Saturday, 21 March 2015 10:26

ነገ የ35 ሺህ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ ይወጣል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(102 votes)

በዚህ ዓመት በሦስት ፕሮግራሞች ለነዋሪዎች ከሚተላለፉት 75ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ በአቧዶ፣ በባሻወልዴ ችሎት፣ በልደታ፣ … ሳይቶች ግንባታቸው የተጠናቀቁ ከ35ሺህ በላይ ቤቶች ዕጣ ነገ እንደሚወጣ ተገለፀ፡፡               
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር፣ የኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት አስተዳደርና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የቤቶች ማስተላለፍ ቅድመ ዝግጅት ምን ደረጃ ላይ እንዳለ በሳምንቱ አጋማሽ በካቢኔው ጽ/ቤት በጋራ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በዕጣ አወጣጡ ነባርና አዲስ ተመዝጋቢዎች እንደሚካተቱ አስታውቀዋል፡፡
በ2005 ዕጣ ከወጣ በኋላ  በተደረገው ማጣራት ከ317ሺህ ወደ 135ሺህ የወረዱት ነባር ተመዝጋቢዎች ቅድሚያ የማግኘት መብት አላቸው ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት አስተዳደር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን መንግሥቱ፤ ከ10/90 እና 20/80 ዕጣ ከሚወጣላቸው ቤቶች ውስጥ ለሴቶች 30 በመቶ፣ ለመንግሥት ሰራተኞች 20 በመቶ ቅድሚያ ከተሰጠ በኋላ በቀሪው ሁሉም ተመዝጋቢዎች እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል፡፡
አቶ መስፍን ከሰኔ 2005 እስከ የካቲት 2007 ባሉት 16 ወራት ውስጥ የቆጠቡ ሰዎች በመጀመሪያው ዙር በሚተላለፉት 35ሺህ ቤቶች ዕጣ ላይ ይሳተፋሉ ብለዋል፡፡ በ2005 የወጣው መመሪያ ለ6 ወር ያልቆጠበ ሰው ይሰረዛል ቢልም፣ ዜጎች በተለያዩ ምክንያቶች ላይመቻቸው ስለሚችልና ዕጣው የሚወጣው በመጋቢት ስለሆነ ከተማ አስተዳደሩ ከባንክ ጋር በመመካከር እስከ ፌብሩዋሪ 28 ያጠራቀሙ ሰዎች በዕጣው እንዲሳተፉ መደረጉን፣ ከዚያ ወዲህ ቤት አገኛለሁ በሚል ተስፋ እየቆጠቡ ያሉ ሰዎች በ11ኛውና በ12ኛ ዙር እንደሚሳተፉ አስረድተዋል፡፡
ለልማት ተነሺዎች የሚሰጡትን 6ሺህ ቤቶች ጨምሮ በዚህ ዙር ለነዋሪዎች የሚተላለፉት ቤቶች ቁጥር 41 ሺህ እንደሆነ የጠቀሱት ሥራ አስኪያጁ፤ እስካሁን ድረስ ይህን ያህል ቁጥር ያለው ቤት ስላልተላለፈ፣ በነባር 20/80 ስቱዲዮ የተመዘገቡ ሰዎች በሙሉ በዚህ ዙር ያገኛሉ። ለ10/90 ቤቶች የተመዘገቡ ሰዎች ቁጥር 22 ሺህ ሲሆን እየተገነቡ ያሉት 10/90 ቤቶች ከተመዝጋቢው ቁጥር በላይ ስለሆኑ ከ135ሺህ ነባር ተመዝጋቢዎች ውስጥ ከግማሽ በላይ በዚህ ዓመት የቤት ባለቤት ይሆናሉ ብለዋል፡
ባለፉት ዙሮች ለነዋሪዎች ይተላለፉ የነበሩት ቤቶች ግንባታቸው 20 በመቶ የተጠናቀቀ ስለነበረ ለማስረከብ ረዥም ጊዜ ይወስድ ነበር ያሉት አቶ መስፍን አሁን ግን መንግሥት 100 ፐርሰንት የተጠናቀቁ ብቻ ሳይሆን መሰረተ ልማት (መብራት፣ ውሃ፣ መንገድ…) ተሟልቶላቸው ለኑሮ ምቹ እንዲሆኑ በወሰነው መሰረት፣ የቤቶቹ ግንባታ የተጠናቀቀ ስለሆነ ዕጣ ከወጣ በኋላ ማጣሪያ ተደርጎ ርክክቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ መሰረተ ልማቱ ይሟላል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ዕጣ የወጣለት ሰው በባንክ ያጠራቀመው የአጠቃላዩን ቤት ግንባታ ወጪ 20 በመቶ ካልሆነ እንዲያሟላ ይደረጋል እንጂ አይሰረዝም ያሉት ስራ አስኪያጁ፤ 20 በመቶ ማጠራቀም ያልቻለም ዛሬ ባያገኝ ነገ ሊያገኝ ስለሚችል የፕሮግራሙ አካል እንደሆነ ይቆያል፡፡ ነገር ግን በራሳቸው ፍላጎት እንዲሰረዙና ገንዘባቸው እንዲመለስላቸው የጠየቁ ሰዎች መብታቸው ስለሆነ ተሰርዘው የቆጠቡትን ከባንክ መውሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡

Read 16914 times