Saturday, 02 May 2015 11:41

ዓይናፋሯ የሎግያ ከተማ!

Written by  ሐናንያ መሐመድ (ሉሲ በሪ)yeneafrica@gmail.com
Rate this item
(5 votes)

የሌላ አገርን ዝናብ ዳመና፣ ጉምና ጭጋግ ያጅበዋል፡፡ የሎግያ ሰመራን ዝናብ ደግሞ  እንደቤተ-ዘመድ አቧራ ያጅበዋል፡፡ ዝናብም በሰማይ ያገኘውን አቧራ እየጠረገ  ከሰማይ ወደ መሬት ሲወረወር፣ የዝናብ ትርዒት ወይም ውድድር የምታይ ይመስልሃል፡፡ አንተ የምታውቀው ከዝናብ ጋር የሚወርድ በረዶ ከሆነ በዚህ ግን  ፌስታል፣  ፕላስቲክ፣ ካርቶን፣ የጫት ገረባ፣….የመሳሰሉትን ናቸው፡፡

  ‹‹የበርሀ ውሃ የቀመሰ ሌላ አገር ሄዶ አይለምድም››  ሲባል ሰምተህ ይሆናል፡፡ ተረት ተረት እንዳይመስልህ፡፡ ሞክረህ ማረጋገጥ ትችላለህ፡፡ ማንኛውም ተራ ተርታ ሰውና ከፍተኛ ባለስልጣናት ያለ ልዩነት እኩል የሚኖሩባት ሥፍራ ያለው በእዚህ በዓይናፋሯ ከተማ ሎግያ ውስጥ  ነው፡፡
በበርሀ የሚኖሩ ማህበረሰቦች ለሚበላና ለሚጠጣ ነገር አይጨካከኑም፡፡ ተደብቆ መብላትን፣ እያለው የለኝም ማለትን ነዋሪዎቹ አያውቁበትም። መተጋገዝ፣ መተሳሰብ ሰብአዊነት ብቻ ሳይሆን የውዴታም ግዴታ ነው፡፡ ለብቻህ ለየት ማለት ብትፈልግም የበርሀው አየር በራሱ አይፈቅድልህም። ስስታሙን ቸር፣ ጨካኙን ሩህሩህ፣ ዝምተኛውን ተጫዋች በማድረግ  ረገድ የበርሀ ውሃ  ትልቅ ተጽእኖ አለው፡፡ በዚህች ከተማ ባይኖርህም አትራብም፣ አትጠማም፤ ቢኖርህም ከማንም አትበልጥም፤ መንቀባረርም አያምርብህም፡፡
በድሃና በሀብታም መካከል ያለው ልዩነት አንዳንዴ ከስም የዘለለ የማይሆንበት ጊዜ አለ። የሰው ልጅ የሚከበረው በሰውነቱ እንጂ ባለው የገንዘብ መጠን አይደለም ይሉሃል፡፡ አንቱታ ከፈለክ ሲያምርህ ይቀራል እንጂ የሚያጎበድድልህ አይኖርም፡፡ ለምሳሌ በርሀ የተወለደ ልጅ ‹‹የአባዋራ አልጋ ላይ አትቀመጥ›› ቢሉት መደናገር ብቻ ሳይሆን ግርምትም ይፈጥርበታል፡፡ ምክንያቱም በዚህ አካባቢ ከአልጋ  ይልቅ ጋሌታ ታላቅ ክብር አለው። ደግሞ ይሄ የኔ ነው፤ ያ ያንተ ነው የሚል ገደብና አጥር በዚህ አካባቢ አይታወቁም፡፡ ቀለል አድርጎ ቀለል ብሎ መኖር ነው እንጂ፡፡
ሙቀቱን ፈርተው  ሥራ የቀየሩ ወይም የለቀቁ ወራት ሳይቆዩ በናፍቆትና በአካባቢው የኑሮ ፍቅር ተነድፈው ብዙም ሳይቆዩ ይመለሳሉ፡፡ ያኔም ‹‹የበርሀ ውሃ የቀመሰ ሌላ ቦታ ሄዶ አይለምድም›› ብለው በፍቅር ይቀበሉሃል፤ ጎረቤቶችህ እንደበፊቱ ይንከባከቡሃል፡፡ መደገፍም ካለብህ ያቋቁሙሃል፡፡
ከተለያዩ የፌደራል መስሪያ ቤቶች ተልከው የመጡ  ኦዲተሮችና አማካሪዎች  ሳይቀሩ እዚሁ ሰምጠው ቀርተዋል፡፡ ምክንያቱም ኑሮን ቀለል አድርጎ የሚኖር፣ የማያካብድና ፍቅርን የማይነፍግ ማህበረሰብ በዚህ አለ፡፡
የማወራችሁ የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መዲና ስለሆነችው ሰመራ ሎግያ ከተማ ነው፡፡
በአይናፈሯ ከተማ ሎግያ ሠመራ፤ ብዙ አስገራሚና አስደሳች ነገሮች በየዕለቱ ይስተወላሉ፡፡ ለምሳሌ የዝናብ ሠርገኛ በየትም ሀገር የሚታወቀው ጥቁር ደመና አለዚያም ጭጋግና ጉም ነው፡፡ ነገር ግን በሎግያ ኑሮ ብቻ ሳይሆን፣ ሙቀት ብቻ ሳይሆን፣ ፍቅር ብቻ ሳይሆን፣ ንግድ ብቻ ሳይሆን፣ አኗኗር ብቻ ሳይሆን የዝናብም አመጣጥ የተለየ ነው፡፡
 ከምስራቅ የሰማዩን ጥግ ይዞ ሲገሰግሰስ የምታየው ግጥም ያለ ጥቁር የደመና ደለል  ሊመስልህ ይችላል፡፡ ሲቀርብህ ግን ጠራርጎ የሚወስድህ ነፋስ ሆኖ ታገኘዋለህ፡፡ የገርጀሌ ሜዳን አቧራ ተሸክሞ አምጥቶ ያለ ወዛደር ያራግፍብሀል፡፡ አንተ ያኔ አቧራህን በፍጥነት ካላራገፍክ እሱን አጅቦት የሚዘንበው ዝናብ ወይ ያጥብሀል አለበለዚያም ጭቃ ላይ የተንደፋደፍክ ያስመስልሀል፡፡  
የሌላ አገርን ዝናብ ዳመና፣ ጉምና ጭጋግ ያጅበዋል፡፡ የሎግያ ሰመራን ዝናብ ደግሞ  እንደቤተ-ዘመድ አቧራ ያጅበዋል፡፡ ዝናብም በሰማይ ያገኘውን አቧራ እየጠረገ  ከሰማይ ወደ መሬት ሲወረወር፣ የዝናብ ትርዒት ወይም ውድድር የምታይ ይመስልሃል፡፡ አንተ የምታውቀው ከዝናብ ጋር የሚወርድ በረዶ ከሆነ በዚህ ግን  ፌስታል፣  ፕላስቲክ፣ ካርቶን፣ የጫት ገረባ፣….የመሳሰሉትን ናቸው፡፡
ያለምንም የዝናም  ጠብታ፣ የመብረቅ ጩኸት እና ብልጭታ የሰማዩን ጥግ እየቀረደደው ሲወርድ ስታይ ፎቶ የማንሳት ፍቅር  ካለህ ድንቅ ነገር ነው። አንሳው፤ ለፌዝ ቡክህ ይሆንሃል፡፡ እርግጠኛ ነኝ በአቧራ የታጀበ ድፍርስ ዝናብ የሚዘንበው በዚያ አካባቢ ብቻ ነው፡፡ እንግዲህ ለበርሀ ዝናብ የውሃ ትነት ብቻ ሳይሆን የአቧራ ቡነትም ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡
ሌላው አስገራሚ ነገር  እየዘነበም ማቃጠሉን የማይተወው የቤት ሙቀት፣ የቦነነብህን አቧራ (በላብ) በፍጥነት ወደ ጭቃነት ይቀይረዋል፡፡
ዝናብ ሲዘንብ ሌላው አጃቢ መብራት ኃይል ነው፡፡ የመብራት ቦሎች (ባሎዎች) በንፋሱ ሃይል ሊወድቁ ስለሚችሉ አቧራው እንደተነሳ መብራት ወዲያው ይጠፋል፡፡ ያኔ በዝናብ ውስጥ የማይታመን ሙቀት ያቀልጥሃል፡፡  
አቧራ ሲመጣ ሁሌም መብራት ስለሚጠፋ የፋን ቅዝቃዜ እንኳን ለመጽናኛ አታገኝም፡፡ የመብራት ኃይል አጃቢ ደግሞ ቴሌኮሙኒኬሽን ነው፡፡ እንግዲህ የዝናብ አጃቢዎች ሁለት ታላላቅ መስሪያ ቤቶች፣ ብዙ ቆሻሻዎች ፣የምጻት ቀን ደረሰ እንዴ የሚያስብል አቧራ ናቸው፡፡
አልደብቅህም፤ ሙሉ ቀን ስታጥብና የቤት እቃዎቿን ስታስተካክል የዋለች ሴት መነጫነጭ የምትጀምረው ገና ነፋሱን በሩቅ ስታየው ነው። የተፈጥሮን ህግ ለማድነቅ ከሚያስገድዱ ነገሮች አንዱ በቀን ብዙ ጊዜ ቢነፍስም፣ ቀኑንም ሙሉ በአቧራ ብትውልም በዚህ ምክንያት እንኳን ሌላ በሽታ ጉንፋንም አይዝህ፡፡ አቧራ በሽታ ነው የሚልህ ሰው አታገኝም፡፡ ዶክተር ብታማክርም በዚህ አካባቢ በአቧራ ምክንያት የሚመጣ ችግር የለም፡፡ አቧራውም ይቦናል፤ ኑሮም ይቀጥላል፡፡
‹‹እንዴት በአቧራ ምክንያት ጉንፋንም አይዝህ ብለህ ታካብዳለህ›› ብትለኝ አልቀየምህም፡፡ ብዙ መልስ የሌላቸው ነገሮች በዚህ አካባቢ ታገኛለህ። ለምሳሌ በምትኖርበት ሰፈር በወር አርባ፣ ሃምሳ ህጻናት ሊወለዱ ይችላሉ፡፡ ለቅሶ ግን በወር አንዴም ላትሰማ ትችላለህ፡፡ ‹‹ሞት ተጠርዞ ከዚህ ተባሯል እንዴ?›› ያስብላል፡፡ አናትህን የሚበረቅስ ጸሃይ እየወጣ ፊትህን አይለበልብህም ወይም አያቃጥልህም፡፡ ቀዝቃዛ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች በጥላ ሲከለሉ ለይስሙላ እንኳን በኛ ምድር ጥላ አንጠልጣይ አታገኝም፡፡ ከማህጸን የወጣን ልጅ እንኳ የማይጋጭ የአየር ንብረት በዚህ አለ፡፡ ታድያ ምን እንላለን፡፡ ተፈጥሮ ግሩም ነው ብሎ ማለፍ እንጂ፡፡ ብዙ ተዓምር ቀስ እያልኩ አወራሃለሁ። በአምላክ ጥበብ እጅህን አፍህ ላይ ጭነህ እንድትገረም ካሰኘህ፡፡
የሎጊያ ከተማ  ሁሌም ቅዳሜ ምሽት የበዓል ዋዜማዋ ነው፡፡ ከተማዋ ቀንና ማታ ፍጹም ትለያያለች፡፡ ቀን ‹‹አንገት ደፊ አገር አጥፊ›› እንደሚባለው እንደ ልጃገረድ ስትሽኮረመም ትውልና ፀሀይ ለጽልመቱ ስፍራውን ሳታስረክብ ገና በቅጽበት  ሐፍረቷን ትጥላለች፡፡  ለዚህም ነው ዓይናፋሯ ከተማ ያልኳት፡፡
ቀን ራቁታቸውን በየበረንዳው ጫት ከሚሸጡትና ከሚያደቁት፣ እየተሯሯጡ በሀሩሩ ጸኃይ ከሚደልሉት፣ እንደ ወፍ ብር ብር ከሚሉት ባጃጆች፣ መንገድ እየዘጉ ከሚያስቸግሩት ከባድ መኪኖች በተጨማሪ አስፓልቱን ሞልተው የምታገኛቸው ተማሪዎችንና ትራፊኮችን ነው፡፡
ሠመራ ሎግያ ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ ታላቅ ለውጥ በማምጣት ላይ ትገኛለች፡፡ ይህ ሪፖርት እንዳይመስልህ፡፡ ከዛሬ አምስት እና አስር ዓመታት በፊት እንግዳ ቢመጣ የሚያርፍበት ሆቴል እንኳን ይቸግር ነበር፡፡ አሁን ግን ማማረጥ ትችላለህ። ሎግያ ብትፈልግ ካሰኘህ ሠመራ በኤሲ ቅዝቃዜ የተንበሻበሹ ሆቴሎች ተገንብተዋል፡፡ እሰይ የሚያስብልን ነገር እሰይ ማለት ይበጃል ብዬ ነው። ለነገሩ በቀደሙት ዓመታትም ቢሆን ሎግያ ሠመራ ከተማ ለማደግ ሳትመች ቀርታ እንዳይመስልህ፡፡  በሎግያ ከተማ ተሸቅሎ በሌሎች ከተሞች ስንትና ስንት ፎቅ እንደተሰራ አዳማ፣ አዲስ አበባ፣ መቐሌ፣ ኮምቦልቻ እና ደሴ ምስክሮች ናቸው፡፡
ያም ሆነ ይህ ምንም እንኳን ጥናት ባላደርግም አሁን ያለችበት እድገት ጥሩ ይመስላል፡፡ በከተማዋ ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች፣ ነጋዴዎች፣ መንግስት እና ግለሰቦች ለልማቱ መፋጠንም ሆነ መጓተት መንስኤ ናቸው፡፡
ንግድ በሎግያ ከተማ በከራማ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ እቃ ልትገዛ ሄደህ የመቶ ብሩን ሁለት መቶ ሃምሳ ይሉሀል፡፡ ሌላ ከተማ ሄደህ ብትገዛ ብዙ ወጪ እንዳለብህ ስለምታውቅ አማራጭ አይኖርህም፡፡ ወይም ዋጋው ይሄ ይመስልሀል፡፡  በሁለተኛው ቀን  ልትገዛ ከተመልስክ  ወዶታል ማለት ነው በሚል እሳቤ  “ሶስት መቶ” ልትባል ትችላለህ፡፡ “ትላንት  ሁለት መቶ ሸጠህልኝ?!” ካልከው  ‹‹አመጣጡ ነው›› ብሎህ ያርፋል፡፡ “ባንዴ መቶ ብር ታድያ እንዴት ይጨምራል?” ስትለው ደግሞ፤ ‹‹ትናንት በገዛሃ›› ይልሀል፡፡ አለበለዚያም ‹‹ወላሂ፣ ነብያችንን፣ እመብርሃንን፣ መድሃኒያለምን ፣ ገብርኤልን” በማለት አዲስ እንደመጣ ሊያስረዳህ ይኳትናል፡፡
አንዳንዱ ደግሞ  እንደ አመለኛ በሬ ‹‹እፍ..›› በማለት አፍንጫውን ነፍቶ፣ በንቀት አይቶህ የማይከራከሩትን ያስተናግዳል፡፡ እያካበድኩ ከመሰለህ በዚች ከተማ የመርፌ ዋጋ እንኳን አንድ ብር ከአስር ሳንቲም ገብቷል፡፡ ያንንም ካገኘህ ነው፡፡ ደግመህ ከጠየቀከው ዋጋው እንደሚጨምር አትጠራጠር፡፡
አንዳንዴ ደግሞ ጥሩ ትርኢት ታያለህ፡፡ አንተ ላይ የተዘባነነብህን ባለሱቅ አንዱ አፋር መጥቶ፤ ‹‹አንተ አውቶቡስ በራው (መኪና የወለደህ)›› ሲለው አንጀትህ ቅቤ ይጠጣል፡፡ “መጤ” የሚለውን ቃል አውቶቡስ በራው የሚለው ይወከለዋል። ስለ መጤ ብዙ መናገር ይቻላል፡፡ አንተ መጤ ሲባል የምታውቀው ከሌላ ቦታ መጥቶ የሠፈረን ሰው ሊሆን ይችላል፡፡ ከሌላ ቦታ መጥቶ የሰፈረ አፋር “አውቶቡስ በራው” ይባል ይሆን? ኧረ ምን አደከመን፤ ወደ ዋናው ወሬያችን እንመለስ፡፡
 ሙዝና ቲማቲም ልትገዛ ሄደህ፣ ሌላ ሀገር የዘበኛ የወር ደመወዝ የሚያክል ጭማሪ ሊደረግብህ ይችላል፡፡ ምናልባት ‹‹እዚሁ ዱብቲ ከተማ በርካሽ እየተሸጠ›› ብትለው፤ ‹‹ታድያ ለምን እዚያ ሄደህ አትገዛም›› ይልህና ዘወር ብሎ ሌሎቹን ደንበኞች ያስተናግዳል፡፡ የተጠየቁትን ሳይከራከሩ የሚከፍሉ ብዙ ሰዎች ይገጥሙሀል፡፡ አንተ ብቻ ቀብቃባ እንደሆንክ ይሰማህና ሳትከራከር ትገዛለህ፡፡ ነገር ግን አንተ  በወር ደመወዝህ ብቻ  የምትኖር ከሆነ፣ በወሩ አስራ አራተኛው ቀን ላይ ብድር መግባትህ አይቀሬ ነው፡፡ ምክንያቱም አንተ የምትጋፋው ብር ከሚያፍሱ ሰዎች ጋር ሊሆን ይችላል፡፡
የቀን አይናፏሯን፣ የሌሊት መንጃጋዋን ሎግያ ከተማ ብር የሚያፍሱም የሚያፈሱም ሰዎች ይኖሩባታል፡፡ በከተማዋ የምትፈልገው ነገር ሁሉ አለ፡፡ ዋጋው ተራራ ቢያክልም እንኳ የሌለው ነገር የሌለ ብቻ  ነው፡፡
የማልደብቃችሁ ነገር በሎግያ ከተማ የማይገኙት የሸበተ ሽማግሌ  እና ባልቴት ናቸው። ምናልባት ሚስትህ አርግዛ ‹‹በምርኩዝ የሚሄድ ሽማግሌ ማየት  አማረኝ›› ብትልህ ጉድህ ይፈላል። ይህ ከሚያምራት አውሮፕላን ግዛልኝ ብትልህ ይሻልሃል፡፡
ሌላው ላታገኝ ትችላለህ ብዬ የምገምተው የፈለግኸው ዓይነት የሚከራይ ቤት ነው፡፡ የቤት አከራዮች ዋጋ እና ቤቱ ካለመመጣጠናቸው የተነሳ ዘጠኝ መቶ ብር የተባልከው ቤት ውስጥ  የተቀመጠ ስድስት መቶ ብር ያለ ሊመስልህ ትችላለህ፡፡
ሲጥጥ ሲጥጥ ሲል የጦር አውሮፕላን የሚመስል ፋን ገጥመው ‹‹ፋን አለው ፣መብራት አለው፣ ውሃ ግን ገዝተህ መጠቀም ትችላለህ›› ሲሉህ ላፋቸው እንኳን አይከብዳቸውም፡፡
እስኪ ልየው ስትል፤ ‹‹ቆይ ቆይ ብቻህን ነህ? ጓደኛ ታበዛለህ እንዴ? ስራህ ምንድን ነው?፣ ፍሪጅ አለህ? ስቶቭ ትጠቀማለህ?” የመሳሰሉትን ኢንተርቪው ካለፍክ በኋላ አፓርታማ እንደሚያከራይ ሰው እየተዘባነኑ ያሳዩሀል፡፡ አሪፍ ቤት ያገኘህ መስሎህ ስትገባ፣ የቤቱ ግድግዳ ከመጣመሙ የተነሳ የማርንጌጃ ዳንሰኛ የሚመስል ሊሆን ይችላል። አለዚያም  የግድዳው ቀለም ከማስጠላቱ ወይም ከማርጀቱ የተነሳ  የቀለማት ማህበርተኞችም እንደማያውቁት ትገምታለህ፡፡ ኮርኒሱ የአቧራ ማቆር ልማት  ላይ ሊመስልህ ይችል ይሆናል፡፡ በመደነቅ እጅህን አፍህ ላይ ጭነህ፤ ‹‹ይሄው ነው ዋጋው?›› ካልካቸው፣ ‹‹ብቻህን ስለሆንክ እንጂ ይጨምር ነበር›› ይሉሃል ኮራ ብለው፡፡
በአንተ ብር ቤተሰባቸውን ማስተዳደር እንዳማራቸው ወይም ሌላ አገር ያስጀመሩትን ቤት ለማስጨረስ እንዳሰቡ ልትገምት ትችላለህ፡፡ ግምትህ ስህተት ነው ብለህ አታስብ፡፡  ቤት በመፈለግ ደክሞህ ከሆነ ‹‹እሺ በቃ ለጊዜው ልከራየው›› ስትል፤ ‹‹ሴት ይዞ መምጣት ክልክል ነው›› የሚል ሌላ አንቀጽ ይጨምሩብሃል፡፡ ፍቅረኛው ልታየው መጥታ ሆቴል ተከራይቶ የሸኘ ወጣት እንደማውቅ እነግርሃለሁ፡፡  ግን ብዙ አትፍራ፡፡
እድለኛ ከሆንክ አሪፍ አከራይ ይገጥምህ ይሆናል፡፡ እናት የሆኑ፣ በዓመትህም ኪራዩን ብትከፍላቸው የማይቀየሙ አከራይዎችም በዚህቹ ሎግያ ከተማ አሉ፡፡  አንዳንድ ምርጥ ቤቶች ምርጥ ባለቤቶችም እንዳሉ ልጠቁምህ እወዳለሁ። አንተን ከነጉድህ መሸከማቸው ብቻ ሳይሆን ልጄ ብለው የሚጠሩህ አከራዪችም አሉ፡፡ ሲርብህ አጉርሰው፣ ሲጠማህ አጠጥተው አንቀባረው አኑረውህ፣ እዳህን ሳትከፍል ላሽ እንዳትል  ብቻ ተጠንቀቅ፡፡  ቀላቢት (የጫረው) በልተው የሚጠፉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ምንም ሁን ግን ለአምላካቸው ብለው የሚወዱህ፣ ደግነታቸው በአደባባይ የሚመሰክርላቸው ሞልተዋል፡፡ “ተመስገን ነው” የሚል መጽናኛ  በምድር ላይ አለመጥፋቱ አትልም!
በነገራችን ላይ የቤት አከራዮች ባለትዳር ብትሆን ደስ ይላቸዋል፡፡ የቤት ሰራተኞች ደግሞ ወንደላጤ ስትሆን ይመርጡሃል፡፡ አከራዮች ባለትዳር የሚፈልጉት ግቢያቸውን ለማስከበር እንዲመቻቸው ሲሆን የቤት ሰራተኞች ደግሞ ወንደላጤ የሚወዱት ከአስዝቤዛ ከሚገኙ ትርፋ ትርፎች በተጨማሪ ከተመቻቹ ወደ ገደለው ጭልጥ ለማለት ነው ይባላል፡፡
በተከራይነት ገብተው ቤት የሰሩ እንዳሉ ሁሉ በሰራተኝነት ገብተው አግብተው፣ ወልደው የሚኖሩ የቤት ሰራተኞች በሎግያ በጣም ብዙ ናቸው፡፡ እንደውም አንዳንዶቹ  ፍቅረኛ ያለውን አስከድተው፣ ትዳር ያለውን አስፈትተው፣ ኑሮአቸውን በቁጥጥር ሥር ያዋሉ ናቸው ይባላል፡፡
(ይቀጥላል)

Read 2785 times