Tuesday, 21 April 2015 08:24

የጥጥ አምራቾችና የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ትስስር

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

መንግሥት፣ ከወዲህ ሲለው ከወዲያ እያፈተለከ አስቸገረው እንጂ አገሪቷን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ የጀመረውን ጥረት ገፍቶበታል፡፡
አገሪቷ በፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ ስለሆነች የውጭ ኢንቨስተሮች መጥተው በተለያዩ ዘርፎች ቢሰማሩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ግብዣ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ በጥሪው መሰረት መጥተው በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎችም በርካታ ናቸው፡፡
ከእነዚህ ውስጥ በጨርቃጨርቅ ዘርፍ ተሰማርተው ፋብሪካ ከፍተው ስራ የጀመሩ ኢንዱስትሪዎች ይገኙባቸዋል፡፡ ለእነዚህ ኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልገው ዋነኛ የምርት ግብአት (ጥሬ ዕቃ) ጥጥ ነው፡፡ የጥጥ ምርት ደግሞ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አልሳካ እያለ ነው፡፡ በጨርቃጨርቅ ዘርፍ የተሰማሩትን የአገር ውስጥና የውጭ ፋብሪካዎች ችግር ለመፍታት የተዳመጠ ጥጥ ከውጭ ለመግዛት የተደረገው ጥረት ብዙም አልተሳካም፡፡
እንደ ህንድ ካሉ ጥጥ አምራች አገሮች ለመግዛት ቢሞከርም የተፈለገውን ያህል መጠንና የጥራት ደረጃ ማግኘት አልተቻለም፡፡
የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ እንዲሉ… እዚሁ በአገር ውስጥ ገበሬዎች ችግሩን ለመፍታት ባለፈው ዓመት የተጀመረ አንድ ፕሮጀክት ወደ ውጤት እያመራ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የአምናው የተደረገው ጥረት፣ በመተማ ዩኒየን እና በአይካ አዲስ ቴክስታይል መካከል የገበያ ትስስር መፍጠር ነበር፡፡ በስምምነቱ መሰረት፤ መተማ ዩኒየን ለአይካ አዲስ፣ ዘላቂነት ባለው መልኩ 50ሺህ ኩንታል ጥራት ያለው የተዳመጠ ጥጥ እንዲያቀርብ፣ አይካ አዲስም በዓለም አቀፍ ዋጋ እንዲገዛ የገበያ ትስስር ተፈጥሮ ሁለቱም ወገኖች ተጠቃሚ መሆናቸውን የጥጥ አምራቾች ማኅበር ገልጿል፡፡
ፕሮጀክቱ ሲኤምአይኤ የሚባል ሲሆን “በአፍሪካ የተመረተ ጥጥ” የንግድ ስያሜ የእንግሊዝኛ ምህፃረ ቃል መሆኑ ተነግሯል፡፡ ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ12 የአፍሪካ አገሮች እየተሰራበት ሲሆን በአነስተኛ አርሶ አደሮች ማሳ የተመረተ ጥጥ ጥራቱን ጠብቆ ዘላቂነት ባለው መልኩ ለፋብሪካዎችና ለተጠቃሚዎች ማቅረብ ነው፡፡ ትስስሩ ውጤታማ ስለሆነ ወደ ሌሎች ዩኒየኖችና የጨረታ ጨርቅ ፋብሪካዎች ለማስፋፋት ለ2007/2008 የምርት ዘመን አራት ዩኒየኖችና የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች ባለፈው ረቡዕ በኢሊሌ ሆቴል ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
በዚህ ስምምነት መሰረት ከ53 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ያቀፉ ዩኒየኖች 19 ሺህ ቶን የተዳመጠ ጥጥ በማቅረብ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ 10ሺህ አባላት ያሉት ጥረት ወይም መተማ ዩኒየን 3ሺ ቶንስ የተዳመጠ ጥጥ ለአይካ አዲስ ለማቅረብ ተስማምቷል፡፡ በተመሳሳይ 10 ሺህ አባላት የያዘው ዳንሻ አውሮራ ለካኖሪያ አፍሪካ 5ሺህ ቶንስ ያቀርባል፡፡ ባለ 10 ሺህ አባላቱ ሰላም ለኤልሴ 5,500 ቶንስ፣ 13ሺህ አባላት የያዘው ሰቲት ሁመራ ለአልመዳ 5ሺህ ቶንስ፣ ለምለም ወልቃይት ለባህርዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ 3ሺህ ቶንስ ጥጥ ያቀርባሉ፡፡ በአጠቃላይ 53 ሺህ አባላት ያሏቸው አራቱ ዩኒየኖች 21,550 ቶንስ የተዳመጠ ጥጥ በማቅረብ 754 ሚሊዮን 250 ሺህ ብር ያገኛሉ፡፡
ስምምነቱ አነስተኛ የአፍሪካ የጥጥ አምራቾችንና ጥጥ ማዳመጫዎችን የሚያካትት ሲሆን የደላሎችን ጣልቃ ገብነት እንደሚያስቀር ታውቋል፡፡ ሲኤምአይኤ ለጥጥ አምራቾቹ ገበሬዎች የተለያዩ እገዛዎችን ያደርጋል፡፡ የፀረ ተባይ ኬሚካል አያያዝና አጠቃቀም፣ ጥራት ያለው የጥጥ ዘር፣ ውሃ፣ አፈር እንዲጠቀሙ፣ የእንስሳት አያያዝና የደን እንክብካቤ፣ የተፈጥሮ ግብአት አጠቃቀም፣ ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ እንዲከተሉ ስልጠና ከመስጠቱም በላይ ምርታቸውን በጥሩ ዋጋ እንዲሸጡ ከገዢዎች ጋር ያስተሳስራል፡፡

Read 1598 times