Saturday, 06 June 2015 14:05

የሱዳን ጉዞዬ ማስታወሻ

Written by  ነቢይ መኮንን
Rate this item
(2 votes)

(ካለፈው የቀጠለ)
  ማታ ሎቢውጋ የሚዲያ ሰዎች እንገናኝ ተባባልን፡፡
በእርግጠኝነት፤ አማረ አረጋዊ፣ መዓዛ ብሩና እኔ እና ሌሎችም፤ የሚዲያ ቡድን ምን መሥራት አለበት? ለመባባል ነው የምንገናኘው! ሁሉም ሴክተር እንደኛው ይሰባሰባል!!
ማታ በ3 ሰዓት አብዮት አደባባይ የመሰለ ቦታ የብሔራዊ ቴአትርና የሱዳን ኦርኬስትራ ወደሚዘፍኑበት ፌስቲቫል ቦታ ሄድን፡፡ ቴምርና ኦቾሎኒ እንዲሁም ውሃ ቀረበልን፡፡ በተራ በተራም፣ በህብረትም የቀረበ ትርዒት ነበር፡፡ የመጨረሻው “ጤና ይስጥልኝ” ነው ያኔ መላው ቀለጠ!
ጥምሩ ዘፈን ደግሞ “ሹክረን ዐባይ፣ ሹክረን ዐባይ” የሚል ነው፡፡ በኛ በኩል ሴት አቀንቃኝ አለች። እንደ አባሪ ዘፈን ተደርጐ፣ የዐባይ ስሜት እንዲመጣ ተብሎ መሰለኝ፤ የተዘፈነውን ያዝማሪ ዘፈን  ሁላችንም ተናደንበታል! አያስደንስ፣ አያስጨፍር፣ አያስጨበጭብ ከንቱ መድረክ! ቅኔ ለሱዳን አድማጭ ምኑ ነው?! ከዚያ በኋላ ንግግር በንግግር ሆነ መድረኩ፡፡ ከየኢትዮ ሱዳን ማህበር ሊቀመንበር ጀምሮ ማለቂያ የሌለው ንግግር! በዚህ ምክንያት “የንግግር - ፌስቲቫል” የሚል ስም ሰጠነው!
ከሌሊቱ 9 ሰዓት ይመጣሉ የተባሉትን የሊቢያ ስደተኞች ኢትዮጵያውን (ከፌስቲቫሉ በኋላ) ልናገኝና ልንቀበል መሆኑ ተነግሮናል - Excited ሆነናል፡፡ ዘጠኝ ሰዓት ይመጣሉ ተብሎ 10፡30 አውሮፕላኑ አረፈ፡፡ ለመቀበል ወደ መሠላሉ ሄድን።
አባዱላ ንግግር አደረጉ፡፡ እንዲህ ሲሉ፡- …“በዛሬው ቀን የኢትዮጵያ መንግሥት ከአካባቢው አገሮች ጋር በመተባበር ለችግሩ የተጋለጡ ዜጐቻችንን ወደ አገራቸው የመመለሱ እንቅስቃሴ ቀጥሏል፡፡ በተለይ በሊቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩትን ወገኖቻችንን የውጪ ጉዳይ ሚ/ርና በየአካባቢው ያሉት የኢትዮጵያ ሚሽኖች ከስደተኞቹ ጋር በመደማመጥና ሁኔታዎችን በማመቻቸት፤ እንዲሁም ትሪፖሊ ካለው የሱዳን ኤምባሲ ጋር በመተባበር፤ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የማድረግ እንቅስቃሴ፤ በተሳካ ሁኔታ እየፈፀሙ ይገኛሉ፡፡ ዛሬ 2ኛው ዙር ተመላሽ ካርቱም ገብቷል፡፡ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ አ.አ ይገባል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ዜጐቻችን በምንም መንገድ በምንም መልኩ፤ ለህይወታቸው አስጊ ወደሆነ አካባቢ በየትኛውም ደላላ ይሁን በየትኛውም መንገድ መሄድ እንደሌለባቸው የሚያስተምረን ትልቅ ነገር እንደሆነ፤ ከዚህ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የሱዳን መንግሥትና በአካባቢው ያለውንም ሱዳን ኤምባሲ ከልብ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ እንደዚሁም የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴራችንንና ባጠቃላይ በዚያ ያሉ ሚሲዮኖች ኢትዮጵያን ለመታደግ እያደረጉ ያሉት እንቅስቃሴ የመበረታታትና ትልቅ ተግባር ነው፡፡ ለወደፊቱም በዚህ እንዲቀጥል፣ እስካሁን ለተደረገውም ትልቅ አክብሮት ያለን መሆናችንን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ አመሰግናለሁ!”
ስደተኞቹ ልጆች እንደተጠበቁት አይደሉም። ምናልባትም ሰው ቤት ሲሠሩ ቆይተው ስለሆነ የመጡት ሊሆን ይችላል፣ ፈገግታ በፈገግታ ናቸው። እኛ እየጠበቅናቸው መሆኑን አላወቁም፡፡ ወይም ከጉዳይ አልፃፉንም፡፡ እንቅልፋችንን አጥተን ግማሹ ከናካቴው ሳይተኛ፤ (እኔ እንኳን 2 ሰዓት ያህል አርፌያለሁ፤) እስከ 10.32 ጠዋት ጠብቀናል፡፡
አንዳንዶች ሲጠየቁ፡፡ “ቤተሰቦቼ ስለፈሩ ነው የተመለስኩት” ይላሉ፡፡
አንዷ ስትጠየቅ “ሰው ቤት ነበር የምሠራው፤ ሂሳቤን ተቀብዬ ነው የመጣሁት” ትላለች፡፡
“የት ነበር የምትሠሩት?” ሲባል “እዛው አካባቢ ነው” ትላለች፡፡
“ትሪፖሊ?”
“እዛው አካባቢ” (የት ይሆን እዛው አካባቢ?)
“ስንት ጊዜ ቆየሽ?”
“ሶስት ዓመት”
“ስለደረሰው ዕልቂት ስትሰሙ ምን ዓይነት ስሜት ነበር የተሰማችሁ?”
(ዝም)
“ምን ትሠሩ ነበር?”
“ሰው ቤት”
“ደሞዝ ወስዳችኋል?”
“አዎ ተከፍሎናል”  
አንደኛዋ፤ ጓደኛዋ ኢንተርቪው መስጠቷንም አልወደደችውም፡፡ ነገ ነገር ያመጣብናል ብላ ሳይሆን አይቀርም፡፡ “ነይ” እያለች ትጐትታታለች፡፡ የሱዳን ሠራተኞች ግቡ እያሉ ይገፏቸዋል፡፡ ሹማምንቱ ወደ ንግግር ማድረጊያው ምስማክ ሄዱ፡፡
የአበሻ ነገር በካርቱም - ግንቦት ልደታ 2007
ካረፍንበት ከኮራል ሆቴል በዳማስ (መለስተኛ ሚኒባስ - በኛ ላዳ መሆኑ ነው) 10 ኪ.ሜ ሄደን ነው የጥበብ ወዳጄ ጓደኛ ቤት የደረስነው
መንገድ ላይ ቆንጆ መኪና የምትነዳ ኤርትራዊት አይተናል፡፡ “ባለ ሬስቶራንት ናት” አለን፡፡ “ብልጥና ቀልጣፋ ናት፡፡ ንግዱ ተሳክቶላታል፡፡ በሱዳን በርካታ ኤርትራውያን አሉ”
እዚህ ወዳጃችን ሠፈር ደረስን፡፡ የወዳችን ቤት ጠባብ ናት፡፡ ቤት ውስጥ ባልና ሚስቱ ከአንድ የ4 ወር ልጃቸው ጋር ይኖራሉ፡፡
ቤቷ እግር ገብቶ ፍራሽ ላይ የሚያርፍባት ዓይነት ናት፡፡ የዕቃ ቢፌ አላት፡፡ የአየር ማረጋጊያው  (air conditioner) የቤቷን የማይናቅ ቦታ ግድግዳው ላይ ይዟል፡፡ ቲቪም አለ፡፡ “በቻናል እናያችኋለን” ያለን ወዳጃችን በዚህ ነው፡፡ (“ያገሬን ነገር አውቃለሁ ማለቱ ነው”) ፍሪጅ አለ፡፡ ፍሪጁ ሲከፈት የተወሰነው ወለል ስፋት ይሰረቃል፡፡ ቤቷ ይብስ ትጠባለች፡፡
ባለቤቲቱ ከነረከቦቷና ምድጃዋ ስትጨመር ቤቷ ጢም አለች፡፡ ማንም ሳሎን የሚይዘውን ዕቃ ይዛለች ይቺ ቤት፡፡ በሰው አገር “ኑሮ ካሉት” የሚባለው ይሄው ነው፡፡ ቀን እስኪያልፍ ያለፋል ማለት ይሄው ነው፡፡ ከዚህ በፊት ሰፊ ቤት ተከራይተው ይኖሩ እንደነበር ገለፀልን - ወዳጃችን፡፡
የወዳጀችን ባለቤት ልጁዋን ለጐረቤት ሰጥታ ነው ያስተናገደችን፡፡ እንዲህ ያለ ደግነት እግር እስኪነቃ ቢሄዱ አይገኝም፡፡ እጅግ ለስላሳ፣ ሳቂታ፣ ሰው ወዳድ ናት፡፡ የአንድ ደግ ኢትዮጵያዊ ምልክት ናት፡፡ ደግነቷ እስከዛሬ ውስጤ ያለ ደግነት ነው፡፡
“ስንት ጊዜ ሆነሽ ከመጣሽ?” አልኳት፡፡
“ተከታትለን ነው ካርቱም የመጣነው፡፡ አምስት ዓመታችን ነው፡፡”
“ለምን ወዳገር አትገቡም?”
“ዛሬ ነገ ስንል! ይሄው 5 ዓመት ሞላን!”
አሁን እያስተናገደን ያለው ወዳጃችን በእንጨት ሥራ ይተዳደራል፡፡ ግቢው ውስጥ ያሉት ሌሎች ቤተሰቦች ኤርትራውያን ናቸው፡፡ “ተስማምተን እንኖራለን፡፡ ውሃና መፀዳጃ በጋራ እንጠቀማለን። በጋራ እናፀዳዋለን፡፡ ሆድ ለሆድ ግን አንግባባም። ሥራ ግን በጋራ ይሠራል፡፡ ግቢው ውስጥ አንድ አምስት ቤተሰብ አለ” አለን፡፡
ስንገባ የድሬዳዋ ቤት የገባን ነው የመሰለን። በግድግዳና በቤት መካከል አልፈን ወደግራ ዞረን ወደቀኝ ቤቷ ውስጥ ገባን - የጓደኛችን መኖሪያ ቤት፡፡
አልጋ ባንድ ወገን አለ፡፡ ፍራሽ መሬት ላይ አለ፡፡ ከግድግዳው ጋር የቆመ ፍራሽ እንደመደገፊያ ያገለግላል፡፡
ወደዚች ቤት ስንመጣ መንገድ ላይ “ካርቱም ቁጥር ሁለት” የሚባለውን አይተናል - የወርቅ መሸጫ ሰፈሩን አልፈን ነው ካርቱም ቁጥር ሁለት ያለው፡፡ “ወርቅ በግራም በኛ 800 ብር ገደማ ይሸጣል” አለ ወዳጃችን፡፡
“አንተ ይሄን ሙቀት እንዴት ቻላችሁት?” አልኩት፡፡
“ለምደነዋል” አለኝ፡፡ ይሄ ወዳጃችን ድንቅ ጠይም ወጣት ነው፡፡ ሲያብራራ ይመቻል፡፡
ወተት ጥርሱ የበረዶ ግጥም የተፃፈበት ይመስላል!
“ዋናው መስጊድ ይሄ ነው” አለን፡፡ (በእኛ አኑዋር መስጊድ እንደማለት ነው፡፡) የመንገዳቸው ስፋት አይታመንም፡፡
ባለሦስት ሰምበርም መንገድ (Three – lane) አላቸው፡፡ ሱዳን በስፋት አትታማ መቼስ!
እዛች ቤት ውስጥ ፖምና ወይን ሌላም ሌላም ተጋብዘናል፡፡ ባለቤቱ ተቸግራልናለች፡፡ የምትገርም ደግ ልጅ ናት፡፡ ቅልል ያለች ጠይም፡፡ ብዙ ውይይት አድርገናል፡፡ አንድ የሱዳን ነዋሪ ኢትዮጵያውን አገኘሁ ማለት ነው፡፡
ከወዳጃችን ቤት ስንመለስ እግረመንገዳችንን ለሻይ ቡና Africa Village የሚባል ቡና ቤት ገባን። በዲኤስቲቪ የአርሴና ማንቼ ግጥሚያ የሚያዩ ብዙ አበሾች መሀል አልፈን ጓዳ ካለው ሶፋ ወንበር፤ ላይ ክብ ሠርተን ተቀመጥን፡፡ የምታስተናግደን ልጅ፤ በእናቷ ኢትዮጵያዊ በአባቷ ኤርትራዊ ናት፡፡
“ለምን ኤርትራ ሄድሽ?” አልናት፡፡
“አባራችሁን ነዋ!” የመልሱዋ ፍጥነት እንደመተንፈስ ያህል ቀላል ነው፡፡
“ስንት ጊዜ ሆነሽ በሱዳን?”
“8 ወሬ ነው”  
“ቀጥሎስ ወዴት ነሽ?”
“ወደ አሜሪካ”
ቡና አዘዝን፡፡ ቡና ስታቀርብልን እስኪሰክን ወንበር ስባ፣ አራት ወንዶች መካከል ገብታ፣ ተቀመጠች፡፡ ኢትዮጵያዊነቷ ሁላችንንም ተሰማን። ምንም የከበዳት ነገር የለም፡፡ አዲሳባ በነበረች ጊዜ እንደምታውቀን ዓይነት ነው ነገረ - ሥራዋ!
እጅግ ወጣት ናት፣ አማርኛ ግን ታቀላጥፋለች። ኢትዮጵያ ነው የተወለደችው፡፡ አሁን እናቷ ኢትዮጵያ ሄዳለች፡፡ እህቷም እዚያው ናት፡፡
“ለምን ኢትዮጵያ አትሄጂም?”
“አሃ! በወር መቶ ዶላር እየከፈልኩ ልቀመጥልህ?” አለች ፍርጥም ብላ፡፡
እህቴ በወር 100 ዶላር እየከፈለች ኢትዮጵያ እየቆየች ናት!” አለች፡፡ ይሄንን አናውቅም ነበረና ገርሞናል፡፡ ምናልባት ኤርትራዊነትን የውጪ አገር ዜግነት ነው ብለን ከልባችን ስላልተቀበልነው ሊሆን ይችላል፡፡  
የአፍሪካ ቪሌጅ ባለቤት ኤርትራዊ ነው - አሉ። የልጅቷ እዚህ መሥራት ለዚህ ሊሆን ይችላል፡፡ ሱዳን ጨርሶ ቢራ የለም። ቡናና ውሃችንን ጠጥተን ከቡና ቤቱ  ወጣን ።
ሰፈሩ የ Class ነው - የሀብታም ሠፈር፡፡ ሰፋ ሰፋ ያሉና ground +1 ዓይነት ቤቶች አይተናል። “አማራት” ይባላል ስሙ፡፡ ግብፆችም አሉበት የሚባል ሠፈር ነው!
ስንመለስ፤ “ኦባሃማማ” የሚባል የሥጋ ሠፈር አየን፡፡ የጊርጊሮን ሠፈር ይመስላል - የአራት ኪሎውን፡- ዛሬ ነብሱን ይማረው ፈርሷል፡፡ በሜዳ ላይ የሚጠበስ ዶሮ በላን፡፡ በኦቾሎኒና በቃሪያ እና በውሃ ብቻ የሚሠራው ዳጣ መሳይ ነገር አለ፡፡ ሲያቃጥል ለጉድ ነው! ዶሮ አሮስቶ በዳጣ በላን፡፡ በጣም ይጣፍጣል፡፡
እኔም ቤቴ ልሠራው ተመኝቻለሁ፡፡ አሮስቶውን በሚገባ ያባላል፡፤
ኩባያ በሰንሰለት የታሠረበት እንሥራ ውሃ አለ አጠገባችን፡፡ ወዳጃችንን “ምንድን ነው” አልኩት፡፡
“ይሄ የውሃ እንሥራ ነው፡፡ ከጠማህ እየቀዳህ መጠጣት ነው፡፡ ማንም ሊጠጣ ይችላል፡፡ ችግሩ ግን ኩባያው አይታጠብም፡፡ ለጋሥነትንና ሃይጅንን እያሰብን ዝም አልን፡፡
ቸሮኒ የአውቶብስ ማቆሚያ ፌርማታ ነው፡፡ “ኩራብ” የሱዳን የአሸዋ አውሎ ነፋስ ነው፡፡ ጅሬፍ የአበሻ መኖሪያ ነው፡፡ ልክ የመርካቶ ዓይነት ሰፈር! የሱዳን ቃላት እሰበሰብኩ ነው፡፡
“ዴም” የሚባልም የአበሻ መኖሪያ አለ፡፡ እዚያ “ሰላም ምግብ ቤት”፣ “ኢትዮጵያ ሬስቶራንት” የሚል አይቻለሁ፡፡
ገበያ ገብቼ ካየሁዋቸው ያስገረመኝን የጉማሬ አለንጋ መሸጫ አየሁ፡፡
“ምንድነው?” ብል “ሚዜ የሚገረፍበት ነው” አለን ሻጩ፡፡
“ምን? እንዴት?” አልኩና ጠየኩ፡፡
(ይቀጥላል)

Read 1833 times