Saturday, 28 March 2015 10:02

“ማሳቅ፣ ማሳዘን፣ ማሸበር”

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(1 Vote)

አንድም - ሦስትም
 
(የመጽሐፍ ዳሰሳ)
   ሀብታሙ ስዩም በቀድሞው “አዲስ ጉዳይ” መጽሔት ላይ ሲተነፍሳቸው የነበሩትን ፖለቲካ ዘመም ግሩምሩምታዎች በ176 ገጽ ተምኖ፣ የድርሳን ግርማን አላብሶ፣ ለአንባቢ ካቀረበ ከረምረም አለ። የጥበብ ስራውን ገና በጠዋቱ ለተቀጨችው ለ“አዲስ ጉዳይ” መጽሔት እንደ ዝክር የሚወስዱለት ባይታጡም በጉያው የተሰበሰቡትን አፍላ ታሪኮች መልሶ ለመደባበስ ለፈቀደ አንባቢ ግን ግለታቸው አዲስነትን፣ የእስትንፋሳቸው ሙቀት ትኩስነትን እንደሚያውጁ አያጣውም፡፡ ደግሞም በመጽሔቱ ያልተካተቱ አዳዲስ ሥራዎች እንደ አጃቢ እዚያም እዚህም ስለተሰለፉ ታማኝ የመጽሔቷ አንባቢ ለነበረም ቢኾን ሌላ የንባብ ጉልበት እንደሚሆኑት ይታመናል፡፡ ፖለቲካን በረሃ ሳይወርድ በመጽሐፍ ገጾች ውስጥ ብቻ በስላቅ መልክ ማጣጣም ለመረጠ፣ የሀብታሙ ብዙዎቹ ትርክቶች የሚስማሙት ይመስለኛል፡፡ መጽሐፉ ላይ የተካተቱት ብዙዎቹ ታሪኮች አንባቢን በስሜት ለማወበራየት የማይሰንፉ፣ ደመ-ግቡ የምናብ ፍሬዎች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡
ጥልቅ ዳሰሳ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለመልዕክት የሚጨነቁ የሽፋን ምስሎች አልፎ አልፎም ቢሆን ማየታችን ተስፋ ነው፡፡ የሀብታሙ “ማሳቅ፣ ማሳዘን ማሸበር” በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው፡፡ መጽሐፉ አዲስ የተመረቀ የሰፈር ጥርጊያ መንገድ ይመስላል። በኮብል ስቶን በተዥጎረጎረ ገጽታው ላይ እንደ ኩል በኳሉት ሶስት አንጓ ምልክቶች እየተዘጋ የአንባቢን አምሮት ይለኩሳል፡፡ የቀድሞው ኢቴቪ “ሎጎ”፣ የዘመን ጋዜጣን የስያሜ ቁራጭ እንዲሁም አንድ የወታደር ጫማ በመጽሐፉ ሽፋን ላይ ጎልተው ይታያሉ፡፡ እንደ አንባቢ ሳንወድ በግድ የነዚህን ምልክቶች አንድነትና ልዩነት ለማሰላሰል እንገደዳለን። በርዕስነት የተቀመጡትን ሦስት አንኳር ቃላት (ማሳቅ፣ ማሳዘን፣ ማሸበር) ከነዚህ ሦስት ጉልህ ምልክቶች ጋር እያጋባን፣ ደግሞም እያፋታን እንብሰለሰላለን። የሦስትነትና አንድነቱን ቋጠሮ ለመፍታት በምናደርገው መውተርተር የመጽሐፍ ሽፋኑ ላይ ሳናስበው ጊዜ እናጠፋለን፡፡ የመጽሐፉን አንድ ቅጠል የምንገልጠውም ለዚህ አንኳር መጠይቅ ምላሽ ፍለጋ ነው፡፡
ከሃያዎቹ አጫጭር ታሪኮች ውስጥ “መጽሐፍ እና ሥጋ” የተሰኘው ቀዳሚ ተረክ የዋርካውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ሌሎች ታሪኮች ዋርካውን የተጠጉ ልምላሜዎች አድርገን ልንወስዳቸው እንችላለን። በእርግጥ ልምላሜው ሌጣውን አይደለም፡፡ አብሮት የሚፈካ አበባ፣ የሚጎመራ ፍሬ እዚህም እዚያም ይኖራል፡፡ ሆኖም ዋርካው ላይ በቁመናም፣ በቅርንጫፉም፣ በፍሬም፣ በልምላሜም የሚደርስ ተረክ አላገኘሁም፡፡
“መጽሐፍ እና ሥጋ” የሥጋ ጠኔ ከመንፈስ ጠኔ ጋር የሚሽቀዳደሙበት አውደ ርዕይ ተደርጎ ነው በደራሲው የተሳለልን፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ አንድ መጽሐፍ መደብር በተከፈተች ሌላ ሥጋ መደብር ጋር የሚደረግን ምናባዊ ሙግት እንቃኛለን፡፡ የአለማየሁ ሥጋ ቤትን የሚታደሙት ደንበኞች ኩታገጠም የሆነችውን መጻሕፍት ቤት ቀስ በቀስ ከእነመፈጠሯ  ሲዘነጓት እናያለን፡፡ ታሪኳ የአንባቢን ቁጥር መመናመን ብቻ ሳይሆን ዘመኑ ለስጋ እንጂ ለነፍስ ምግብ ብዙም የማይጨነቁበት እንደሆነ ታመለክታለች፡፡ ይህቺን ታሪክ የደራሲው የሀብታሙ ስዩም የፈጠራ ማማ አድርጌ እወስዳታለሁ፡፡ ገጽ 7 ላይ ከሰፈረው በጥቂቱ፡-
“… (ጎረቤቴ) አለማየሁ መጽሐፍ ለመግዛት የመጡ ደንበኞቹን መደብ ሥጋ ማስገዛት የሚያስችል መተት ሳያስቀብር አልቀረም፡፡ ሥጋ ቤቱ በተከፈተ በመጀመሪያው ቀን ወትሮ በሳምንት አራት ውድ መጻሕፍትን የሚገዙኝ ሰዎች ከሱ ሁለት መደብ ሽኮና ገዙና ከኔ ሁለት የተረት መጻሕፍትን ብቻ ገዝተው ሄዱ፡፡ በሁለተኛው ቀን እኒሁ ደንበኞቼ በሱ እልፍኝ ተሰገሰጉ፤ ለእኔ ግን የእግዜር ሰላምታ እንኳ ነፈጉኝ…፡፡”
የሥጋ ቤቱ እና የመጻሕፍት ቤቱ ተቃርኖ የሞት እና ሕይወት ነው፡፡ በላተኛው ስጋ ወይም ሞት ይላል፤ አንባቢው ተሽቀዳድሞ በሚያመነዥጋቸው መጻሕፍት የመብል ፍላጎቱን ይቆልፋል፡፡ አንዱ በአንዱ መቃብር ላይ  ነው የተቀለሰው፡፡ ኋላ ላይ ሥጋ አይሎ መንፈስን እንዴት አድርጎ አሟሙቶ እንደሚገድል በመጻሕፍት ቤቷ ውልደት እና ሞት እንመለከታለን፡፡ ነገሩ እየከፋ ሄዶ የመጽሐፍቱ ገጾች የሥጋ መጠቅለያ እየሆኑ ነፍስ እየተበደለ እንዴት እንደሚሄድ በዚህ ግሩም ታሪክ ጭብጥ ውስጥ ተካትቷል፡፡
ደራሲው “መጽሐፍና ሥጋ” የተሰኘችዋን ታሪክ ለመጽሐፍ መግቢያ መጠቀሙ እንደ ግሩም “አፕታይዘር” አገልግሎታል፡፡ ይቺን ታሪክ አንብበን ከደራሲው ብዙ ሳቅና ስላቅ መጠበቃችን ግድ ነው፡፡ በዚህ የስሜት ከፍታ ሆነን ነው “አባቴ ሲመረቅ፣ እኔ ስረገም” የሚል ታሪክ የምናገኘው፡፡
በርግጥ ከማንበብ የመናጠቡ ልማድም ሆነ የከሸፈ ጥቁር ቆብ ደፊነት በአንድ ማሕፀን የተኙ መንትያዎች ናቸው፡፡ ደራሲው ኮሌጅ መበጠሱን፣ ቆብ መድፋቱን ከሥራ አጥነት እና ከእንዝላልነት ጋር ማጎዳኘትን ቢመርጥም ክስረቱ ሁለንተናዊ ስለሆነ ይሄኛውም ውድቀት ሌላ መገለጫው ነው፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ ድሮ ዲፕሎማ መድፋት ዛሬ ማስተርስ ከመድፋት የበለጠ ክብር እንደነበረው ደራሲው የአባቱን ዲፕሎማና የሱን ማስተርስ ተምሳሌት አድርጎ በቁጭት ይነግረናል፡፡
በሀብታሙ መፅሐፍ ውስጥ የታሪክ አደራደሩ ተስማምቶኛል፡፡ ሆን ተብሎ ይሁን በአጋጣሚ እንጃ እንጂ 20 ታሪኮች የተቀመጡበት ፍሰት ስሜት የሚሰጥ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ የፊተኞቹ ታሪኮቹ መጋቢ ናቸው፡፡ በአመዛኙ አንዱ ታሪክ የሌላው ውጤት ነው፡፡ ለምሳሌ በመጀመርያው ታሪክ ይህ ትውልድ ከመጽሐፉ ይልቅ ሙዳ ሥጋ አብዝቶ መውደዱን የሚናገር ሆኖ፣ በሁለተኛው ታሪክ ደግሞ የዲግሪና ማስተርስ ቆቦች በሥጋ በተለበጡ “ቀፎ” ጭንቅላቶች ላይ የተደፉ የሸክላ አክሊሎች እንደሆኑ የሚነግረን ታሪክ ይከተላል። ይህም “አባቴ ሲመረቅ፣ እኔ ስረገም” በሚል ርዕስ ስር የተቀመጠ ነው፡፡ ሁለቱ ታሪኮች  በርእስም በይዘትም የሚያገናኛቸው ነገር ባይኖርም በጭብጥ ደረጃ ግን መንስኤና ውጤት ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ነገሩ በዚህ ብቻ አያበቃም። በሦስተኛው ታሪክ (“ኳስና ፖለቲካ” ይሰኛል) መጽሐፍ የማይሚገልጠው ትውልድ የልብ ልብ የሰጣቸው ፖለቲከኞች ቅሪላ ሊያለፉ ከኮምቦሎጆ ወርደው እናያለን፡፡ በርግጥም በሥጋ የሰባ ሰውነት ካምቦሎጆ መውረዱ የሚጠበቅ ነው፡፡
“ኳስ እና ፖለቲካ” ብሎ በሰየመው  በዚህ ግሩም ተረክ፣ ደራሲው ከንጉሡ ጀምሮ በነበሩ ሦስት መንግስታት የእግር ኳስ ቀጥታ ስርጭት ምን ይመስል እንደነበር የሚነግረን  ይምሰል እንጂ ማውጠንጠኛው አሁንም ጭልጥ ያለ ፖለቲካዊ ስላቅ ነው፡፡ የእግር ኳስ ጨዋታ በቀጥታ በሬዲዮ የምንኮመኩም ቢመስለንም ተለውሶ ወደ ጆሯችን የሚንጠፈጠፈው ግን የፖለቲካ ጠብታ ነው፡፡ በርግጥ ጽሑፉ ያስቃልም፣ ያሸብራልም ያሳዝናልም፡፡ ይኸ ተረክ በፖለቲካዊ መልዕክቱም ሆነ ፈገግታን በማጫር የተሳካለት ነው ማለት ይቻላል። እዚህ ታሪክ ላይ ስንደርስ ነው ታዲያ በዐይናችን ማንበባችንን ገታ አድርገን ጆሯችንን የምናነቃው። የየዘመኑ የቅሪላ ለፋፊ (“ኮሜንታተር”) ድምጸት ለመለየት ጆሯችን አቅም ሲከዳው ደግሞ የምናባችንን ጉልበት ለመጠቀም እንታትራለን፡፡ ቁርበት ቁርበት ከሚለው ፖለቲካዊ ልፊያ የምንቃርመው ፈገግ ብሎ አፍታም ሳያቆዩ ፊትን ማደምን ነው፡፡ “ማሳቅ ማሳዘኑ” ስጋ ለብሶ ከፊት ለፊታችን ገጭ የሚለው ታዲያ ይሄኔ ነው፡፡ ገጽ 22 ላይ የሰፈረውን በምሳሌነት እናንሳ፡-
ጨዋታው የሚካሄድበት ዘመን - ዘመነ ጃንሆይ
ጨዋታው የተካሄደበት ቦታ - ጃንሜዳ
ጨወታውን የሚያንበለብለው ጋዜጠኛ - የጃንሆይ አሽከር
በመላው ጠቅላይ ግዛቶች የምትኖሩ በጃንሆይ መልካም ፈቃድ ራዲዮ የተሰኘውን ታምር ተጠግታችሁ የጃንሆይ ቡድን የሚያደርገውን ይህንን ጨዋታ ለማድመጥ ያቆበቆባችሁ የጃንሆይ አሽከሮችና ሌሎች … እንደምን አመሻችሁ፡፡ የጎዣም አድማጮች “እግዜር ይመስገን!” የማትሉ ጥጋብ ነው? ዋ! ጭስ እንጂ ጭሰኛ ማምለጫ ያለው መስሎሻል፡፡ በላይ ዘለቀ ለምን ተሰቀለ ብላችሁ ነው እንዲህ ምትጀበረሩ?
ለማንኛውም የሁለቱን ቡድኖች አሰላለፍ ከዚህ እንደሚከተለው እንገልጻለን፡፡
1ኛ. የግራዝማች ሞገሴ ልጅ ዳኛቸው ሞገሴ
2ኛ. የብላታ ዳርጌ የአጎት ልጅ አስታት ቢልልኝ
3ኛ. የነጋድራስ ባንት ይርጉ ውሽማ ዘበነ አስተስ
ከላይ የዘረዘርኳቸው ሀገር የመሰከረላቸው የጨዋና የመኳንንት ልጆች ሲኾኑ የሌሎችን ግን የመጫኛ ነካሽና የሸማኔ ልጆች እንደመሆናቸው ቢጠሩም ባይጠሩም ለውጥ ስለሌለው በቀጥታ ወደ ማላጋሲ ቡድን አሰላለፍ በንጉሡ ፈቃድ እሄዳለሁ፡
ደራሲው በድቡልቡሏ ኳስ አሻግሮ የሚለጋቸው ፖለቲካዊ ስላቆች ግሩም ፖለቲካዊ ጎሎችን የሚያስቆጥርባቸው ናቸው፡፡ የሦስቱ መንግስታት የካሞቡሎጆ ልፊያ ማሳደጊያ ባዶ ለባዶ ውጤት ነው፤ ምንምነት፡፡ በብዙዎቹ ተከታይ ታሪኮች የደራሲውን ለቀቅ ያለ አጻጻፍ እንታዘባለን፡፡ ምናብ እና አፍላ ፍቅር በሚፈጥሩት ሽኩቻ ውስጣችን አብዝቶ ይፈግጋል። በአጫጭር ዐረፍተነገሮች ውስጥ የሚፈነዳውን ጭብጥ እናደንቅለታለን፡፡ ለምሳሌ “83ን መጠበቅ” ብሎ በሰየመው ተረክ  የመጀመርያ አንቀጽ ደራሲው  በከተማ ድህነት ላይ እንዲህ ይቀኛል፡-
“ሀብታሞች አንበሳ አውቶብስን የድሃ መጋዘን ይሉታል፡፡ ድሆች “የጭቁኖች ባቡር” እያሉ ያቆላምጡታል፡፡ እኔ በበኩሌ “ክርስቶስ” እለዋለሁ፡፡ መምጫው አይታወቅም፡፡ ጠባቂዎቹ  ግን ብዙ ነን።” (ገጽ-32)
ብዙ አንቀጾች ላይ ደራሲው ቀልድ ሲመዠረጥ አይሰስትም፡፡ ምናባዊ ምልልሱ ሲናኝ አይጎረብጥም፡፡ ሁሉም ለስለስ ብሎ ከአንጀት ይደርሳል፡፡
እንደ ስንቅ የያዝነው ፈገግታ ሲሟጠጥብን ተዋከቦ ፊት ለፊታችን የሚደነቀረው “ባለቆቡ ወጣት” የተሰኘው ንኡስ ታሪክ ነው፡፡ “ባለቆቡ ወጣት” የቆመበት ፌርማታ ለአእምሮ ሰላም የሚሰጥ ስፍራ አይደለም፡፡ አጓጉል ትካዜን የሚያጭር፣ የድብርት ቆሌን የሚያስነሳ፣ የሐዘን ማቅን እንደ ጃኖ የሚያከናንብ ኬላ ነው፡፡ እዚህ ላይ ማሸበር ከቃል ጨዋታ አልፎ የውስጥ ስሜትን ለመደቆስ ይሰናዳል፡፡ ከፍቅር ጭወውቱ አደባባይ ተስተጓጉለን ጫፉ ወደማይታይ ሸለቆ ውስጥ እንወረወራለን፡፡ ገጽ 130 ላይ ከሰፈረው በጥቂቱ፡-
“…አምባገነንነት ከመጠን በላይ ከመመለክ ፍላጎት የመጣ በሽታ ነው፡፡ ጨካኝነት ከመጠን በላይ ከመፍራት ፍላጎት የመነጨ ደዌ ነው፡፡ ውሸታምነት ከመጠን በላይ ከመሞገስ ፍላጎት የመነጨ ወረርሽኝ ነው፡፡ በተመሳሳይ መጨቆን ከመጠን በላይ ዝም የማለት ውጤት ነው፡፡ መረገጥ ከመጠን በላይ የመፍራት ዳርቻ ነው፡፡ መበደል ከመጠን በላይ የመለጎም መጨረሻ ነው፡፡ የሰው ልጆች ልካቸውን ቢያውቁ አሊያም ልካቸውን እንዲያውቁ ቢደረግ ዓለም ያየቻቸው እጅግ አስከፊ ምዕራፎች ቀድሞውኑ አይታሰቡም ነበር፡፡” (ገጽ 130)
የደራሲው “ኤርትራዊው” ገጸ ባህሪ ተስፋዚጊ ይባላል፡፡ ተስፋዚጊ የመወለድ ቋንቋነትን ከቃል ባለፈ በተግባር በተከፈለ የሕይወት መስዋዕትነት ያስተምረናል፡፡ ተስፋዚጊ እንደ ረመጥ የሚፋጅ የሃገር ፍቅርን ገዢዎች ሚዛን ሰፍረው፣ ደረጃ አውጥተው የሚያድሉት ራሽን አይደለም ይለናል፡፡ ለተስፋዚጊ ታላቅነት እማኝ ከሚሆኑ አንቀጾች መካከል በገጽ 138 ላይ የሚገኘውን እንመልከት፡-
“የአያቴ የቅድመ አያቴ ሀገር አሁንም የምኖርበት ነው፡፡ ወሰኑን የጠገቡ አንዴ ሲያሳጥሩት፣ አንዴ ሲለጥጡት፣ የሚለጠጥም ኾነ የሚጠብ ማንነት የለኝም፡፡ የጃንሆይ ሕፃን፣ የደርግ ጎልማሳ ነበርኩ፡፡ ኤርትራዊያን ስንት ግፍ እንደደረሰባቸው አውቃለሁ። ይሄ ግፍ የደረሰው ኤርትራዊ ስለኾኑ አልነበረም። በጨቋኝ መሪ ስር ከነበሩ የታሪክ ተጋሪዎች ውስጥ ስለነበሩ እንጂ፡፡ ኤርትራ ውስጥ ካለቀው ወጣት ያልተናነሰ ጐንደር ቀብራለች፡፡ ሰው በእግዜር ደንብ ማረኝ ተብሎ እስኪለመን ድረስ፡፡ አብዮት የበላው የአሰብን ወጣት ብቻ አልነበረም፡፡ አብዮት ሁሉን በልታለች፤ አብዮት ሆዳም ናት፡፡” የተስፋዝጊ ነፍስ ወሰን፣ አጥር ለመሻገር ትቃትታለች፡፡ በጣምራ ዜግነት መካከል እንድትጓጉጥ ወጀቡ፣ ውዥንብሩ ቢያጥበረብራትም የማኅተቧን ክር እንዳጠበቀች እስከ ወዲያኛው ታሸልባለች፡፡
መጽሐፉን ያሳሱት ገጾች
ሀብታሙ ስዩም “ተስፋ የሚጣልበት ቀልድ ፈጣሪ ነው” ብለን ለመደምደም አራት ነጥቦችን ስናፈላልግ ባልገመትነውና ባልጠበቅነው ሁኔታ ራሱ አውጥቶ ከሰቀለን የሳቅ ማማ ገፍትሮ የሚጥለን ደራሲ ነው። ፖለቲካዊ ስላቅ (Political satire) አሳክቶ መጻፍ፣ ጽፎም ማሳቅ፣ አስቆም መራር መልዕክት ማስተላለፍ ጥቂቶች ብቻ የሚታደሉት ትልቅ ጥበብ ነው፡፡ ሀብታሙ ስዩም በዚህ ጥበብ ደጅ ላይ ሆኖ የሚያንኳኳ ጀማሪ ፀሐፊ ይመስላል፡፡ ሆኖም በሩ እንዳይከፈትለት ያደረጉት ብረት መዝጊያዎችን መጠቋቆም በጐን ከሚመኝ ሀያሲ የሚጠበቅ ነው። አንዱ የደራሲው ማነቆ በጽሑፎቹ ውስጥ ጊዜና ሁኔታን ያላገናዘቡ መናኛ ቧልቶችን መርጨቱ ነው። ቧልቶቹ በግድ የተፈጠሩ ስለሆኑ አይወሃዱንም፡፡ እንዲያውም ይጐረብጡናል፡፡ የሳቅና የምቾት ጉዟችንን የፒስታ መንገድ ያደርጉብናል። ሄዶ ሄዶ መንገጫገጭ!
በርግጥም ደራሲው ውብ ታሪኮችን አጥምዶ በሳቅ ሊያፈነዳን ልባችንን ሰቅሎ ሲያበቃ በነዚህ መናኛ ቧልቶች ምክንያት ሳቅ አምካኝ ሆኖብን ያስቸግረናል። ለአብነት የሚሆኑ ጥቂት አረፍተ ነገሮችን ልጥቀስ፡-
“መጽሐፍና ሥጋ” በሚለው ታሪክ (ገጽ 9) ላይ የሥጋ ነጋዴውን አለማየሁን ሸንቋጭነትና የንግግር ግብረ መልስ በቀልድ መልክ ለመግለጽ ደራሲው እንዲህ ይላል፡-
“የአለማየሁ መልስ ከአለማየሁ ቴዎድሮስ አጽም አለመመለስ በላይ ያበሳጫል”
(ደራሲው አለማየሁ የሚለውን ስም በግድ ከአፄ ቴዎድሮስ ልጅ አለማየሁ ጋር አዛምዶ ሊያስቅን በከንቱ እንግሊዝ አገር መዳከሩ እኛ አንባቢዎቹን ያበሳጫል፡፡)
በገጽ 41 ላይ፡ “ታጋዩን በጥንቃቄ አስተዋልኩት፡፡ እንዴ…እንዴ! ይሄ የማየው ዋልተንጉስ አይደል እንዴ። አይ ዋልተ ንጉስ! ዋልተ ንጉስ ማለት በስልጠና ላይ እያለን ደንግጦ ሱዳን ከገባ በኋላ ለዓመታት ያላየነው ጓድ ነው፡፡ እሱን ብሎ ጓድ፤ ጉድ ብለው ይሻለኝ ነበር”
(“ጓድ” እና “ጉድ” የሚሉ ቃላትን በማገናኘት ሳቅ ለመፍጠር የተሞከረ፣ ነገር ግን ያልተሳካ ጥረት እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ሁለት ተመሳሳይ ቃላትን አገናኝቶ ሳቅ መፍጠር ሁለት ባልጩት ድንጋዮችን አጋጭቶ እሳት የመፍጠር ያህል ቀላል እንዳልሆነ ደራሲው ብዙም የተረዳው አይመስልም፡፡)
ምናልባት ደራሲው ይህን ዘዬ እጅግ በተሳካ ሁኔታና በተገቢው ቦታ መጠቀም አለመጠቀሙ ለራሱ እምብዛምም ላይታወቀው ይችል ይሆናል። እንዲያ ከሆነም ተመሳሳይ ቃላት በማጋጨት ሳቅ የመፍጠር አቅሙን ምን ያህል እንደተሳካለት ለወዳጅ እያስነበበ ቢያስመሰክር ቀሪ አንባቢን ከሰቀቀን መታደግ ይቻላል ባይ ነኝ፡፡ በርግጥ ሀብታሙ በዚህ ቃላትን አመሳስሎ በማጋጨት ሳቅን የመፍጠሪያ ዘዴ ተጠቅሞ ያሳካው ምንም አረፍተነገር የለም አይባልም፡፡ ሆኖም ከተሳኩለት ይልቅ ያልተሳኩለት ይበዛሉ፡፡ ደግሞም በኮሜዲ ዘውግ ከሺ ሳቅ ይልቅ አንድ የሳቅ ምክነት ጐልታ መታየቷ እሙን ነው፡፡
በነገራችሁ ላይ ቃላት እያጣመሙ ቀልድ የመፍጠር ስልት በምዕራቡ ዓለም malapropism እየተባለ ነው የሚጠራው፡፡ ይህ ዘዬ እንደ ቀልድ ዘውግ የተዋወቀው በ1775 በሪቻርድ ብሪንስሌይ የኮሜዲ ሥራ አማካኝነት ሲሆን ምዕራባዊያኑ ገና ድሮ ሳቃቸውን አንጠፍጥፈው የጨረሱበት የአቀላለድ ዘዴ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ወቅታዊነት ችግር
አንዳንድ ታሪኮች የወቅታዊነት ችግር ይስተዋልባቸዋል፡፡ ይህ ችግር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከጋዜጣና ከመጽሔት ወደ መጽሐፍ በሚመለሱ ብዙ የጥበብ ሥራዎች ላይ የማስተውለው ድክመት ነው። በደራሲ ሀብታሙ ስዩም ሥራ ውስጥ ለዚህ እንደ አብነት የምወስደው “አሮጌ፣ አረቄ፣ አዲስ ዓመት” የሚለውን ታሪክ ነው፡፡ ታሪኩ ስለ አዲስ ዓመት ዋዜማ ነው የሚያወራው፡፡ ታሪኩ በተጻፈበት ወቅት የነበሩ አሁን ግን ስሜት የማይሰጡ ጉዳዮችን ደጋግሞ ያነሳል፡፡ “አፈር ስሆን ወደ ሳኡዲ እንዝመት” የሚለው ፅሁፍም እህቶቻችን ከሳኡዲ በ“ግፍ” በተባረሩበት ወቅት የተፃፈ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡  ተመሳሳይ ችግር ያስተዋልኩበት “ማንዴላ ሞቷልና እንደንስ” የሚለው ጽሑፍ ነው፤ ይህም የጊዜ ልኬት አፈር ድሜ ያስጋጠው ጽሑፍ ሆኗል፡፡ ሀብታሙ ሥራዎቹን ጥሩ አርታኢ ቢከረክማቸው ኖሮ ችምችም ያሉ ተክሎች በሆኑለት ነበር፡፡ እንዲህ ጊዜ ያጠወለጋቸው ከአረም ያልተናነሱ ታሪኮችም ተቆርጠው መውጣታቸው አይቀርም ነበር ስል ተመኘሁ፡፡
ፋታሊዝም /ጨለምተኝነት/
የሀብታሙ ስዩም “ማሳቅ፣ ማሳዘን፣ ማሸበር” የገዢውን ፓርቲ ጉድፍ በአጉሊ መነጽር የሚያሳይ ፖለቲካዊና ልቦለዳዊ የሥነ - ጽሑፍ ሥራ ነው ብዬ ማጠቃለል እችላለሁ፡፡ ይህ የጥበብ ሥራ መንግሥትን የማይተቸው “ማውጫ” በሚለው ክፍል ላይ ብቻ ይመስለኛል፡፡ ደራሲው ወዳጆቹን እጅ በሚነሳበት የምስጋና ገጹ እንኳን የመንግሥትን ጨቋኝነት ጠቆም ለማድረግ የሚታትር ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ በዚህም የተነሳ ከመግቢያው እስከ መውጪያው የናኘው ታሪክ ተስፋ የነጠፈበት ጭጋጋማ ከባቢ አድርጐታል። ብንስቅም ተስፋን አናይም፡፡ በእርግጥ ደራሲው ወደ ሌሎች ዘውጐች ዘው ብሎ ሌሎች ምልከታዎችን በማቀበል ጭጋጉን በተወሰነ ደረጃ እየገፈፈ፣ በስሜት ሽቅብ ወደ ላይ የመሰቀላችንን መጠን ማሳደግ ይቻለው ነበር፡፡ “መጽሐፍ እና ሥጋ” እንዲሁም “የዘገየው ዓላሚ”ን በከወነበት እጁ ሌሎች ተመሳሳይ ማኅበራዊ ጦሶችን በሳቅ ክዳን ቆርቆሮ ቢቀልስልን ምንኛ ባፍነከነከን ነበር፡፡
ክረት የተጠናወተውን ውጥንቁጥን የፖለቲካ ምህዳር በቀልድ ለመገዳደር መሞከር ትልቅ ወኔን ይጠይቃል፡፡ በእዚህ ረገድ ደራሲ ሃብታሙ ስዩም ብዙ ርቀት ተጉዞ ፈር ቀዶልናል፡፡ የማኅበረሰብን ህመም፣ የሕዝብን የተዳፈነ እሮሮ በቧልትና ስላቅ ውስጥ አሾልኮ ለዚያው ማኅበረሰብ ማቀበል መታደል ነው፡፡
በአጠቃላይ ደራሲው ይህ ሁለተኛ ሥራው እንደመሆኑ፣ ከዕድሜ ጋር ስክነትን፣ ከጊዜ ጋር ብስለትንና ጥበብን የመታደል እድል እንደሚኖረው በመገንዘብ፣ በርግጥም ተስፋ የሚጣልበት ወጣት እንደሆነ ለመመስከር ጉልበት እናገኛለን፡፡

Read 3025 times