Saturday, 30 May 2015 12:23

ፊፋ በሙስና ቀውሱ የገቢና የክብር ኪሳራ ደርሶበታል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 

 

 

በሳምንቱ አጋማሽ ላይ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር 7 አመራሮች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በኤፍቢአይና በስዊዘርላንድ ፖሊስ ቅንጅት በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ዓለምአቀፉ የእግር ኳስ ማህበር በሙስና ቀውሱ የገቢና የክብር ኪሳራ እንደደረሰበት በመገለፅ ላይ ነው፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ፕሬዝዳንት ፕላቲኒ፣ የፈረንሳይና የእንግሊዝ እንዲሁም የአሜሪካ ባለስልጣናት ሴፕብላተር ከስልጣን እንዲወርዱ ጠይቀዋል፡፡

የራሽያው ፕሬዝዳንት ፑቲን አሜሪካ ዜጎቿ ባልሆኑ ሰዎች ላይ የወሰደችው እርምጃ ጣልቃ ገብነት ብለው ሲያወግዙት፤ ማራዶና በበኩሉ ባንድ ወቅት የፊፋን አመራሮች ስግብግብ ሙሰኞች ናቸው ብሎ ሲናገር እንደእብድ መቆጠሩን አስታውሷል፡፡ ፊፋ በካዝናው እስከ 1.5 ቢሊዮን ዶላር አካብቶ በዓለም እግር ኳስ ግን ከ150 ዶላር በታች ገቢ ያላቸው ተጨዋቾች አሉ የሚለው ማራዶና አሁን ያለው የፊፋ አመራር ያለአንዳች ቅድመሁኔታ ከስልጣን መውረድ እንዳለበት ተናግሯል፡፡

 ብላተርና የፕሬዝዳንት ምርጫው

ሰሞኑን ከተፈጠረው ቀውስ ጋር በተያያዘ 65ኛው የፊፋ ኮንግረስ ጉባዔ እና የፕሬዚዳንት ምርጫው መካሄዱ አጠያያቂ መስሎ ነበር፡፡

የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር አባል አገራቱ በዚሁ የምርጫ ሂደት ላይ እንዳይሳተፉ የጠየቀ ሲሆን በሌሎች ክፍለዓለማት የሚገኙ አገራትም ሁኔታውን በጥርጣሬ እየተመለከቱት ሰንብተዋል፡፡

በፊፋ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ የ79 ዓመቱ ሴፕ ብላተር ለ5ኛ ጊዜ እንደሚመረጡ የተጠራጠረ አልነበረም፡፡  ብላተር አስተዳደራቸው በሙስና ወንጀሎች በተናጠበት ወቅት ለ5ኛ ጊዜ በፕሬዝዳንትነት ለመመረጥና ፤በእስራኤልና በፍልስጤም ፌደሬሽኖች መካከል እርቅ ለመፍጠር ትኩረት አድርገው ሰንብተዋል፡፡ ከመረጣችሁኝ በሚቀጥለው የስራ ዘመኔ ለፊፋ የተንሰራፋውና ችግር ለመቅረፍ እችላለሁ በሚልም ቃል ገብተዋል፡፡

የፊፋ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ስድስት ኮንፌደሬሽኖች 209 አገራትን በመወከል ይሳተፋሉ፡፡ 54 አገራት ከአፍሪካ ዞን፤ 53 አገራት ከአውሮፓ ዞን፤ 46 አገራት  ከኤሽያ ዞን፤40 አገራት ከሰሜንና መካከለኛው አሜሪካ ፤ 10 አገራት ከደቡብ አሜሪካ ዞን፤ 11 አገራት ከኦሽኒያ ዞን ናቸው፡፡ ሴፕ ብላተር በይፋ ድጋፋቸውን ከገለፁላቸው ከአፍሪካ እና  ኤሽያ ዞኖች በሚያገኙት 100 ድምፅ የማሸነፍ እድላቸው ያመዝናል፡፡ ፕሬዝዳንት ሆኖ ለመመረጥ ቢያንስ ከ140 አገራት የድምፅ ድጋፍ መገኘት አለበት፡፡ በፕሬዝዳንትነት ምርጫው ከብላተር ጋር ለመፎካከር አመልክተው የነበሩት ሦስት ግለሰቦች ነበሩ፡፡ ታዋቂው እግር ኳስ ተጨዋች እና ፖርቱጋላዊው ሊውስ ፊጎ የመጀመርያው ነበር፡፡ ብዙም ወደ ምርጫ ዘመቻው ሳይገባ ፊፋ በአንድ ሰው አምባገንነት የሚመራ ተቋም ነው ብሎ በምሬት ራሱን አግልሏል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የሆላንድ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ሲሆኑ የኤስያ እና የአፍሪካን ድጋፍ ማግኘት እንደሚከብድ ገልፀው ለድምፅ ፉክክር ሳይገቡ ቀርተዋል፡፡ ከሴፕ ብላተር ጋር ለመፎካከር የመጨረሻው እጩ ሆነው የቀሩት ግን የ39 ዓመቱ የጆርዳን ልዑል አልቢን ናቸው፡፡ ከአውሮፓ ዞን አገራት ከአሜሪካ እና ከሌሎች አገራት እስከ  50 ድምፅ ድጋፍ ማግኘት እንደሚችሉ ተገምተዋል፡፡  ሴፕ ብላተር በምርጫ አሸንፈው ፊፋን በ5ኛ የስራ ዘመን በፕሬዝዳንት መምራት ሲችሉ በአጠቃላይ 27 አመታት በስልጣኑ ይቆያሉ ማለት ነው፡፡

 በሙስና መረቡ ከሳሾችና ተከሳሾች

የፊፋ አመራሮች በቁጥጥር ስር ሲውሉ የስዊዘርላንድ መንግስት ከፍተኛ ሚና ነበረው፡፡ የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደህንነት ቢሮ ሰባቱን ባለስልጣናት ዙሪክ በሚገኝ  ባለአምስት ኮከብ ሆቴል በቁጥጥር ስር አውሏቸዋል፡፡ በሰው 4ሺ ዶላር የሚከፈልበትና ከፍተኛ ድሎት ያለው ያለው ባወር የተባለ ሆቴል ነበር፡፡  ኤፍ ቢ አይ ያለፉት 24 ዓመታት በፊፋ እንቅስቃሴ ዙሪያ ምርመራ እና ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዓለም ዋንጫ አዘጋጆች ምርጫ፣ በፊፋ የፕሬዝዳንትነት ሹመትና ከስፖንሰርሺፕ ውሎች በተገናኘ ብዙ ወንጀሎች ተፈጽመዋል በሚል መነሻ ነው፡፡ ከዚህ በተያያዘ 9 የእግር ኳስ አመራሮች እና አምስት የትልልቅ ስፖርት ሚዲያ እና ፕሮሞሽን ኩባንያ አመራሮች በሙስና መረብ መውተብተባቸውን ሲገለፅ ከ150 ሚሊዮን ዶላር መመዝበሩ ተረጋግጧል፡፡ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሰባቱ የፊፋ አመራሮች ከላቲንና ከካራቢያን አገራት ውክልና አግኝተው ለፊፋ የሚሠሩ ናቸው፡፡ ከተከሳሾቹ መካከል ሁለቱ ብቻ ናቸው የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው፡፡

14ቱ ፊፋ ባለስልጣናት  እና የማርኬቲንግ ወኪሎች በህገወጥ ድለላ፤ ሴራና ጉቦ  በአሜሪካ ፍትህ አስተዳደር በ47 ወንጀሎች ተከስሰዋል፡፡ በአለም አቀፍ እግር ኳስ ውድድሮች በማርኬቲንግ እና የሚዲያ መብት ለሚኖሩ ገቢዎች ሲባል ጉቦ የበዛባቸው ድርድሮች ተካሂደዋል ይባላል፡፡ከላይ የተጠቀሱት የውስጥ ወንጀሎች የአሜሪካ የፍትህ አስተዳደር ያቀረባቸው ክሶች ናቸው፡፡ ክስ በ2010 እኤአ ላይ ደቡብ አፍሪካ 19ኛውን ዓለም ዋንጣ ለማዘጋጀት በባልስልጣናቷ በኩል 10 ሚሊዮን ዶላር ጉቦ መክፈሏን የሚያረጋግጥ ማስረጃ አለኝ ብሎ ተጨማሪ ክስ የሚያቀርበው የአሜሪካ መንግስት በ2011 እኤአ ላይ ብላተር ለ4ኛ ጊዜ የፊፋ ፕሬዝዳንት ሆነው ሲመረጡ ድምፅ ለሰጧቸው አገራት በነፍስ ወከፍ እስከ 40ሺ ዶላር መክፈላቸውን እየገለፀም ነው፡፡

በሙስና ወንጀሎቹ ላይ የ24 ዓመታት ክትትል ማድረጉን ያሳወቀው የአሜሪካ የፍትህ አስተዳደር ሴፕ ብላተርን በክሱ ዝርዝር ባይጠቅስም አሜሪካ ቢገቡ ያስራቸዋል የሚል ዘገባ የተናፈሰ ቢሆንም ማረጋገጫ አልሰጠም፡፡ ብላተርም የክሱ አካል እንዳልሆኑ በልበ ሙሉነት ሲናገሩ ሌሎች ትልልቅ የፊፋ ባለስልጣናት ሊታሰሩ እንደሚችሉ እርግጠኛ ነኝ ብለዋል፡፡

ፊፋ ለዓመታዊ ደሞዝ እስከ 88 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሲሆን የስራ አስፈፃሚ አባል ለሆኑት 13 ባለስልጣናቱ እስከ 40 ሚሊዮን ዶላር መክፈሉ የሙስናው መገለጫ እንደሆነም የአሜሪካ ሚዲያዎች ይዘግባሉ፡፡

ሌላው ከሳሽ የስዊዘርላንድ መንግስት ሲሆን ክስ ያቀረበው ራሽያ እና ኳታር የዓለምዋንጫዎች አዘጋጆች ሆነው የተመረጡት በሴራ ተቀናብሮ እና ጉቦ ተሰጥቶ ነው ይላል፡፡

ባለፈው አመት በፊፋ ተቀጥሮ የነበረው ማይክል ጋርሺያ የተባለው የቀድሞ አቃቤ ህግ በሁለቱ አዘጋጆች አመራረጥ ዙርያ በ432 ገፆች የምርመራ ሪፖርት አቅርቦ ነበር፡፡

ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ይህ ሪፖርት ይፋ እንዳይሆን በማገዱ ከሃላፊነቱ ራሱን ማግለሉ አይዘነጋም፡፡

በተለይ በ2012 እ.ኤ.አ ራሺያ እንዲሁም በ2022 ኳታር 21ኛውና 22ኛውን የዓለም ዋንጫ እንዲያዘጋጁ የተመረጡት በሙስና በተደለሉ የፊፋ አመራሮችና ሌሎች ተቋማት የተቀናጀ የወንጀል መረብ ነው የሚል ውንጀላ ቀርቧል፡፡

የተበጠበጠው የስፖንሰርሺፕ ገበያ

የፊፋ ቀውስ ዓለም አቀፉን የእግር ኳስ የስፖንሰርሺፕ ገበያ የበጠበጠው ሲሆን አንዳንድ ትልልቅ ስፖንሰር አድራጊ ኩባንያዎች ከፊፋ ጋር የላቸውን ውል ለማውረስ እያጤኑ ናቸው ተብሏል፡፡

ፊፋ የገባበት የሙስና ቀውስ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙለትን ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችም እያስከፋ ነው፡፡ በተለይ ቪዛ ካርድ የተባለው ኩባንያ ፊፋ በአስተዳደሩ ላይ ስርነቀል ለውጥ ካላደረገ የውል ስምምነቱን ለማፍረስ እንደሚገደድ ገልጿል፡፡ የፊፋ አብይ ስፖንሰሮች ከሆኑት መካከል አዲዳስ፤ ኮካኮላ እና ሃዩንዳይም ሁኔታውን የሚያወግዝ መግለጫዎች አቅርበዋል፡፡

 እነዚህ ትልልቅ ኩባንያዎች በዓመት እስከ 28 ሚሊዮን ዶላር በነፍስ ወከፍ ለፊፋ በመክፈል እስከ የሚቀጥሉት ሁለት ዋንጫዎች በመስራት ለመቀጠል ይፈልጋሉ፡፡

አዲዳስ የሙስና ቀውሱ ወደየተባባሰ ሁኔታ እንዳያመራ በማለት ስጋቱን ሲገልፅ፤ ኮካኮላ በበኩሉ የዓለም ዋንጫን ገፅታ ጥላቻ የቀባ ክስተት ብሎ አውግዟል፡፡

ፊፋ የገቢውን 90 በመቶ ከዓለም ዋንጫ እንደሚያገኝ ይታወቃል፡፡ ብራዚል በ2014 እኤአ ላይ ያዘጋጀችው 20ኛው ዓለም ዋንጫ ላይ ፊፋ ያገኘው ንፁህ ትርፍ 2 ቢሊዮን ዶላር፡፡

ዓለምዋንጫው በተከናወነባቸው ከ2011 እስከ  2014 እኤአ  ባሉት አራት አመታት በሚዲያ እና የማርኬቲንግ መብት ገቢ የሆነው 6.4 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ለዓለም ዋንጫ ትኬት በመሸጥ ያስገባው ደግሞ 527 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ከስፖንሰሮች ደግሞ 106 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ነበረው፡፡

 

 

 

Read 2747 times