Saturday, 25 April 2015 10:15

የኢትዮጵያውያን ሃዘን እጥፍ ድርብ ሆኗል

Written by  ኤልሳቤጥ እቁባይ
Rate this item
(26 votes)

በሊቢያ ከተገደሉት ውስጥ 5ቱ የጨርቆስ ወጣቶች ናቸው
ልጆቻቸው ሊቢያ የሄዱባቸው ወላጆች በጭንቀት ተወጥረዋል  
   በደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ በደረሰው ዘረኛ ጥቃት ማግስት፣ በሊቢያ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ላይ የተፈፀመው የአሸባሪ ቡድኑ አይኤስአይኤስ  ዘግናኝ ግድያ፤ የኢትዮጵያውያንን ሐዘንና ቁጭት መራር አድርጎታል፡፡ እስካሁን የዘጠኙ  ሟቾች ማንነት የታወቀ ሲሆን ቤተሰቦች መርዶ ተነግሯቸው፣ ለቅሶ መቀመጣቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ወላጆችና ቤተሰብ፣ ወንድምና እህት፣ ጎረቤትና ወዳጆች ሁሉ ውስጥን በሚያደማ ቅፅበታዊ ሐዘን ተመተዋል።    በሊቢያ የአሸባሪው ቡድን ‘አይኤስአይኤስ’ ታጣቂዎች ’30 ኢትዮጵያዊያን ክርስትያኖችን ገድለናል’ ብለው አሰቃቂ የግድያ ቪዲዮና ፎቶ ማሰራጨታቸውን ተከትሎ፣ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች መርዶ ሲደርሳቸው ነው የሰነበቱት። እስካሁን በደረሰን መረጃ፤ በሊቢያ ከተገደሉት ውስጥ 5ቱ የጨርቆስ ወጣቶች ሲሆኑ ከትግራይ አንድ፣ከወለጋ ሁለት እንዲሁም ከሐረርጌ አንድ ኢትዮጵያውያን መገደላቸው ታውቋል፡፡ ከወለጋ የመንግስቱ ጋሼና የአወቀ ገመቹን እንዲሁም ከሐረርጌ “ከክርስቲያን ወገኖቼ አልለይም” በማለቱ አብሯቸው ተገድሏል የተባለውን የጀማል ራህማን  ቤተሰቦች ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡ ባለፈው ሰኞ  የጓደኛሞቹ ኢያሱ ይኩኖአምላክ እና ባልቻ በለጠ መርዶ የተነገረ ሲሆን በቀጣዮቹ ቀናት የሌሎች ሦስት ወጣቶች መርዶ ለየቤተሰቦቻቸው ተነግሯል፡፡ ሟቾቹ ኤልያስ ተጫነ፣ ብሩክ ካሣና  በቀለ ታጠቁ ናቸው፡፡ በሰላሳዎቹ ዕድሜ ላይ የነበሩት ኢያሱና ባልቻ፤ጨርቆስ ውስጥ ያደጉ ጎረቤታሞች ሲሆኑ ከሁለት ወራት በፊት በሊቢያ አድርገው ወደ አውሮፓ ለመሻገር ወጥነው ነበር
ጉዞ የጀመሩት፡፡ ነገር ግን በሊቢያ አሸባሪ ቡድን ‘አይኤስአይኤስ’ በግፍ ተገደሉ፡፡  አቶ ካሳ አግና የ24 አመቱ ወጣት ብሩክ ካሳ አባት ናቸው፡፡ ልጃቸው ከቤት ከወጣ ሶስት ወር እንደሞላው ይናገራሉ፡፡ “ተግባረእድ መማር ጀምሮ ነበር፤ሆኖም ስድስት ወር ሳይሞላው ተወውና ከኔ ጋር ሱቅ መስራት ጀመረ፡፡ አንድ ቀን ሱቅ ሲሰራ ውሎ ማታ የዘጋበትን ቁልፍ እንኳን ሳይሰጠን ጠፋ። መተማ ሲደርስ ነው የነገረን፤ ሱዳን ላይ ደወለ፣ ከዚያም ሊቢያ ሲደርስ  ስልክ ሰጥቶኝ ስለነበር ስደውልለት ገንዘብ ያስፈልገኛል አለኝና  ላኩለት፤ ከዚያ በኋላ ግን አልደወለም፡፡” ይላሉ የሟች ብሩክ አባት፡፡ አቶ ካሣ ባለፈው ረቡዕ የአሸባሪው ቡድን ‘አይኤስአይኤስ’ ን አረመኔያዊ ተግባር ለማውገዝ በተጠራው ሰልፍ ላይ ተገኝተው ነበር፡፡ እዚያው ሳሉ ከልጃቸው ጋር ሊቢያ የሄደው ጓደኛው ሞቷል ተብሎ ተነገራቸውና ሰልፉን አቋርጠው ወደ ሰፈር ሄዱ፡፡ “እዚያ ስደርስ የእኔንም ልጅ መርዶ ነገሩኝ” ያሉት አቶ ካሣ፤ “እኔ አይቼ አላረጋገጥኩም፤ የሰፈር ልጆች ግን አብረውት ስለሚውሉ እሱ
መሆኑን  በፌስ ቡክ ማረጋገጣቸውን ነግረውኛል” ብለዋል፡፡ ከትናንት በስቲያ በለቅሶው ላይ የተገኙ አንድ የሰፈሩ ነዋሪ፣ የብሩክ እናት ከአንድ ወር በፊት ጠበል ሊቀምሱ መጥተው ሰዉን “እባካችሁ ሆዴ እየተረበሸ ነው፤ ልጄ ብድግ ብሎ ሄዷል፤ በፀሎታችሁ አትርሱኝ” ማለታቸውን በሀዘን ያስታውሳሉ፡፡ አቶ ተጫነ ዘለቀ የ24 አመቱ ወጣት ኤልያስ አባት ናቸው፡፡ እድሜያቸው የገፋ አዛውንት ሲሆኑ እሳቸውም ልክ እንደ አቶ ካሳ የሰፈር ልጆች “በመልክ ለይተን ምስሉን አግኝተናል” ባሏቸው መሰረት የልጃቸውን ሞት እንደተረዱ ይናገራሉ፡፡ ልጃቸው ከአገር ለመውጣት ማሰቡን ሲነግራቸው፣“በዚህ  በእርጅና እድሜዬ ምነው ጥለኸኝ ትሄዳለህ” አሉት፤ “አይ እሄዳለሁ፤ እዚህ ምንም አላለፈልንም፤ እዛ ሄጄ ትንሽ እሞክራለሁ” ብሎ መሄዱን አባት ተናግረዋል። ሊቢያ እስኪገባ ድረስ በስልክ እንገናኝ ነበር፤ በኋላ ግን ጠፋብን ፤ልጆቼ በፌስቡክ ቢፈልጉትም ሊያገኙት አልቻሉም፤ ያለበትን እያፈላለግን ሳለ ይሄ መአት ወረደብን” ብለዋል በሃዘን ተውጠው፡፡  አሸናፊ ቦጋለና ውድነህ ታደሰ  የሟቾቹ  የኤሊያስና የብሩክ አብሮ አደጎች  ናቸው፡፡ ከመሄዳቸው
አንድ ቀን በፊት ማታ ብሩክን ወደ ቤት ሲገባ አግኝተነው፤ “እንዲህ -- ሰምተናል” ስንለው፣ “አዎ
አስቤያለሁ” አለን፡፡ ኤሊያስ ግን እንደሚሄድ ነግሮን፣ መልካሙን ሁሉ ተመኝተንለት ነበር የተሰናበትነው፡፡ ደስታና ሀዘን አብረን ያሳለፍን ጓደኞቻችን ናቸው፤ረቡዕ ጠዋት ሰለማዊ ሰልፉን ለመውጣት ስንዘጋጅ አንድ የሰፈራችን ልጅ፣ “ሁለቱ ልጆች በአይኤስአይኤስ ቡድን ሲገደሉ በግልፅ የሚያሳይ ምስል አየሁ” ብሎ አሳየን፤ግን አላመነውም፤ ሌላ የሰፈራችን ልጅ ፊልሙን በኮምፒዩተሩይዞ መጥቶ “ይህ ጓደኛችሁ አይደለም ወይ?” ብሎ አሳየን፡፡ መጀመሪያ ኤሊያስን አየነው፡፡ ቀጥሎ ሁሌም አቀርቅሮ በመሄድ የሚታወቀው ብሩክ፤ በምስሉም ላይ ከገዳዮቹ ስር አቀርቅሮ አየነው፤ብለዋል፡፡  “በጓደኞቻችን ላይ የተፈጠረው ነገር ልባችንን እጅግ ሰብሮታል፤ ቃላት ከሚገልፁት በላይ አዝነናል። አይደለም በምንወዳቸው፣ ጥምቀትን አብረን የምናሳልፍ ጓደኞቻችን ላይ ቀርቶ በግብፃውያኑ ላይ የተፈጠረውም እጅግ አሳዝኖናል፡፡ ኤሊያስም ሆነ ብሩክ ብዙም የመሄዱ ሀሳብ አልነበራቸው፤ እገሌ እዚህ ገባ፣ እከሌ እዚህ ደረሰ የሚሉ ወሬዎች አነሳስተዋቸው መሆን አለበት” ብለዋል የሟቾቹ ጓደኞች፡፡ ከጉራጌ አካባቢ መጥቶ ጨርቆስ ያደገው በቀለ ታጠቁ ወይም በቀለ አርሴማ እድሜው 20 መሆኑን  የአካባቢው ሰዎች ይናገራሉ፡፡ በቀለ እዚያው ጨርቆስ ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ በሚገኝ የሞባይል ቤት ተቀጥሮ ይሰራ ነበር፡፡ የበቀለ ቤት ከኤሊያስና ከብሩክ መኖሪያ ብዙም ባይርቅም ከአገር አብረው ባይወጡም ስደት ላይ ተገናኝተዋል፡፡ የበቀለ መርዶም ቤተሰቦቹ ወዳሉበት ጉራጌ ዞን ደርሷል፡፡ ለጨርቆስ ነዋሪዎች የሰሞኑ መርዶ እርም ማውጣት ብቻ አይደለም፤ “ቀጥሎ ማን ይሆን ተረኛ?”
የሚል ስጋት ያዘለ ነው፤ ይላሉ ነዋሪዎች። ሀዘንተኞቹ ቤት እየመጡ ከሚያለቅሱ የሰፈሩ ሰዎች በርካታዎቹ  የልጆቻቸውን ቁርጥ አላወቁም-ይኑሩ ይሙቱ በጥርጣሬ ውስጥ ናቸው፡፡ ወሬው ሁሉ የስጋት ነው፡፡ “እከሌ ሄዷል፤ እዚህ ፎቶ ላይ አልታየም ነገርግን ድምፁ ከጠፋ ቆይቷል፤ የእከሌ መርዶ ሊነገር ነበር ፤ ፎቶውን እርግጠኛ ስላልሆንን ተውነው፤የእከሌ ልጅ ካምፕ ነኝ ብሏል፤ እነእከሌን ግን ማግኘት አልቻለም” እያሉ ጥርጣሬያቸውን ይተነፍሳሉ፡፡  ልጆቻቸው ወደ ሊቢያ የተሰደዱባቸው ቤተሰቦች፣ ነገን በስጋትና በፍርሃት ነው የሚጠብቋት፡፡ ምን ይዛላቸው እንደምትመጣ እርግጠኛ አይደሉም፡፡ ከሁሉም አሳዛኙ ደግሞ ልጆቻቸው በስደት መሞታቸው እየታወቀ ቢነገራቸው በድንጋጤ አንድ ነገር እንዳይሆኑ በሚል ፍራቻ ፣ከዛሬ ነገ የልጄን ድምፅ እሰማለሁ እያሉ በተስፋ የሚኖሩ ወላጆች መኖራቸው ነው፡፡ በትግራይ ክልል በማእከላዊ ዞን አህፈሮም ወረዳ በምትገኘው የእንትጮ ከተማ ነዋሪ የነበረው ዳንኤል ሀዱሽ  ሌላው የሊቢያው አሸባሪ ቡድን የጥፋት ሰለባ ነው፡፡ የ25 አመቱ ወጣት ዳንኤል፣ ባለፈው አመት ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በኮምፒዩተር ሳይንስ ተመርቋል። በተማረበት ሙያ ሥራ ሲያፈላልግ እንደነበር ቤተሰቦቹ ይናገራሉ፡፡ በመጨረሻ  ለወላጅ እናቱ ለወይዘሮ ዛፉ ገብረእየሱስ፣ ሁመራ ስኳር ፋብሪካ ስራ እንዳገኘ በመንገር ነበር  ጥር 25 ቀን 2007 ዓ.ም የተለያቸው፡፡ ከቀናት በኋላም “ያለሁበት ቦታ የኔትወርክ ችግር ስላለ እኔ ካልደወልኩኝ አታገኙኝም” ማለቱን፣ ከዚያም
ሊቢያ መግባቱን ለእናቱ ደውሎ እንደነገረ ቤተሰቡ ይገልጻል፡፡ የዳንኤልን መልክ በፎቶ ለመለየት
የሚያስቸግር እንዳልሆነ የተናገሩት ምንጮቻችን፤ ከትላንት በስቲያ ለእናቱና ሌሎች ቤተሰቦቹ
መርዶው ተነግሮ፣ በእንትጮ ማርያም ደብረገነት ፍትሀት እንደተደረገለትም ጠቁመዋል፡፡  በፌስቡክ ምስል በማየት ሞትን  ማርዳት  ልጆቻቸውን ያጡትንም ሆነ ሌሎች በስጋት ላይ ያሉትን ሙሉ በሙሉ ላያሳምን  ይችላል የሚል ጥርጣሬ ቢፈጠርም  ወላጆች የሰፈር ልጆች አይተናል ባሉት የምስል መረጃ ነው ሀዘን የተቀመጡት፡፡ አንድ የመቀሌ ወጣት ከሟቾቹ አንዱ እንደሆነ ተደርጎ በፌስቡክ የተለጠፈውን ፎቶውን እያስተባበለ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡ ሆኖም በስደት ላይ ያለ ሰው ለማፈላለግ ከፌስቡክ የተሻለ መንገድ አልተገኘም፡፡ በዚህም የተነሳ ወደ ሊቢያ የሄደ ሰው ያላቸው
ቤተሰቦች በፌስቡክ ፎቶውን በመለጠፍ አፈላልጉን እያሉ ነው፡፡   

Read 8371 times