Saturday, 16 May 2015 10:50

የስደት ስለት!

Written by  መሐመድ ነስሩ
Rate this item
(4 votes)

የእናት መጥፎና የስደት ጥሩ የለውም፡፡ ጥሩ ቢኖርም በጥቂቱ ነው፡፡ እሱም ከብዙ መከራና ስቃይ በኋላ የሚደረስበት ነው፡፡ ይህን ተራራ ውጣው፤ ይሄን ወንዝ ተሻገረው፤ ይሄን ዳገት ቧጠው፣ ይሄን ቁልቁለት ሩጠው፤ ይሄን ሜዳ ጋልበውን ወዘተ የተባልከውን ካደረግክ በኋላ የምትደርስበት ነጥብ ነው፡፡  
በተረፈ እንደ ጠል በረሃ ላይ ረግፈው፤ እንደ ጠጠር አሸዋ ላይ ወድቀው፤ እንደ ዝንጀሮ ከጫካ ጫካ ተንከራተው የሚጨብጡት ወይም ሊጨብጡ የሚመኙት ህልም መሳይ ነገር ነው፤ ስደት!
እውነት ነው፤ የስደት ጥሩ የለውም፡፡ ቁሳዊ ፍላጐትን ማሟላትና ከገቢ አንፃር ስኬትን ማስመዝገብ ቢቻልም፤ ይህ የተጣራ ደስታ የሚሰጥ ክስተት ሊሆን አይችልም፡፡ ሆድ ሲሞላ አዕምሮ ይራባል፡፡ ስጋ ሲደልብ መንፈስ ይታረዛል። አንዱን ሲይዙት አንዱ ያመልጣል፡፡ ዓለም እንዲህ ናት፡፡
የስደት ስለት ወደፊትም ሆነ ወደ ኋላ ሲመለስ እንደ መጋዝ ሁሉን ይቆርጣል፡፡ የተቆረጠ መድማቱ አይቀርም፡፡ የየትኛውም ሰው ደም ሲፈስ ይቆረቁራል፡፡ ደሙ ኢትዮጵያዊ ሲሆን ደግሞ ልብን ያሸብራል፡፡ ቅስም ይሰብራል፡፡ ቀልብ ይሰልባል፡፡ ሰላም ይነሳል፡፡ እንቅልፍ ያሳጣል፡፡ ምኞት ይከላል፡፡ ህልም ይቀላል፡፡
ብንችልና ስደት እስከ ዓለም ጥግ ብናሳድደው፤ ከነነፍሱ ገንዘን ብንቀብረው፤ ቀብረን አፈር ብናለብሰው፤ አፈር አልብሰን ድንጋይ ብንጭነው፤ እልል… ልልልል ማለት ዕጣችን በሆነ ነበር፡፡
ነገር ግን አልሆነም፡፡ ምኞታችንና እውነታው እስከመቼም ሊታረቁ የሚችሉ አይመስልም፡፡
ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ ሊገጥሙት ከሚችሉት ነገሮች አንዱ ስደት ነው፡፡ በተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ በሆነ ምክንያት መሰደድ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ሰዎች ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ፤ የብሱን እየተፈናጠሩ፤ ባህሩን እየተሻገሩ፤ ከሀገር ሀገር እየቀየሩ፤ በመስራት ኑሯቸውን ሊደጉሙና ህይወታቸውን ሊያቀኑ መለስ ቀለስ ሊሉ ይችላሉ። ይህ ህያው በመሆን ምክንያትና የተሻለ ነገር ለማግኘት ባለመ የዕለት በዕለት እንቅስቃሴ መነሻነት ሊያጋጥም የሚችል ነው፡፡
የስደት ስለት ለማንም አይራራም፡፡ ፊት የሰጠውን ሰው ሁሉ አንገት ይቀነጥሳል፡፡ ህያውን ወደሙትነት ይቀይራል፡፡ ብርቱውን ስጋውን ያጣምናል፡፡ ነፍሱን ያልማል፡፡ ደመነፍሱን ይንጣል፡፡ መንፈሱን ይድጣል፡፡
የስደት ስለት ዶልዱሞ አያውቅም፡፡ ሁሌም ስል ነው፡፡ ሞረዱ እጦት፤ ጉልበቱ ድህነት ነው። ትንሽ ኑሮው የደከመ ሰው ሁሉ ነፃ ነኝ ማለት የሚችል አይመስልም፡፡ ስደት ያሳድደዋል፡፡
በምኞት መላ ሰውነቱ ሰክሮ፣ በተስፋ ነፍሱ ይለመልምና ለመሰደድ ቆርጦ ይነሳል፡፡ ከስደት ጨርሰው የተመለሱትንም ሆነ ለዕረፍት የሚመጡትን በማየት መንፈሱ እረፍት ያጣል። በምኞት ይናጣል፡፡ እንደነሱ መናገር፤ እንደነሱ መልበስ፤ እንደነሱ ትልልቅ ሆቴሎች ገብቶ መመገብ፤ እንደነሱ በርከት ያለ ጉርሻ (ቲፕ) መስጠት ይፈልጋል፡፡ መታወቂያና ፓስፖርት ሳይዝ በተመቸው መንገድ ሀገሩን ለቆ ይርቃል። ህልሙን አቅፎ ይሮጣል፡፡ ከባይተዋርነት ኩሬ የሚበቃውን ይጠልቃል፡፡ ከመፃተኛነት ደሴት ሰብዕናውን ይነጥቃል፡፡ ከእንግልት እቅፍ ማንነቱን ይመዛል፡፡
ነቢዩ እያሱ “ስደት በጋዜጠኛው ዓይን” በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሐፍ ላይ የሚከተለውን ይላል፤
“በሱዳን በረሃዎች ከእባብና ከጊንጥ እየታገሉ፣ በኬንያ የስደተኞች ካምፖች በችግር እየተበሳጩና የባዕድ ፊት እየገረፋቸው፣ የአፍሪካን አህጉር በተገኘው መጓጓዣ ሲያቋርጡ በጉቦና በእስራት የተዋከቡ፣ ወዲያውን ሲሻገሩ በጀልባቸው መስጠም የአዞ እራት የሆኑ ዛሬም ስደትን የተሻለ አማራጭ አድርገው የቀጠሉ አያሌ ናቸው። ኢትዮጵያ ከአጐራባች አገሮች ሁሉ የተሻለ የተፈጥሮ ሃብትም፣ አገሩን የሚወድ ህዝብ ያላት ሆና ዜጐቿ ለስደት የመዳረጋቸው እንቆቅልሽ መሪዎች የፈጠሩት ፍትህ አልባ ማሽቆልቆል ነው።”
ያሳዝናል፡፡ በጣም ያሳዝናል፡፡ እጅግ በጣም ያሳዝናል፡፡
የአንቀፁን የመጨረሻ ዓ.ነገር መተንተን በሁለት አቅጣጫ የሚከወን ነው፡፡ አንደኛው በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት የሚሰደዱትን ሲያመለክት፣ ሁለተኛው መልካምና ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ሁኔታ ባለመቻቸቱ ምክንያት የሚሰደዱትን ይጠቁማል፡፡ ሁለቱም በመንግሥት ደካማ አስተዳደር ምክንያት የሚከሰቱ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡
ስደት ወይም ከትውልድ ሀገር መውጣት ከመንጋው እንደተለየ ጅብ ወይም አንበሳ የሚያቅበዘብዝ ሲሆን፤ እንደ አሳ ከለመደው ባህር ወጥቶ ምድረ በዳ ላይ የመጣልን ያህል ከባድ ነው።
የዶ/ር ፍቃደ አዘዘን “ውጭ አገር” የተሰኘ ግጥም እንመልከት፤
“ብቸኝነት ማለት
አንድ ክፍል አንድ ቤት፤
አራት ግርግዳ
እውስጧ ጠባብ አልጋ፤
አይምሰልህ ልጄ!
ነውና ብቸኛ የረገፈ ቅጠል፣
ከባህሉ ውጪ ከድንበሩ ኮለል፡፡
በዚህ ግጥም ስደተኛው “በረገፈ ቅጠል” ተመስሏል፡፡ እውነት ነው፤ መሰደድ ከለመዱትና የራስ ከሆነ ማንነት ርቆ በሰው ሀገር ከበቀለ ዛፍ ላይ የሚወድቅ ቅጠል መሆን ነው፡፡
በሊቢያ በረሀ በአይኤስ የታረዱት ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች አብዛኞቹ ሳይነግሯቸውና ሳይሰናበቷቸው መሄዳቸውን ገልጸዋል፡፡
ይህም ቅር የሚል ሀሳብ መንጭቶ ከስደት ሀሳባቸው እንዳያሰናክላቸው ከማሰብ ነው፡፡ ያሰቡትን ለወላጆቻቸው ቢነግሩና ቤተሰቦቻቸውን ቢያማክሩ ሊገጥማቸው የሚችለውን ተቃውሞ በመስጋት ሳይሰበናቱ ለመሄድ ወስነዋል፡፡
ይሄ በአንድ ስነቃላችን ውስጥ ተጠቅልሎ ይገኛል፡፡ እነሆ፤
“አንበሳ ጋሜውን ቢያኩት ይደማል ወይ
የከፋው ሰው ሲሄድ ይሰናበታል ወይ”
ሌላኛው የስደት አስቀያሚ ገፅታ ይህ ነው። መመለስ እንደ መውጣት ቀላል አይደለም፡፡ መሄዱ አልጋ ባልጋ ባይሆንም መመለሱ ግን ፅንን ያለ ቀጋ ነው፡፡
“ምን ይዤ ልመለስ ወደ እናቴ ቤት” የሚለው ገለጻ እምቅ ስሜታቸውን የሚገልፅ፣ ስውር ሀሳባቸውን የሚያሳይ ነው፡፡
የኑረዲን ዒሳ “እመጣልሻለሁ” የተሰኘ ግጥም እንዲህ ይላል፡-
“ወርቅ ስትይኝ ወርቅ
ጨርቅ ስትይኝ ጨርቅ
አምባር ስትይ አምባር
አልቦም ስትይ አልቦ
ምን ያላኩት አለ
ምንድን ቅራቅንቦ
ላክ ያልሽኝን ሁሉ ስልክ ባጅቻለሁ
አሁንም ና ስትይ ቦርቄልሻለሁ
ደሞ አንቺ ብለሽኝ እንዴት እቀራለሁ
አንድ ቀን አንድ ቀን
ካልሽኝ ነገር ተርፎ
መሳፈሪያ ሳገኝ እኔም እመጣለሁ፡፡”
ግጥሙ የስደተኞችን እውነተኛ ስሜትና ብሶ ብቻ ሳይሆን ከአገር ከወጡ በኋላ ለመመለስ ምን ያህል እንደሚቸገሩ ይገልጻል፡፡ ስደተኛው ሀገር ውስጥ ያሉ ቤተሰቦቹንና ዘመዶቹን ቀዳዳ  ሊደፍን ሲፍጨረጨር እንዴት ለ‘ራሱ መሆን አቅቶት እንደሚቀር የሚያሳይ ነው፡፡ ገጣሚው ይህንኑ እውነት በሚያጎላ መልኩ “መሳፈሪያ ሳገኝ እኔም እመጣለሁ” በማለት ይደመድማል፡፡ ከቀዳዳው ብዛት የመሳፈሪያ እንኳን ለማግኘት ምን ያህል እንደሚቸገሩ የሚያሳይ ነው፡፡
የአብዛኛው ተሰዳጅ የስደት ምክንያት ኑሮን ማሸነፍ ነው፡፡ “የዕለት ጉርስ፣ የዓመት ልብስ” መቻልና እንጀራ ፍለጋ! …
ሀገር በቀል ስነ-ቃል እንዲህ ይላል፤
“እሄዳለሁ ብዬ ነገር አላበዛም
እንጀራ ነው እንጂ ሰው ሰውን አይገዛም፡፡
እንጀራ ሆነና የሰው ቁም ነገሩ
አልከበር አለ ሰው ሁሉ ባገሩ!”
ዓለም ፀሐይ ወዳጆ መታሰቢያነቱን ለስደተኞች ባደረገችው “የማታ እንጀራ” የግጥም መድበልዋ “ባርቀህ ትጮኸለህ” በሚል ርዕስ ስር፤ የስደትን ክትያዎችና በስደት ሲኖር የሚሰማውን ባይተዋርነት አስነብባናለች፡፡ ከዚሁ ግጥም ቀንጨብ አድርገን ተወሰኑ ስንኞችን በማንበብ እንሰናበት፡-
“ከእናትህ ማህፀን በጭንቀት ስትወጣ
አታውቀው ዓለም ውስጥ ሳትፈልግ ስትመጣ
እንደ ጮህከው ጩኸት ያኔ ስትወለድ
ዳግም ታለቅሳለህ ከሀገር ስትሰደድ
እንኳን የማያውቅህ የሚያውቅ ይረሳሃል
ለብሰህ ይበርድሃል ጠግበህ ይርብሃል
ብቸኝነት ማርኮ ኦና ያደርግሃል…”


Read 3331 times