Saturday, 30 May 2015 11:45

ዋናዎቹ ተቃዋሚዎች የምርጫ ውጤቱን አንቀበለውም አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(28 votes)

 

 

 

ምርጫ ቦርድ የተቃዋሚዎች ውንጀላ መሰረተቢስ ነው ብሏል

ባለፈው እሁድ በተከናወነው 5ኛው አገር አቀፍ ምርጫ የተወዳደሩ ዋና ዋናዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣የምርጫውን ፍትሃዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ግድፈቶችና የህግ ጥሰቶች መፈጸማቸውን ጠቅሰው የምርጫውን ውጤት እንደማይቀበሉ አስታወቁ፡፡ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በ442 የምርጫ ክልሎች ኢህአዴግ ሙሉ በሙሉ እንዳሸነፈ መግለጹን ተክትሎ  መድረክ፣ ሰማያዊ፣ ኢዴፓና መኢአድ የምርጫውን ውጤት አንቀበለውም ብለዋል፡፡

ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግን ተከትሎ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው እጩዎች ለውድድር ያቀረበው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ፣ምርጫውን አስመልክቶ ባለፈው ረቡዕ በሰጠው መግለጫ፤ የምርጫውን ፍትሃዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ግድፈቶችና የህግ ጥሰቶች በመፈጸማቸው የምርጫውን ውጤት ሙሉ ለሙሉ እንደማይቀበለው ጠቁሟል፡፡  

በቅስቀሳ ወቅት በአባላትና ደጋፊዎች ላይ ወከባ መፈፀሙንና በምርጫው ዕለት ታዛቢዎች ከምርጫ ጣቢያዎች መባረራቸውን የጠቀሰው መድረክ፤ ጉድለቶቹንና ግድፈቶቹን ዘርዝሮ ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በደብዳቤ ማመልከቱንና ምላሹን እየተጠባበቀ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

ባለፈው ረቡዕ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ 442 የምርጫ ክልሎችን ውጤት ያስታወቀ ሲሆን ኢህአዴግ ሁሉም ላይ ማሸነፉን ጠቁሞ፣ የተቃዋሚዎች ውንጀላ ሙሉ በሙሉ መሰረተ-ቢስ አሉባልታ ነው ሲል አጣጥሎታል፡፡ 

የመድረክ ምክትል ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና በበኩላቸው፤“የዘንድሮ ምርጫ ውጤት ከ2002 ምርጫ የባሰ የሃገሪቱን ዲሞክራሲ ያጨለመ ነው” ብለዋል፡፡ “ባለፈው ምርጫ ቢያንስ ሰረቁ ነው የሚባለው፤ አሁን ግን ዘረፋ ነው ያካሄዱት” ያሉት ዶ/ር መረራ፤ ኢህአዴጐች በሪከርድነት የያዙትን 99.6 በመቶ ውጤት ወደ መቶ ለማሳደግ አስበው ያደረጉት ይመስለኛል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ “ኢህአዴግ ያሸነፈው ወደ ዘረፋ ስለገባ ነው እንጂ ተቃዋሚ ስለተዳከመ አይደለም” ያሉት የመድረክ አመራር፤ “ምርጫ በዚህ ሀገር ላይ በትክክል የማይካሄድ ከሆነ በየ5 ዓመቱ ምርጫ እያሉ ህዝብን ከማሰቃየት፣ እንደነ ሰሜን ኮርያ እና ቻይና የአንድ ፓርቲ አገዛዝ ነው ብሎ ማወጁ ይመረጣል” ብለዋል፡፡ ገዢው ፓርቲ የምርጫ ውጤቱን ተመልክቶ “ስልጣን ወይም ሞት” የሚለውን አመለካከቱን መፈተሽ እንደሚገባው ጠቁመውም መንገዱ ብዙ ርቀት አያስኬድም ብለዋል፡፡ “ኢህአዴጎች በዚህ አካሄዳቸው ከቀጠሉ ማንንም የማትጠቅም ኢትዮጵያን ትተው እንዳይሄዱ ደግመው ደጋግመው ማሰብ አለባቸው” ሲሉ አሳስበዋል - ዶ/ር መረራ፡፡ “ህዝቡ ሰላማዊና ህጋዊ ትግሉን መቀጠል አለበት” ያሉት የፓርቲው አመራር፤ “ምርጫው ተጭበረበረ ብለን እጃችንን አጣጥፈን አንተኛም፤ ህዝቡ ከኛ ጋር ስለሆነ ትግላችንን እንቀጥላለን” ብለዋል፡፡

በምርጫው ከኢህአዴግ ቀጥሎ የተሻለ ድምፅ ያገኘው ሠማያዊ ፓርቲ ትናንት በሰጠው መግለጫ፤ ምርጫው ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ከተካሄዱት ምርጫዎች ጋር እንኳ ሊወዳደር የማይችል እጅግ ኢ-ፍትሃዊ፣ ወገንተኛና ተአማኒነት የሌለው በመሆኑ የምርጫውን ሂደትም ሆነ ውጤት አልቀበለውም ብሏል፡፡

“ነፃነት በሌለባት ኢትዮጵያ ህዝባዊ አስተዳደር መትከል ዘበት ነው” ያለው ፓርቲው፤ “በኃይል በተቀማ ድምፅ የሚመሰረት መንግስትም በህዝብ ተቀባይነት የለውም” ብሏል፡፡ በኢትዮጵያ የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እስከሚከበሩ ድረስ የነፃነት ትግሉ በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥልም ሰማያዊ  አስታውቋል፡፡

በዘንድሮ ምርጫ የተሳተፈው ምርጫውን ሊያስፈፅሙ የሚችሉ ገለልተኛና ብቃት ያላቸው ተቋማት እንደሌሉ እያስገነዘበ መሆኑን የጠቆመው ፓርቲው፤በምርጫው ምክንያት የተቃዋሚ ተወዳዳሪዎች፣ ታዛቢዎችና አባላት በገዥው ፓርቲ ካድሬዎች አፈናና እንግልት ደርሶባቸዋል ብሏል፡፡ “በህገ ወጥ አሰራሮች ታጅቦ የተከናወነ” ሲል የገለጸው የዘንድሮ ምርጫ፤ በምንም መመዘኛ ነፃ፣ ፍትሃዊና ተአማኒ ሂደት ያልታየበት በመሆኑ ሂደቱንም ውጤቱንም አልቀበለውም ብሏል-ሰማያዊ ፓርቲው፡፡

ከኢህአዴግና መድረክ ቀጥሎ በርካታ እጩዎችን ለምርጫው ያቀረበው የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ በበኩላቸው፤ በቅድመ ምርጫው ወቅት ኢዴፓ በሚዲያ የሚያስተላልፋቸው መልእክቶች ሳንሱር እየተደረጉበት መሆኑን በተደጋጋሚ መግለጻቸውን አስታውሰው፣በምርጫው ላይ ችግር መታየት የጀመረው በሂደቱ ላይ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በሂደቱ ወከባዎች በዝተውብን ነበር ያሉት ዶ/ር ጫኔ፤ በነዚህ ችግሮች ውስጥ ሆኖ ፓርቲያቸው በሂደቱ መሳተፍ መቀጠሉን ጠቁመው ሂደቱ ከህግ አፈፃፀም አንፃር ዲሞክራሲያዊ ነበር ማለት አይቻልም ብለዋል፡፡

 የኢህአዴግ ፅ/ቤት የህዝብና ኮሚኒኬሽን ኃላፊው አቶ ደስታ ተስፋሁ በሰጡት አስተያየት፤ “ሂደቱ ጥሩ ነው ብለው ወደ ምርጫው ከገቡ በኋላ ውጤት አይቶ ሂደቱ ትክክል አልነበረም ማለት ተቀባይነት የለውም” ሲሉ የኢዴፓን ሃሳብ ተቃውመዋል፡፡   አንዳንድ ፓርቲዎች በሂደቱ አምነው ከገቡ በኋላ ህዝብ እንዳልመረጣቸው ሲያውቁ ምርጫው ተቀባይነት የለውም ማለታቸው እኛ ካላሸነፍን ከሚል አባዜ የሚመነጭ ነው ያሉት  አቶ ደስታ፤ በምርጫው ህዝቡ መብቱን በትክክል ተግባራዊ ስለማድረጉ የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ ሌሎች ታዛቢዎች ያረጋገጡት በመሆኑ የምርጫውን ውጤት አልቀበልም ማለት ለህዝቡ ውሳኔ ያለመገዛት ፀረ ዲሞክራሲያዊ አካሄድ ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡ “ፓርቲዎች ህዝብ ለምን አልመረጠኝም ብለው ራሳቸውን መገምገም እንጂ ድክመታቸውን ወደ ሌላ አቅጣጫ ማዞር የለባቸውም” ብለዋል አቶ ደስታ፡፡

ከምርጫው በፊት የገዢው ፓርቲ አባላት ህግ በመጣስ ብዙ አፈናዎችና ወከባዎች ሲፈጽሙ ነበር ያሉት የኢዴፓ ፕሬዚዳንት፤ በምርጫው እለት የፓርቲያቸው ታዛቢዎች ከምርጫ ጣቢያዎች መባረራቸውን ጠቁመው፣“ታዛቢዎች በሌሉበት የተካሄደው ምርጫ ተአማኒ ነው ብለን አናምንም” ብለዋል፡፡ “ምርጫው ሚስጢራዊ በሆነ ሁኔታ አይደለም የተከናወነው” የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፤ “መራጮች እየተገደዱ ሲመርጡ ታዝበናል፣አሁንም ድረስ ታዛቢዎቻችን ለምን የተቃዋሚ ፓርቲ ታዛቢ ሆናችሁ በሚል እየተዋከቡብን ነው” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

ቅድመ ምርጫውም ሆነ የምርጫው እለት እንዲሁም ውጤት አገላለፁ የምርጫ ደንቦችንና ህጎችን ሙሉ በሙሉ የጣሰ ነው ያሉት ዶ/ር ጫኔ፤ ምርጫ ቦርድ ከአደረጃጀት አኳያ ራሱን ሊፈትሽ የሚያስገድደው ሂደት ተስተውሏል ብለዋል፡፡ የምርጫ ውጤቱ አገላለፅ ህዝቡ ትክክለኛ መረጃ እንዳያገኝ የሚያደርግ መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፤ ውጤቱን ሙሉ ለሙሉ ለምን መግለፅ እንዳልተቻለ ጠይቀዋል፡፡

“መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ድምፅ ለማግኘት አስቸጋሪ የነበረ ቢሆንም የተወሰነ ወንበር በፓርላማ እንደምናገኘን  ጠብቀን ነበር፤ነገር ግን ምርጫው አሳታፊ ባለመሆኑ አልተሳካም” ብለዋል፡፡ ፓርቲያቸው የሚጠብቀው ዓይነት ምርጫ እንዳልተደረገ ጠቁመውም አሳታፊ ባልሆነ ሂደት ሰላማዊ ትግሉን የትም ማድረስ እንደማይቻል ገልፀዋል፡፡

ኢዴፓ ስትራቴጂውን እንደገና በመቀየር ለተሻለ ትግል እንደሚዘጋጅ በመጠቆምም ተመሳሳይ ርዕዮተ ዓለም ከሚከተሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ግንባር ፈጥሮ ለመንቀሳቀስ ማቀዱን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን አሁንም ቢሆን ፓርቲው በምክንያታዊነት መንቀሳቀሱን ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ፓርቲያቸው ከገዢው ፓርቲ ጋር ከፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ባለፈ በተለየ ሁኔታ መነጋገር እንደሚፈልግም ዶ/ር ጫኔ አስታውቀዋል፡፡ ሌላው የምርጫ ተፎካካሪ የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሃሪ እንዲሁ፤ የምርጫውን ውጤት ለመቀበል እንደሚቸገሩ ተናግረዋል፡፡ “የተሰራው ስራ ለሀገር የሚበጅ አይመስለኝም” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ “ምርጫው ትክክለኛ አይደለም፤ አንቀበልም” ብለዋል፡፡ በሃገሪቱ ትክክለኛ ዲሞክራሲ ለማምጣት ጥረት የሚያደርጉ አካላትን ተስፋ የሚያስቆርጥ የምርጫ ውጤት መሆኑን የጠቆሙት አቶ አበባው፤ በሰላማዊ ትግል ለውጥ ማምጣት የማይቻል ከሆነ የፓርቲዎች መኖር ጥቅም የለውም ብለዋል፡፡ ምርጫ የህዝብ ፍላጎት በትክክል የማይገለፅበት ከሆነ የትግሉ ጉዳይ አጠያያቂ ይሆናል ሲሉም አቶ አበባው አክለዋል፡፡ የምርጫ ውጤቱን ረቡዕ ማታ መስማታቸውን የተናገሩት የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፕሬዚዳንት አቶ ትዕግስቱ አወሉ፤ስለ ምርጫው መረጃዎች እያሰባሰቡ እንደሆነና አቋማቸውን ለመግለጽ የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ መወያየት ስላለበት ምላሽ ለመስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ግንባር (ኢፌድሃግ) በበኩሉ፤ህዝብ ለመረጠው አካል እውቅና እንደሚሰጥ ጠቁሞ፣ለቀጣይ ምርጫ  ድክመትና ጥንካሬውን ገምግሞ ዝግጅት እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባለፈው ረቡዕ 442 የምርጫ ክልሎችን ውጤት ይፋ ያደረገ ሲሆን በሁሉም ክልሎች ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግና አጋሮቹ ማሸነፋቸውን ገልጧል፡፡

 ምርጫው በታሰበለት የጊዜ ሰሌዳ ያለምንም ችግር አሳታፊ፣ ፉክክር የታየበትና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ ተጠናቋል ያሉት የቦርዱ አመራሮች፤ከምርጫው ጋር የተገናኙ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ቅሬታዎችን መሰረተቢስ ናቸው በማለት ውድቅ አድርገዋቸዋል፡፡ “በምርጫው እለት ታዛቢዎችን ተባረውብናል፣ ኮሮጆዎች ሳይፈተሹ ድምፅ ተሰጥቷል፣ ኮሮጆዎች ተቀይረዋል፣ ምርጫው ተጭበርብሯል----የሚሉት መሰረተ ቢስ አሉባልታ ነው” ብለዋል - አመራሮቹ፡፡

 

 

 

 

 

 

Read 7721 times