Saturday, 02 May 2015 12:43

ልቦለድ በመጨረሻ እስትንፋስ ላይ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 ይሄን ጉዳይ ይዘን ወደኛ አገር ስንመጣ፣ ምን እንገነዘባለን? እውነት ልቦለድ እያጣጣረ ነው? ወግ እያንሰራራ ነው? ግለ ታሪክስ? ልቦለድ ለሞት ይሁን ለእንቅልፍ፤ ባለየለት ሁኔታ እያንጐላጀ ነው፡፡ ንቃት አይሰማውም፡፡ አዳም ረታ በ “መረቅ” የቀሰቀሰው መስሎን ነበር፡፡ መልሶ ተኛ፡፡ ይስማዕከ ወርቁ በ  ልቦለዱ የዘርፉን ሞተር ሳይቀሰቅስ ማለፉ ሌላው የሥጋት ምንጭ ነወ፡፡ ከዚያስ? ምንም

      ተፈጥሮ ጋጠ - ወጥ አይደለችም፡፡ የምታከብረውና የምታስከብረው ህግ አላት፡፡ እርስበእርስ የሚናበብ ድንጋጌ፤ የማይዛነፍ፣ የማይንከረፈፍ ስድር ሥርዓት አላት፡፡ እንደ ሰዎች ህግ ተደብቀው የማይጥሱት፣ እሳት በላሰ ጠበቃ የማይሞግቱት፣ በጉቦ የማይቀለብሱት…ይሄንን የተፈጥሮ ህግ ፓይታረጐስ (Pythagoras) “ኮስሞስ” (Cosmos) ይለዋል፡፡ ሔራክሊተስ ደግሞ “ሎጐስ” (Logos) በሚል ይጠራዋል፡፡ ከእነሱ ሁሉ በኋላ የመጣው ሂዩም (Hume) ደግሞ “የተፈጥሮ ህግ” (Laws of nature) ሲል በጥሬው ያመለክተዋል፡፡
የተፈጥሮ ህግ ዘንድ ሥርዓተ አልበኝነት አይታሰብም፡፡ ሥርዓተ - አልበኝነት የተፈጥሮ እንቅፋት ብቻ ሳይሆን ፀርም ጭምር ነው፡፡ ከዛፍ የወደቀውን አንዱን ሰብራ ሌላውን አትምርም፤ ያልበላውን ከመራብ፣ ያልጠጣውን ከመጥማት አትዛነፍም፡፡ ብርሃን የሌለበት አናይም፣ ድምጽ ያልነዘረበት አንሰማም፣ ያልጐረሰውን አንቀምስም…
…የሰው ልጅ እንጂ ተፈጥሮ ከሰው ልጅ ጋር ለመግባባት መንገድ አትቀይስም፡፡ የልብ ምታችንን ሰከንድ ቆጣሪ አይተካውም፡፡ ረሃባችን ሰዓት ቆጣሪ እየተከተለ አይደውልም፣ ልደታችን በካላንደር ድንጋጌ እርምጃውን አይተካም፡፡ በህይወት የመቆያ ጊዜአችን የተባበሩት መንግሥታትን ያገናዘበ አይደለም፡፡ እኛ እንጂ ተፈጥሮ ከኋላ አይደለችም፡፡
ውኃ አንዳንዴ በመቶ ሌላ ጊዜ በአምስት መቶ ዲግሪ አይፈላም፡፡ መዘላበድ የሰው እንጂ የተፈጥሮ አይደለም፣ አድርባይነት የእኛ እንጂ የእሷ አይደለም … እንኳን እኛ ፈጣሪዋም በተፈጥሮ ህግ ሥር ነው፡፡  
መስሏት እንጂ መስላው አትኖርም፡፡ የሰው ልጅ ኮምፒዩተርን ስለፈጠረ ከኮምፒዩተር ህግና ከተጫነው ፕሮግራም ውጭ ማዘዝ ይችላል? እንዲያ ነው!!
ግን ደግሞ …
በተአምርና በተረት መሰል ዘመን ውስጥ እንገኛለን፡፡ ዴቪድ ሺልድ የተሰኘ ፀሐፊ “Fictions times” ይለዋል፡፡ ልቦለዳዊ፣ ምናባዊ፣ የፈጠራ መሰል ዘመን ለማለት ነው፡፡ እስኪ አካባቢያችንን እንመልከት፡፡ ከምንም ጋር ባልተገናኘ ኩርማን ብረት ዓለም ጫፍ ያለ ሰው እናነጋግራለን፤ ቦታው ላይ ሳንገኝ ክንውኖችን በቀጥታ እናያለን፤ ብረት ቀጣጥለን እናዛለን፣ እንበራለን፣ በምድር እንሽከረከራለን፤ በርቀት መቆጣጠሪያ ሁሉን እናከናውናለን…እኛ ለጥንቱ ዘመን ሰው ምንድነው?
“Human Cloning” ላይ እስክንደርስ ሔዋን ከአዳም ግራ ጐን መገኘቷ ምክንያት አልባ፣ የእግዚአብሔር ብቻ ተአምር ነበር፡፡ የመብረር ጥበብ እስኪከሰት የኤሊያስ የእሣት ሰረገላም የተፈጥሮ መታዘዛዊ ተአምር ነበር፡፡ ኒውክሊየር እስኪፈጠር የሶዶምና ጐሞራህ በእሳት ባህር መጥለቅለቅ ሩቅ ነበር፡፡ ባዮሎጂካል ጦር መሣሪያ እስክናይ የግብፆች መቆሳሰል ታላቅ ተአምር ነበር፡፡
ዛሬ እነዚህ ሁሉ ተአምሮች የሚከናወኑበት ተረትና ልቦለድ መሰል ዘመን ላይ ነን፡፡ “ስለዚህ ሌላ ተረትና ልቦለድ አያስፈልገንም” ይላል ዴቪድ ሺልድ “Reality Hunger፡ A manifesto” በተሰኘ ሥነ - ፅሁፋዊ ጥናቱ፡፡ “ፈጠራ ያልሆኑ እውነተኛ የጥበብ ሥራዎችን እንወዳለን፤ ምክንያቱም ምናባዊ ልቦለድ በመሰለ ጊዜ ውስጥ ስለምንኖር” (We like nonfiction because we live in fictitious times)
በዚህ ዘመንና ቴክኖሎጂ አመጣሽ ህይወት ሳቢያ አደጋ የተጋረጠበት የሥነ ጽሑፍ ዘርፍ ረጅም ልቦለድ እንደሆነ ጥናቱ ላይ በአጽኖት ተጠቅሷል፡፡ “Good bye to the Novel, 2015 will be the year of the Essay” በሚል ርዕስ ኒውስዊክ መፅሔት ላይ ባለፈው ጥር ወር ሺልድ ባቀረበው መጣጥፍ የያዝነው አመት በእውነታ ላይ የተመሠረቱት ወግ (essay)፣ ግለታሪክ በከፍተኛ ደረጃ ተፈላጊ ሆነው መገኘታቸው የልቦለድ ግብአተ መሬት መፈፀሙ አይቀሬ መሆኑን ይጠቁማል ይላል፡፡
ይሄን ጉዳይ ይዘን ወደኛ አገር ስንመጣ፣ ምን እንገነዘባለን? እውነት ልቦለድ እያጣጣረ ነው? ወግ እያንሰራራ ነው? ግለ ታሪክስ? ልቦለድ ለሞት ይሁን ለእንቅልፍ፤ ባለየለት ሁኔታ እያንጐላጀ ነው፡፡ ንቃት አይሰማውም፡፡ አዳም ረታ በ “መረቅ” የቀሰቀሰው መስሎን ነበር፡፡ መልሶ ተኛ፡፡ ይስማዕከ ወርቁ በ     ልቦለዱ የዘርፉን ሞተር ሳይቀሰቅስ ማለፉ ሌላው የሥጋት ምንጭ ነወ፡፡ ከዚያስ? ምንም
በሌላ በኩል በሺልድ እንደተጠቆመው፤ በእኛም አገር ያለፉት ጥቂት አመታት የወግ እና ግለታሪክ መጽሐፍት “ይዞላቸው” ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከፍተኛውን የገበያ እርከን ከተቆናጠጡት መፃሕፍት መካከል አብዛኞቹ (በሙሉ ላለማለት) መጣጥፍ ወይም ግለታሪክ ናቸው፡፡ “ፒያሳ ሙሐሙድ ጋ ጠብቂኝ”፣ “ሮዛ”፣ “የአዲስ አበባ ጉዶች”፣ “ታወር ኢን ዘ ስካይ” ፣ “ፈተና”፣ “የሐበሻ ጀብዱ”፣ “አሥራ ሰባት መድፌ” ወዘተ
ገበያው በሩን ገልጥጦ ባይቀበላቸውም መልካም ፊት ያልነፈጋቸውም መጽሐፍት ቢሆኑ እዚያው መጣጥፍና ግለታሪክ ላይ የሚያጠነጥኑ ናቸው፡፡ “የይሁዳ ድልድይ”፣ “እኛ የመጨረሻዎቹ”፣ “የሰማይ ላይ ማማ”፣ (የገብሩ አስራት)
ህይወት ወደ ምናብነት ስትኮበልል፣ የንባብ ፍላጎት ወደ እውነታ አፈግፍጓል፡፡ መጣጥፍና ግለ-ታሪክ መፈለጋቸው ለዚህ ነው፡፡ ህይወት እውነታ በነበረበትና የተፈጥሮ ህግ በበላይነት በረበበት ዘመን የሰው ልጅ የንባብ ፍላጎቱ ወደ ምናባዊ ልቦለድ ያደላ እንደነበር እሙን ነው፡፡ እርግጥ ነው፤ ዛሬም ቢሆን የተፈጥሮ ህግ ውሉን አላላላም፡፡ ይሁንና የተፈጥሮ ህግ በግትርነት የሚጠብቀውን መግቢያ በር የሰው ልጅ በአሳባሪ አልፎ ከበስተጀርባው ያሻውን እየሆነና እየሰራ ነው፡፡
ተፈጥሮ ጋጠ-ወጥ ባትሆንም፣ የምታከብረውና የምታስከብረው ህግ ቢኖራትም፣ እርስ በእርስ የሚናበብ ድንጋጌ ላይ ብትቆምም የማይዛነፍ፣ የማይንከረፈፍ ስድር ስርዓት ብታቆምም ሳይንስን ተገን አድርጎ ሽምቅ በወጋት የሰው ልጅ ሳታውቀው እጇን ሰጥታለች፡፡ በእውነታ የቀነበበችው የሰው ልጅ አፈትልኮ ተረትና ምናባዊ ዓለም ውስጥ ገብቷል፡፡ በመሆኑም የዚህን ተቃራኒ በእውነታ ላይ የተመሰረተ የጥበብ ስራ ሽቷል፡፡ እዚህ መሃል ሙሉ ለሙሉ ምናብ ላይ የተመሰረተው ልቦለድ ዕጣ - ፈንታው ምንድንነው?
“ሞት!” ይላል ዴቪድ ሺልድ በጥናቱ፡፡
“የመዳን፣ የማንሰራራት ዕድል የለውም?”
“አለው”
“እንዴት?”
“ልቦለድ በጭብጥ ሳይሆን በቅርፅ(Form) ብቻ ከብዙዎቹ ይለያል፡፡ ይሄንን የቅርፅ ጉዳይ በህይወት ለመቆየት ሲል መተው ይኖርበታል፡፡ ከተንዛዛ ገለፃ ቀጥታ ጉዳዩን በአጭር መንገድ ወደ መንገር መሸጋገር ያስፈልገዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዘመኑ ግድ ያለውን የወግ፣ የግለ ታሪክ ባህርያት በመውረስ ወደ እውነታ ድብልቅ ምናብ መምጣት አለበት፡፡” ይላል በአጠቃላይ፡፡
ሺልድ ይሄን ያለው ከአራት አመታት በፊት ባቀረበው ጥናት ላይ ነበር፡፡ ይሁንና ልቦለድ ከምናብነት ወጥቶ ከውነታ ጋር በመደባለቅ የወግ (essay)፣ የግለ ታሪክ (Autography) እና ትውስታ (Memoir) ባህርይ መያዝ ከጀመረ አስርት ዓመታት እያስቆጠረ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የቼኩን ደራሲ የሚላን ኩንዴራ (Milan Kundera) ሥራዎች ማየት ይበቃል፡፡ “The Book of Laughter and Forgetting” የተሰኘው ልቦለዱን ፅፎ ያቀረበው በ1978 ዓ.ም ነበር፡፡ ይሄ ልቦለድ የወግ፣ የግለታሪክ፣ የትውስታ፣ የምናብ ድብልቅ ነው፡፡ “The Unbearable lightness of being” የተሰኘ ስራውም ተመሳሳይ ባህርይ ከመያዙም በላይ ፍልስፍናን አካትቶ በዚው ዘመን አካባቢ ወጥቷል፡፡ ሌሎችም ተመሳሳይ ስራዎችም አሉት፡፡
ኩንዴራ “The book of Laughter and Forgetting” ውስጥ ነባሩ የልቦለድ ጠባይ የማይፈቅደው ብዙ ወግ መሰል ፅሁፎች ተካትተው ይገኛሉ፡፡ በፖለቲካ ረገድ እራሱ ደራሲው የነበረውን የለውጥ ውጥንቅጥ እንዳለ ተርኮታል፡፡ በተለይ ሩሲያ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ አገሩን (ቼክን) ስትቆጣጠር እርሱ ላይ ደርሶ የነበረውን መከራ እንደወረደ ይተርከዋል፡፡
ወደኛ አገር ልቦለድ እንምጣ
ልቦለዱን ከነባር ታሪክና ከተከናወነ ድርጊት ጋር ደባልቆ የማቅረብ ሥራ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀመረ ነው፡፡ ቀደም ሲል እነ ብርሃኑ ዘሪሁን (የታንጉት ምስጢር) የተሳተፉበትና አሁንም በሀብታሙ አለባቸው (“አውሮራ” እና “የቄሳር እንባ”) የተቀጠለበት ልቦለዳዊ ዘውግ፤ “ታሪካዊ” የሚሰኝ ነውና እዚህ የሚካተት አይደለም፡፡ ልክ በኩንዴራ ስልት የአማርኛ ልቦለድን የተቀላቀሉ ወጣት ደራሲያን ግን አልጠፉም፡፡ የመጀመሪያው በዕውቀቱ ስዩም “እንቅልፍና እድሜ”ን ይዞ በመምጣት ገድ ብሎናል፡፡ ቀጥሎም “በመግባትና መውጣት” መቀጠል እንደሚችል አሳይቶናል፡፡
ከበዕውቀቱ በመቀጠል ጥቂት የማይባሉ ወጣት ደራሲያን ከምናብ የተፋታ እውነት ቀመስ ልቦለድና አጫጭር ልቦለድ አቅርበውልናል፡፡ አሌክስ አብርሃም፤ “ዶ/ር አሸብር”፣ ሌሊሳ ግርማ “የንፋስ ህልሞች”፣ የአሸናፊ ውዱ “ሚስት መሆን” … እና ሌሎቹንም ከዚህ የኩንዴራ ዘውግ አንፃር እየተመለከትን ሳምንት እንተነትናለን፡፡ እስከዚያው ቸር ይግጠመን፡፡   

Read 1722 times