Monday, 20 April 2015 15:42

ዘመድ ጥየቃ የመጡት ጉዲፈቻ ልጆች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

እንዴት ነው በጉዲፈቻ የተሰጠሽው?
ታሪኩ እንግዲህ የሚጀምረው ገና የ5 ዓመት ህፃን እያለሁ ነው፡፡ እናቴ በኤችአይቪ ኤድስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች፡፡ አባታችን ደግሞ ታናሽ ወንድሜ ከተወለደ በኋላ ቤተሰቡን ጥሎ በመሄዱ ከዚያ በኋላ አይተነው አናውቅም፡፡ እናታችን ስትሞት አክስታችን ወደ አዲስ አበባ አመጣችን፡፡ ለ6 ወር ከእሷ ጋር ከኖርን በኋላ እኛን የምታስተዳድርበት አቅም ስላልነበራት ትምህርት ቤት ልታስገባን አልቻለችም፡፡ የተሻለ ህይወት እንዲኖረን በማሰብም “የዘላለም ምንጭ” የተባለ ድርጅት አስገባችን፡፡ ይሄ ድርጅት ልጆችን መፅሃፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶችንና ሥነ ምግባርን እያስተማረ የሚያሳድግ ነው፡፡ በዚህ ድርጅት እኔና ወንድሜ ከሌሎች ህፃናት ጋር ለ4 ዓመት ኖርን፡፡ እዚያ እያለን የዛሬ ወላጆቻችን “ኦስበርን” ቤተሰቦች በጉዲፈቻ ልጆቻቸው አድርገው ወሰዱን፡፡ እኛ ከሄድን ከ3 ዓመት በኋላ ደግሞ “የዘላለም ምንጭ” ድርጅት ውስጥ አብሮን ይኖር የነበረው ይድነቃቸው የኛን ቤተሰብ ተቀላቀለና አሁን በኦስበርን ቤተሰብ ውስጥ ሶስት ኢትዮጵያውያን አለን ማለት ነው፡፡
ስትሄጂ ደስተኛ ነበርሽ? ቅር አልተሰኘሽም?
እኛ እዚህ እያለን ሁሌም ቤተሰቦች እንዲሰጣችሁ ፀልዩ እንባል ነበር፡፡ የዛሬ አሳዳጊዎቻችንን ስናገኝ የተሰማኝ ደስታ ልዩ ነበር፡፡ ከጓደኞቻችን መለየቱ ግን በጣም ከብዶን ነበር፡፡ እዚያም ስንደርስ መጀመሪያ አካባቢ ቀላል ነበር ማለት አይቻልም፡፡ አዲስ ቤተሰብ ውስጥ ነው የገባነው፤ ባህሉ የተለየ ነው እና ለአንድ ዓመት ያህል ትንሽ ይከብድ ነበር፡፡ ነገር ግን አሳዳጊዎቻችን መልካምና የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ስለነበሩ በሚገባ ተንከባክበው አላምደውናል፡፡ እናት እና አባት የሚባል ነገር ምን እንደሆነ ያወቅነው እነሱ ጋ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ቀላልና ጥሩ ነው ማለት ባይቻልም እኛ እድለኞች ሆነን መልካም ቤተሰቦች ናቸው ያጋጠሙን፡፡
በትምህርት በኩል ምን ላይ ደረሽ አሁን?
12ኛ ክፍል ነኝ፡፡ ዘንድሮ ጨርሼ ኮሌጅ እገባለሁ። ነርስ መሆን ነው የምፈልገው፡፡ ለወደፊትም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ በዚህ ሙያ ህብረተሰቡን ማገልገል እፈልጋለሁ፡፡ እግዚአብሔር ለእኔ መልካም እድል የፈጠረው እዚህ ያሉ ወላጅ አልባዎችን እንድረዳ ፈልጎ ነው ብዬ ስለማምን፣ አሁን በምማርበት ት/ቤት ሎራ ከምትባል ጓደኛዬ ጋር የገቢ ማመንጫ ዘዴ ፈጥረን እርዳታ እየሰበሰብን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ 24 ልጆችን እንረዳለን፡፡ እነዚህ ህፃናት በማደጎ ያሉ ሳይሆን የዘላለም ምንጭ ድርጅት አማካኝነት በየቤቱ የሚረዱ ናቸው፡፡
እንዴት ነው እርዳታውን የምታሰባስቡት?
እኔ የራሴን ታሪክ ለተማሪዎች እነግራለሁ። ትምህርት ቤታችን ውስጥ 2000 ተማሪዎች አሉ። ለሁሉም በቪዲዮ ኮንፈረንስ መልክ የተለያዩ ፕሮግራሞች እያዘጋጀን ስለጉዳዩ እንናገራለን፡፡ በፌስ ቡክም “Wolove” የሚል ገፅ ከፍቼ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች በማዘጋጀት እርዳታ እናሰባስባለን፡፡ እስካሁን ወደ 18 ሺህ ዶላርና የተለያዩ ቁሳቁሶችን አሰባስበን ለኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እርዳታ አድርጌያለሁ፡፡ ለወደፊትም በዚሁ እቀጥላለሁ፡፡ ታሪኬን ስለማውቅና እግዚአብሄር እድል የሰጠኝ ይህን እንዳደርግ ስለሆነ በዚሁ እገፋበታለሁ፡፡ ለልጆቹ ቤት መከራያና የመማሪያ ገንዘብ እንሰጣለን፡፡ አሁን ለሁለት ዓመት የሚሆን በቂ ገንዘብ አለን፡፡ ለወደፊትም እርዳታ ማሰባሰቡን በተለያዩ መንገዶች እንቀጥላለን፡፡ ብዙዎች ይሄን ፕሮጀክት በጣም ስለወደዱት እየረዱን ይገኛሉ፡፡
ብዙ ጊዜ ጉዲፈቻ ተደርገው ወደ ውጪ የሚሄዱ ህፃናት በአሳዳጊዎቻቸው ተፅዕኖ ማንነታቸውን፣ ቋንቋቸውንና ባህላቸውን እንዲረሱ ይደረጋሉ ይባላ። አንቺ ደግሞ አማርኛ አቀላጥፈሽ ነው የምትናገሪው፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?
እኔና ወንድሜ አንድ ቤተሰብ ውስጥ ስለገባን ስለሆነ የገባነው በአማርኛ ነበር የምንነጋገረው። አሳዳጊዎቻችንም የራሳችንን ቋንቋ እንድንጠቀም ያበረታቱን ነበር፡፡ እንግሊዝኛ የግድ የትምህርት ቋንቋ ስለሆነ ነው ለመልመድ የታገልነው፡፡ አሳዳጊዎቻችን በእንግሊዝኛ እርስ በእርስ ስናወራ እንኳን ይቆጡን ነበር፡፡ ከሌሎች አሜሪካ ካሉ ኢትዮጵያውያን ጋር እያስተዋወቁን የሃገራችንን ባህልና ታሪክ ከነሱ እንድንረዳ ያደርጉናል። እናታችን በመንገድ ላይ ያገኘነውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሰላም እንድንልና እንድንተዋወቅ ታስገድደን ነበር፡፡
በጉዲፈቻ ተወስደው እዚያ ሃገር ችግር ላይ የወደቁ ህፃናት አልገጠሙሽም፡፡ እንዲህ ያሉ ታሪኮች ሲነገሩስ አልሰማሽም?
እኔ እዚህ ሃገር ስመጣ ነው ህፃናት ኢ-ሰብአዊ ተግባር ይፈፀምባቸዋል ነው የሚለውን የምሰማው። እዚያ እንዲህ ያለ ነገር አይሰማም፡፡ በአካባቢዬ ብቻ ከ20 በላይ የሚሆኑ የጉዲፈቻ ልጆችን አውቃለሁ፤ አንዳቸውም እንዲህ አይነት ችግር ገጥሞኛል ሲሉ አልሰማኋቸውም፡፡ አብዛኞቹ ፈረንጆች ከራሳቸውም ልጆች በላይ ለጉዲፈቻ ልጆቻቸው ስነልቦና ይጨነቃሉ። ምናልባት አንዳንድ ህፃናት ሁኔታውን ለመልመድ ይከብዳቸዋል፡፡ ወደ አሜሪካ በብዛት ጉዲፈቻ ተደርገው የሚመጡት የቻይናና የኮሪያ ህፃናት ናቸው፡፡ ሁላችንም እድለኞች ነን ብለን ነው የምናስበው፡፡
አሁን ወደ ሀገርሽ ስትመጪ ምን ዓይነት ስሜት ተፈጠረብሽ? ስለ ሀገርሽስ ምን ታስቢያለሽ?
እኔ ስመጣ ሁለተኛ ጊዜዬ ነው፡፡ መጀመሪያ የመጣሁ ጊዜ ልክ ከአውሮፕላን ስወርድ እንባ ተናንቆኝ አልቅሻለሁ፡፡ ሀገሬን በጣም እወዳታለሁ፡፡ እዚያ ሆነን ኢትዮጵያ ናፈቀን እንላለን፤ ነገር ግን ምን እንደናፈቀን አናውቅም፡፡ እዚህ ስንደርስ ግን ሁሉም ነገር ትዝ ይለናል። ስንመጣ ያሳደጉንን ዘመዶቻችንን እንጠይቃለን፡፡ በፊት የማስበው ስለራሴ ብቻ ነበር፡፡ ትንሽ ከፍ ካልኩ በኋላ ተመልሼ ስመጣ ግን ከራሴ ባሻገር ስለ ሌሎች ህፃናት ማሰብ እንዳለብኝ ተረዳሁ፡፡ ወደፊት ከኢትዮጵያ ሀገሬ መለየት አልፈልግም፡፡ በነርሲንግ ሙያ ብዙ ላበረክትላት እፈልጋለሁ፡፡ “የዘላለም ምንጭ” አሳዳጊዎቻችን ያስተማሩን ሁላችንም እንደ እህትና ወንድም ተሳስበን አብረን እንድናድግ በመሆኑ፣ በውስጣችን ይሄ መንፈስ አለ፡፡ አሁን አሜሪካ ያለነውም እዚህ ያሉትም በዚህ መንፈስ ነው የምንተሳሰበው፡፡ አሜሪካ ያለነው በየአመቱ በቀጠሮ እንገናኛለን፤ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀምም እንጠያየቃለን፡፡



አሣዳጊዎችህ ላንተ ምን አይነት ሰዎች ናቸው?
በጣም ጥሩዎች ናቸው፡፡ እድለኛ ነኝ፡፡ ብዙ ነገር እያደረጉልኝ ነው የሚያስተምሩኝ፡፡ በህይወቴ የምፈልገው ደረጃ እንድደርስ የጠየኳቸውን ድጋፍ ሁሉ ያደርጉልኛል፡፡ የነሱ የስጋ ልጆች አግብተው የራሳቸውን ኑሮ እየኖሩ ቢሆንም ሁሉም እንደ ታናሽ ወንድማቸው  ይንከባከቡኛል፤ ይጠይቁኛል፡፡
ስትወሰድ ምን ዓይነት ስሜት ነበር የተፈጠረብህ?
ደስ ብሎኝ ነበር፡፡ ምክንያቱም አዲስ ህይወት አዲስ አለም እንደማይ አስብ ነበር፡፡ የእናትና አባት ፍቅር ምን እንደሆነ ለማወቅም እጓጓ ነበር፡፡ ሁላችንም ወላጅ አልባዎች ቤተሰብ እንዲኖረን እንፈልጋለን፡፡ ሌሎች ልጆች ያላቸውን ነገር ሁሉ እንዲኖረን እንሻለን፡፡
አዲሶቹን አሣዳጊዎችህን ለመላመድ አልከበደህም?
ብዙም አልከበደኝም፡፡ እነሱ ጥሩ ፍቅርና እንክብካቤ ያደርጉልኝ ስለነበር እንደዚያ ዓይነት ችግር አልገጠመኝም፡፡ ነገር ግን እዚህ ያሉት ጓደኞቼ ይናፍቁኝ ነበር፡፡ በኋላ ግን እየለመድኩ ስመጣ፣ ትኩረቴን ሙሉ ለሙሉ ወደ ትምህርቴ ለማድረግ ችያለሁ፡፡ ቤተሰቦቼም እንደ ልጃቸው ነው የሚያዩኝ። እንደውም ትንሽም ያቀብጡኛል። ሞባይልና መኪና ከልጆቻቸው በፊት ነው ለኔ ገዝተው በስጦታ ያበረከቱልኝ፡፡
የወደፊት ህልምህ ምንድን ነው?
ኢንጅነሪንግ ወይም ኢንተርናሽናል የቢዝነስ ትምህርት ተምሬ ኢትዮጵያን ማገልገል እፈልጋለሁ። ሀገሬን መርዳት ከቻልኩ ለኔ ትልቁ ደስታዬ ነው። በአሜሪካውያን አሣዳጊዎች እያደግሁ አሜሪካ ብኖርም ኢትዮጵያዊ መሆኔን መቼም አልረሣውም። ድሃ ነበርኩ፤ እግዚአብሔር ከፍ አድርጐኛል፡፡ ድሃ የሆኑትንም እግዚአብሔር ከፍ እንዲያደርጋቸው እየፀለይኩ ብዙዎችን በማደጐ ወስጄ የመርዳት እቅድ አለኝ፡፡
እዚህ ከመጣህ በኋላ ዘመዶችህን አገኘህ?
ዘመዶቼ ናፍቀውኝ ስለነበር ሳገኛቸው በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ እነሱም በጣም ደስ ብሏቸዋል። እነሱን ሳያቸው ለካ አሜሪካ መሄዴ ከነሱ የተሻለ እንድኖር ነበር የሚል ስሜት ተሠምቶኛል፡፡ እግዚአብሔር ከፈቀደ እነሱንም የመርዳት ሃሳብ አለኝ፡፡
በጉዲፈቻ ተወስደው የማንነት ቀውስ የገጠማቸው ኢትዮጵያውያን ህፃናት የሉም?
የማንነት ቀውስ የሚገጥማቸው ልጆች፣ ችግሩ የሚመነጨው ከመሠረታቸው ነው ፡፡ ከዚህ ሲሄዱ ትንሽ ስለ ጉዲፈቻ ምንነት እንዲያውቁ ቢደረግ ችግሩ አይገጥማቸውም፡፡ ከኢትዮጵያ ሲሄዱ ቆዳቸው ተገፎ አሜሪካዊ የሚሆኑ የሚመስላቸው ከሆነ ግን የማንነት ቀውስ ይገጥማቸዋል፡፡ አሜሪካዊ ለመሆን መሞከር ራሱን የቻለ ስራ ነው፤ ኢትዮጵያዊ ለመሆን ግን ቀላል ነው፡፡
*       *        *
ሁለቱም የጉዲፈቻ ልጆች በዚህ ጉዳይ ይስማማሉ። “እኛ አሜሪካዊ እንሁን ብንልም አንችልም፤ ኢትዮጵያዊ ደማችን የት ሄዶ?...” ነገር ግን በጉዲፈቻ መሠጠታችን ለህይወታችን መልካም እድልን ከፍቶልናል፡፡ ሰዎች እንደሚያስቡት ሳይሆን የወላጅ ፍቅር አግኝተን ህይወታችን የተሟላ ሆኖልናል፡፡ ጉዲፈቻን ጨለማ ብቻ አድርገን አንየው” ብለዋል፡፡
ታዳጊዎቹን ከአሳዳጊዎች ጋር ያገናኘው “የዘላለም ምንጭ”፤ ዛሬ ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ ላይ የሚሠራ ሲሆን ወደ 1500 የሚሆኑ ችግረኛ ህፃናት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው እንዲረዱ እንዲሁም ኢትዮጵያውያን አሣዳጊዎች እንዲያገኙ እያደረገ መሆኑን ስራ አስኪያጁ አቶ ነሲቡ ከበደ ይገልፃሉ፡፡ በአሁን ሰአትም ድርጅቱ ራሱን አሳድጐ ሰበታ አካባቢ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ለመገንባት እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 

Read 3141 times