Saturday, 16 May 2015 10:55

ፖንሴት እና ጎንደር

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(3 votes)

ፖንሴት በኢትዮጵያ ግዛት በተመለከተው ሁኔታ ተደንቋል፡፡ አበባው፣ ቅመማቅመሙ፣ ዛፉ እና ሣር ቅጠሉ ሁሉ ገነትን የሚያስታውስ ሆኖ ታይቶታል፡፡ በኑቢያ እና በሰናር ከተመለከተው ጥቁር የፊት ገፅ ለየት ያለ፤ ጠይም ዓሳ መሳይ የሚባል ገፅታ ያላቸው ልዩ ህዝቦች መካከል መግባቱንም ይናገራል፡፡


ከ1632 ዓ.ም (እኤአ) ወዲህ፤ አውሮፓውያንን በኢትዮጵያ ማየት ብርቅ ነገር ሆኖ ነበር፡፡ አውሮፓውያን ካቶሊኮች ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ፤ የወቅቱ ፀሐፊያን፤ ‹‹አቢሲኒያ›› እያሉ የሚጠሯትን ኢትዮጵያን የረገጠ የመጀመሪያው አውሮፓዊ ዶ/ር ቻርልስ ጃክዌዝ ፖንሴት ነው፡፡ ፖርቹጋሎች በኢትዮጵያ የፈጠሩት ሐይማኖታዊ ግጭት ነበር፡፡ ይህን ችግር ለማስወገድ ሲባል እነሱ ከሐገር እንዲባረሩ ተወሰነ፡፡ ፖንሴት፤ እነሱ ከተባረሩ ከስድሳ ዓመታት ገደማ በኋላ ነበር ወደ ኢትዮጵያ የመጣው፡፡ ለፖንሴት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በይፋ የተገለፀው ምክንያት ህክምና ቢሆንም፤ ሌላ ምስጢራዊ ተልዕኮም ይዞ ነበር - ሐይማኖታዊ ተልዕኮ፡፡
ታሪክ ፀሐፊዎች እንዳሰፈሩት፤ ‹‹ታላቁ ኢያሱ›› ወይም ቀዳማዊ ኢያሱ የተባለው ኢትዮጵያዊ ንጉሥ (1683-1706) የቆዳ ካንሰር የመሰለ ደዌ ይዟቸው ተቸግረው ነበር፡፡ ስለዚህ ፖንሴት የመጣው አፄ ኢያሱን ለማከም ነበር፡፡ እናም ዶ/ር ቻርልስ ጃክዌዝ ፖንሴት፤ እ.ኤ.አ ጁላይ 21፣ 1699 ዓ.ም ጎንደር ከተማ ገባ፡፡ ያጠናው የህክምና ትምህርት ቢሆንም፤ ሥራዬ ብሎ የመድኃኒት ቅመማ ሥራ ይሰራ ነበር፡፡
ፖንሴት ለህክምና ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ፤ዓሊ ሐጂ በተባለ ኢትዮጵያዊ ነጋዴ አማካኝነት ነው፡፡ ዓሊ ነጋዴ ነው፡፡ የሲራራ ነጋዴ የሚጓዝበትን ጎዳና ተከትሎ የሱዳን በረሃን አቋርጦ፤ የአባይ መነሻ ወደ ሆነችውና በወቅቱ ‹‹ካቶሊኮችን አምርሮ ይጠላል›› ተብሎ የሚታሰብ ህዝብ ከሚኖርባት ኢትዮጵያ ለመምጣት ጉዞው አደገኛ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ፖንሴት ጉዞ ለማድረግ የወሰነው፤ የኢትዮጵያውን ንጉስ ካልታወቀ የቆዳ በሽታ ህመም ለመፈወስ ነበር፡፡ ሆኖም ለጉዞው ሰበብ የሆነ፤ ሌላ ሐይማኖታዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ምክንያት ነበር፡፡ በምስጢራዊ ተልዕኮው፤ በካይሮ የሚገኘው የሌዊ 14ኛ ቆንስል ወኪል ሆኖ ነበር ወደ ጎንደር የመጣው፡፡ በጎንደር እና በቨርሳይለስ መካከል ለሚኖር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመሰረት ድንጋይ እንዲጥል ታስቦ ነበር የተላከው -ፖንሴት፡፡
ከዚህ ሌላ፤ በፈረንሳይ መንግስት ሞግዚትነት፤ ኢየሱሳውያን በኢትዮጵያ ሚሽናቸውን እንደገና ለማቆም የሚችሉበት ዕድል መኖሩን የማረጋገጥ ተልዕኮም ተሰጥቶታል፡፡ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዶክትሪንን ለመጠበቅ ከ66 ዓመታት በፊት ከኢትዮጵያ እንዲወጣ የተደረገው የካቶሊክ ሚሽን ተመልሶ እንዲተከል ለማድረግ የሚያስችል ቀዳዳ መኖሩን እንዲሰልል ታዝዞ ነበር፡፡ ከዚህ አለፍ ብሎ፤ የቦርቦን ንጉሳዊ መንግስት፤ ኤምፓየር በመፍጠር ፍላጎት የሚገፋ እንቅስቃሴውን ለማሳደግ፤ከምሥራቅ አፍሪካ አለፍ ብሎ በህንድ ውቂያኖስ አካባቢ ያለውን የፈረንሳይ መንግስት የተፅዕኖ ምህዳር እንዲሰፋ የማድረግ ዓላማም ይዞ ነበር፡፡
የፖንሴትን ጉዞ ልዩ የሚያደርገው፤ ከ66 ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያን ድንበር የተሻገረ የመጀመሪያው አውሮፓዊ መሆኑ፤ ወይም በዚያ ጊዜ ስለነበረው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ  ሁኔታ የሚያሳይ በዓይን ምስክርነት የተደገፈ የታሪክ ሰነድ የፃፈ ሰው መሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ ከሐይማኖታዊ ዕይታ ወጣ ብሎ፤ ‹‹ሴኩላር›› በሆነ አተያይ ስለ ኢትዮጵያ ህዝብ የበኩሉን አስተያየት ያቀረበ ፀሐፊ በመሆኑም ጭምር ነው፡፡
ፖንሴት እስኪመጣ ድረስ፤ ስለ ኢትዮጵያ በፅሑፍ የሰፈረው ነገር ሁሉ የተሰራው፤ በ1632 ዓ.ም ከኢትዮጵያ እስከተባረሩ ድረስ በሐገሪቱ ይኖሩ በነበሩ የፖርቹጋል ኢየሱሳውያን ነበር፡፡ በ15ኛው ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ ይኖሩ እና ይሰሩ የነበሩት ኢየሱሳውያን ከፃፏቸው ሰነዶች በቀር በሌላ አውሮፓዊ የተጠናቀረ ሥራ አልነበረም፡፡ እነኚህ ሥራዎች በጣም ዝርዝር ነገሮችን የሚያስነብቡን ቢሆንም፤ ማንም ሊገምተው እንደሚችለው ሥራዎቹ፤ የፀሐፊዎቹ የጋለ ሚሲዮናዊ ስሜት እና ተልዕኮ የሚንፀባረቅበት ነበር፡፡ የፖንሴት ሥራም ካቶሊካዊ ስሜት የተጫነው መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ ግን ተፅዕኖው ከእነሱ ለየት ያለ ሁኔታን የሚያሳይ ነው፡፡
ፖንሴት የሚያየውን ነገር ትርጉም እና አንድምታ ከመግለፅ ይልቅ፤ ያየውን ነገር እንዳየው በመግለፅ ላይ ያተኩር ነበር፡፡ ፖንሴት በሐገሪቱ እንደ ልብ ለመንቀሳቀስ የሚችል አልነበረም፡፡ የአማርኛ ቋንቋ መናገር ባለመቻሉ፤ በአረብኛ ቋንቋ እያስተረጎመ ይሰማ ነበር፡፡ ይህም ስለ ሐገሪቱ ጉዳይ ለመረዳት እንቅፋት መሆኑ ባይቀርም፤ የፖንሴት ሥራ በጣም የረቀቀ የጉዞ ማስታወሻ ባህርይ የሚታይበት ልዩ የታሪክ መዝገብ ነው፡፡
የፖንሴት ሥራ ‹‹ኤትኖግራፊክ›› ባህርይ አለው፡፡ በአውሮፓዊ ዓይን ሳይሆን በሐገሬው ዓይን (የሀገሬውን ባህላዊ አገላለፅ በመጠቀም የተሰራ ሥራ በመሆኑ አበጀህ የሚያሰኝ ይዘት አለው፡፡ የእርሱ ሥራ፤ ኢየሱሳውያን ከኢትዮጵያ ከተባረሩ በኋላ፤የአባይን ምንጭ ለመፈለግ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ታዋቂው እንግሊዛዊ ተጓዥ ጀምስ ብሩስ (1769-71) ከ1632 እስከ 1771 ባሉት ዓመታት ያለውን ሁኔታ በዓይን ምስክርነት የሚያሳይ ብቸኛ ሥራ ነው፡፡ የፖንሴት ሥራ ትልቁ ፋይዳ ያለው በዚህ ረገድ ነው፡፡ እርግጥ፤ በ1699 ዓ.ም ኢትዮጵያ ለአውሮፓ የማትታወቅ ሐገር አልነበረችም፡፡ ለሐይማኖታዊ ጉዞ  ወደ ኢየሩሳሌም የሚሄዱ አውሮፓውያን፤ በዚያ ከሚያገኗቸው ኢትዮጵያውያን ስለሐገሪቱ የተወሰኑ መረጃዎች ነበራቸው፡፡
በ1541 ዓ.ም የተመሠረተው የሁለቱ ህዝቦች ግንኙነት ጥሩ ነበር፡፡ ሆኖም 1577 ዓ.ም የመጀመሪያዎቹ ኢየሱሳዊያን ከመጡ በኋላ ባሉት 70 ዓመታት ውስጥ ግንኙነቱ እየተበላሸ ሄደ፡፡ ኢየሱሳውያን የተዋህዶ ኦርቶዶክስ እምነትን ትተው የካቶሊክ እምነትን እንዲይዙ በተደረገው ጥረት ግንኙነቱ ተበላሸ፡፡ ይህ ሁኔታ ከካህናት እና ከህዝቡ የ‹‹ይውጡልኝ›› እንቅስቃሴን አስነሳ፡፡ ከአውሮፓውያን ጋር የተፈጠረው ፀብ እየተካረረ መጥቶ የኢትዮጵያ መንግስት አውሮፓውያን ድንበር ተሻግረው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ ለማድረግ የሚረዳ ስምምነት ከቱርክ መንግስት ጋር ተፈራረመ፡፡ አካባቢውን ይቆጣጠር ከነበረው የኦቶማን ፓሻ ጋር በተደረገው በዚህ ስምምነት፤ አውሮፓውያን  በቀይ ባህር የተለያዩ ዳርቻዎች ሾልከው እንዳይገቡ ለማድረግ ተሞክሮ ነበር፡፡
በዚያ ጊዜ፤ ድንገት ሾልከው ወደ ሐገር የገቡ ካቶሊካውያን በንጉሡ ውሳኔ ወይም በተቆጣው ህዝብ በድንጋይ ተወግረው ተገድለዋል፡፡ ጀምስ ብሩስ ወደ ኢትዮጵያ እስከ መጣ እስከ 1769 ዓ.ም ድረስ ቁጣው አልበረደም ነበር፡፡ ስለዚህ፤ ብሩስ ወደ ሐገሪቱ ሲገባ የተፈጠረበትን ስሜት ሲገልፅ፤ ‹‹በዚያ ጊዜ፤ በጣም ፍርሃት ያሳደረብኝ ነገር፤ የሀገሪቱን የመንግስትን ወይም የታላላቅ ሰዎችን ጥበቃ ለማግኘት ከመቻሌ በፊት፤ ሞገደኛ ቄስ እንዳይገጥመኝ ነበር›› ሲል ፅፎ ነበር፡፡ ታዲያ በ1698-99 ባሉት ዓመታት ቻርልስ ፖንሴት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ጎልቶ ይታይበት ነበር፡፡
ፖንሴት ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት መነሻ የሆነው ነገር ብዙ ግልፅ ባይሆንም፤ የተለያዩ መረጃዎች የሚያመለክቱት አንድ ነገር ነው፡፡ በግብፅ እና በጎንደር መካከል ባለው የሲራራ ንግድ መስመር ይነግድ የነበረ ሐጂ ዓሊ የተባለ አንድ ታዋቂ ነጋዴ አለ፡፡ ይህ ነጋዴ ለንጉስ ቀዳማዊ ኢያሱ የቆዳ በሽታ ፈውስ የሚሰጥ ሐኪም እንዲፈልግ ተልኮ ካይሮ ገባ፡፡ በካይሮ ይኖር የነበረውና የፈረንሳይ ቆንስል ሆኖ ያገለገል የነበረው ቤኖይት ዲ ሜይሌት (Benoît de Maillet) የተባለ ሰው፤ ሐጂ ዓሊ ሐኪም ፍለጋ እንደመጣ ሲሰማ ምንም ጊዜ አላባከነም፡፡ ወዲያው ነገሩን ሁሉ በእርሱ አመራር ስር እንዲከናወን ለማድረግ ተንቀሳቀሰ፡፡ ሐገሩ ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት እንድትመሰርት እና በሊዊ 14ኛ ሞግዚትነት የኢየሱሳውያን ሚሽን ዳግም እንዲያንሰራራ የማድረግ ተስፋ ይዞ ተነሳ፡፡
ምንም እንኳን መጀመሪያ ላይ ቤኖይት ዲ ሜይሌት (Benoît de Maillet) ከቦርቦን ንጉሠ ነገሥት መንግስት ትዕዛዝ ሳያገኝ በገዛ ራሱ ውሳኔ የተንቀሳቀሰ ቢሆንም፤ የእርሱ ፍላጎት በመንግስት ዘንድ ከነበረው ፍላጎት ጋር የገጠመ ሆነለት፡፡ በዚሁ ፍላጎት ተነስቶ ሐጂ ዓሊን በእጅ በእግር ብሎ አጠመደው፡፡
ቻርልስ ፖንሴት፤ ከ1691 ዓም ጀምሮ መኖሪያው ካይሮ ነበረች፡፡ በዚያ የሚገኙ አውሮፓውያንን እና የኦቶማን ቱርክ ባለሥልጣናትን እያገለገለ ይኖር የነበረ ሐኪም ነው፡፡ በካይሮ ህክምና እየሰጠ እና መድሐኒት እየቀመመ ደንበኞቹን ያገልግል ነበር፡፡ ታዲያ ሜይሌት፤ ዶ/ር ፖንሴትን ለጎንደር ተልዕኮ መረጠው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ሊልከው ወሰነ፡፡ ከእርሱም ጋር አብሮ የሚጓዝ አንድ ኢየሱሳዊ ወንድም አብሮ እንዲሄድ ለማድረግ አስቦ፤ በዚያ የሚኖሩ ኢየሱሳውያንን አነጋገራቸው፡፡ ለዚህ ሥራ የተመረጠው ፍራንኮይስ ዛቪየር ዲ በርቬደንት (François Xavier de Brèvedent) የተባለ ሰው ነበር። ይህ ሰው የዶ/ር ፖንሴት አገልጋይ ሆኖ ‹‹የሱፍ›› በሚል የምስጢር ስም ማንነቱን ደብቆ እንዲሄደ ተወሰነ። ይህ ሰው የተመረጠው፤ አረብኛ ስለሚያውቅ እና የተወሰነ የህክምና ዕውቀት ስለነበረው ነው፡፡ ስለዚህ አስተርጓሚ ሆኖ እንዲሰራ፤እንዲሁም የከፋ ነገር ተፈጥሮ ፖንሴት ከሞተ፤ እርሱን በመተካት ንጉሱን እንዲያክም ታስቦ ተላከ፡፡ ሆኖም የእርሱ ዋነኛ ተልዕኮ በኢትዮጵያ የካቶሊክ አስተምህሮን ለማስፋፋት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መኖሩን መሰለል ነበር፡፡
ዶ/ር ፖንሴት ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ ከመጀመሩ በፊት፤ ከቆንስሉ ቤኖይት ዲ ሜይሌት የተሰጠው መመሪያ ነበር፡፡ በመጀመሪያ ንጉሱን ማከም፤ የንጉሱን ፍቅር እና ታማኝነት ካገኘ በኋላ፤ በሁለቱ ነገስታት መካከል ግንኙነት እንዲመሰረት ጥያቄ ማቅረብ ነበር። ለኢትዮጵያዊው ንጉስ የሚበረከት የስጦታ ዕቃዎችም ተሰጠው፡፡ እንዲሁም፤ የሰውየውን ክብር ከፍ ለማድረግ በማሰብ፤ ፖንሴት በካይሮ የኦቶማን ፓሻ ሐኪም መሆኑን የሚገልፅ በአረብኛ የተፃፈ ማስረጃ ደብዳቤ እንዲይዝ ተደረገ፡፡ የተሰጠው ደብዳቤ፤ ፖንሴት በአንድ ወይም በሁለት ዓመት ጊዜ እንዲመለስ፤ የፈረንሳዩ ንጉሥ የኢትዮጵያውን ንጉስ ወዳጅነት እንደሚፈልግ እና የፈረንሳይ መንግስት አምባሳደር ለመላክ ፍላጎት እንዳለው የሚገልፅ ደብዳቤ ነበር፡፡ እንዲህ አድርገው ጓዛቸውን ከቀረቀቡ በኋላ፤ ጁን 10 ቀን 1698 ዓ.ም (እኤአ) ዶ/ር ቻርልስ ፖንሴት እና ፍራንኮይስ ዛቪየር ዲ በርቬደንት (François Xavier de Brèvedent) ወደ ጎንደር ለመሄድ ከካይሮ ተነሱ፡፡ ቀላሉ የነበረው መንገድ፤ የቀይ ባህርን ቀዝፈው በምፅዋ ወደብ በኩል ወደ ኢትዮጵያ መሄድ ቢሆንም፤ ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው በኢትዮጵያ እና በኦቶማን ቱርክ መካከል ከብዙ ጊዜ ጀምሮ የፀና ካቶሊክ አውሮፓውያንን ያለማሳለፍ ስምምነት ስለተደረገ፤ በዚያ በኩል ለመሄድ እንደማይቻል ተረድተው፤ ጉዟቸው በሱዳን በኩል እንዲሆን ወሰኑ፡፡ በዚህ አስቸጋሪ መንገድ ተጉዘው ከካይሮ በተነሱ ልክ በዓመታቸው እነዶክተር ፖንሴት፤ጁን 11 ቀን 1699 ዓ.ም (እኤአ) ከኢትዮጵያ ድንበር ደረሱ፡፡ ከበርሃው ወጥተው ከደጋው አካባቢ ሲደርሱ፤ መልክአ ምድሩ እና የህዝቡ አካላዊ ቁመና ልዩ እንደሆነበት ፖንሴት ይገልፃል፡፡
ፖንሴት በኢትዮጵያ ግዛት በተመለከተው ሁኔታ ተደንቋል፡፡ አበባው፣ ቅመማቅመሙ፣ ዛፉ እና ሣር ቅጠሉ ሁሉ ገነትን የሚያስታውስ ሆኖ ታይቶታል፡፡ በኑቢያ እና በሰናር ከተመለከተው ጥቁር የፊት ገፅ ለየት ያለ፤ ጠይም ዓሳ መሳይ የሚባል ገፅታ ያላቸው ልዩ ህዝቦች መካከል መግባቱንም ይናገራል፡፡ የሚያማምር ዓይን፣ ስስ ከንፈር፣ ሰልካካ አፍንጫ እና ወተት የመሰለ ጥርስ የታደሉ ከሚላቸው ህዝቦች መሀል ገባ፡፡ በምድሩ ማማር፣ በሰዉ ቁመናና እንግዳ ተቀባይነት የተደነቀው ፖንሴት፤ ‹‹ጥሩ ሰዎች የሚኖሩበት እና ለም አፈር የታደለ ምድር እንደ ኢትዮጵያ ያለ ሐገር፤ ምን እግር ቢቀጥን ማግኘት አይቻልም›› (there is no country whatever better peopled or more fertile than Æthiopia) ሲል ፅፏል፡፡
በድንበር ላይ በምትገኝ ‹‹ጊራና›› ከተባለች ከተማ ግመላቸውን በፈረስ ቀይረው ወደ ኢትዮጵያ ጉዟቸውን ቀጠሉ፡፡ ሆኖም ጁላይ 9 ቀን 1699 ዓ.ም ማንነቱን ደብቆ የዶክተሩ አገልጋይ መስሎ ጉዞ የጀመረው ፍራንኮይስ ዛቪየር ዲ በርቬደንት፤ በድካም ጫና እና በተቅማጥ በሽታ ተዳክሞ ሞተ፡፡ ዶ/ር ፖንሴትም ለጊዜው በጠና ታምሞ ጉዞውን መቀጠል አልቻለም፡፡ በአካባቢው የሚገኙ የኦርቶዶክስ ካህናት በልዩ ፍቅር እና አክብሮት ፀሎተ ፍትሃት አድርገው፤ አስከሬኑን በቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን አግብተው ቀበሩት፡፡ ‹‹ሰውየው የካቶሊክ ቄስ መሆኑን ያላወቁት ኢትዮጵያውያን በክርስትያን ወግ አክብረው ቀበሩት›› ይላል ፖንሴት፡፡ ለሦስት ቀናት ታምሞ ከቆየ በኋላ የቀዳማዊ ኢያሱን ጥበቃም ለማግኘት የቻለው ፖንሴት በግማሽ ቀን ጉዞ ጎንደር ከተማ ገባ፡፡
በ1636 ዓ.ም (እኤአ) የኢትዮጵያ መዲና ሆና የተቆረቆረችው ጎንደር ሦስት ዋና ዋና የንግድ መስመሮችን በማማከል በተራሮች ታቅፋ የምትገኝ ከተማ መሆኗን የሚገልፀው ፖንሴት፤ ከተማይቱ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እና የንግድ ሚና ያላት መሆኗን ያስረዳል፡፡ ልክ እንደ አውሮፓ የንጉሡ ምስል የታተመባቸው ንፁህ የወርቅ ሳንቲሞች እና አሞሌ ጨው በመገበያያነት እንደሚያገለግሉ ያስረዳል፡፡
ፖንሴት፤ ‹‹በጎንደር ከተማ መቶ የሚደርሱ አብያተ ክርስቲያናት ነበሩ፡፡ የንጉሱ እና የሊቀጳጳሱ መቀመጫ ከተማ ነች፡፡ ከፓትርያርኩ መኖሪያ አጠገብ‹ተንስአ ክርስቶስ› የተሰኘ ቤተ ክርስቲያን ይገኛል፡፡ የአቡኑ መኖሪያ በጣም የተንጣለለ ትልቅ ቤት ነው፡፡ በከተማዋ እጅግ ጎልቶ የሚታይ አዲስ ቤተ መንግስት አለ፡፡ ከ1685 ዓ.ም ጀምሮ ሲሰራ የቆየ የንጉሡ መኖሪያ ነው፡፡ ቤተመንግስቱ በጣም ውብ አፓርትመንቶች ያሉት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዜና መዋዕሎች፤ ‹ከሰለሞን መኖሪያ ይበልጥ ውብ የሆነ መኖሪያ እያሉ የሚያሞግሱት ነው› ሲል ፅፏል፡፡
ዜና መዋዕል ፀሐፊዎቹ ብቻ ሳይሆኑ ራሱ ፖንሴት በቤተመንግስቱ ውበት እና በተጌጠበት ሁኔታ እጅግ ተመስጧል፡፡
ከጎንደር መሀል ቁጭ ያለው ቤተመንግስት፤ የአካባቢውን ገጠራማ ግዛት ቁልቁል ለማየት ከሚያስችል ሥፍራ የቆመ ነው፡፡ በቤተመንግስቱ ቅጥር ግቢ በርካታ ቤቶች እንደሚገኙ እና የግቢው አጥር፤ በድንጋይ ግንብ የተሰራ መሆኑን፤ ሁለት ክንፎችን ሰርተው የቆሙና ከበላያቸው የመስቀል ምስል ያላቸው ሁለት ማማዎች እንዳሉም ፖንሴት አትቷል፡፡ ‹‹በግቢው አራት ቤተክርስትያናት ነበሩ፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቀሳውስት አሉ፡፡ የነገስታቱ ልጆች የሚማሩበት ትልቅ ኮሌጅም በዚያ አለ›› ይላል ፖንሴት፡፡ ሌላውን ሣምንት አጫውታችኋለሁ፡፡ ደህና ቆዩኝ፡፡

Read 2320 times