጣጡታል፣ ይወርፉታል፡፡
‹‹ገባኝኮ አሁን ገባኝ›› ይላል እህል ሊበደር የመጣው ጭሰኛ፡፡ እሳቸው ግን መለስ አይሉም፡፡ የነገር አኮርባጃችውን ይሰነዝራሉ፤ የጭቃ ጅራፋቸውን ያለ ፋታ ይሰነዝራሉ፡፡ወ/ሮ አሰጋሽ፤ ያን ‹‹ይገባኝል….ይገባኛል›› እያለ የሚለማመጣቸውን ጭሰኛ፤ ኑሮውን እና እግዚአብሔርን እየታከኩ፤ ደግሞም ‹‹ቆይ ቆይ ልጨርስ!...›› እያሉ በወቀሳና በትችት ዱላ ያርበደብዱታል፡፡
‹‹ቆይ ቆይ ልጨርስ! እግዚአብሔር ሁልጊዜ ማስታወሻ ነገር ይልካል፣ ለሚረሱት ሁሉ፡፡ ማጉረምረም የለብንም - ለኛ ሲል ነው የሚያደርገው - እንዲገባን ያሻል። አስቀድመን አስታውሰነው በነበር፤ እሱም በበትረ መንግስቱ ባልረሳን፤ የፈለግነውን በሰጠን ነበር -ጤፍ - ስንዴ - ገብስ - ማሽላ - ባቄላ - ጨረቂት ያውልህ የፈለገህን ያህል ባለን ነበር፡፡ አሁን ግን ይኸውልህ - የእጅን ፈለግ፣ የእግርህን ንቃቃት፣ የለበስከውን ቡትቶ…›› ይሉታል፤ እሬሳ ላይ የሚተኩሱት ወ/ሮ አሰጋሽ፡፡ ጭሰኛው እየደጋገመ፤ ‹‹ምን‘ኮ አላጣሁትም….›› እያለ ቢለምናቸውም፤ ወ/ሮ አሰጋሽ መለስ አይሉለትም፡፡፡
‹‹ዐውቃለሁ እመየቴ!
‹‹ምናልባት ታውቀው ይሆናል፤ ግን አዙረህ ብትመለከት፣ ሥራ ላይ እንዳልዋለ ልትረዳ ትችላለህ፡፡ አሁን ለምሳሌ ትንሽ ማሽላ ልትበደር መጣህ፡፡ እርግጥ ነው፤ የዛሬን አያድርገውና አክባሪዬና መልካም ሰው ነበርህ፡፡ ነገር ግን አምና ትዝ ይልህ እንደሁ፤ ትዝ ይልሃል፤ ርግጠኛ ነኝ፤ ላጨዳና ለውቂያ እንድታግዘኝ ብጠይቅህ ምን ብለህ ነበር የመለስክልኝ? ‹ደህና ዋል ስልቻ፣ ፍሬውን ከትቻለሁ› …. ራሴንም አላጨድሁ - የራሴንም አልወቃሁ፤ እኔም የሚረዳኝ እፈልጋለሁ! አላልክም? ለመንግስት እኮ ግብር ከፋይ ነኝ፤ ግዳጅ የለብኝም እስከዚህ አላልክም? አምቧትረህብን ነበር እኮ በል፤ ታዥረህብን ነበር! ‹ዝናብ ባይመጣ ሁሉ ቤት፤ እንግዳ ባይመጣ ሁሉ ሴት!› አዎ፤ ርግጥ ነው፤ ግዳጅ የለብህም …. ግን እየው…. እየው…. ጊዜው ባይሆንልህ ፤ እንዲህ ሱልል ብለህ፤ ጭራህን እንደ ቡችላ ስታወናውን -! ‹የወደዱትን ቢያጡ፤ የጠሉትን ይቀላውጡ!› በኔ ላይ ተንዣርረህብኝ ነበር…   
 ‹‹‹ጠጉራም ውሻ አለ ሲሉት በራብ ይሞት› የለም…?
‹‹በጣም ኩሩ ነህ፡፡ ስለዚህ ነው ችግር የጎለሰሰህ … ግን ምን ታደርግ፤ ‹አወራ ዶሮ በየፍጉ ክምር ላይ ቆሞ ይጮሃል› … እኔን ተመልከተኝ ለምሳሌ - አዎ እግዜር ሞገሱን፣ ንጉሠ ነገሥቴ ክብርን አልነሡኝም፡፡ ሆኖም አልኮራም፤ እንዴት ልኮራ እችላለሁ? ማነኝና! ትል ለራሴ! ትንሽ ፍጥረት - ምናምን! ግን እንደምታየው ራሴን ዝቅ ዝቅ በማድረጌ እግዜርና ንጉሤ ከፍ ከፍ አደረጉኝ በፊታቸው … በሰማያዊ ኃይል የጎለበተ እንዲህ ነው ይኸውልህ … እግዜር ሞገሱን ሰጥቶ፤ በንጉሤ ፊትም ሞገስ እንዳገኝ አደረገኝ…
‹‹የዱሮው ጊዜ ይሻል ነበረ እመየቴ፤ እንዲህ እንደ ዛሬው ሳይሆን ባላባትና ገበሬ የሚተሳሰቡበት …
‹‹እንዴታ ምን ጥርጥር አለው እንዲህ እንደዛሬ የጌታና አሽከር መንገራበብ ያልነበረበት- በየጊዜው የሚያፈጠፍጥ ክፉ ዐመል ... ጥሩው ጊዜ አለፈ፤ ዓለማችሁን ያያቸሁበት - አደንጓሬው፣ በቆሎው፣ ደንጎሎው፣ ጨረቂቱ፣ ዘንጋዳው … ምን ያረጋል ብቻ ያለፈውን ቢያስታውሱት? አሁን ማስታወሱ አይበጅም፡፡ ዱሮ ዱሮ ነው - ስለዱሮው የረሳሁትን. ..! ‹ፍላጻ ባየር ውስጥ አለፎ ፍለጋ አይተውም!› እና አሁን ታዲያ የመጣኸው ትንሽ ዘንጋዳ ለመበደር ነው አልክ ...?››
‹‹ነበራ እመየቴ ማስቸገሬ ባይሆን…
‹‹ለመግዛት ነው የምትፈልገው…?
‹‹ከየቴ እመየቴ፤ ብሩ ከየት ተገኝቶ? በዚያው ባይነቱ ለመክፈል ነው እንጂ በትሣሥ...
‹‹ ነገር ማሞዳሞድ ገንዘብ አይሆንም ይኸውልህ! ‹ለቀንዳም በሬ ቤት አትከልክለው፤ ቀንዱ ይከለክለዋል!› ነው››
‹‹መቼምኮ የሚሉት ሳይገባኝ ቀርቶ አይደለም ... ብቻ እንዲያው ሰኔና ሰኞ…
‹‹አዎ ካጡ ወዲያ ማንኛውም ነገር አያምር ‹በሰም የተጣበቀ ጥርስ፤ ቢስቁበት አይደምቅ፤ ቢበሉበት አያደቅ..!›
‹‹ታዲያ ምን ተሻለኝ ይመስለዎታል አሁን...?
‹‹መከልከሌ አይደለም እኮ ‹ሰው ሆኖ የማይብስ እንጨት ሆኖ የማይጨስ!› … ‹ሰው ከስህተት ብረት ከዝገት..›
‹‹ታዲያ ያሉትን ብለውኝ ብሄድ…
‹‹ ‹ብረት ካልፈላ አይላላ› - እንዲህ ልክ ገባህ ይኸውልህ…
‹‹ድሮምኮ እንዲያው ባንጣጣም ይሆናሊ …
‹‹ያለፈው አለፈ፤ አሁን አንድ ልልህ የምፈልገው… ምን ነበር እቴ! አዎ፤ ለሁሉ እግዚአብሔርን... ማለቴ ‹ከሆነ ወዲያ ደም ማልቀስ ድንጋይ መንከስ› አያስፈልግም.. ‹ወረቱን እንደተቀማ ነጋዴ ዋግ እንደመታው ስንዴ› መሟሰስ የወንድ ልጅ ተግባር አይደለም…›› እያሉ ካረገረጉበት በኋላ፤
‹‹እና አሁን የምትፈልገው አስራ አምስት ቁና መሆኑ ነው…?
‹‹አዎ እመየቴ ፈቃድዎ ከሆነ …
‹‹ጥሩ ነው.. አሥራ አምስት ቁና.. ዘጠኝ ቁና እሰጥሃለሁ ማለት ነው፤ በትሣሥ አሥራምስት አድርገህ ትመልሳለህ..
‹‹አይ እኔ እንኳን…
‹‹እንደምታየው ወለድ አልፈልግም ያው ዓይነት ባይነቱ ነው በብዛት አምርተህ ከምታገባው፡፡ አዎ ብዙ አይደልም፡፡ ደግሞ በደንብ እየተንቸረፈፈ ይሰፈርልሃል፤ ‹ወዶ የዋጡት ቅልጥም ከፍርምባ ይጥም›
‹‹ትንሽ አልበዛም እመየቴ..;
‹‹ በዛ? አይ እንግዲያው ከበዛ ሌላ ሰው ብትጠይቅ ይሻላል፡፡ ……
‹‹ይሁና እንግዲያው መቼስ ምን አደርጋለሁ..
‹‹አዎ እንዲያ ይሻላል... ዘንድሮ አመናን አይደል፤ የምታደርገው ነገር የለም… በነገራችን ላይ እኔ ላንተ አንድ ነገር ስውልልህ አንተም ለኔ መዋል ሳይኖርብህ አይቀርም... የክርስቲያን ምልክቱ ነው…
‹‹ምን ከፍቶኝ የሚሆንለኝ ከሆነ…
‹‹የክርስቲያን ምልክቱ ነው ሲውሉልህ መዋል ነው ትልቁ ትምርት እና ታዲያ እዚያ አንተ አዋሳኝ ያለውን ድርቆሼን ብታስተጫጭደኝ… እንደምታየው ወለድ አልጠየኩህም …… ድርቆሹን እንግዲህ ካጨድከው በኋላ … አንድ ሰማኒያ ሸክም ቢሆን ነው… እያመጣህ እደጄ እንድትከምረው… መንገዱ ትንሽ ይርቅሃል ... ስለዚህ አላቻኩልህም- ባስራ አምስት ቀንም ቢሆን በወር ልትጨርሰው ትችላለህ...››
እንዲህ ሲመላለሱ ቆይተው፤ ‹‹ቢኖረኝ ነው ወደኔ የመጣኸው›› ሲሉት፤
‹‹የመሄጃ እጦት ነው እመየቴ ….›› ይላል፡፡ እርሳቸውም፤
‹‹ግርምቢጠኛነትህን ትንሽ አብርዶልሃል፤ መቼስ ጨርሶም ባይጠፋ፤ አዎ፤ ለወደፊቱ መንገድ ስንገናኝም ቢሆን ከፊትለፊቴ ሸረር ብለህ መንገዱን ብትለቅልኝ ነውር የለውም…. አንዳንዴ እንደሚማልግ ነብር፤ አንዳንዴ እየተፍረገረገ እንደሚለማመጥ ድመት መሆን ያስተዛዝባል …. አዎ ፊት ማጭገግ ወይም መሰንገጭም በኔ አይደለም ….ከግንባርህ ትህትናን አታጥፋ …››
እንግዲህ ወደ አሌክሲስ ቶኮቪሌ እንመለስ፡፡
የቶኮቪሌ እይታ
ከፍ ሲል በጠቀስነው ተረክ የሚታየው ሁኔታ በቅድመ አብዮት ኢትዮጵያ የነበረውን ህይወት የሚያሳይ ነው፡፡ በቅድመ አብዮት ኢትዮጵያ የዘር ግንድ እየቆጠሩ፣ በፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ብዙሃኑን የነበሩ ንጉሣውያን ቤተሰብ፣ መሳፍንት፣ መኳንንት ወዘተ…  ነበሩ፡፡ የኅሩያን ምስፍና መንግስታዊ አስተዳደር (Aristocracy) ሊባል የሚችል አገዛዝ ነው፡፡ ቶኮቪሌ ንጽጽር ሲያደርግ፤ በዲሞክራሲ እና በኅሩያን ምስፍና አስተዳደሮች የሚገኙ ‹‹ጌታ›› እና ‹‹ሎሌ››ዎችን ወስዶ ነው፡፡ የኅሩያን ምስፍና በህብረተሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ባላቸውና ‹‹ምርጥ›› ነን በሚሉ ጥቂት ሰዎች የመንግስት ሥልጣን የተያዘበት የአገዛዝ ስርዐት ነው፡፡ ይህ በአብዛኛው እውን የሆነው በባሪያው አሳዳሪና በፊውዳሉ ሥርዐተ ማህበሮች ውስጥ ነው፡፡ የኅሩያን ምስፍና መንግስታዊ አስተዳደርን የሚደግፉ የፖለቲካ ፈላስፎች (አፍላጦን፣ ስፒኖዛ፣ ሆብስ ወዘተ) እንደሚሉት፤ ‹‹የሀገር አስተዳደር እና የመንግስት አመራር ውስብስብ በመሆኑ ከፍተኛ ችሎታና ልዩ ሰዎችን የሚጠይቅ ነው፤ ስለዚህም ከማንኛውም ዜጋ የተውጣጣ ኃይል ሊያካሂደው አይችልም፡፡ የዚህ ዐይነቱ ኃላፊነት በትውልድ ለተመረጡ፤ በተለየ ስጦታቸውና የችሎታ ብቃታቸው ለላቁ ለተወሰኑ ምርጥ ሰዎች መሰጠት አለበት፡፡
በእንዲህ ዓይነት ስርዓት ውስጥ የሚገኙ ሎሌዎች እና መሳፍንት በግልፅ የሚታይ መደባዊ ማንነት ይዘው ይቆማሉ፡፡ እነዚህን ሁለት መደቦች የሚገዛ እና እርስ በእርስ የሚገናኙበትንም ሥርዓት የሚደነግግ ህግ ይፀናል፡፡ እያንዳንዱ መደብ፤በየራሱ መደብ ውስጥ የበላይ እና የበታች የሚያደርግ መሰላል አለው። በየመሰላሉ የተቀመጡት የህብረተሰብ ክፍሎች የተለያየ ባህርይ ይዘው፤ የተሰጣቸውን ማህበራዊ ደረጃ ጠብቀው፤ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተተካኩ ያላንዳች ለውጥ ዘመናትን ተሻግረዋል፡፡
‹‹እሺ በጎ›› ብሎ የማደር የህይወት ዕጣን የተሸከሙት ታዛዥ እና ተገዢ የሆኑት ሰዎች ስለ ክብር፣ ሐቀኝነት፣ ዝና፣ ጨዋነት ያላቸው አመለካከት ከጌቶቻቸው ፍፁም የተለየ ነው፡፡ ሆኖም በራሳቸው መንገድ ክብር፣ ጨዋነት፣ ሐቀኝነት ስለሚባሉ ጉዳዮች ከራሳቸው ህይወት ጋር የተጣጣመ ግንዛቤ ይኖራቸዋል፡፡ ምክንያቱም አንድ መደብ ዝቅተኛ መደብ በመሆኑ ብቻ፤በዚያ መደብ ውስጥ የተካተቱ ሰዎች በሙሉ ‹‹ልበ ወራዳ›› ናቸው (mean hearted) ብሎ መደምደም ስህተት ይሆናል፡፡ አንድ ሰው የዝቅተኛ መደብ አባል ቢሆንም፤በሚገኝበት መደብ ውስጥ ‹‹ከፍ ያልኩ ነኝ›› ብሎ እንዲያስብ የሚያደርገው ሞራላዊ ድንጋጌዎች ይኖራሉ፡፡
እናም ሞገስ የሚያስገኝለትን የክብር ደረጃ አስጠብቆ ለመኖር የራሱን ‹‹መሳፍንታዊ›› ማዕረግ ይደነግጋል፡፡ ይህን ማዕረግ፤ የቸገረው ሰው፤ ‹‹የባሪያ ክብር›› ሊለው ይችላል። ይህን ወግ አክብሮ መኖር፤ ተገዢው ትልቅ እንዲያስብ እና ራሱን እንዲያከብር ወይም የክብር ስሜት እንዲፈጠርበት ያደርጋል፡፡ ‹‹ምንም ብቀጥን ጠጅ ነኝ›› ዓይነት ክብር ይጎናፀፋል፡፡  ስለዚህ ለሁኔታው የሚመጥን ጨዋነትን ያሳያል። ተራ ከሚባሉት ድርጊቶች ላቅ ያለ ድርጊት ለማከናወን ይገፋፋል፡፡ ‹‹እኔ የጠቅል አሽከር፤እንዲህ አላደርግም›› እያለ ይፎክራል፡፡  ታዲያ ይህ ሰው (አገልጋይ) የአገልጋይነት መንፈስ አይሰማውም። ስለዚህ፤ ለጌታው ፈቃድ ያላንዳች ቅሬታ ፍፁም ተገዢ ይሆናል፡፡
ሆኖም በፈረንሳይኛ ቋንቋ ውስጥ የመሳፍንቱ የቤት አገልጋይ ለሆኑ ሰዎች መጠሪያ ሆኖ የሚያገለግል ሆን ተብሎ የተፈጠረ አንድ ቃል አለ፡፡ ፈረንሳዮች፤ የመሳፍንት ቤት አገልጋዮችን ‹‹Lackeys›› ሲሉ ይጠሯቸዋል፡፡ ‹‹ላኪ›› የሚለው ቃል የሰው አሰር ወደ ማለት ይቀርባል፡፡ ዝቅተኛ የሚባሉት ሰዎች ተዘርዝረው በመጨረሻ የሚሰለፈው ሰው መጠሪያ ነው፡፡ በጥንታዊው ፈረንሳዮች በመንፈሱ ዝቅተኛ እና የተናቀ ሰውን ለመጥቀስ ሲፈልጉ፤ ‹‹እሱ የላኪ ነፍስ ያለው ነው›› (he had a soul of a lackey) ይላሉ፡፡ በዚህ ቃል ለመግለፅ የተፈለገው፤ ንቀት እና ዝቅተኛነት ሲሆን ቃሉም ይህን በትክክል ያስተላልፋል፡፡
እኩልነት በሌለበት ወይም የበላይ እና የበታችነት የኑሮ ዘይቤ በሰፈነበት ማህበራዊ ስርዐት፤ በአገልጋዮቹ እና በጌቶቻቸው መካከል ያለውን ግንኙነት የሚገዛ፤ የጨዋ እና የባለጌነት ሚዛን እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ በመሳፍንታዊ ሐገራት የሚገኝ አንድ ደሀ፤ ገና ከህፃንነቱ ጀምሮ ከመታዘዝ መንፈስ ጋር ይዛመዳል፡፡ ዓይኑን ወደየትኛውም አቅጣጫ ቢወረውር፤ የማህበረሰቡ የበላይ እና የበታችነት መዋቅር ይታየዋል፡፡ በየቦታው የታዛዥነት ህይወት ይጋፈጠዋል፡፡
ከፍ ሲል ያየነው፤ የወ/ሮ አሰጋሽ እና የጭሰኛው ዓይነት ግንኙነት በብዙ መሳፍንታዊ ሐገሮች የሚታይ ነው፡፡ በነዚህ ሐገሮች ውስጥ የሚኖር ጌታ፤ ከአገልጋዮቹ ማቅማማት የሌለበት ፈጣን እና ፍፁም ታዛዥነትን በቀላሉ ያገኛል፡፡ አገልጋዮቹ ለጌቶቻቸው የሚያሳዩት አክብሮት፤ ለአንድ ጌታ ሳይሆን ለጠቅላላ መሳፍንታዊ መደቡ የሚሰጥ ክብር ነው። ጌታው፤የአገልጋዩን ፈቃድ (will) የሚጫነው፤ በመሳፍንቱ መደብ አባላት ሰዎች ጥቅል ክብደት ልክ እንጂ በአንድ ግለሰብ መጠን አይደለም፡፡
ጌታው የተገዢዎቹን ድርጊት ፍፁም ይወስናል፡፡ በተወሰነ ደረጃም ሐሳባቸውን ይገዛል፡፡ በመሳፍንታዊ ስርዓት ውስጥ ጌታው (አንዳንዴም ሳያውቀው) በተገዢዎቹ አስተሳሰብ ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል፡፡ አኳኋናቸውን እና ባህርያቸውንም ይቀርፃል፡፡ በጥቅሉ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ካለው ስልጣን እጅግ በጣም የሚበልጥ ነው፡፡
በመሳፍንታዊ ስርዐት ውስጥ ከዘር ወደ ዘር የሚሸጋገር የ‹‹ሎሌነት›› እና ‹‹ጌትነት››ይኖራል፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ የአንድ አሽከር ቤተሰቦች ለአንድ ጌታ ቤተሰቦች ለተከታታይ ትውልዶች ተገዢ የሚሆኑበት ሁኔታም ይኖራል፡፡ እንደ ሁለት ትይዩ መስመሮች መቼም የማይገናኙ ግን የማይለያዩ ሆነው ይዘልቃሉ፡፡ የሁለቱ መደቦች አባላት ሰዎች ግንኙነት ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ያለው ጉዳይም ይህ ነው፡፡ ስለዚህ በመሳፍንታዊ ህብረተሰብ ውስጥ ጌታና ሎሌ ምንም ዓይነት የባህርይ ዝምድና ባይኖራቸውም፤ በማህበራዊ መሰላሉ አንዱ ከአንዱ እጅግ የተራራቁ ቢሆኑም፤ እንዲሁም በትምህርት በአስተሳሰብ ፍፁም ቢለያዩም፤ በቀላሉ የማይበጠስ ትስስር ይዘው ይዘልቃሉ፡፡
በመሳፍንታዊ ስርዓት ውስጥ ገዢው አገልጋዮቹን የሱ የበታች መሆናቸውን ያምናል፡፡ ነገር ግን እንደራሱ ተቀጥላ የአካል ክፍል ይቆጥራቸዋል፡፡ የራሱን ጥቅም ለማስከበር ባለው ፍላጎት፣ የነርሱን ጥቅም ለማስከበር ይቆማል፡፡ ግን የእነርሱን ጥቅም ለማስከበር የሚቆመው፤ የእርሱ ጥቅም ሲለጠጥ የእነርሱ ጥቅም ስለሚሆንበት ብቻ ነው፡፡ አገልጋዮች በበኩላቸው፤ራሳቸውን በጌቶቻቸው ዓይን ማየትን የሚጠሉ እና የሚፀየፉ አይደሉም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ራሳቸውን ከጌታቸው ህይወት ጋር አንድ አድርገው ይመለከታሉ፡፡ ስለዚህ በእነሱም ሆነ በጌቶቻቸው ዓይን የገዢያቸው ተቀጥላ ናቸው፡፡
በመሳፍንታዊ ሥርዐት ውስጥ አገልጋይ ያለው ሥፍራ የተዋራጅነት ነው፡፡ ከዚህ የተዋራጅነት ቦታ የሚያወጣው የለም፡፡ ሁሌም፤ ከሱ በላይ ሌላ ሰው አለ፡፡ ከሱ ደረጃ ከፍ ያለ ደረጃ የተቀመጠ ጌታ አለ፡፡ ሎሌውም ሆነ ጌታው ቦታቸው የፀና ነው፡፡ በአንድ በኩል፤ ‹‹አባ ከና›› የሚለው የማጣት፣የድህነት እና የተገዢነት የዕድሜ ልክዕጣ ፈንታ ሆኖ ተደንግጓል፡፡ በሌላ በኩል ዝና፣ ሀብት እና አዛዥ- ናዛዥነት ዘላለማዊ መስሎ ቆሟል፡፡ እነኝህ ሁለት መደባዊ ማንነቶች፤እንደ ትይዩ መስመሮች የተለያዩ እና ሁልጊዜም ጎን ለጎን የሚኖሩ ናቸው፡፡ እነኝህን ሁለት መደቦች የሚያገናኛቸው ገመድም ዘላቂና ዘላለማዊ ነው።
በእንዲህ ዓይነት ዕጣ የተሸከመው አገልጋይ፤ከራሱ ፍላጎት እና ክቡር ሐሳብ ወይምህሊና፤ በአጭሩ ከራሱ ነፍስ የተጣላ ወይም የተነጠለ ይሆናል፡፡ የገዛ ፍላጎቱን ይክዳል፡፡ የሌሎች ሰዎች ፍላጎት አሽከር ይሆናል፡፡ የራሱን ትቶ ለጌታው ፍላጎት ጥብቅና ይቆማል፡፡ በአንድ ቃል ራሱን ይክዳል፡፡ ራሱን በጌታው ማንነት ውስጥ ይደብቃል፡፡ ስለዚህ ማንነቱ ምናባዊ ይሆናል፡፡ አንዳች ሳያቅማማለጌታው ብልፅግና ራሱን ማዳበሪያ ያደርጋል፡፡ በጌታው ዝና እና ሐብት የሚኮራ ሰው ይሆናል፡፡ በጌታው ማዕረግ፤ ራሱን ከፍ ከፍ አድርጎ ማየት ይጀምራል፡፡ አዕምሮውን በብድር ታላቅነት ይለጉመዋል፡፡ የክብሩ እና የሐብቱ እውነተኛ ባለቤት ከሆኑት ሰዎች በላይ ለጌታው ሐብት እና ክብር ትልቅ ግምት ይሰጣል፡፡
ጌታው የሚሰማው የክብር እና የታላቅነት ስሜት ወደ ሎሌው ሊዘምት ይችላል፡፡ ግን ሲዘምት፤ ባህርይውን ቀይሮ ‹‹ወራዳ ከሆነው ሰው›› ዝቅተኛ መንፈስ ጋር የተስማማ ባህርይ ይይዛል፡፡ ያ የክብር እና የታላቅነት ስሜት ይኮማተር እና ቁልቁል ወርዶ የዝቅተኝነት ስሜት ይሆናል፡፡ በአንዱ ሰው ውስጥ የነበረው የክብር ስሜት፤ በሌላኛው ውስጥየሞኝ ግብዝነት እና ጅላጅል አስመሳይነት ይሆናል፡፡ የትላልቅ ሰዎች አሽከር የሆኑ ሰዎች፤ የጌታቸው የክብር መገለጫ ከሆኑ ነገሮች አንድ እንኳን እንዳይጎድል ልዩ ጥንቃቄ ያደርጋሉ፡፡ ከጌታቸው በላይ ለጥቃቅኗ የክብር መግለጫ ወግ እና ስርዓት ጥንቃቄ ያደርጋሉ፡፡ እነኝህ ሁለት መደቦች የጋራ የሆነ ታሪክና ትዝታ አላቸው፡፡ ይህም አዕምሮአዊ ትስስር ይፈጥርላቸዋል፡፡ አንዱ ከሌላኛው ምንም ሚያገናኘው ነገር ባይኖረውም አብረው አድገዋል፡፡
ቶኮቪሌ ይህን መጣጥፍ በፃፈ ጊዜ፤ ፈረንሳይ ውስጥ የጥንቱ መሳፍንታዊ ስርዓት ርዝራዥ የሆኑ ሎሌዎች አልፎ አልፎ ይታዩ እንደ ነበር ገልጧል፡፡ ‹‹ሆኖም በቅርብ ጊዜ ‹ዘራቸው› ጨርሶ ይጠፋል›› ብሎ ነበር፡፡ አሁን ሄደን ድፍን ፈረንሳይን ብንዞር አናገኛቸውም ይሆናል፡፡ እኛ ዘንድ ግን የሁለቱም ‹‹ጎሳ›› አባላት አሁንም በህወይወት እንዳሉ በእርግጠኝት መናገር ይቻላል፡፡
በአሜሪካ ጉብኝቱ፤ እንደ ፈረንሳይ ሎሌዎች ያሉ ሰዎች እንዳልገጠሙት የጠቀሰው ቶኮቪሌ፤ አሜሪካውያን እንዲህ ያሉ ሰዎችን አይተው አያውቁም ብቻ ሳይሆን፤ ስለነዚህ ሰዎች ብትነግሯቸው ለመረዳት እጅግ ይቸገራሉ ይላል፡፡ ሆኖም፤ በፈረንሳይእንዲህ ያሉ ሰዎች እንዲፈጠሩ ካደረገው ስርዓት መወገድ ጋር ቀስበቀስ የሎሌ መንፈስ ተሸክመው የሚገኙሰዎች እየጠፉ መሆኑን ይናገራል፡፡
ዲሞክራሲ
በተቃራኒው፤ የዲሞክራሲያዊ ማህበረሰብ አባላት አንዱ ከአንደኛው ጋር ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ናቸው። ሆኖም፤ አንዱ ለሌላኛው ሁልጊዜም እንግዳ ነው። ከእኩልነት ስርዓት መፈጠር ጋር፤ የድሮዎቹ‹‹ሎሌ›› እና ‹‹ጌታ››ዎች አዲስ ሰውነት ይይዛሉ፡፡ አዲሱ ስርዐት የሁለቱን መደቦች ተነፃፃሪ ማኅበራዊ ቦታ እንዲቀየር አድርጎታል፡፡ ማህበራዊ ምህዳሩ ከሞላ ጎደል የእኩልነት ባህርይ ሲይዝ፤ ሰዎች በኑሮ አውድ ውስጥ የሚይዙት ቦታ ያለማቋረጥ የሚለወጥበት ሁኔታ አለ። በዲሞክራሲያዊ ስርዐት ውስጥ ‹‹የጌቶች›› እና ‹‹የአሽከሮች›› መደብ መኖሩ አልቀረም፡፡  ሆኖም፤ የእነዚህ መደቦች አባላት የሆኑት ሰዎች ሁልጊዜም አንድ ዓይነት ሰዎች ወይም አንድ ዓይነት ቤተሰቦች አይሆኑም፡፡ ይቀያየራሉ፡፡ የአዛዥነት ዕድል ያገኙት እና የታዛዥነት ዕጣ የደረሳቸው ሰዎች እንዲያ እንደሆኑ ሊቆዩ አይችሉም፡፡
ታዛዡ ሰው፤ ‹‹ታዛዥ እንደሆንኩ ዕድሜዬን እገፋለሁ›› የሚል ስጋት ሊኖረው እንደማይችል ሁሉ፤ አዛዡም፤ ‹‹ያለ አንዳች ስጋት ሁልዜም እንዳዘዝኩ እኖራለሁ›› የሚል መተማመን የለውም፡፡ አገልጋዮቹ የተለየ መደብ አይፈጥሩም። ስለዚህ የተለየ ባህርይ፣ ዝንባሌ ወይም የእነሱ ብቻ መገለጫ የሚሆን አድራጎት አይኖቸውም፡፡ የእነሱ ልዩ መገለጫ ሆኖ የሚጠቀስ የአስተሳሰብ እና የስሜት ዝንባሌ የላቸውም፡፡ ከማህበራዊ አቋማቸው የመነጨ ጥሩ ወይም መጥፎ ምግባር ተብሎ የሚነሳ ነገር የላቸውም፡፡ ይልቅስ፤ የዘመነኞቻቸውን የትምህርት፣ የአስተያየት፣ የስሜት፣ የጥሩ ወይም መጥፎ ምግባር ባህርያትን ይጋራሉ፡፡ ያው ጌታ እንደሚባሉት ሰዎች ሐቀኛ እና ሸፋጮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
የአሽከሮቹ የኑሮ ሁኔታ ያን ያህል ከጌቶቹ የተለየ አይደለም። ምክንያቱም፤ በመሳፍንታዊው ስርዐት እንደምንመለከተው፤  በሁለቱ ቡድኖች መካከል የማይለወጥ የደረጃ፣ የማዕረግ ወይም የታዛዥነት መገለጫ የለም። የትንሽነት ወይም የታላቅነት መገለጫ ባህርይ የሚያሳዩ አይደሉም፡፡ ‹‹በአውሮፓ አሁንም ርዝራዡ ያልጠፋውን የአሽከሮች መደብ ባህርይ እና ድርጊት እንዳስታውስ የሚያደርግ ሰው አሜሪካ ውስጥ አልገጠመኝም›› የሚለው ቶኮቪሌ፤ ‹‹በፈረንሳይ እንዳለው lackey የሚል ቃል በአሜሪካ አልሰማሁም፡፡ የሁለቱ መደቦች መገለጫ የሆኑ ነገሮች ሁሉ ድራሻቸው ጠፍቷል›› ይላል፡፡
በዲሞክራሲ ውስጥ አገልጋዮቹ እርስ በእርስ የሚበላለጡ አይደሉም፡፡ ፍፁም እኩል ናቸው። እኩልነታቸው እርስ በእርስ ብቻ ሳይሆን፤ በሆነ መንገድ ካየነው ከጌቶቻቸውም እኩል ናቸው፡፡ ይህን ሐሳብ በደንብ ለመረዳት ነገሩን ትንሽ አፍታቶ ማየት ይጠይቃል።
አንድ ሎሌ በማናቸውም ጊዜ ጌታ ሊሆን ይችላል፡፡ ከእርሱ በላይ ወዳሉት ሰዎች መድረስን ይመኛል፡፡ ስለዚህ አገልጋዩ ከጌታው የተለየ ሰው አይደለም፡፡ ታዲያ ጌታው የማዘዝ መብቱን ያገኘው፤ ሎሌው የታዥነት ግዴታ የተጫነት በምን ምክንያት ነው?በዲሞክራሲ ስርዐት በነፃ ፈቃድ ከተመሠረተው ጊዜአዊ ስምምነት ሌላ፤ ታዛዡን እና አዛዡን የውል ግዴታ ውስጥ የሚያስገባ ምን ነገር አለ? በተፈጥሮ አንዱ ከሌላው ያነሰ አይደለም፡፡ አንዱ የሌላው ታዛዥ የሆነው በጊዚያዊ ስምምነት ነው፡፡ ከዚህ የውል ስምምነት በመነጨ ሁኔታ አንዱ አዛዥ ሌላው ታዛዥ ይሆናል። ከዚህ ውጭ ሁለቱም ሰዎች የአንድ ፖለቲካዊ ህብረት ዜጋ የሆኑ ሁለት ሰዎች ናቸው፡፡ ይህም ነገር በታዛዡም ሆነ በአዛዡ ህሊና ተቀባይነት አግኝቶ ያደረ ጉዳይ ነው፡፡ ታዛዦቹ የሚገኙበትን የኑሮ ሁኔታ የሚመለከቱት ከአዛዡ ሰው በተለየ አይደለም፡፡ የስልጣን እና የታዛዥነቱ ድንበር በግልፅ የተሰመረ እና በሁለቱም ህሊና ውስጥ መልስ አግኝቶ ያደረ ጉዳይ ነው፡፡
የሚበዛው የፖለቲካ ማህበረሰቡ አባላት የኑሮ ሁኔታ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ሆኖ ውሎ ካደረ  እና እኩልነት በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ ብዙ በቆየበት ሁኔታ፤ የህዝቡን አስተሳሰብ የሚያዛባ ልዩ ግምት የሚያገኝ ሰው በሌለበት ሁኔታ፤ የሰውን ልጅ ዋጋ የሚወስን አንድ አጠቃላይ ገመታ ይፀናል፡፡ ለአንድ ሰው ከተሰጠው ‹‹ሲቪክ ዋጋ›› በላይ ወይም በታች የሆነ ዋጋ የሚሰጠው ሰው አይኖርም፡፡
በዲሞክራሲ ስርዐት፤  ሐብት እና ድህነት፤ አዛዥነት (ስልጣን) እና ታዛዥነት (ተመሪ) መሆን፤ በመካከላቸው ትልቅ ልዩነት ወይም ርቀት መጋረጡ አይቀርም፡፡ ሆኖም፤ የዘወትራዊ ህይወት ስርዐት ላይ ተደላድሎ የተቀመጠው ህዝባዊ አስተያየት ወይም ህሊና (public opinion)፤ ይህን ልዩነት ጎትቶ ወስዶ በአንድ ሰልፍ ያቆመዋል፡፡ በዚህም በሁለቱ ሰዎች መካከል ያለው ተጨባጭ የኑሮ ሁኔታ ልዩነት እንዳለ ሆኖ፤ ሌላ ሐሳባዊ የእኩልነት መንደር በመፍጠር እኩል አድርጎ ያስተካክላቸዋል፡፡ ይህ ፍፁም ኃያል የሆነ የህዝብ አስተያየት፤ ሌላው ቀርቶ ይህን አመለካከት እንዳይቀበሉና ግድግዳ ሰርተው እንዲከላከሉ የሚያደርግ ጥቅም ካላቸው ሰዎች ልብ ዘልቆ በመግባት፤ መሻታቸውን በማንበርከክ በህሊና ዳኝነታቸው ላይ ተፅዕኖ ያሳርፍበታል፡፡ ስለዚህ፤ ጌታ እና የሎሌዎች፤ ከጥልቅ የልባቸው በኣት ገብቶ ያደረና ሥር ሰድዶ የተቀመጠ ልዩነት በመካከላቸው መኖሩ አይሰማቸውም።
በተለመደ የነገሮች ስርዓት ላይ ተመስርቶ የሚፈጠረው የህዝብ አስተያየት፤ ሁለቱንም ወገኖች ጎትቶ ወስዶ በአንድ ደረጃ ላይ እንዲቆሙ ያደርጋቸዋል፡፡ ተጨባጭ የኑሮ አቋማቸው ውስጥ የሚታየው ተጨባጭ ልዩነት (የበታች እና የበላይ እንዲሆኑ ያደረገው ነገር) እንዳለሆኖ፤ በሁለቱ ወገኖች ህሊና ምናባዊ እኩልነት እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡
ይህ ኃያል ጉልበት ያለው አመለካከት፤ ተጨባጩ ጥቅማቸው እኩልነቱን እንዳይቀበሉ ከሚገፋፋቸው ሰዎች ልብ ውስጥ እንኳን ዘልቆ በመግባት፤ የውስጥ ምኞት እና ፍላጎታቸውን አንበርክኮ፤ ለነገሮች በሚሰጡት ዳኝነት ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ በእኩልነት እንዲያምኑ ያደርጋቸዋል፡፡
በጌታ እና በሎሌው ህሊና ጥልቅ የእኩልነትእምነት ተፈጥሯል፡፡ ሁለቱም በመካከላቸው ጥልቅ መሠረት ያለው ልዩነት መኖሩን የሚያምኑ አይደሉም፡፡ በማናቸውም ሰዓት፤ አንዱ አንደኛውን ለመገናኘት በፍርሃት ወይም በተስፋ አይጠብቅም፡፡ ስለዚህ፤ አንዱበሌላው ላይ የቁጣ ወይም የንቀት ስሜት የለውም። አንዱ ሌላውን በመለማመጥ ወይም በኩራት ስሜት አይቀርበውም፡፡ ‹‹በጌታው›› ዘንድ ያለ ትልቅ ብቸኛው የስልጣን ምንጭ የስራ ስምምነቱ ነው። በተመሳሳይ፤ ‹‹ሎሌው›› ለቀጣሪው እንዲታዘዝ ምክንያት የሚሆነው ብቸኛ ነገር ይኸው የሥራ ስምምነት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ጌታው የማዘዝ መብት እንዲያገኝ፤ ሎሌው የመታዘዝ ግዴታ እንዲቀበል የሚያደርግ ነገር የላቸውም፡፡ ሁለቱም ሚናቸውን ያውቁታል፡፡ ከሚናቸው ጋር በተያያዘ ፀብ ውስጥ አይገቡም። ሁለቱም ወገኖች በየበኩላቸው የሚጠበቅባቸውን ነገር ያውቁታል፡፡ አውቀውም ያከብሩታል፡፡ አሌክሲስ ዲ. ቶኮቪሌ (Alexis de Tocqueville)፤ በምሣሌ የሚያነሳው አንድ ነገር አለ፡፡ በፈረንሳይ መከላከያ ሠራዊት ውስጥ በተራ ወታደርነት የሚቀጠሩት እና በመኮንንነት የሚያገለግሉት ሰዎች ብዙ ጊዜ ከተወሰነ መደብ የሚወጡ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እናም ከሁለቱም መደቦች የተውጣጡት የሠራዊቱ አባለት፤ በሰራዊቱ የሚሰጣቸው ኃላፊት ተመሳሳይ ላይሆን ይችላል፡፡ ሆኖም፤ ከወታደራዊ ማዕረጉ ውጭ የበታቹ ከበላዮቹ ጋር ፍፁም እኩል እንደሆነ ያስባል፡፡ በተጨባጭም እኩል ናቸው፡፡ ሆኖም፤ ወታደራዊ ተግባሩን በሚያከናውንበት ጊዜ፤ የበላዮቹን ትዕዛዝ ለመቀበል ፈፅሞ አያመነታም። ታዛዥነቱ፤ በጎ ፈቃደኝነትን የተጎራበተ፣ ተፈጥሯዊ የመሰለ እና ወትሮ ዝግጁነት ያልተየው ነው፡፡ ይህ ምሳሌ፤ በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ በጌታ እና በሎሌ መካከል ያለው ግንኙነት ምን እንደሚመስል ፍንጭ ሊሰጠን የሚችል ነው፡፡ ሆኖም፤ በመሳፍንታዊ ስርዓት ባሉ ‹‹ጌታ›› እና ‹‹ሎሌ››ዎች መካከል፤ በቤት ውስጥ አገልግሎት አንዳንዴ ሲፈጠር የምናየውን ዓይነት የጋለ እና ጥልቅ የሆነ ፍቅር ወይም መተሳሰብ በዲሞክራሲ ስርዓት ውስጥ በሚኖሩ ጌታ እና ሎሌዎች መካከል ይፈጠራል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ እንደ መሳፍንታዊ ስርዓት ራስን መስዋዕት የማድረግ ጠንካራ ዝንባሌ፤ በዲሞክራሲ ሊኖር አይችልም፡፡
በመሳፍንታዊ ስርዓት ጌታ እና ሎሌ በአንድ ቦታ አብረው አይኖሩም፡፡ ብዙውን ጊዜ፤ በሁለቱ መካከል የሚደረገው ንግግር በሦስተኛ ሰው አማካኝነት የሚከናወን ነው፡፡ ይሁንና አንዱ ሲጠቃ ሌላው ዘወትር ጠበቃ ሆኖ ይቆማል፡፡ በዲሞክራሲያዊ ስርዓት፤ ጌታ እና ሎሌ ተቀራርበው ይኖራሉ። በየዕለቱ ይገናኛሉ፡፡ ሆኖም አዕምሯቸው ውህደት የለውም። አንዱ ለአንደኛው ጥቅም መከበር ፀንቶ አይቆምም፡፡ ምክንያቱም፤ የዲሞክራሲ ስርዓት ጌታ እና ሎሌዎች የጋራ ሥራ ወይም ተልዕኮ እንጂ፤ መቼም ቢሆን የጋራ ጥቅም ሊኖራቸው አይችልም። በእንዲህ ዓይነት ህብረተሰብ፤ ሎሌው ሁልጊዜም ራሱን የሚመለከተው፤ በጌታው የመኖሪያ አካባቢ (መንደር) ለተወሰነ ሰዓት እንደመጣ ጎብኚ ነው፡፡ የጌቶቻቸውን አያት ወይም ቅድም አያት ቀይ ይሁኑ ጥቁር አያውቅም። አብሮ ኖሮ ቀጣይተወላጆቹን ሊያይ አይችልም፡፡ ለዘለቄታው ከእነሱ አገኛለሁ ብሎ የሚያሰበው ነገርም የለውም፡፡ ታዲያ የእርሱን ህይወት ከእነርሱ ጋር አያይዞ ለማየት ምን ምክንያት ይኖረዋል? ጌታ የነበረው ሎሌ፤ ሎሌ የነበረው ደግሞ ጌታ ሊሆን የሚችልበት ዕድል አለ፡፡ የግንኙነታቸው መልክም ይቀያየራል፡፡ቶኮቪሌ እንደጠቀሰው፤ በአሜሪካ ሰሜናዊ እና ደቡባዊ ክፍል በሚገኙ ግዛቶች ያለው ሁኔታ የተለያየ ነው፡፡ በሰሜኑ ባርነት ተወግዷል፡፡ በደቡቡ ገና እንደ ፀና ነው፡፡ ስለዚህ ስለ አሜሪካ ሲናገር ይህን ልዩነት ከግምት ሳያስገባ አይደለም፡፡ በሰሜኑ ከባርነት ነፃ የወጡ ሰዎች ወይም የእነሱ ልጆች ይገኛሉ። እነዚህ ሰዎች በማህበራዊ ምህዳሩ የሚሰጣቸው ግምት ወላዋይ ወይም እርግጠኝነት የሚጎድለው ነው፡፡ በህግ ደረጃ ከጌቶቻቸው እኩል ቦታ ይዘዋል፡፡ ሆኖም፤ በሐገሪቱ አያያዝ ፍፁም ዝቅ ያለ ቦታ እንዲይዙ ተደርገው ይገኛሉ። ራሳቸው ማህበራዊ ቦታቸውን በትክክል አያውቁትም። ይሁንና፤ ነፃነት እና እኩልነት የሰጣቸውን ፀጋ ይዘው፤ የኑሮ ሁኔታቸው የሰጣቸውን ግዴታ ተቀብለው፤ ሰዐት አክባሪነት እና ብቃት በሚታይበት አኳኋን ሥራቸውን በትክክል ያከናውናሉ፡፡
እነዚህ ሰዎች ያለ አንዳች ማቅማማት የሚታዘዙትን ይሰራሉ፡፡ ሆኖም፤ከቀጣሪያቸው ወይም ከሚያዛቸው ሰው በተፈጥሮ እንደሚያንሱ የሚያስቡ አይደሉም፡፡ እነዚህ ሰዎች የዲሞክራሲ ስርዐት የወለዳቸውን ባህርያት ተላብሰው፤ በነፃ ፈቃዳቸው የገቡበትን የሥራ ውል አክብረው፤ ሳይሸፍጡ በጀግንነት የሚኖሩ ናቸው፡፡ አዛዦቻቸውን ለማታለል ሳይሞክሩ፤ የሰጧቸውን የሥራ ኃላፊነት በአግባቡ የመወጣት የባህርይ ብቃት ያላቸው ራሳቸውን የሚያከብሩ ጀግኖች ናቸው፡፡ አዛዦቹም ከሠራተኞቻቸው የሚፈልጉት፤ የሥራ ውላቸውን አክብረው፤ በታማኝነት እና በትጋት እንዲሰሩላቸው እንጂ፤  እንዲያሸረግዱላቸው ወይም እንዲወዷቸው ወይም ‹‹እኔ ከርሱ ሌላ…›› የሚል ፍቅር እና  መስዋዕትነትን አይደለም፡፡ እንደ ሠራተኛ፤ ጥንቅቅ ያለ ሥራ እንዲሰሩ እና በሐቀኝነት እንዲያገልሏቸው ብቻ ይፈልጋሉ፡፡
ሆኖም ሠራተኞች፤ ቀጣሪያቸው በህይወታቸው ላይ ያን ያህል ስልጣን እንደ ሌለው ያውቃሉ፡፡ ይህን ሐቅጌታውም ያውቃል፡፡ይህን መቀበል የሚቸግረው ሰው ግራ ይጋባል፡፡ ዘላቂ ሊሆን በማይችለው የሥራ ግንኙነት ውስጥ ሠራተኞቹ የማይለወጥ እና ዘላቂ ባህርይ እንዲያሳዩት ይመኛል፡፡ እንደ ቤት ሠራተኛ ቢሆኑለትም ይፈልጋል፡፡ ዕድሜ ልክ፤ ‹‹ራሳቸውን የማይችሉ›› የእርሱ አገልጋዮች መሆናቸውን ተቀብለው፤ በዚህም ኮርተው እንዲኖሩ ይሻል፡፡ ሆኖም አንድ ቀን ተቀጣሪ አገልጋይነታቸውን ትተው ቀጣሪ ሊሆኑ ይችላሉ።
በመሣፍንታዊ ስርዐት ውስጥ እንዲህ ያለ ነገር የለም። ሁለቱም ወገኖች የያዙት ማህበራዊ ሥፍራ የማይለወጥ የእግዜር ስጦታ ነው፡፡ በመሳፍንታዊ ስርዐት ያለው አገልጋይነት ሰብእናን የሚያዋርድ ነው፡፡ በዲሞክራሲ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ነገር የለም፡፡ በዲሞክራሲ ስርዐት መቀጠር እንደመሳፍንታዊ ስርዓት አዋራጅ ባህርይ የለውም፡፡ ምክንያቱም፤ ግንኙነቱ በነፃ ፈቃድ የሚወሰን እና አገልጋይነቱም ጊዜአዊ ነው፡፡
በህዝብ ህሊና ውስጥ ተቀባይነት ያለው አስተሳሰብ፤ በቀጣሪ እና በተቀጣሪ መካከል ያለው መበላለጥ ጊዚያዊ እና ሊለወጥ የሚችል መሆኑን የሚቀበል አስተሳሰብ ነው። ሠራተኛው ታዛዥነትን የሚጠይቅ ግንኙነት ውስጥ እንደ ገባ ያውቃል፡፡ ግን ይህ ግንኙነት ጠቃሚ ሆኖ ስለታየው በነፃ ፈቃዱ የገባበበት እና በርትቶ በመስራት ሊቀየር የሚችል ግኙነት መሆኑን ያምናል፡፡ አንዳንዴ፤ እኩልነቱ ከንቱ ህልም ሆኖ እየታየው ግራ ሊጋባ ይችላል። ስለዚህ አንዳንዴ በልቡ ያምፃል፡፡ ‹‹በእርግጥ እኩልነት የሚገኘው በዲሞክራሲ ክበብ ውስጥ ነው ወይስ ከዚያ ውጪ?››የሚል ሐሳብ ሊፈጠርብት ይችላል፡፡ ጥቅም ስለሚያገኝበት ማገልገልን ይፈልጋል፤ ግን መታዘዝ ስላለ ቅር ሊሰኝ ይችላል፡፡ በዲሞክራሲ ስርዓት ውስጥ ያሉ ተቀጣሪዎች፤ ከአገልግሎት የሚገኘውን ጥቅም እንጂ አዛዣቸውን አይወዱትም፡፡ ‹‹በዲሞ ጨዋታ አይቆጡም ጌታ›› ማለት ይቻላል፡፡
መደምደሚያ
ብዙ ጭቆናዎች የተሳኩት፤ የጭቆና አገጋዞቹ በህዝቡ ዘንድ ህጋዊነት ወይም ተቀባይነት በማግኘታቸው ነው። ለምሳሌ፤ ባርነትን መውሰድ ይቻላል፡፡ እንደ ባርነት ያለ የከፋ አገዛዝ የለም፡፡ ጌታው በዚህ ስርዐት፤ ሰው እንደ ዕቃ ሊሸጥ ሊለወጥ ይችላል፡፡ አስገራሚው ነገር፤ በሆነ መንገድ ለማመፅ እንኳን፤ በማሰብ ደረጃ እንኳን ተገዥዎች ለማመፅ የሚቸገሩበት ስርዐት ቢኖር የባርያ አሳዳሪ ስርዐት ነው። የባሪያ አሳዳሪ ስርዐት ታሪክን ብንመለከት፤ በሆነ መንገድ ስርዐቱ ፍፁም ተቀባይነት አግኝቶ ነበር፡፡ የሴቶችን የመብት ጥሰት ጉዳይ ተመልከቱ አሁንም ተቀባይነት ያገኙ ጭቆናዎች ትመለከታላችሁ፡፡
ጭቆና በህብረተሰቡ ዘንድ በሰፊው ተቀባይነት አግኝቶ፤ በሰዎች ህሊና ቅቡል ሆኖ፤ እንደ ተገቢ ጉዳይ ታይቶ ሊተገበር ይችላል፡፡ የሠራተኞችን ጉዳይ ተመልከቱ፡፡ በአሜሪካ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ምንዳ ለመቀበል መስራት ከባርነት (chattel slavery) ተለይቶ የሚታይ ገዳይ አልነበረም፡፡ በአሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት ዘመን ‹‹የሪፓብሊካን ፓርቲ›› የትግል መፈክር ‹‹ባርነትን›› (chattel slavery) ማጥፋት ነበር፡፡ ዘማቾቹ፤ ‹‹እኛ ተንቀሳቃሽ ባርነትን እና የምንዳ ባርነት እቃወማለን›› (We’re against chattel slavery and wage slavery) የሚል ነበር፡፡ በዘመኑ አስተሳሰብ፤ ነፃ ሰዎች ራሳቸውን ለሌሎች ሰዎች በኪራይ መልክ አይሸጡም። ምናልባት፤ አንድ ሰው ለጊዜው የሌሎች ተቀጣሪ ሊሆን ይችላል፡፡ አንድ ሰው የሌሎች ተቀጣሪ እና ታዛዥ የሚሆነው፤ በወቅቱ የአነጋር ፈሊጥ ‹‹ነፃ ሰው ወይም የራሱ ለመሆን በሚያደርገው የትግል ሂደት ነው፡፡››
በወቅቱ አስተሳሰብ፤ አንድ ነፃ ሰው የሚሆነው የሌሎችን ትዕዛዝ ለመፈፀም የማይገደድ ሰው ሲሆን ነው፡፡ ሰዎች ‹‹ራስን ማከራየት›› (to rent yourself) ተገቢ እና ነውር የሌለው ነገር ነው›› የሚለው እምነት ተቀባይነት እንዲያገኝ የማድረጉ ሥራ ብዙ ድካምን ጠይቋል፡፡ ከ150 ዓመታት በፊት ጨርሶ ተቀባይነት ያልነበረው ‹‹ራስን የማከራየት›› ጉዳይ ዛሬ ፍፁም ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ አሁንማ ቀጣሪው ባለሐብት፤ የቀጠራቸው ሰዎች በትክክል እየሰሩ መሆናቸውን ለመቆጣጠር ብዙ ፍላጎት የለውም፡፡ ምክንያቱም፤ ራሱ ተቀጣሪው ራሱን የሚመራበት ሙያዊ የሥነ ምግባር ደንብ አውጥቶ ራሱን ለገዛ ደንቦቹ ተገዢ ስለሚያደርግ ክትትሉ ያን ያህል አስፈላጊ አይደለም፡፡ ስራውን ቢያጓድል፤ ከባለቤቱ በላይ የህሊና ወቀሳ የሚደርስበት እርሱ ይሆናል፡፡ ለውጡ ይህን ያህል ነው፡፡

Read 2207 times