Saturday, 30 May 2015 12:01

ተውላጠ መክሊት

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(3 votes)

 

 

 

በአንዱ ባልደረባ ላፕቶፕ የጥላሁን ዘፈን ተከፍቶ እያዳመጥን አንድ ሃሳብ አናቴን ወጠወጠኝ፡፡

“ይኼ ዘፈን የጥላሁን ነው አይደል?” ስል በዙሪያዬ ያሉትን ጠየቅኳቸው፡፡

“አዎ ነው…” ካሉኝ በኋላ መልሰው “አይ የጥላሁንን አስመስሎ የዘፈነው…ማነው ስሙ” ብለው የአስመስሎ ዘፋኙን ስም ከኮርኒሱ ላይ ትንሽ ከፈለጉት በኋላ ሲያጡት “ያው የጥላሁን ነው” ብለው ጭጭ አሉ፡፡

አድቤ ሳደምጠው፤ ተመሳስሎ የተዘፈነው ከኦርጅናሌው ጋር የሚለያይበት ድምፅ የቱ ጋ እንደሆነ ማወቅ ተሳነኝ፡፡ በቃ ጥላሁን አይደለም፤ ግን ጥላሁን ነው፤ ብዬ ማድመጤን ቀጠልኩ፡፡  እያደመጥኩ የሃሳብ ሰንሰለቶች ተቀጣጥለው ይወጣጡብኝ ጀመር፡፡ “ታሪክ የሚፃፈው በአሸናፊዎች ነው” የምትል አባባል ከሃሳቤ ዜማ ጋር ምት ጠብቃ ታንቃጭልብኛለች፡፡

አዲሱ ዘፈን የጥንቱን ዘፈን አስረስቶ፣ የራሱን ባለጊዜነት ማረጋገጥ እንደሚችል እርግጠኛ ሆንኩኝ፡፡ አሮጌው ታሪክ በአዲሱ ይተካል፡፡ አሮጌው ዜማ በአዲሱ፡፡ ግን በአሮጌው እና በአዲሱ መሀል ምንም አዲስ ነገር ከሌለ… አዲሱ አሮጌውን ወርሶ ነው አዲስ የሆነው፡፡

ይኼንን እይታ ይዤ ወደማውቃቸው ወይንም ከዚህ በፊት ወደታዘብኳቸው ነገሮች ተመለከትኩ፡፡

መጀመሪያ ትዝ ያለኝ ስለ ገጣሚ በእውቀቱ ስዩም እና ስለ ተመሳሳዮቹ የተወራልኝ ጉዳይ ነው፡፡ “ተውላጠ” በእውቀቱ ልላቸው እችላለሁ፡፡ በፌስ ቡክ ማህበረሰብ ውስጥ እውነተኛው በእውቀቱን በስምም በአፃፃፍም ተመስለው ስራቸውን የሚያቀርቡ ሰዎች እንዳሉ ሰምቻለሁ፡፡

እውነተኛው ኦርጅናሉ ነው፡፡ ግን አርቴፊሻሉ የኦሪጅናሉን ስም እና ስራ ተመርኩዞ አዳዲስ እና ኦሪጅናል ግጥሞች መፍጠር ቢጀምር…እና ይጠጌውን ከይነኬው መለያየት ቢያቅትስ?

እንደዛማ እንዴት ይሆናል? ልክ መልካችን እና የጣታችን አሻራ የተለያየ እንደሆነው አስተሳሰብ እና ፈጠራችንም መጠነኛ ወይንም ከፍተኛ ልዩነት ሳይኖረው አይቀርም፡፡

ልዩነቱን ማወቅ አለመቻል ነው የአንዱን ታሪክ ለሌላው የሚያወርሰው፡፡

በሰማዩ ታሪክም ላይ የመውረስ ሙከራ ተደርጐ ነበር፡፡ ሰይጣን መላዕክቱን፤

“እኔ ነኝ እውነተኛው እግዚአብሔር” ብሎ አሻራ ለመውረስ ተፈራግጦ ነበር፡፡ አንድ የነበረው ቅዱስ ስብስብ ወደ ሁለት የተሰነጠቀው በዚህ መንስኤ ምክንያት ነው፡፡ ግን እግዚአብሔር አልፋ እና ኦሜጋ ስለሆነ ታሪኩንም ሆነ ማንነቱን መውረስ እንዲህ ቀላል አልሆነም፡፡

አዲሱ የአንድነት ፓርቲ የቀድሞውን ወርሶ፣ አንደኛው የሌላኛውን አጥፍቶ እንደፃፈው አይደለም የላይኛው ታሪክ፡፡ ግን ከዚያ ጊዜ እስካሁን ተመሳሳይ ድርጊት፣ ቅርፅ እና ይዘቱን እየለወጠ መወራረሱ ቀጥሏል፡፡

እንበልና፤ ከዛሬ አምስት መቶ አመት በኋላ… በአምስት መቶ የተለያዩ ድምፃዊ የጥላሁን ዜማ ቢዘፈን ማነው ኦርጅናል ማነው ቅጂ? ለማለት በጣም አዳጋች ነው የሚሆነው፡፡ “የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውም” በሚል እምነት የሚያመልክ ሁሉ በዘመኑ ያገኘውን ዘፈን ይወዳል፡፡ የወደደውን ደግሞ ከህይወቱ ጋር ያስተሳስራል፡፡ ህይወቱ እና መውደዱ ኦርጂናል ስላለመሆኑ ቢነገረው እንኳን አንቅሮ መትፋት አይችልም፡፡ አንቅሮ ተፍቶ የዛሬ አምስት መቶ አመት ወደ ኋላ ተመልሶ በትዝታ ለመኖር? አይመስልም፡፡

የአይሁድ ንጉስ ሰለሞን በአንድ ወቅት ገላውን ለመታጠብ የጣት ቀለበቱን አወለቀ፤ አሉ፡፡ የጣት ቀለበቱ የእሱን ማንነት የማወቂያ እና የማረጋገጫ ብቸኛው ማህተሙ ነው፡፡ እና  ገላውን ታጥቦ ሲጨርስ ሌላ ተራ ሰው የጣት ቀበለቱን አንስቶ አጥልቆታል፡፡ ያጠለቀው ተራ ሰው የንጉሥን ካባ ተደርቦለት ወደ ቤተመንግስቱ ገባ፡፡ ኦሪጅናሉ ንጉስ ስልጣኑንና ከሰማይ በታች ሁሉን የማድረግ አቅሙን ከቀለበቷ ጋር አጣ፡፡ ምናልባት፤ በዚህ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም መጽሐፈ መክብብ እና የሰለሞን መዝሙር ተብለው የሚታወቁለትን ስራዎች ለመፍጠር የተገደደው፡፡ “ከሰማይ በታች ምንም አዲስ ነገር የለም…ንፋስን እንደመከተል ነው… አይንም ከማየት አይጠግብም ጆሮም ከመስማት አይሞላም… በአለም ያለ ሁሉም የከንቱ ከንቱ ነው” ለማለት የበቃው ምናልባት ከቀለበቱ መወረስ፣ ከመክኪሉቱ መነጠቅ በኋላ ሳይሆን  አይቀርም፤ ማን ያውቃል?

ቀለበቱ ሲመለስለት (እንዴት እንዳስመለሰ ባይነግሩኝም) በድጋሚ ስዩመ እግዚአብሔር ሆነ፡፡

እንግዲህ በዛች ቀለበቱ የተወከለው መክሊቱ ወይንም ኦሪጅናልነቱ ወይንም ከፈጣሪ የተሰጠው የስልጣን ቅቡልነት ሊሆን ይችላል፡፡ ገጣሚው በእውቀቱም ሆነ ድምፃዊው ጥላሁን ገሰሰ ይህ ቅባት አላቸው፡፡ የጥበብ ስራዎቻቸውን እንደ ሰለሞን የቀለበት ማህተም መመሰል እንችላለን፡፡ ግን የሰለሞንም ቀለበት በተመሳሳይ እንደተቀዳው ጥላሁን እና በእውቀቱም የሚቀዳቸው አያጡም፡፡ ቀጂው እውነተኛውን ተመሳስሎ የራሱን ተራ ማንነት በውዱ ይለውጣል፡፡ ሲቆለል የኖረ ስም፣ ዝና እና ታሪክን የራሱ ያደርጋል፡፡ የራሱ ለማድረግ ማሸነፍ መቻል አለበት፡፡ ጦርነቱ በጣም ጠላቱን በመምሰል እና ራሱን በመደበቅ ወይ በማስረሳት ችሎታው የሚወሰን ነው፡፡

የቀድሞውን የፖለቲካ ስርዓት እና ስርዓቱ ያቆማቸውን ታሪኮች መውረስ የሚቻለው… በድጋሚ ስርዓቱን በተመሳሳይ ድርጊት በመድገም ብቻ ነው፡፡ መድገም ወይንም መደጋገም መነሻውን ያስረሳል፡፡ በመጀመሪያው እና በተከታዮቹ መሀል ያለውን ልዩነት በተመሳሳይነት ውስጥ ያድበሰብሳል፡፡

የደራሲ በአሉ ግርማን ታሪክ ለመውረስ የሚፈልግ እንደ በአሉ ግርማ ይፅፋል፡፡ ይፅፍና “በዓሉ ግርማ አልሞተም” ወይንም “ከመሞቱ በፊት የሰራቸው ስራዎች” በሚል ስም መጽሐፍ ያሳትማል፡፡ ስኬታማም ይሆናል፡፡ ምክንያቱም የድሮው ታሪክ አዲሱን ዘመን የማስቆም አቅም የለውም፡፡ የድሮው ታሪክ በቆመበት ስፍራ ጥንት ላይ ነው ያለው፡፡ ከቆመበት የአላፊ ጊዜ ወደፊት የሚሻገረው ዝናው ብቻ ነው፡፡ በአዲሱ ዘመን የድሮውን ታሪክ መድገም የሚችል ባለ ጊዜ ግን ዝናውን የራሱ አድርጐ ይወርሳል፡፡ መውረስ ማለት ተወራሹን ደብዛውን አጥፍቶ በራስ መተካት ማለት ነው፡፡

በተሰጥኦ ውድድር ስም የተለያዩ ታዳጊዎች አምሳያ የሌላቸውን ሰዎች ለማስመሰል ሲሞክሩ ማየት የተለመደ ነው፡፡ አዲስ ማንነትን ከመፍጠር፣ ማንነት ያላቸውን መምሰል በቀላሉ (በአቋራጭ) ተቀባይነትን ያስገኝላቸዋል፡፡ ግን ደግነቱ፤ ሙሉ ለሙሉ ኦሪጅናሉን የመሆን አቅም ያለው አይገኝም፡፡ ቢገኝ እና የኦሪጅናሉን ስራ ከመድገም ወደ መፍጠር ቢሸጋገር፣ ኦሪጅናሉ አስመሳዩ ሆኖ አሮጌው በአዲሱ እንደሚረሳ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡

በጊዜና በዘመን ላይ አካል ሳይሆን ሃሳብ ነው የሚነግሰው፡፡ ጥበብም በመሰረቱ ሃሳብ ነው፡፡ የፖለቲካ ስርዓትም ሃሳብ ነው፡፡ ታሪክ ከሀሳብ ድምር የተሸመነ ከጊዜ ውስጥ ራሱን በሰዎች መንፈስ አስገብቶ የሚላወስ ሃይል ነው፡፡ ሀይሉ፤ ሀገርን፣ ማህበረሰብን፣ ሃይማኖትን ይፈጥራል፡፡ ኃይሉ፤ የሰው ልጅን በስልጣኑ ስር የሚያደርግ ብቸኛው የፈጣሪ ተምሳሌት እና የመክሊት መግለጫ ነው፡፡ ይኼንን የሃይል ውክልና ለመሻማት መሞከር ተፈጥሯዊ ነገር ነው፡፡ ውክልና በተሰጥኦ የተቸራቸው ብቻ ግን አይደሉም ሃይሉን የሚፈልጉት፡፡

እግዜርን መሆን የሚችለው እግዜር ብቻ ቢሆንም፤ መሆን ያልቻለው ስልጣኑን ከመፈለግ ወደ ኋላ አስቀርቶት አያውቅም፡፡ ሰይጣን በእግዜር ስልጣን ላይ ለመቀመጥ ብቁ ባይሆንም ለመቀመጥ ከመሞከር ቦዝኖ እንደማይተወው እንደማለት፡፡

እንደ ሰይጣን እግዜርን በአንድ ጊዜ የሚወድ እና የሚጠላ ያለ አይመስለኝም፡፡ መውደዱ የሚያስታውቀው እግዜርን ለመሆን ከመሞከር ቦዝኖ አለማወቁ ላይ ነው፡፡ ጥላቻው ደግሞ የሚመነጨው ሊሆን እንደማይችል በማወቁ ይመስለኛል፡፡

ስልጣንን የማይፈልግ የለም፡፡ ስልጣን የሚገባውም የማይገባውም ይፈልገዋል፡፡ ጥበበኛም ህዝቡን የሚነቀንቅ ስልጣን ይጨብጣል፡፡ ከጨበጠው ለመንጠቅ አስመሳይ ይነሳል፤ ታሪኩን በዝና ስም ለመውረስ፡፡ ታሪክም ሆነ ዝና የስልጣን ዘውጐች ናቸው፡፡

በእውቀቱን ተመሳስለው የሚጽፉት ሰዎች እንደ በእውቀቱ ስራ የሚወዱት እና በዛው መጠን የሚጠሉት ነገር የለም፡፡ መውደዳቸው የሚታወቀው ማንነታቸውን በገጣሚው ማንነት ለመቀየር ምንም አለማንገራገራቸው ነው፡፡ መጥላታቸው የሚታወቀው የእሱን ማንነት አስረስተው በራሳቸው ማንነት ለመቀየር እና ታሪኩን በታሪካቸው (ቢሳካላቸው) ለመተካት አይናቸውን አለማሸታቸውን ልብ ስንል ነው፡፡

የማስመሰል ወይንም የመውረስ ፍላጐት ስልጣንን በተመለከቱ መስተጋብሮች ሁሉ ተመሳሳይ አካሄድ ያለው ይመስለኛል፡፡

ያ የፈረደበት “Animal Farm” የሚለው ድርሰት፣ ይሄንኑ እምነቴን ለማረጋገጥ በውስጤ በቂ ሆኖ ይደቀንብኛል፡፡

የእንስሶቹ ማህበር፣ ከሰው ልጆች ጭቆና ነፃ ለመውጣት መርጦ አመጽ ቀሰቀሰ፡፡ ሰይጣን መላዕክቶቹን በእግዜር ላይ ለማስነሳት በሞከረበት መንገድ ተመሳስሎ፡፡  አመፁ ተሳካ፤ እንስሳቱ ነፃ ወጡ፡፡ ነፃ ሲወጡ የሰው ልጅ እነሱን ለመጨቆን የሚገላገልባቸውን ኮተቶቹን ሁሉ ሰብስበው አስወገዱ፡፡ ሰውን ሰው ካደረጉት መገለጫዎቹ ማንኛውንም ነገሮች ልብሱን፣ መጠጡን የቁማር ሱሱን… የቤት ውስጥ ቁሳቁሶቹን፣ አልጋ እና የምርት መሳሪያዎቹን ላለመገልገል ምለው አስወገዱ፡፡ በታሪኩ ሂደት ውስጥ ግን የእንስሳቶቹ መሪዎች ቀስ በቀስ ሰውን ለመምሰል እየተፍጨረጨሩ መሆኑ ግልጽ ይሆን ጀመር፡፡ ከበፊቱ ለመለየት ሳይሆን የበፊቱን ለመምሰል እና ለመሆን ብቻ አመጽ እንደቀሰቀሱ ልብ ማለት እንችላለን፡፡

በስተመጨረሻ የምንረዳው ነገር እንስሳቶቹ ድሮውኑ (በደመነፍሳቸው ባያውቁትም) ሰውን መሆን እንዲችሉ ነው ሰውን ከመክሊቱ ያፈናቀሉት፡፡ ታሪኩንም ለመፋቅ የሞከሩት፡፡ እንስሳትን ነፃ ለማውጣት ሳይሆን የተመረጡ እንስሳት ሰው ሆነው ያልተመረጡት ላይ ስልጣን እንዲቀዳጁ ነው ያ ሁሉ ውጣ ውረድ፡፡ እንደ እንስሳት የሰውን ጭቆና የሚጠላ እና የሚወድ የለም፡፡ የሚወደው፤ እሱም ራሱ አንድ ቀን ጨቋኝ ለመሆን ምኞት ስላለው፤ የሚጠላው ደግሞ የመጨቆኛ ስልጣን በተፈጥሮው (በመክሊቱ) ስላልተቸረው ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ማስመሰል ይገባል፡፡

መንግስትን አውርዶ በሌላ መንግስት የሚተካ አመፀኛ፤ ለመተካት የሚነሳው አዲስ ለውጥ ለማምጣት ሳይሆን ያወረደውን ቀዳሚውን ታሪክ ራሱ ወጥቶ ለመምሰል እንዲችል ነው፡፡ በኪናዊ ጥበብም ሆነ በህዝብ አስተዳደር ጥበብ፤ በመክሊት ያልተገኘ ውክልናን መክሊት ካላቸው በተመሳሳይ ካርቦን በመገልበጥ የስልጣን ባለቤት መሆን ይቻላል፡፡ ስለዚህ፤ ዜማውን እና ጊዜውን ይዞ የተገኘ ባለስልጣን ነው፡፡ ባለታሪክ ነው፡፡ ጊዜውን መያዝ የቻለ፤ እየወደደ መሆን ያቅተው ያቃተውን ቅናቱን… በማስመሰል ጥበብ፣ በተውላጠ መክሊት ወርሶ መሆን ይችላል፡፡  

 

 

 

Read 1745 times