ከ2 ወራት በኋላ ካናዳ በምታዘጋጀው 7ኛው የሴቶች የዓለም ዋንጫ ኢትዮጵያዊቷ ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ በዋና ዳኝነት እንድትሳተፍ ተመረጠች። ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ ለሴቶች ዓለም ዋንጫው በዋናና በረዳት ዳኝነት ከ49 አገራት የተውጣጡ 73 ያህል ዳኞችን ሹመት ከሳምንት በፊት አሳውቋል፡፡ በዋና ዳኝነት ከተሾሙ 22 ዳኞች መካከል አፍሪካን የወከሉት ሦስት ዳኞች ብቻ ሲሆኑ ከኢትዮጵያዊቷ ሊድያ ሌሎቹ ከዛምቢያና ከካሜሮን የተመረጡት ናቸው፡፡
የጅማ ልጅ የሆነችው ሊድያ ወደ ስፖርቱ የገባችው በቅርጫት ኳስ ተጨዋችነት ነበር፡፡ ለኦሮምያ ምርጥ ቡድን ስትጫወት ቆይታ ከዚያም በክለብ ደረጃ ለኪራይ ቤቶች ተጫውታለች፡፡ በ1989 ዓ.ም ላይ ወደ እግር ኳስ ዳኝነት መግባቷን ለስፖርት አድማስ የገለፀችው ሊዲያ ታፈሰ፤ ታዋቂው የዳኝነት ኢንስትራክተር ሽፈራው እሸቱ በጅማ ከተማ በቅርጫት ኳስ ለተመለከቷቸው ሴቶች የመጀመርያውን የዳኝነት ኮርስ በመስጠት መነሻ እንደሆኑላት ታስታውሳለች፡፡ የመጀመርያውን የዳኝነት ስራም በ1992 ዓ.ም በተደረገ የታዳጊ ውድድሮች ላይ በስኬት አከናውናለች፡፡ ከዚያ በኋላ በርካታ የዳኝነት ኮርሶችን እየወሰደችና በተለያዩ ውድድሮች በዋና ዳኝነት እየተመደበች ለ15 አመታት አገልግላለች፡፡ ከ1993 እስከ 2005 ዓ.ም ባሉት የውድድር ዘመናት በኢትዮጵያ የክለብ ውድድሮች በዋና ዳኝነት ያገለገለችው ሊድያ፤ በስፖርት ቤተሰቡ በልባምነት በምትመራቸው ጨዋታዎች እና ውሳኔዎቿ አድናቆት አትርፋለች፡፡ በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ደረጃ በርካታ ትልልቅ ጨዋታዎችን በዋና ዳኝነት በመምራት ከፍተኛ ልምድ ማግኘቷን ለስፖርት አድማስ ስትገልፅም፤ ፌደሬሽን የፕሪሚዬር ሊግ ዳኞችን የመምረጫ መስፈርት ለሴቶች ዳኞች እንደ ወንዶች 150 ሜትርን በ30 ሰከንዶች መሮጥን በመመርያ ማውጣቱ እንድትቀጥል አላደረጋትም፡፡ ብዙዎቹ ሴት ዳኞች 150 ሜትርን በ35 ሰከንድ በአማካይ መሸፈን ይችላሉ ያለችው ሊድያ፤ እንደ ወንድ ዳኞች በ30 ሰከንዶች ፍጥነታቸውን ለሚያስመዘግቡ ሃላፊነቱ እንደሚሰጥ ተናግራለች፡፡
በፊፋ ኢንተርናሽናል ዳኝነት ተመዝግባ በመስራት 10 ዓመታትን ያሳለፈችው ሊድያ በአፍሪካ ውድድሮች ያካበተችው ልምድም አለ፡፡ በናሚቢያ በተደረገው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች እና ከዚያም በኢኳቶርያል ጊኒ በተካሄደው የአፍሪካ ሴቶች የእግር ኳስ ዋንጫ እስከ ግማሽ ፍፃሜ ውድድሮችን መምራት ችላለች፡፡ በቅርቡ በፖርቱጋል በፊፋ የተሰጠውን የ1 ሳምንት ስልጠና ተከታትላ ወደ አገሯ የተመለሰችው ሊድያ፤ ኢትዮጵያን በዓለም ዋንጫ ዋንጫ ለመወከል በመቻሏ ከፍተኛ ክብር እንደተሰማት ለስፖርት አድማስ ገልፃለች፡፡
ከወራት በፊት ኢኳቶሪያል ጊኒ ባስተናገደችው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል አልቢትር ባምላከ ተሰማ በዋና ዳኝነት ተመርጠው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት የኢትዮጵያ እግር ኳስ በፊፋ የተሾሙ ኢንተርናሽናል ዳኞች ቁጥር እያደገ መምጣቱን ለመገንዘብ ይቻላል። በትልልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች በዳኝነት መስራት በተለያዩ አህጉራዊና ዓለምአቀፍ ውድድሮች፣ ሥልጠናዎች ላይ ልምድ ለማግኘትና ለመካፈል የሚያስችል ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የኢንተርናሽናል ዳኞች ቁጥር በሁለቱም ፆታዎች 22 እንደደረሰ በፊፋ ድረገፅ ከቀረበው መረጃ ሲታወቅ 8ቱ ሴቶች ናቸው ፡፡ በፊፋ ፈቃድ ከተሰጣቸው 22 የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል አልቢተሮች መካከል 11 ያህሉ ዋና ዳኞች ሲሆኑ ሰባቱ ወንድ እንዲሁም አራት ደግሞ ሴት ዋና ዳኞች ናቸው፡፡ ከዚህ በታች በሁለቱም ፆታዎች በፊፋ ፈቃድ የተሰጣቸው የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ዳኞች ዝርዝር ቀርቧል፡፡
በወንዶች
ዋና ዳኞች የትውልድ ዘመን ኢንተርናሽናል ከጀምሮ
----------------------------------------------------------------------------------------
ሃይለየሱስ በለጠ ባዘዘው 1985 2012
ግርማ ፊጋ ዘካርያስ 1979 2015
የማነብርሃን ካሳሁን ብሩክ 1983 2015
ለማ ንጉሴ 1983 2014
በላይ ታደሰ 1986 2014
ባምላክ ተሰማ ወይሳ 1980 2009
ሃይለስላሴ አማኑኤል ወርቁ 1984 2015
ረዳት ዳኞች የትውልድ ዘመን ኢንተርናሽናል ከጀምሮ
------------------------------------------------------------
ግዛው በላቸው ትግሌ 1980 2012
ክንዴ ሙሴ 1976 2007
ተመስገን ሳሙኤል አታንጎ 1984 2013
ተባበል ታደሰ ሸዋንግዛው 1978 2012
ሃይለራጉኤል ወልዳይ 1978 2007
በላቸው ይታየው 1971 2004
ክንፈ ይልማ 1977 2011
-----------------------------------------------
በሴቶች
ዋና ዳኞች የትውልድ ዘመን ኢንተርናሽናል ከጀምሮ
አስማይኔ ፍቅረገነት አነሳሽ 1989 2015
ከተማ ኪዳኔ ጌራወርቅ 1986 2015
ፅጌ ሲሳይ 1975 2005
ሊድያ ታፈሰ 1980 2005
ረዳት ዳኞች የትውልድ ዘመን ኢንተርናሽናል ከጀምሮ
ትርሃስ ገብረዮሃንስ 1982 2007
ወይንሸት ካሳዬ አበራ 1986 2013
ወጋየሁ ዘውዱ ብዙአየሁ 1985 2013
Monday, 06 April 2015 09:53
ኢትዮጵያ በሊዲያ ታፈሰ ለዓለም ዋንጫን በቃች
Written by ግሩም ሠይፉ
Published in
ስፖርት አድማስ