Monday, 06 April 2015 08:26

እድሜ ለጣልያን! (ወግ)

Written by  ተአምር ተክለብርሃን
Rate this item
(5 votes)

ከቤን እፈራታለሁ። ከሰፈራችን ውስጥ ወንድ አሊያም ሴት መሆኑዋን ማጣራት አለብን ተብላ ክትትል የተደረገባት ብቸኛዋ ሴት ናት ። በምን እንደተጣላን ትዝ አይለኝም ግን ጥምድ አድርጋ ይዛኛለች ። ታዲያ ጠምዳ ብቻ አታበቃም። ማረስ ባትችልም መውጫ መግቢያዬን ጠብቃ ነገር ትፈልገኛለች። በዚህ ምክንያት ነው ሰቀቀን የወለደው  ፀሎት የጀመርኩት ። ጠዋት ከቤት ስወጣ፤
አባታችን ሆይ በሰማይ የምትኖር
                   .
                         .
                         .
የእለት ጉልበተኞቻችንን ያዝልን
እኛም በሌሎች ላይ ጉልበተኛ እንደማንሆን ሁሉ---
ብዬ ፀልዬ እወጣለሁ፡፡ ከትምህርት ቤት አልያም ከሄድኩበት ስመለስ ካላጋጠመችኝ “ተመስገን” ብዬ ማደር ጀመርኩ። እግረመንገዴንም ፀሎት ያለውን ሀይል አረጋገጥኩ። ከዚህ ልምዴ ተነስቼ የምመክራችሁ፤ሰፈር ውስጥ አላስገባ አላስወጣ የሚል የወንድ ወይም የሴት ጎረምሳ ካጋጠማችሁ ለፈጣሪ አሳልፋችሁ ስጡ። ይህ የሀገራችሁ ኢትዮጵያ ድምፅ ሳይሆን ከፍርሃት የመጣ የኔ የአለምትሁን ድምፅ ነው። ያ ሁሉ ታለፈ። ታጋይ ᎐᎐᎐᎐᎐ የሚለው ዘፈን ትዝ አለኝ።
በገዛ ሰፈሬ። በገዛ አብሮ አደጌ። ፆታዊ ባይባልም ትንኮሳ ደርሶብኛል፡፡ “ከመከም ከመከሜ” የሚለውን ዘፋኝ አስታወሳችሁት? ይሄ ዘፋኝ አፍንጫው ሰልካካ ነው፡፡ ሰልካካ ብቻ ሳይሆን   ከመርዘሙ የተነሳ ወደ ጎን ሁሉ መጣመም ጀምሯል፡፡ ይሄን ዘፋኝ ከሚተካ አፍንጫ ሰልካካ ጎረቤታችን ጋ ስናልፍ የኔ ጎረምሳ ቆማ ነበር።
“አንተ መኮረኒ አፍንጫ!” አለችው፤ሰልካካውን ጎረቤታችንን፡፡
“ሰላም ነው ከቤ” አላት ዘና ብሎ፡፡
“ዶዘር የሄደበት እኮ ነው የሚመስለው!” ደገመችው ሽሙጡን፡፡
እኔ አንጀቴ ሲያርር ፤ እሱ ጥርሱን ሸፍኖ ሲፍነከነክ አየሁት። “ምነው ተጣልታችኋል እንዴ?” አለኝ ያልሳቀ ለመምሰል እየታገለ። ድፍጥጥ የሚለው ቃል በሷ የተነሳ የቤት ስሜ ሁሉ ይመስለኝ ጀምሯል። እንግዲህ አፍንጫዬን ምን ላደርገው እችላለሁ፡፡ የሰፈራችን ጎረምሳ ድፍጥጥ እያለች መጥራት ከጀመረች በኋላ ሰው “ጥፍጥፍ” ሲለኝ የኔ ቆንጆ የተባልኩ ያህል ልቤ ትፈነጥዛለች፡፡
“አላስወጣ አላስገባ አለችኝ ባክህ” አልኩት፡፡
“ላስታርቃችሁ እንዴ?”
ቢያስታርቀን ከመሳቀቅ እንደምገላገል ባውቀውም በገዛ እጄ ቅኝ መያዙን አልፈለግሁትም። “አያስፈልግም” አልኩት፡፡ ‘እጅህን ስጥ አለኝ ፈረንጅ’  የሚለው ግጥም ነው ትዝ ያለኝ፡፡
 አንዳንዴ ከቤት ስወጣ ቢላዋ ይዤ ወጥቼ ልወጋት አስባለሁ። ግን ደግሞ የቤታችን ቢላ ትልቅ ስለሆነ ደብቆ ለመውጣትም ሆነ ለመያዝ አይመችም እንጂ ያን ያህል አማ`ራኝ ነበር። በወንድሜ ላስደበድባት እልና ለሷ አንሳ እንዳልባል ብዬ ብዙ ታገስኩ። ትዕግስት ፍራቻ ምናምን በሚለው ሳይሆን ተሟጥጦ በማለቁ ለወንድሜ ነገርኩት። ወንድሜ ታናሼ ቢሆንም የወንድ ትንሽ የለውም ይባል የለ። አደራውን ተቀብሎ የጀግንነት መዝሙር እየዘመረ ሄደና ወደ ጦርነት ከመግባቱ በፊት የሰላማዊ ድርድር ጥያቄ አቀረበላት፡፡ ይሄኔ  መንደርተኛው ሁሉ፤ “ከሷ ምላስ ይጠብቀን” ለሚላት እናቷ ነግራ ጉድ አደረገችኝ።
ከእናንተ ውስጥ ቀበሌያችሁ ከቤታችሁ አምስት ቤት ያህል ራቅ ብሎ የሚገኝ እስቲ እጃችሁን አውጡ? የነሱን ቤትም፣ ቀበሌ አጠገብ የሚኖሩ ሰዎችን ነገረኝነትም ትረዳላችሁ። እናቷ እዛ ጋ ቆማ እኛ ቤት በር ላይ ከሰፈር ልጆች ጋር ተሰብስበን እንደተቀመጥን ድምፅ ማጉያ ሳያስፈልጋት መናገር ጀመረች፤
“ስሚ አንቺ “ ስትል ከተሰበሰብነው መሀል ሴት የሆንን ሁሉ ዞርን ። ስሜን ስድብ በሚመስል ድምፀት ጠርታ፣ እኔን መሆኑን አረጋገጠችና  ቀጠለች፤
“አንቺ ያልተገረዝሽ--”
ሁሉም ዞር ብለው አዩኝ። እኔ ደግሞ እናቴን አስታወስኩ ። እናቴ በሷ ቤት መምከሯ ነው። ፊቴ ቀላ። አፍንጫዬ ከይዞታው በባሰ ሁኔታ ሰፋ። ሴትየዋ  እኩያ የሚመስሉ በእድሜ ተቀራራቢ ልጆች አሏት። ቤተሰብ መምሪያ ቤታቸው ባይገባ እኔ ልግባ ብላ ነው እናቴ ልጆቿን እንዳታስገርዝ የመከረቻት። ለምሳሌነት ደግሞ ባልጠፋ ልጅ እኔን ነበር የምትጠቅስላት፡፡ የእናቴን ምክር ለልጆቿ ልትጠቀምበት ሲገባት፣ እኔን ጓደኞቼ ፊት ለማዋረድ ተጠቀመችበት። ሆኖም እናቴ የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቀረት ከመንግስት የማበረታቻ ሽልማት ሳታገኝ ለሀገሯ የበኩሏን አስተዋጽፆ ማድረጓን ታሪክ አይዘነጋውም፡፡ “አንቺ ያልተገረዝሽ እንደሆን ልጄ ምን ታድርግሽ-- ሴት እኮ ናት”
ሴትየዋ ለሰፈራችን ልጆች የከቤን ሴት መሆንና የኔን አለመገረዝ ለማረጋገጥ እንደፈለገች አልጠፋኝም፡፡ ስናደድ ንግግር ስለሚጠፋብኝ  እንባዬ ማውራቱን ያገዘኝ እየመሰለው እንደጉድ ይፈሳል፡፡
“ቤትሽ እቃ ጨረሽ፤ እናትሽ ትቻልሽ ከኔ ልጅ ላይ ወረጂ”
“እናቴ መገረዙ የሚያስከትለው ነገር ቢኖር እቃ መስበር ብቻ ነው” ብላት ይሆን እንዴ? በፍጹም አትላትም። እቃ ስሰብር፤ ስለማትተኪ እኮ ነው እንዲህ የሚሰበርብሽ ትለኛለች እንጂ ባለመገረዝሽ ነው ብላኝ አታውቅም። እቺ ልጆቿን ላለማስገረዝ ያመጣቻት ሰበብ ናት ብዬ ተፅናናሁ። አስሬ “ልጄን ለቀቅ” የምትለኝ፣ ከቤ ወንድ መስላኝ ባለመገረዜ እያስቸገርኩዋት ያለሁ ለማስመሰል መሆኑን ስገነዘብ  አፈርኩ። ሴት መሆኔንም ሆነ አለመገረዜን ጠላሁት።
ከቤና ቤተሰቦቿን ቀላል ሰው አድርጋችሁ በመንበርከኬ እንዳትታዘቡኝ። እስቲ ጣሊያን ለሁለተኛ ጊዜ ኢትዮጽያ ውስጥ የተንበረከከው የት ነው? ብላችሁ ጠይቁ። የመጀመሪያው አድዋ ላይ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እናንተ እማታውቁት፣ እኔ ማውቀው እነ ከቤ ቤት ነው። ለረዥም አመታት ፆታዋን ስንጠራጠረው የነበረችው ከቤ አገባች። እሷ ብቻ አይደለችም፤ከቤታቸው ሶስት ሴት ልጆች በተከታታይ አገቡ ።
ለስራ ጉዳይ በጥዋቱ ትምህርት አቋርጠው ከሄዱበት አገር ተራ በተራ ሶስት ጣሊያን ማርከው ይዘው መጡ። በምን ቋንቋ ሊግባቡ ነው ብለን ተጨንቀን ነበር፡፡ የትምህርት ፖሊሲያችን ብዙም እንደማያወላዳ እናውቀዋለና! ፍቅር መግባባት ይፈልጋል። ጦርነት ግን ቋንቋ አይጠይቅም፡፡ እኛ የምናስበው እነ ከቤ ከጣልያን ጋ ትዳር እንደያዙ አይደለም፡፡ ጣሊያንን ማርከው ወደ አገር ውስጥ እንዳስገቡት ነው፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ ለመድገም ጣሊያንን ቅኝ እንደገዙት! እናም እድሜ ለጣልያን! ጣልያን እነከቤ ቤት ከገባ ወዲህ ነፃነቴን አወጅኩ።

Read 3019 times