Saturday, 28 March 2015 09:17

የምሁር ገዳም ጉዞ ማስታወሻዬ

Written by  ነቢይ መኮንን -
Rate this item
(6 votes)

ካለፈው የቀጠለ

“ተፈጥሮና በገና ባይኖሩ ፆም ምን ይውጠው ነበር?” ያሰኘኝ ገዳም

    ከእግር አጠባው ሥነ ሥርዓት በኋላ ለጸሎት ወደ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን መሄድ ነው ፕሮግራሙ፡፡ ቤተክርስቲያኑ ከገዳሙ ሆነው ሲያዩት አንገቱን አስግጎ በማዕረግ ቆሞ በእጅ የሚነካ ይመስላል፡፡ ሲሄዱት ግን ቁልቁለቱና ዳገቱ መከራ ያሳያል፡፡ ያለመከራ ረድኤቱን ማግኘት የማይቻል ይመስላል፡፡ የባለቤቴን የወገብ በሽታዋን የቀሰቀሰ ቀጥ ያለ ዳገት አለው፡፡ አንድ ቦታ አረፍ ስንል  ባጠገባችን ያለፈ ተጓዥ ሁሉ “አይዞሽ ትንሽ ናት የቀረችሽ” እያላት ያልፋል፡፡ አንዲት ሩህሩህ ልጅ ወደ ጫካው ሄዳ አንድ ምርኩዝ ብጤ አምጥታ ሰጠቻትና መንገድ ቀጠልን፡፡ ዕውነትም ብዙም ሳንሄድ ቤተክርስቲያኑ ጋ ደረስን፡፡ ከተሳለምን በኋላ የቆሎ ተማሪዎች እንዴት እንደሚማሩ ወደ ሚታይበት ቦታ ሄድን፡፡ ሁለት መምህራን መካከል ላይ አሉ፡፡ የቆሎ ተማሪዎቹ መምህሩ እየጠቆሟቸው እየተነሱ በተሰጣቸው ርዕስ መሰረት ያንበለብሉታል። ግሩም ትዕይንት ነው፡፡ የፕሮግራሙ /መርሀ - ግብሩ/ አንዱ አካል መሆኑ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ በግርማ - ሞገስ ወደ ቆመበት አምባ ጠርዝ ላይ ሄጄ መልክዐ - ምድሩን ተመለከትኩ - እጅግ ድንቅ፣ ትንፋሽ - አስጨራሽ አረንጓዴ ገፅታ አለው፡፡ በሰማያዊ ሰማይ ተከቦ የተፈጥሮን መንፈሣዊ ኃይል ያገዝፋል፡፡ እያንዳንዱ ቤተክርስቲያን በረከቱን ለአካባቢው ዛፍና ዕፅዋት የለገሠ ከመምሰሉ የተነሳ ያለውሃ ያለፀሐይ የህይወትን መጎናፀፊያ የደረበ ያስመስለዋል፡፡ ቢሆን ነው፡፡ ቅዳሴውና ትምህርቱ እንዳለቀ እኛ ቁልቁለቱን ተያያዝነው፡፡ እንዳመጣጣችን አላዳገተንም፡፡ (‘ማዳገት’ የሚለው ቃል ‘ከዳገት’ መምጣቱን ልብ ይሏል) መንገድ ወደ አለማወቅ ሲሄዱ ሩቅ ነው፤ ወደማወቅ ሲመለሱ ግን አጭርና ቀላል ነው፡፡
ማደሪያችን ሜዳው ላይ ነው፡፡ ከገዳሙ ቅፅር ካሉት ለቢሮነት በዘመናዊ ሞድ ከተሠሩት አለፍ አለፍ ብለው እንደተቆራረጠ የሸንኮራ አንጓ በእኩል ቁመት ከተሰሩት ክብ ቤቶች አካባቢ፡፡ እዚያ ግድግዳውን ትራስ እንደምናደርግ ዓይነት አመቻችተን አነጠፍን። አንዲት የመንገድ ጓደኛችን፤ ከዚህ ቀደም ደጋግማ ወደ ገዳሙ የመጣች፣ አብረን እንድንተኛ አንጥፋለች። ምንጣፋችንን በቀላሉ ከአውቶብሳችን ለማግኘት አልቻልንም፡፡ ምክንያቱም ሹፌሩም ሆነ ረዳቱ አልተገኙም፡፡ አንድ ያሳቀንና ያሳዘነን ሁኔታ ገጥሞናል። አባን “ኧረ እቃችን አውቶቡሱ ላይ  ቀረብን” አልናቸው። “ቆይ ሹፌሩን ልፈልገው” ብለው ሄዱ፡፡ ቆይተው “ረዳቱ የት እንዳለ የሚያውቅ ሰው አግኝቻለሁ፤ ትንሽ ጠብቁ” አሉን፡፡ ጠበቅን፡፡ የተባለው ሰውና አባ መጡ፡፡ ከሰውዬው ጋር ወደ አውቶብሱ ሄድን። እኛ ይከፍትልናል ብለን ስንጠብቅ እሱ አንኳኳው አውቶብሱን፡፡ ቢያንኳኳ ቢያንኳኳ፣ የሞባይል ባትሪ ቢያበራ፤ “ወይ” የሚል ጠፋ፡፡ አቶ መንግሥቱ ለማ “ወይ የሚለው አጣ ገጠመው ዝምታ” እንዳሉት ዓይነት ነው፡፡ “አውቶብሱን ለማንኳኳትማ እኛስ መች አነስን?! ቀድመን ሞክረን ነበርኮ” ተባባልን፡፡ ምን ይደረግ?
ሹፌሩ ስልክ ላይ (“እጄ ላይ” እንደሚሉት ዳያስፖራዎች) ይደወል ተባለ፡፡ አያነሳም፡፡ በኋላ እኔ “ለምን በመናገሪያው (በ speaker) አታስነግሩም? አልኩ፡፡ ያ ዘዴ ሰራ፡፡ ሹፌሩ ተገኘ፡፡ የሚገርመው ግን ረዳቱ ያንን ሁሉ ጊዜ እውስጥ ተኝቷል፡፡ አንዳንድ ሰው ታድሏል፡፡ ከልቡ ይተኛል፡፡ እኔም በከፊል ይሄ ጠባይ አለብኝ፡፡ እስር ቤት የለመድኩት ይመስለኛል፡፡ የገዳሙ ልጆች  ዕቃችንን  ተሸከሙልን፡፡ በኋላ ሳንቲም እንስጥ ብንል አብራን ያለችው ወዳጃችን “ገዳም ውስጥ ቲፕ (Tip) የለም አለችኝ፡፡ እኔ ቅር ብሎኝ ባህሉን ተቀበልኩ፡፡
ምንጣፍና ልብሳችንን ይዘን ጨረቃን ከአናት እያየን መሬት ላይ መኝታችንን ዘረጋን፡፡ ራት ብሉ ተባለ፡፡ እኔና ባለቤቴ አልሄድንም፡፡ አብራን የምትተኛው ወዳጃችን “ከቻልኩ አመጣላችኋለሁ” ብላን ሄደች፡፡ ስትመለስ የገዳሙ ግብዣ እዚያው ገበታው ላይ የሚበላ፣ ወጡም የሚጨለፍ ነው አለችን፡፡
ጋደም ጋደም እንዳልን የበገና ቅኝት ሰማሁ፡፡ ተነስቼ ወደ መድረኩ አቅራቢያ ተጠጋሁ፡፡ ሰው ጋቢና ኩታውን ለብሶ መኮዲ መስሎ ተኮልኩሏል፡፡ ነጭ በነጭ ሆኗል አገር ምድሩ፡፡ የሞባይል፣ የታብሌት፣ የካሜራ መዓት ከሰው አናት ከፍ ተደርጎ ተይዟል፡፡ መፈክር አውራጅ መስሏል ክንዱ ሁሉ፡፡ የመድረክ መሪው እባካችሁ ከኋላ ያለውን አትከልሉ” ይላል፡፡ ብዙ ማብራሪያ ይሰጣል፡፡ የድምፅ መሳሪያ ገጣሚዎቹ ከፍ ዝቅ ይላሉ፡፡ የፕሮግራሙ ዝርዝር ተነገረ፡፡ የበገና ድርደራ ምሥጋና ይኖራል፡፡ አጭር ዶክመንተሪ ፊልም ይኖራል። መዝሙር በመሰንቆ ይኖራል፡፡ ምሽቱ ግርማ ሞገስ እንዳለውና መንፈሣዊ ስሜት ግዘፍ-ነስቶ እንደሚቆም ታውቆኛል፡፡ የበገናው ቅኝት ገና ንዝረት ሲጀምር አየሩ መሞቅ፣ ሽቅብ ሶምሶማ መዝለል ያዘ፡፡ ልባችን አብሮ ይነዝር ጀመር፡፡ ቀን የሥራ ቢሮዎች ናቸው የተባሉት አለፍ አለፍ ተደርገው የተሰሩት ክብ መስተዋት - ቢሮ ጽ/ቤቶች አሁን መኝታ ቤት ሆነዋል፡፡ ሰዎቹ ግን እንዳይተኙ የበገናው ትርዒት ቀስቅሶ ሰቅዞ ይዞዋቸዋል። እነዚህም ሞባይላቸውን ደግነዋል፡፡ የፕሮግራም መሪው “ግርግር አትበሉ፡፡ ጥሞና ይፈልጋል በገና!” ይላል ደጋግሞ፡፡
በገና ጀመረ፡፡ እዚያው ገዳሙ ያፈራቸው በገናውያን ናቸው፡፡ ከአቅሟም ሆነ ከቁመቷ በላይ የሆነች ትንሽ ልጅ ሳትቀር እየተንጠራራች ከሌሎቹ ጋር ምቱን አስተካክላ ትጫወታለች፡፡ ጣቶቻቸው እኩል ሰምረው ይጓዛሉ - እኩል ከመንፈሳችን እመርታ ጋር ይተምማሉ። አንገታቸውን ሰበር አድርገው፣ ተመስጦዋቸወን ወደ ውስጥና ወደ አርያም እያመጠቁ ሲከይኑ ግርም የሚል ህልም ይመስላሉ፡፡ ዕድሜ - ጠገቦቹ ዛፎች ቅጠሎቻቸውን በለሆሳስ በሽብሸባ አዋጥተዋል፡፡ ወፎች በጥንቃቄ ኅብር ጠብቀው በዝቅተኛ ዜማ ያጅባሉ፡፡ አንድ ገዳም ሙሉ ሰው ኮሽ ሳያደርግ ፍቃደ - ልቦናውን ለምስጋና - ዜማው አንበርክኳል፡፡ ፀጥታ፤ ተፈጥሮ፡፡ ቦልቡና ዝማሬ እና በገና፡፡ ሁሉ ወደየውስጡ ያሰርፃል ይህ የማያሸንፈው ፆም ከወዴት ይገኛል፡፡ የሰው ልጅ ኃይሉ ጫጫታ አይደለም፡፡ የሚል አርምሞ ነው። ቀና ቢሉ ፍፁም ሰማይ፡፡ ዝቅ ቢሉ ፍፁም መሬት - በምዕመናን የተሞላ፡፡ ዙሪያውን ቢያዩ እርጭታ ያጀበው ዛፍና ጫካ፡፡ ከዚያ የሁሉም መጠቅለያ የሆነው መንፈስ!!
የበገና መምህራኑን ጨምሮ እጅግ የማረኩኝ ገዳሙ ያፈራቸው አስር በገና ተጨዋች ሴቶች ናቸው። ከሁሉም በላይ ተስፋ ማየቴ! እኛ የምናውቃቸው እንደ ዓለሙ አጋ ያሉ በገና ተጨዋቾች እንደ ድንቅ እንደ ብርቅዬ የዱር እንስሶች እያየናቸው ስንሰስትና ስንሳሳ፤ ማን ይተካቸው ይሆን ስንል፣ ዛሬ ማታ ያየሁዋቸው ሴቶች እጅግ አድርገው ስጋቴን አስወግደውልኛል። ማርከውኛል፡፡ ተስፋዬን እንደ አካባቢው አለምልመውልኛል፡፡ ሴቶችና ወጣቶች መሆናቸውም የተወሰነ ምናባዊ ጉዞ እንዳደርግ አግዞኛል፡፡ ምነው ቢሉ፣ እስከዛሬ የማውቃቸው በገና ተጨዋቾች አንድም አዋቂዎችና ጠና ጠና ያሉ ናቸው፡፡ አንድም ደግ ወንዶች ናቸው፡፡ ከዚያ የመሰጠኝ ስለሴቶች ምጥቀተ ህሊናና መንፈሳዊ ዕርገት ሳስብ የተሻለ ሽቅብ የመመንጠው ክህሎት ያላቸው ይመስለኛል። ስስነት ለምጥቀተ - ህሊና (Transcendence of Consciousness) ቅርብ ነው ባይ ነኝ፡፡ ጸሎትና ምህላ ስስን ስሜት ከጠንካራ ስሜት ይልቅ በፍጥነት ከፍ እንዲልና የመንፈስ ማማ ላይ እንዲወጣ ያደርገዋል፡፡
ከበገናው መንፈሳዊ ንዝረት በስተቀር ዝር የሚል ድምፅ የለም፡፡ አንዳች የሚያቅፍ መንፈሳዊ ሙቀት አለ። የበገናው ምት አረፍ ሲል ያለው ጸጥታ ይገርማል፡፡ የሚከተለውን ግጥም ያስፃፈኝ ያ ፀጥታ ነው፡፡
ፀጥታ ነው ፀጥ በሉ
የዓለም ድምፃችሁን ክሉ!
በዛፍ ጥላ ተጠለሉ፣ በፀጥታ ተከለሉ
አርምሞ ጉያ ግቡ፣
ፀጥታኮ ድምፅ አለው፣ ላንተ ብቻ የሚሰማ
እገዛ ውስጥህ የሚጮህ፣ እራስህ ውስጥ’ ሚሰማ
ላዕላይ የህይወት ትርጉም፣ የለሆሣሥ መንፈስ ማማ፡፡
በተመስጦ ሞገድ ብቻ፣
የሚያጎንህ መቀነቻ፣
የፀሎት የምህላ አቻ
ወደ አርያም መመንጠቂያ
ከምድረ ዓለም መለያያ
ፀጥታኮ ድምፅ አለው፣ ራስን ከራስ ማስታረቂያ!!
አንድ ነገር አስታወስኩ፡፡ የቺፕ ሳይዷ ዲዳ ሚስት በተሰኘው (The Dumb Wife of Cheapside) ዱሮ በዕደ ማርያም ት/ቤት ሳለን በእንግሊዝኛ የሰራነው ቴያትር ላይ አንደበቷ የተከፈተላት ዲዳ ሚስቱ እየለፈለፈች ስላስቸገረችው ጆሮው እንዲደነቁር የተደረገው መሪው ገጸ-ባህሪ የመጨረሻ ቃል፡-
“Thanks God All is Silent!” የሚል ነበር። አምላክ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ሁሉም ፀጥታ ነው እንደማለት ነው፡፡ (የዶክተሩን ሂሳብ ሳይከፍለው ጆሮው ደንቁሮ ነው) እኔም ያንን የደገምኩ መሰለኝ፡፡
በበገናውና በመሰንቆ ዝማሬው መካከል በቀረበው ዶኩመንተሪ ፊልም የረዥም ዕድሜ ባለቤት የሆነው የእየሱስ ገዳም አመሰራረት የአቡነመልከ ፄዴቅ ታሪክ፣ የገዳሙ የቅኔ ትምህርት፣ የአቋቋም፣ የዝማሬ፣ የድጓ ሥርወ - አመጣጥ በቅጡና በጥሩ ሁኔታ ተብራርቷል። ከአዲስ አበባ ሁለት መቶ አርባ ኪሎ ሜትር ላይ እንዲህ ያለ በመንፈስ የተሞላ ገዳም አለ ብሎ ማመን ያስቸግራል፡፡ 1200 ዓመቱን የያዘ አንጋፋ ገዳም ነው፡፡ 120 የገዳሙ ተማሪዎች አሉ፡፡
*          *         *
በገናው እኩለ ሌሊት ገደማ አበቃ! ወደ መኝታዬ ስመለስ አባ ትልቅ ኮምፎርት ሰጥተውናል ለካ! የፈራነው ብርድ ተሸንፏል፡፡ ጨረቃ በእኛ መሞቅ ተደስታ ትስቃለች፡፡
ወደ ደብረዘይት እኩለ - ፆም ፊታችንን አዙረን ለጥ አልን፡፡
*       *       *
ንጋት ላይ ቅዳሴው ይሰማል፡፡ እስከታቦቱ መውጫ ሁሉም በየፊናው ተመስጦ ውስጥ ገብቷል፡፡ ሰዓቱ ደረሰ፡፡ ደውል ተደወለ፡፡ ጥሩምባ ተነፋ፡፡ እንደ ጥይት ያለ የሚጮህ ድምፅ ተሰማ፡፡
“ተኩስ ነው እንዴ?” አለች ባለቤቴ፡፡
“ይመስላል፡፡ ለታቦቱ መውጣት የደስደስ ይሆን?”
እንደገና ደወል ተደወለ፡፡ ጥሩምባ ተነፋ፡፡ ያ ተኩስም ተደገመ፡፡
በኋላ ስናጣራ ጅራፍ ነው ለካ! እንዴት ቢወነጭፉት ነው እንደጠመንጃ የሚጮኸው? ብቻ ደወሉም፣ ጥሩምባውም፣ ጅራፉም ፀጥታውን ሰንጥቆ አንዳች የድምፅ መብረቅ ፈጥሯል፡፡
ታቦቱ ወጣ፡፡ የሚያጅቡት የማታዎቹ ባለበገናዎች ናቸው፡፡ እንዲህ ያለ በበገና የሚነግሥ ታቦት አይቼ ስለማላውቅ እጅግ ስሜቴን ሰቅዞ ይዞኛል፡፡ እዚህ የታደለ ገዳም ውስጥ የያሬድ ጥበብ ታቦት ያነግሣል! ታቦቱ ዑደት ያደርጋል፡፡ ጥበቡም አብሮት ዑደት ያደርጋል!! ድምቀቱ የማይለካ ነው፡፡ የደበበ ሰይፉ ግጥም ቅኝት ትዝ አለኝ፡-
“ጊዜ በጊዜ ቀለበት -
   ሰተት፡፡”
የሚለው፡፡ በሱ ቅኝት እንዲህ አልኩ፡-
ጥበብ በመንፈስ ቀለበት -
ሰተት፡፡”
ጥበብ በመንፈሱ ዑደት  -
             ፍክት
ፀጥታው በበዓሉ ድምቀት -
               ፍንክት!
ያሬድ በጊዜ ቀለበት -
          ግብት፡፡
በየቦታችን ታደምን፡፡ ታቦቱ ዑደቱን አብቅቶ ደጃፉ መድረክ ላይ ቆመ፡፡ አንድ አባት ትምህርት ሰጡ፡፡ የመድረክ መሪው ከአሮጌው ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት በመሰራት ላይ ያለውን አዲስ ህንፃ አስመልክቶ በስለት መልክ በአዲስ እርዳታ መልክ፣ አሁኑኑ ስሜታቸው ተቀስቀሶ፣ መዋጮ ሊያደርጉ የሚሹ ካሉ፣ መድረኩ ክፍት መሆኑን ገለጡ፡፡ መዋጮ ተዥጎደጎደ፡፡ በሁለት አውቶብስ ከናዝሬት ድረስ የመጡ አማንያን ከፍተኛ የሲሚንቶ መዋጮ አደረጉ፡፡ ታላቅ የምሥራች! “የሲሚንቶ ዘመቻ” የሚል ሎተሪ ካርድ ከ10 ብር እስከ 240 ብር ይሸጣል፡፡ (10፣30፣120፣240) የምሁር እየሱስ ገዳም አበምኔት ረዥም ሰበካ አደረጉ፡፡ ካሉት ነገር ያስገረመኝ “አቡነ መልከ ፄዴቅ በመጨረሻ ንግግራቸው “እባካችሁ ከዚህ ገዳም አትቅሩ ብለው ነበር የሞቱት ሞታቸው ታውቋቸዋል” ያሉት ነው፡፡
ፕሮግራሙ የሚዘጋው በበገና ባለሙያው በመምህር ሲሳይ ምሥጋና ዜማ እንደሚሆን አሳወቁ፡፡ ሆነ፡፡
ቀጥሎ ገዳሙ ያዘጋጀልን ምሳ በአዳራሹ ሆነ። እኛ ባዳራሹ የጓሮ በር በኩል ነው ውሃ ልኩ ላይ የተቀመጥነው፡፡ ጓሮ ጓሮ ነውና የራሱ ትርዒት አለው። (ፍቅር እስከ መቃብር ላይ ወ/ሮ ጥሩዓይነት የፍቅር በር እንዳላቸው ያስታውሷል) የገዳሙ ነዋሪዎች ሽልጦአቸውን የሚቀበሉት በዚህ በር በኩል ነው፡፡ ሽልጧቸው እንዴት አባቱ ጥፍጥና እንዳለው ልነግራችሁ አልችልም - ቀምሼዋለሁ!! ሌላው እንዳጋጣሚ በጓሮው በር በኩል እኛን ያደለን ነገር ዳቤ ነው፡፡ ከቤተክርስቲያኑ መውጫ በር አካባቢ በኋላ ብዙ ሰው ተሰልፎለት ያየነውን ዳቤ እዚህ እጅ በእጅ አገኘነው አቤት ሲጣፍጥ!! ጣና ገዳም ያገኘሁዋቸው መነኩሴ፤ “ፈረንጅ የዳቤን የተመጣጠነ የምግብ አቅም ቢያጠናው ጥሩ ነበር” ስላቸው፤
“መንፈሱንስ ከየት ያመጣዋል?” ያሉኝ ነው ትዝ ያለኝ፡፡ ከምሣ በኋላ ጉዞ ወደ አዲስ አበባ ነው፡፡ ወልቂጤ ላይ ለሻይ አረፍ አልን፡፡
ሻይ የፈለገ ሻይ፣ ቡና ያሻ ቡና፣ ቢራ የከጀለ ቢራ ጠጣና ወደ አገራችን ጉዞ ሆነ፡፡ ደሞ ወደ ትርምሱ፣ ደሞ ወደ ሰልቺው ህይወት፣ ደሞ ወደ ሁካታና ትርምሱ ልንገባ ነው፡፡
ኦቴሎ ከመርከብ ጉዞው በኋላ ወደ ዴዝዴሞና ሲመጣ “ከዚያ ሁሉ የባህር ነውጥ፣ ከዚያ ሁሉ ማዕበል በኋላ እንዳንቺ ያለ ሰላም የሚገኝ ከሆነ ሺ ዓመት ጦርነት ውስጥ ልሁን!” ይላል፡፡ የኛ ደግሞ ግልባጩ ነው - “ከዚያ ሁሉ የመንፈስ ፀጥታ፣ ከዚያ ሁሉ የአርምሞ ትፍስህት በኋላ እንደ አዲሰሳባ ያለ ትርምስ ውስጥ ከምንገባ ምነው እዚያው የፀጥታ ውቂያኖስ ውስጥ ሰምጠን በቀረን” ያሰኛል፡፡
በዓለም  ጤና አካባቢ ስንደርስ፣  ከአውቶብሱ ከኋላ አካባቢ የተቀመጡ ወጣቶች፤ መዘመር ጀመሩ፡፡ እኔና ባለቤቴ፤
“ምነው ከወልቂጤ በጀመሩት? ተባብለናል፡
“ብዙ ሰው ሊወርድ ስለሆነ ፀሎት አድርገን እንለያይ” አለ አንድ ነጭ በነጭ የሀገር ልብስ ያደረገ ወጣት፡፡ ሁሉም ተስማማ!
አውቶብሱ ቆመ! ሁላችንም ተነስተን ፀሎት አደረስን፡፡
ወደ አዲሳባ ከመግባታችን በፊት ማህተም አረግን ማለት ነው (Rubber – stamp ማድረግ እንዲል ፈረንጅ)
እኔም የፅሁፌን (Rubber – stamp) እዚሁ አደረግሁ!

Read 3126 times