Saturday, 25 April 2015 10:56

‹‹ዞዝ!›› ወ ጥበብ

Written by  ተሊኒዮስ አትናቴዎስ
Rate this item
(0 votes)

“የብሔራዊ ትያትሩ አንበሳ ፊቱን ለምን አዞረ?”

እናት፤ ቀኑን ሙሉ ተጎልቶ ፊልም በማየት ከቤት አልወጣ ያለ ልጃቸውን እርሱ ባለበት በቤት ስልክ ለሚያዋሯቸው ወዳጃቸው ሲገልፁ ምን ቢሉ ጥሩ ነው… ‹‹የእሱን ነገር አታንሺብኝ፤በቃ ‹ዞዝ› ሆኖብኛል!››
ዞዝ
የማትንቀሳቀሰው የማትሄደው፣
ትናንትም ዛሬም እዛው፣
       ልበ ደንዳናው ግኡዝ፣
       አንድ ወጡ ዞዝ፣
ሰሜን ወገራን ተጓዝኩ፣
በለሳን ጋይንትን አለፍኩ፣
      ዘወር ብዬ ባስተውልህ፣
      ዞዝ! ዛሬም እዛው ነህ?! …
ዞዝ ምንድን ነው? እነሆ ይኼን ጥያቄ ባጭሩ ብቻ እመልሰው ዘንድ ወደድኩ፡፡ በኔና በውድ አንባቢያን መካከል እንዳንተያይ የሚጋርደን አንዳችም ነገር (ዞዝ) እንዲኖር አልፈቅድምና፡፡ ዞዝ የተራራ ስም ነው፡፡ ምን አይነት ተራራ? የት የሚገኝ? እና አሁን እንዴት እዚህ ሊነሳ ቻለ? ያውም የጥበብ አምድ ላይ? ዝርዝሩን በጽሑፌ ውስጥ ከተለያዩ ሀሳቦች ጋር እያሰናሰልኩ መመለስ መረጥኩ እንበል፤ በቃ ይኼም በራሱ አንድ ዞዝ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የግልፅነት፣ ምላሽ የማንቀራፈፍ፣ የንፉግነት…ወዘተ ዞዝ!
ክቡራትና ክቡራን አንባቢያን፤ ‹‹ዞዝ›› በራሱ ስልጣን (የስልጣንም ዞዝ አለ) የአንድን ከደርግ አፈ ሙዝ (ዞዝ) በተአምር የተረፈን ኢትዮጵያዊ ታጋይ ውብ የእድሜ ዘመን አንክቶ ከበላ የግጥም መድበል መካከል እደግመዋለሁ፤በራሱ የጥበብ ኃይል ተመዝዞ ወጥቶ ከተፃፈ ከ35 አመታት በኋላ ለዚህ ዘመንም የተስማማና በተለይም ሰሞኑን በከተማችን ውስጥ ተምሳሌታዊ፣ ሀሳብ ወካይ የመግባቢያ ቋንቋ Metaphor እስከመሆን የደረሰ ብርቅዬና ድንቅዬ፣ እንግዳና ቤተሰባዊ የግጥም ውበትና ጉልበት  መገለጫ ‹‹ቃል›› ነው፡፡ ለምሳሌ ጓደኛዋ አብራው እንድትቆይ የጠየቃት ኮረዳ፤ አባቷ ወይም ታላቅ ወንድሟ ከፊልድ መመለሱን ነግራው ‹‹እኔም እፈልግ ነበር ፍቅሬ፤ ግን በኋላ ደሞ ቤት ስገባ ‹እስካሁን የት ነው ያመሸሽው?!› ብሎ አይኑን እያጉረጠረጠ ዞዝ ይሆንብኛል!›› ትላለች፡፡ ቀለል ማድረግም ይቻላል…ወዳጆች ሰብሰብ ብለው ሲጨዋወቱ ወይም በስራ ውጥረት ላይ ሆነው ድንገት መብራት ድርግም ቢል ‹‹ኤጭ! አሁንስ ይኼ መብራት ዞዝ ሆነብን’ኮ!›› ይባላል፡፡ ታክሲ ጠፍቶ ከቀጠሮ ብናረፍድ ለቀጠረን ሰው ‹‹ይቅርታ ትራንስፖርቱ ዞዝ ሆኖብኝ ነው›› እንደማለት፡፡ ተግባብተናል ብዬ ላስብና ልቀጥል…     /ባለመግባባት ግብቡነትም እንግባባለን!/
ዞዝ - የቃሉ መገኛ ከሁለት ወራት በፊት ለንባብ የበቃው የታጋይ /አምባሳደር ህላዌ ዮሴፍ ‹‹ታሪክና ጥበብ›› የግጥም መድበል ነው፡፡ ህላዌ በመድበሉ ውስጥ በትግል ዘመኑ የከተባቸው 61 ያህል ግጥሞችን ያካተተ ሲሆን፤ ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ ግን አንዱ ግጥሙ ብቻ ነው፡፡
በመግቢያ ገፆቹ በደራሲ ጌታቸው በለጠ ‹‹በትንታግ እሳት መሀል የተፃፉ ትንታግ ግጥሞች›› በሚል አርዕስት በቀረበው ቅኝት መካከል /ገፅ 30 ላይ/ ‹‹እያንዳንዱ ግጥም በምን ሁኔታና ጊዜ እንደ ተፃፈም በማብራሪያ ተደግፏል›› የሚል አረፍተ ነገር ሰፍሯል፡፡
በእርግጥም ይህ መሆኑ ገጣሚው ካስተዋለውና በስንኝ ከሰደረው Observations and Expressions ባሻገር ምናቡን በቅርብ እንጋራ ዘንድ ማገዙ ሀቅ ነው፡፡ ምናልባትም ሳይለው የቀረው ጉዳይም ቢኖር ስሜቱን ለመታከክ ይረዳል፡፡የግጥም ነገር በወረቀት ከቀረበውም በላይ ያልፋልና። ስታንሌይ ኩኒትዝ እንዲል…”The poem on the page is only a shadow of the poem in the mind. And the poem in the mind is only a shadow of the poetry and the mystery of the things of this world.”
      ዞዝ ዛሬም እዛው ነህ?!
      የት ሆኜ ነው የማላይህ?!
      ከፊት ከጀርባዬ የማጣህ?!
‹‹ወንዞች ተሻገር! ድንበር ስበር፡
አገር አቋርጥ፡ ሂድ ብረር፣››
       ነው የምትለኝ፣
     ወይስ አትራቀኝ፣
ዞዝ!
አንተ ግዑዝ! …
ህላዌ ለዚሁ ዝነኛ ለሆነው ዞዝ የተሰኘ ግጥሙ የፃፈውን የግርጌ ማስታወሻ እንይ…
‹‹ዞዝ - በሰሜን ጎንደር ዞን በምዕራብ በለሳ ወረዳ (በቀድሞው ሊቦ አውራጃ በለሳ ወረዳ በዘሀዬ ምክትል ወረዳ) የሚገኝ፣ በአካባቢው ካሉት ተራራዎች ሁሉ ለየት ያለና የጠረጴዛ ቅርፅ ያለው፣ከሩቅና ከሁሉም አቅጣጫ የሚታይ ተራራ ነው፡፡ ከተራራው ግርጌ፣ላሊበላና ሰቆጣ አካባቢ የሚገኙ አይነት፣ከውቅር ድንጋይ የታነፀው ዞዝ አምባ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ይገኛል፡፡
ዞዝ  በኢሕአሠ የአመራር ብቃት መጓደል ምክንያት ካለበት አካባቢ ወጣ ብሎ መስፋፋት ያልቻለው የሪጅን ሦስት ሠራዊት አባላት እዛው በለሳ ውስጥ ስንንከላወስ ጧት ማታ የምንመለከተውና ከአይናችን የማይሰወር ተራራ ነበር፡፡ ግጥሙ እንደ ዞዝ ተራራ የተገተረውንና መነቃነቅ የተሳነውን የኢሕአሠ አመራር በሾርኒ የወረፍኩበትና የታጋዩንም ብሶት ለማንፀባረቅ የሞከርኩበት ግጥም ነው፡፡
መጀመሪያ ረቂቁን ‹‹አብሩክ›› ላይ ሆነን፣ተራራውን እያስተዋልኩ፣ ከተቃጠለ ዛፍ በተፈረካከሰ ጥቁር ከሰልና በቢክ እስክሪብቶ፣ በነጭ አቡጀዲ የአንገት ልብሴ ላይ ሞነጫጭሬ፣ ‹‹ኣዲ›› ውስጥ ባረፍን ጊዜ በወረቀት ላይ አስፋፍቼ አሰፈርኩት፡፡ ግጥሙ በለሳ ውስጥ የኢሕአፓ/ሠን አመራር የሚቃወመው ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄውን ማቀጣጠል በጀመረበት ወቅት፣ በተለይ በ1972 ዓ.ም፣ በሠራዊቱ ስብሰባዎች ላይ በተደጋጋሚ ተነቧል፡፡›› /ገፅ-48-49/
በመድበሉ ውስጥ ጋሽ ጌታቸው በለጠ፤‹‹ከሺህ ቃላት አንድ ስዕል የበለጠ ይናገራል›› ይላሉ›› ብሎ ያወደሳቸውና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ጥበብ ረዳት ፕሮፌሰር ሰአሊና ገጣሚ በቀለ መኮንን ‹‹እሳትን ለመስራት እሳትን መብላት›› በሚለው የቅድመ ህትመት የመግቢያ ፅሑፉ ውስጥ‹‹በሰአሊዎቹ ነፃ ፈቃድ የተፈጠሩት ስልተ-ብዙ ስዕሎችና ከጋመ የሕይወት ውጣ ውረድ የተጨመቁት ስነ ግጥሞች የጣምራ ጉዞ ራሳቸውን በቻሉ የጣምራ ሰልፎች ሰምሯል ለማለት ይቻላል።› ብሎ አድናቆቱን የቸራቸው ፤የበርካታ ሰዓሊያን፤ በግጥሞቹ ላይ ተመርኩዘው የሰሯቸው የስዕል ቅቦችም መካተታቸው የመድበሉን አቀራረብ አዲስ የሚያሰኘው ነው፡፡ የሚገርመው ታዲያ ዞዝ ግጥም በሰአሊያኑ መካከልም ልዩ ትኩረት ያገኘ ነበር፡፡ ገጣሚው በግጥሙ ዞዝን ከተራራነት ባለፈ በ‹ሾርኒ. የቀሸረበትን ሀሳብ ከእውነታዊነት Realistic በዘለለ የModern Art አሳሳል ለማማጥ፡፡ በመጨረሻም  ግጥሙ የደረሰው  ሰአሊ ዮናስ ደገፉ /ገፅ 46/ በሚገርም  መንገድ  አስቀምጦታል፡፡ በድጋሚም  ሰአሊ ሰለሞን ኃይሉ፤ ‹‹ጓዶቻችን››    ለሚለው  ግጥም  ባበረከተው /ገፅ 156/ ስራው ዞዝንም በስእል ድርሰቱ ውስጥ አካትቶት ይገኛል፡፡
ይህ መነጋገሪያ ግጥም ግን በመፅሀፉ ምረቃ ዕለት (መጋቢት 27 ቀን 2007 ዓ.ም) የመነበብ እድል ካላገኙት መሀል ነበር አሉ፡፡ እኔ አልተገኘሁም፡፡ መረጃ የማግኘት ዞዝ ገጥሞኝ፡፡ እናም አልተጠራንም ወይም እንዳንሳተፍ ተገልለናል የሚሉ አኩራፊ የጥበብ ቤተሰቡ አባላት መኖራቸውንና ከእነርሱም አንዳንዶቹ በፊልም ሙያ እንደ የቲኬት ቀረጥና የአዳራሽ ኪራይ ዞዝ አናውዞናል ባዮች መሆናቸውን ሰምቻለሁ፡፡
በጣም ከባድ ይቅርታ፤ አርቲስቶች ግን መቼ ነው በጋራ የምትቆሙትና ህብረት የነሳችሁን ዞዝ ሰንኮፉን ላንዴው ነቅላችሁ የምትጥሉት? ስማ! እንትና ሲደማ፣ አብረህ ከምታማ፣ አንተም አብረህ ድማ! እንደ ታጋዩ ገጣሚ፤ ‹‹ደማቁ ደምህ ነው ህይወት የዘራብኝ፤አንተ ደሜ! የጓዴ ደም!›› ተባባሉ እስቲ? (SOLIDARITY!)  በምረቃው ላይ ባለመገኘቴ እኔን የቆጨኝ ነገር ቢኖር ግን ሌላኛው ታጋይ በረከት ስምኦን በጣም የሚወደድለትን የትግል ዘመን ግጥሙን ‹‹መቸስ ምን እንላለን››ን ለወዳጁ መፅሀፍ ምረቃ በብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ቆሞ ማንበቡን ስሰማ ነው፡፡ Poetry becomes alive when it is read aloud!
ስለ ሰአሊያን ካነሳን አይቀር አንድ ነገር ማለት ይገባናል፡፡ ሙያውንና ሰአሊያኑን የሚያበረታታውን የማኩሽ ጋለሪ ባለቤትን አቶ ተስፋዬ ህይወትን ማመስገን፡፡ ማመስገንም ይልመድብን። እናም ከእኒህ  አይነት ቅን ሰዎች ጋር በመተባበርም አንዳንድ የሰአሊያኑን ችግር ለመፍታት ቢሞከር? አንድ ሰአሊ ወዳጄ እንደነገረኝ፤ የባለሙያዎቹ የጥበብ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ ያደገ ቢሆንም ቅሉ ሀሳባቸውን እንደ ልብ ለመሳል ለምሳሌ የተወጠረ ሸራ በፈለጉት ጊዜ ለማግኘት በከተማው ውስጥ የአቅርቦት እጥረት (ዞዝ) አለ፡፡
ከዚያው ከብሔራዊ ቴአትር ሳንወጣ አንድ ሰሞንኛ ወሬ (ዞዝ) ብንጨምርስ ምን ይለናል…የወሬኝነት አባዜ (ዞዝ) በሉት ከፈለጋችሁ፡፡ እና ባለፈው አርብ እለት በአዲሱ የቴአትር ቤቱ ሥራ አስኪያጅ፣ አንድን ተዋናይ ‹‹በአስቸኳይ›› በሌላ ተዋናይ ስለመለወጥ የተላለፈ ውሳኔ ቅዳሜ ምሽት በኢትዮፒካሊንክ ቀርቦ ነበር፡፡ እኔን ዞዝ የሆነብኝ ነገር ምን መሰላችሁ? ተዋናዩ በተደጋጋሚ መቅረቱ ቢገለፅም ከ15 ቀናት በፊት በቴአትር ቤቱ በተመረቀው ‹‹የፍቅር ማዕበል›› ፕሮግራም ላይ የተሰራጨው ህትመት ፤ ይኸው ተዋናይ ትርኢት እንዳይቋረጥ ሲል እናቱንም ሳይቀብር መድረክ ላይ መቆሙን፤ እንዲሁም ሀዘኑንም ደስታውንም ከዚያው መድረክ ሳይለይ፣ የቀለበት ስነ ስርአቱንም ቴአትር ሰርቶ ሲጨርስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ በቴአትሩ ታዳሚያን ፊት ማከናወኑ መገለፁ ነው፡፡
በነዚህ ሁለት ‹‹እውነታዎች›› መሀል ያለው ክፍተት (ዞዝ) ምን ይሆን? እናላችሁ ስመጥሮቹ መራሔ ተውኔቶች ቴአትር ቤቱን ለ5 አመት ገደማ ያስተዳደረው ማንያዘዋል እንደሻውና የቴአትር ክፍሉን ለ6 አመታት ያህል የመራው ተስፋ ገብረማሪያም ‹‹ተዋናዩ በፍፁም በድንገት አልቀረም፤ ከቀናት በፊት ከአቅሙ በላይ የሆነ ችግር እንደገጠመው ነግሮን ፈቃድ ጠይቆን፣ እኛም ይህንኑ ለሚመለከተው ክፍል በፅሑፍ አሳውቀናል።›› በማለት የአዲሱን ስራ አስኪያጅ በተቋሙ ከቶም ያልተለመደና ተወዳጁን ተዋናይ በሌላ የመተካት ቀጭን ትዕዛዝ እንደማይቀበሉ አመልክተዋል፡፡ ቀድሞ በትወና ክህሎቱ ከሌሎች ሁሉ መርጠን ለምን በክብር ጋበዝነውና!  
ውሳኔው የተላለፈበት ‹‹እድል ላላገኙ ወጣቶች እድል ለመስጠት ቦታችንን መልቀቅ ይገባናል እና ‹ከአቅም በላይ የሆነ ችግር› ካልገጠመን በቀር ትርኢት አይቋረጥም ”The Show Must go on” በሚል ፅኑ አቋሙ የሚታወቀው ለ8 ሰአት ቴአትር 4 ሰአት መድረክ ጀርባ ቀድሞ በመገኘት ዲስፒሊኑ የሚደነቀው አርቲስት ፈለቀ የማርውሃ አበበ ግን የእገዳ ውሳኔውን ሰምቶም እንኳ ‹‹ችግር የለም  በቃ፣ ባለመግባባት የተፈጠረ የሆነ ቀላል ነገር (ዞዝ) ነው ብለን እንለፈው›› ብሎ /ልቡ እየደማም ቢሆን/ የቴአትር ተመልካቹን በማክበር ቅዳሜም እሁድም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ጀርባ እንደተለመደው ቀድሞ ተገኝቷል፡፡ በስንብት ጊዜም በተደጋጋሚ የላቀ ችሎታ ሽልማት ባስገኘለትና በበርካታ አንጋፋ ከያኒያን በልዩ ልዩ መድረኮች በተመሰከረለት በአስገራሚ የትወና ተሰጥዖው፣ ዘወትር በጋለ ጭብጨባ በሚቀበለው በሚወደውና በሚያደንቀው ተመልካች ፊት ተንበርክኮ፣ የሚያከብረውንና ያስከበረውን መድረክ በእርካታ ስሟል፡፡ የክብር ስንብት …?
አዲሱ ስራ አሥኪያጅ ሙያውን የተማሩና ለኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የሚጨነቁ ናቸው ይባላል፡፡ ታዲያ እንዲህ አይነት ውሳኔ ለማስተላለፍ የበቁት ምን ያለ ዞዝ ገጥሟቸው ይሆን? ለምን መሰላችሁ እንዲህ የምለው---ቴአትር ቤቱን ማስተዳደር ቀላል እንዳልሆነ ብዙ ጊዜ ሲወራ ምን እንደሚባል ስለማውቅ ነው፡፡ እሺ ምንድነው በሉኛ…“የአንበሳው ሀውልትም ፊቱን ያዞረው እንዲህ አይነቶቹን ለዘመናት ያልተፈቱ ግሳንግሶች (ዞዞች) መስማት ታክቶት ነው!” ሀሪፍ አይደለች? ወደ ታጋይ ህላዌ ዞዝ የመጨረሻ ህያው መስመሮች ላንዴው እንመለስ…
           አንተም እንደ ጓደኞችህ፣
         ...እንደተንበረከኩልህ እንደተጀነንክባቸው፣
           ከበታች እንዳደረግኻቸው፣
እንደ እነርሱ ሰልለህ፣
ግርማ ሞገስህን ተገፈህ፣
አውላላህን ቀርተህ፣
አተር ሽምብራ በቅሎብህ፣
መቼ ይሆን የማይህ?
አለያ የዋርድያ ሰአት ይተከልብህ
ወይ ዋርድያው ራሱ ይጎለትብህ
        በኔ እድሜስ አይሆንም፣
        ዛሬን ነገን አይቻልም፣
ወይስ እንደ ዞዝነትህ ድንጋነትህን ይዘህ፣
መቆየትህን ትመርጣለህ?
በልማ ተንፍስልኝ ፍሬ ያለው መልስ ካለህ፣
ዞዝ!
አንተ ግዑዝ፣
አንተ ግዑዝ!
                      /ጥር፣ 1972፤ በለሳ፣ ጎንደር/
በተለይ ‹‹አተር ሽምብራ በቅሎብህ››የሚለውን ሀረግ እዩት እስቲ? በየ‹‹ዞዞቻችን›› ላይ ልምላሜ እንዲያብብ እንመኝ ዘንድ አይነሽጥም? ከላይኛው አንጓ ውስጥ ያለውስ ‹‹ወንዞች ተሻገር! ድንበር ስበር፣ አገር አቋርጥ፣ ሂድ ብረር፣›› ነው የምትለኝ››የሚለው ስንኝ፤ ዘርፈ ብዙ ‹‹ዞዞቻችንን›› ሽሽት ሀገር ለቅቀን ከመሰደድ እንድን ዘንድ ተስፋ የማድረግን ሰላማዊና ሀገራዊ ራዕይ አያቆጠቁጥም?... በየሀገሩ በስደት ላይ ሆነው የመከራ አለንጋ (ዞዝ) የሚጠብሳቸውን ምስኪን ወገኖቻችንን አንድዬ በምህረቱ ይጎብኝልን። የጥበብ ሁሉ ባለቤት፤ ለታመኑት ከፈተና የሚታደግ፣የሰማዕትነትን አክሊል የሚያቀዳጅ አምላክ፤ ሀገራችንን በምህረቱ ይጎብኝልን፡፡ አሜን!!

Read 1544 times