Saturday, 21 March 2015 11:00

አትሌቶቻችን እስከ 2 ቢሊዮን ብር አፍሰዋል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

ባለፉት 20 ዓመታት በመላው ዓለም በጐዳና ላይ ሩጫ፣ በማራቶን፤ በግማሽ ማራቶን እና ሌሎች ውድድሮች ላይ ከተሰጡ የገንዘብ ሽልማቶች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች እስከ 2 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰባቸውን ለማወቅ ተቻለ፡፡ በኤአርአርኤስ ድረገፅ ከ1980-2015 እ.ኤ.አ በተሰጡ የሽልማት ገቢዎች  በቀረበው  መረጃ መሰረት የኢትዮጵያ አትሌቶች በዓለም አቀፍ ውድድሮች በተለይ ውጤታማ በሆኑባቸው ያለፉት 20 ዓመታት በወንዶች 29‚048‚658 ዶላር በሴቶች 29‚090‚527 ዶላር እንደሰበሰቡ ተመዝግቧል፡፡
በሌላ በኩል የ2015 እ.ኤ.አ የውድድር ዘመን ከገባ ወዲህ  በመላው ዓለም በተካሄዱ የጐዳና ላይ ሩጫ፤ የማራቶንና የግማሽ ማራቶን ውድድሮች የኢትዮጵያ አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች በሰበሰቡት የሽልማት ገንዘብ ዓለምን እየመሩ ናቸው፡፡ 2015 እ.ኤ.አ ከገባ በኋላ በመላው ዓለም በተደረጉ ውድድሮች የኢትዮጵያ አትሌቶች በወንዶች ምድብ 909‚490 ዶላር በመሰብሰብ ሲመሩ፤ የኬንያ በ496‚625 ዶላር ፣  የአሜሪካ በ235‚035 ዶላር፣ የኡጋንዳ በ40‚630 ዶላር፣ የሞሮኮ በ21‚460 ዶላር፣ የጣሊያን በ21‚350 ዶላር እንዲሁም የኤርትራ አትሌቶች በ14‚955 ዶላር ከ2-7 ያለውን ደረጃ አከታትለው ይወስዳሉ፡፡ በሴቶች ምድብ  የኢትዮጵያ አትሌቶች መሪነቱን የያዙት በ857‚975 ዶላር ነው፡፡ የኬንያ በ369‚430 ዶላር፣ የአሜሪካ በ217‚530 ዶላር፣ የኮሪያ ሪፖብሊክ በ66‚200 ዶላር፣ የህንድ በ32‚600 ዶላር፣ የእንግሊዝ በ20‚165 ዶላር እንዲሁም የጣልያን በ18370 ዶላር ከ2-7 ያለውን ደረጃ በሽልማት ገቢያቸው አግኝተዋል፡፡
ባለፉት 35 ዓመታት በወንዶች ምድብ የኬንያ አትሌቶች 86‚407‚048 ዶላር ገቢ በማግኘት በአንደኛ ደረጃ ሲቀመጡ፣ የአሜሪካ አትሌቶች በ30‚653‚055 ዶላር፣ የኢትዮጵያ አትሌቶች በ29‚048 658 ዶላር ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይወስዳሉ፡፡ የሞሮኮ በ5‚ 608 ‚104፣ የሜክሲኮ በ5‚277‚ 483፣ የደቡብ አፍሪካ በ4 ‚691 ‚978፣ የጣሊያን በ3‚ 417‚ 841፣ የብራዚል በ3‚003‚132፣ የእንግሊዝ በ2‚769‚842 ዶላር ገቢያቸው እስከ 10ኛ ደረጃ ይወስዳሉ፡፡  በሴቶች ምድብ ደግሞ ባለፉት 35 ዓመታት በሰበሰቡት የሽልማት ገቢ አንደኛ ደረጃ  በአትሌቶቿ 35‚332‚043 ዶላር ገቢ ያስመዘገበችው አሜሪካ ናት፡፡ ኬንያ በ33‚230‚146 ዶላር ሁለተኛ ደረጃ ስትወስድ ኢትዮጵያ በ29‚090‚527 ዶላር ገቢ ሦስተኛ ሆናለች፡፡ የራሽያ አትሌቶች በ14‚846‚746፣ የእንግሊዝ በ4‚387‚203፣ የጃፓን በ3‚713‚838፣ የሮማኒያ በ3‚691‚270፣ የጀርመን በ3‚592‚710፣ የካናዳ በ3‚552‚047 እንዲሁም የሜክሲኮ በ3‚067‚463 ዶላር ገቢያቸው እስከ 10ኛ ደረጃ ተቀምጠዋል፡፡
የዓለም የጐዳና ላይ ሩጫዎች  የስታትስቲክስ ባለሙያዎች ማህበር (ARRS) በድረገፁ በሚያሰራጫቸው አሃዛዊ መረጃዎች  ከ3000 ሜትር እና ከዚያ በላይ በሆኑ የረጅም ርቀት ሩጫዎች ላይ ያተኩራል፡፡ በኤአርአርኤስ ድረገፅ ላይ ባለፉት 35 ዓመታት በመላው ዓለም የተካሄዱ ከ100ሺ በላይ ውድድሮች ዙሪያ የተመዘገቡ ከ900ሺ በላይ አሃዛዊ መረጃዎችን ተከማችተዋል፡፡ በ35ሺ አትሌቶች የሩጫ ዘመን የተሟላ የመረጃ ስብስብ የሚገኝበት ነው፡፡ ኤአርአርኤስ የሽልማት ገቢ መረጃዎችን በማሰባሰብ ደረጃ ለማውጣት የቻለው በይፋ የሚገለፁ የገንዘብ ሽልማቶችን በመንተራስ በሰራው ስሌት ነነው፡፡ አትሌቶች በውድድር ላይ  በግላቸው፤ በወኪላቸው በመደራደር የሚያገኟቸውን የተሳትፎ ፣ የስፖንሰርሺፕ እና የቦነስ ክፍያዎችን የሽልማት ገቢው አሃዛዊ መረጃ አያካትትም፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቶች ባለፉት 25 ዓመታት በሰበሰቡት የሽልማት ገቢያቸው በኢትዮጵያ ከ1 እስከ 10 የሚኖራቸውና እና ከመላው ዓለም የሚያገኙት ደረጃ እንዲሁም ባለፉት 12 ዓመታት የኢትዮጵያ እና የኬንያ አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች ያገኙት የነበረው ድምር የሽልማት ገቢ ከዚህ በታች በሁለት ሰንጠረዦች ቀርቧል፡

Read 2402 times