Saturday, 30 May 2015 12:17

የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ማደግ ይኖርበታል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

 

 

 

    በሽልማት ገንዘብ ፤ በቴሌቭዥን ስርጭት ፤ በስፖንሰርሺፕና ተያያዥ ንግዶች

    የ2007 የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ነገ ፍፃሜውን ያገኛል፡፡ ቅ/ጊዮርጊስ ሻምፒዮን መሆኑን ያረጋገጠው ከሳምንት በፊት ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ በአዲስ መዋቅር መካሄድ ከጀመረ ወዲህ ቅ/ጊዮርጊስ ለ12ኛ ጊዜ የሻምፒዮናነት ክብሩን መጐናፀፉ ይሆናል፡፡ ከነገው የሊጉ የመጨረሻ ጨዋታ በፊት ጊዮርጊስ በ25 ጨዋታዎች 54 ነጥብ እና 23 የግብ ክፍያ አስመዝግቧል፡፡  የሊጉን ሻምፒዮናት ያረጋገጠው ግን 15 ጨዋታዎችን ድል በማድረግ፤ በ6 አቻ በመውጣት እና በ3 በመሸነፍ ከሳምንት በፊት ነበር፡፡ አዳማ ከነማ በ42 ነጥብ ደደቢት በ41 ነጥብ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለፕሪሚዬር ሊጉ ሻምፒዮን እንዲሁም በተለያዩ ደረጃዎች የውድድር ዘመኑን ለጨረሱ ክለቦች እና ኮከብ ተጨዋቾች ምን ያህል የገንዘብ ሽልማት እንደሚሰጥ አይታወቅም፡፡ ሻምፒዮኑ ክለብ ቅ/ጊዮርጊስ ከሚያገኘው የዋንጫ ሽልማት ባሻገር ከ80-100 ሺ ብር ይሸለማል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ለኮከብ ተጨዋቾች እስከ 50ሺ ብር ሊበረከት ይችላል፡፡

የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ከመቼውም ጊዜ ለተለየ ሁኔታ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ለተለያዩ ዘርፎች ኮከቦች ሆነው ለሚመረጡ ተጨዋቾች ልዩ የመመዘኛ መስፈርት ማውጣቱም ታውቋል፡፡ መሠረት መገናኛ ብዙሐናትና አሰልጣኞች በሚሰጡት ድምፅ መሠረት የዓመቱ የሊጉ ኮከብ ተጨዋች፣ ኮከብ ግብ ጠባቂ እና የስፖርታዊ ጨዋነት ተሸላሚ ተለይተው ይታወቃሉ፡፡ የሊጉን የኮከብ ግብ አግቢነት ፉክክር የደደቢት ተጨዋች የሆነው ናይጄሪያዊው ሳሙኤል ሳኑሚ በ22 ጐሎች እየመራ ነው፡፡  ሳኑሚ የዮርዳኖስ አባይን 14 አመት የቆየ የ24 ግብ በአንድ የውድድር ዘመን የማስቆጠር ሪኮርድ ለመስበር ነገ በመጨረሻው ሳምንት ከቀድሞ ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በሚደረገው ጨዋታ ላይ ሌላ ሐት-ትሪክ መስራት ይጠበቅበታል፡፡

ዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በጊዜ መጠናቀቁ የተለየ ያደርገዋል፡፡  አሠልጣኝ ያሰናበቱት የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች  ሰባት መሆናቸው ደግሞ ሌላው መግለጫ ነው፡፡  ወልዲያ ከነማ፣ ሐዋሳ ከነማ፣ ደደቢት፣ አርባ ምንጭ ከነማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡናና ዳሽን ቢራ አሰልጣኞቻቸውን በማባረር የውድድር ዘመኑን የጨረሱ ናቸው፡፡

 ከፕሪሚዬር ሊጉ የወረደው ክለብ ደግሞ  አንዱ ወልደያ ከነማ ሲሆን ሌላኛው ዛሬ ነገ በሚደረጉት የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች ይታወቃል፡፡

በአዲስ መዋቅር መመራት ከጀመረ ዘንድሮ 17ኛ ዓመት የውድድር ዘመኑን የያዘው የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ በአገር ውስጥ የህትመትና የብሮድካስት ሚዲያዎች እንዲሁም በድረገፆች ከፍተኛ ሽፋን እያገኘ ነው፡፡ በገቢ አቅሙ ግን አላደገም፡፡ በውድድር ዘመኑ መጨረሻ ክለቦች ከተለያዩ ንግዶች የስፖንሰርሺፕ ገቢዎች እና ከሽልማት ገንዘብ ተጠቃሚ አይደሉም፡፡ ለቀጣይ የውድድር ዘመን ይህን ለመለወጥ መሠራት ይኖርበታል፡፡

የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በ2008 ዓ.ም የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ አብይ ስፖንሰር አግኝቶ በውድድር ዘመኑ መግቢያ ዳጐስ ያለ የገንዘብ ሽልማት ሊያበረክትላቸው ይጠበቃል፡፡ የተመረጡ የፕሪሚዬር ሊጉ ጨዋታዎች በቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭት ሽፋን የሚያገኙበት ዕድልም መፈጠር አለበት፡፡ ለሊጉ አብይ የስፖንሰር ሺፕ ውል በማግኘት ውድድሩን ለማንቀሳቀስ በጥናት ላይ የተመሠረተ ርምጃ መፈጠር አለበት፡፡ የፕሪሚዬር ሊጉ ክለቦች የትልልቅ ኩባንያዎችን፣ ባለሀብቶችና፣ የደጋፊዎችን ትኩረት የሚስቡበትን አሰራር በመፍጠር የገቢ አቅማቸውን ለማጠናከር መስራት አለባቸው፡፡

በየውድድር ዘመኑ የሊጉ ፉክክርና የክለቦች ደረጃ ጠቡ ተጠናክሮ መቀጠሉ የአገሪቱን እግር ኳስ ያግዛል፡፡ በተለያዩ አህጉራዊ ውድድሮች ክለቦች የሚኖራቸውን ተፎካካሪነት ያሳድጋል፡፡ የሊጉ በገቢ አቅም መጠናከር የብሔራዊ ቡደኑንም ውጤታማነት የሚደግፍ መሆኑም መታወቅ አለበት፡፡

ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ለፕሪሚዬር ሊግ ተወዳዳሪ ክለቦች፣ ደጋፊዎቻቸውና አመራራቸው መነቃቃት ይፈጥራል በሚል ለአፍሪካ ደረጃ ከፍተኛ ስኬት እያገኘ ያለውን የደቡብ አፍሪካ የኮከቦች ሊግ ስፖርት አድማስ በአጭሩ ለመዳሰስ ሞክሯል፡፡

የደቡብ አፍሪካ ሊግ ከ2 ሳምንት በፊት የተገባደደ ሲሆን በታሪኩ ለ4ኛ ጊዜ የሻምፒዮናነት ክብሩን በመቀዳጀት ካይዘርቺፍ ተሳክቶለታል፡፡ የደቡብ አፍሪካ ሊግ በምርጥ የውድድር ሂደቱ፤ በገቢው ጠንካራነት፤ በቴሌቭዥን ስርጭት ፤ በስታድዬም ተመልካች ብዛት እና ከደጋፊዎች ጋር ባለው መጠነ ሰፊ ትስስር እንደምሳሌ እንደሚጠቀስ  ቬንቹር አፍሪካ የተባለ ድረገፅ በሰራው ትንተና ተመልክቷል፡፡ ከደቡብ አፍሪካ ሊግ ባሻገር በስኬታማ የውድድር ሂደቱ፤ በተመልካቹ ብዛት እና በገቢ አመንጭነቱ ተቀራራቢ ስኬት ያላቸው ሊጐች በአልጄርያ እና በሞሮኮ የሚገኙት ናቸው፡፡ የግብፅ እና የቱኒዝያ ሊጎች ካለፉት አምስት አመታት በስታድዬሞች ስርዓት አልበኝነቱ በመብዛቱ አሽቆልቁለዋል፡፡ የናይጄርያው ሊግ ደግሞ በአስተዳደር ችግሮች፤ በዳኝነት ድክመቶች እና በተለያዩ ውዝግቦች በምሳሌነት የሚጠቀስ አይደለም፡፡

የገቢ ምንጮች

በደቡብ አፍሪካ እንደሚካሄዱ ብዙ የስፖርት እንቅስቃሴዎች የእግር ኳስ ሊጉ በገቢ አመለጭነት ብዙ ርቀት ተጉዟል፡፡ ሊጉ “አብሳ” በተባለ የአገሪቱ ትልቅ ባንክ በኦፊሴላዊ ስፖንሰርነት የሚደገፍ ሲሆን ከስሩ ያሉ ውድድሮች እና የጥሎ ማለፍ ሻምፒዮናው በኮርፖሬት ስፖንሰርሺፕ እና በአጋርነት “ኔድ ባንክ” እና “ኤምቲኤን” ከተባሉ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በፈፀሙት ውል ይከናወናሉ፡፡ እነዚህ ስፖንሰሮች ከደቡብ አፍሪካ የእግር ኳስ ውድድሮች ጋር ለመስራት ፍላጎት ያደረባቸው በሚያገኙት የብራንድ ግንባታ ተጠቃሚ በመሆናቸው ነው፡፡ በሊጉ የሚወዳደሩ ክለቦችን ደጋፊዎቻቸውን በልዩ ፍቅር እና ትኩረት ስታድዬም በመግባት እና በቲቪ ስርጭት መከታተላቸው አንዱ ውጤት ነው፡፡ የሊጉ ሻምፒዮን አሁን ባለፈው ሰሞን የውድድር ዘመኑን በድል ያጠናቀቀው ካይዘር ቺፍ ያገኘው ሽልማት 836ሺ ዶላር ነው፡፡ የናይጄርያው የዘንድሮ ሻምፒዮን ያገኘው 86ሺ ዶላር ብቻ ነው፡፡

የደጋፊ ሃይል የደቡብ አፍሪካ እግር ኳስ የደጋፊዎችን ትኩረት እና ፍላጎት በማግኘት በአፍሪካ የሚስተካከለው የለም፡፡ ስታድዬሞች ከስርዓት አልበኝነት በተያዙ ችግሮች አለመረበሻቸው እንዱ የደጋፊዎችን ትኩረት ያመጣ ነው፡፡ ሊጉ በቲቪ ስርጭት በማላው ዓለም እስከ 86 ሚሊዮን ቋሚ ተከታታይ ለማፍራት መቻሉም ሌላው የስኬቱ ምስጥር ነው፡፡ብቁ የውድድር አመራር በናይጄርያ የውድድር መርሃ ግብሮች መዛባት፤ በሌሎች የአፍሪካ ክፍሎች በዳኝነት ብቃት መዳከም፤ በሰሜን አፍሪካ ስታድዬሞች ያሉ ስርዓት አልበኝነቶች በደቡብ አፍሪካ ሊግ ያጋጥማሉ ተብሎ አይታሰብም፡፡ ለዚህ ዋና ምክንያቱ የሊጉ አስተዳዳሪዎች ውድድሮቹን በብቃት የሚመሩበት ሂደት ነው፡፡የሊጉ አስተዳዳሪዎች ግጥሚያዎች በስታድዬም ሲካሄድ አስፈላጊውን አስተማማኝ የደህንነት ጥበቃ በማድረግ ተመጣጣኝ የስታድዬም ትኬት በማሰራጨት፤ በተሟላ የፕሮፌሽናል መንገዶች ስርጭት እንዲኖራቸው በማስቻል ብበቃት ሃላፊነታቸውን መወጣታቸውም ሌላው ውጤት ነው፡፡

 

 

 

 

Read 2238 times