Monday, 16 March 2015 09:45

“የግል ሪል እስቴት የበለጠ ድጋፍ ካገኘ የቤት ፍላጎትን በየደረጃው ለማሟላት አቅም አለው”

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(4 votes)

አቶ ገብረየሱስ ኢጋታ (የጊፍት ሪል እስቴት መስራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር)

ጊፍት ሪል እስቴት ባለፉት አስር ዓመታት በቤቶች ልማት ዘርፍ የነበረውን ተሳትፎ  እንዴት ይገልጹታል?
ጊፍት ሪል እስቴት በኢትዮጵያ ያለው ዕድገትና የልማት ፍላጎት የወለደው ኩባንያ ነው። በኢትዮጵያ በየጊዜው እየጨመረ ከመጣው የህዝብ ብዛትና ሃገሪቱ እያስመዘገበች ካለው የኢኮኖሚ እድገት ጋር በተያያዘ የዜጎች የመኖሪያ ቤት ጥያቄ በከፍተኛ መጠን ጨምሯል። ምንም እንኳን ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ መንግስት በጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ላይ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ቢያደርግም ይህንን እያደገ የመጣ ፍላጎት ብቻውን ሊፈታው እንደማይችል ተገንዝቧል። ስለሆነም የግሉ ዘርፍ በቤቶች ልማት ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ መሬት በረጅም ጊዜ በሚከፈል ሊዝ ከማቅረብ ጀምሮ አንዳንድ ማበረታቻዎችን ሲያደርግ ቆይቷል። ጊፍት ሪል እስቴትም ሲኤምሲ እና አያት አካባቢ ከመንግስት በተረከበው 16.3 ሄክታር መሬት ላይ 261 የተለያየ አይነት ያላቸው ዘመናዊ ቪላዎችን፣ታውን ሃውሶችንና ሮው ሃውሶችን  እንዲሁም ሁለት መቶ ዩኒት ያላቸው 44 ብሎክ አፓርትመንቶችን ለመገንባት እቅድ ይዞ፣ በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹን ገንብቶ ለተጠቃሚዎች ያስተላለፈ ሲሆን አሁንም በመጠናቀቅ ላይ ያሉትን ጨምሮ አዳዲስ ግንባታዎችን በማካሄድ ላይ ይገኛል።  ጊፍት እንደ ግሩፕ ኩባንያ በኮንስትራክሽን፣በቤቶች ልማት፣በንግድና በማምረቻ ኢንደስትሪ ዘርፍ ከሚያንቀሳቅሳቸው አራት ኢንቨስትመንቶች ውስጥ ግዙፉ ኢንቨስትመንቱ ይኸው የሪል እስቴት ኩባንያው ሲሆን የሚያከናውነው ግንባታ አጠቃላይ ካፒታልም 2 ቢሊዮን ብር ይደርሳል። በግንባታው ሂደት እስከ 2 ሺህ የሚደርሱ ሰራተኞችን በማሳተፍም ከፍተኛ የስራ ዕድል መፍጠር የቻለ ሃገር በቀል ኩባንያ ነው።  
በኢትዮጵያ ያለው የሪል እስቴት ዘርፍ እድገት አዝጋሚ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ። እርስዎ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
ከ5 ዓመት በፊት የተደረጉ አንዳንድ ጥናቶች፣ሪልእስቴት ከኮንስትራክሽን ሴክተር ጋር ተዳምሮ ከአጠቃላዩ የሃገር ውስጥ ምርት  14.9 በመቶ  ድርሻ እንደነበረውና ዘርፉ በአማካይ በየዓመቱ ከ10 በመቶ በላይ እድገት እንዳስመዘገበ ያሳያሉ። ሁለቱ ተደጋጋፊ ዘርፎች በነዚሁ ዓመታት ብቻ ሃገሪቱ ካስመዘገበችው ከ11 በመቶ በላይ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ 1.5 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ይዘው ነበር። አሁን አዲስ ጥናት ቢደረግ ይህ አሃዝ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጨምር አልጠራጠርም። ሪልእስቴቱ ከኮንስትራክሽን ኢንደስትሪው ጋር ተጣምሮ የሃገር ውስጥ ምርት (GDP) መጠንን ከፍ ማድረጉ አይካድም።
ሪል እስቴት በግልም ይሁን በመንግስት የሚካሄዱ የመኖሪያና የንግድ ቤቶች ልማትን የሚያካተት ዘርፍ እንደመሆኑ እኔ በበቂ ሁኔታ አውቀዋለሁ በምለው የግል ሪልእስቴት ዘርፍ ላይ ብቻ አትኩሬ ጥያቄውን ብመልስ ተገቢ ይሆናል። የዘርፉ ዕድገት አዝጋሚ ነው፣ አይደለም ወደሚል መደምደሚያ ለመድረስ ጥናት ማድረግ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ነገር ግን ሪል እስቴት እንደ አንድ ኢንደስትሪ  በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የራሱ የሆነ ድርሻ ይዞ መንቀሳቀስ  ከጀመረበት ሁለት አስርተ ዓመታት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ምን ሰርቷል፣ ምን ያህል ኩባንያዎችንስ ማንቀሳቀስ ችሏል የሚለውን ካየን የምናገኛቸው አሃዞች ዘርፉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ መሆኑን ይመሰክራሉ። ከ2003 ዓ.ም ወዲህ ባሉት አራት አመታት ብቻ 120 ኩባንያዎች በሪልእስቴት ኢንደስትሪ ውስጥ ለመሳተፍ የኢንቨስትመንት ፍቃድ ማውጣታቸውን መረጃዎች  ይጠቁማሉ። ከነዚህ ፍቃድ የወሰዱ ተቋማት ውስጥ ጥቂቶቹ ወደ ሥራ ገብተዋል። እንግዲህ አንጋፋ ከሆኑት ጊፍት ሪል እስቴትን ከመሳሰሉ ኩባንያዎች ጋር ሲደመር በተለይም ከሚያንቀሳቅሰው በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ካፒታል ጋር ሲነጸጸር ይህ በግሉ ዘርፍ የሚካሄድ ግዙፍ ኢንቨሰትመንት  በኢኮኖሚው እድገት ውስጥ ያለው ድርሻ ከፍተኛ ነው ማለት ይቻላል።
ያም ሆኖ የዜጎችን የቤት ፍላጎት ከማሟላት አንጻር ምን ያህን ተንቀሳቅሰናል የሚለውን ካየን፣ የግሉም ይሁን የመንግስት ሪልእስቴት ዘርፍ “የላቀ” የሚባል ደረጃ ላይ አልደረሰም። ይህም ሃገራዊ ፍላጎቱ ካለው አቅርቦት በላይ በመሆኑ  የተፈጠረ ክፍተት ነው። የግል ሪል እስቴት ዘርፍ እድገት የህዝቡን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ከማሟላት አንጻር ከታየ በርግጥ ገና ብዙ ይቀረዋል። በኢትዮጵያ የመኖሪያ ቤት ጥያቄ አሁንም አንገብጋቢ ጥያቄ ነው። ይህም ገበያው ሰፊ እንዲሆን አድርጎታል። አሁን ያለው የሪል እስቴት ዘርፍ በብዙ ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶች ይህንን ገበያ ለመሸፈን በሚያስችል አቅም ላይ እንዳልሆነ ነው የምገነዘበው። ነገር ግን ዘርፉ የበለጠ ድጋፍ ከተደረገለት የሚገነባቸውን ቤቶች ዓይነትና ደረጃ በማስፋት በከፍተኛ ብቻ ሳይሆን በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙትን ዜጎች የቤት ፍላጎት በየደረጃው  ለሟሟላት የሚያስችል አቅም አለው።
  በእርስዎ አተያይ ለሪል እስቴቱ  እድገት ጎታች  ናቸው የሚሏቸው ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት፣ሪልእስቴቱ እንደማንኛውም የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ዘርፍ እድገቱን የሚገቱ ውጫዊና ውስጣዊ እንቅፋቶች አሉበት። ከውጫዊ ችግሮቹ ብንነሳ በአሁኑ ወቅት ያለው የመሬት አቅርቦት ማነስና የዋጋ መናር ስራውን አዋጪ ስለማያደርገው አዳዲስ ተዋናዮች በቤት ልማት ኢንደስትሪው ውስጥ እንዳይገቡ፣ነባሮቹም ስራቸውን እንዳያስፋፉ ምክንያት ይሆናል። ከመሬት አቅርቦት ማነስ ጋር በተያያዘ ብዙ አልሚዎች በተለይ ከተማ ውስጥ ለሚያካሂዷቸው የመኖሪያና ንግድ ቤት ግንባታዎች የሚሆን መሬት ከግለሰቦች ላይ በውድ ዋጋ ቦታ ለመግዛት ተገድደዋል። ይህም የቤት መሸጫ ዋጋቸው ላይ ከፍተኛ ጭማሪ እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል። በሌላ በኩል የኮንስትራክሽን ማቴሪያል አቅርቦት ማነስና ዋጋውም በየጊዜው ማሻቀብ በሪል እስቴት አልሚዎች ላይ የተጋረጠ ዋነኛው ችግር ነው። አልሚዎች ከደንበኞቻችን ጋር  በገባነው ውል መሰረት ግንባታውን በተባለው ጊዜ አጠናቀን እንዳናስረክብ በየጊዜው የሚከሰቱት የግንባታ እቃዎች እጥረት ጎታች ምክንያት እየሆነብን ነው። ይህ እጥረት የፈጠረው የዋጋ ልዩነት ደግሞ በግንባታ ዋጋው ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ስለሚያስከትል የአልሚዎችን አትራፊነት ከመቀነሱ ባሻገር በኮንትራት ጊዜው ውስጥ የሚፈጠረው የዋጋ ጭማሪ (price escalation) ደንበኞች አስቀድመው ከተዋዋሉበት  የቤት ግዢ ዋጋ በላይ እንዲከፍሉ ያስገድዳቸዋል። ይህም ሁለቱንም ወገን ተጎጂ ያደርጋቸዋል።
በሶስተኛ ደረጃ ሊጠቀስ የሚችለው የዘርፉ ዕድገት እንቅፋት የፋይናንስ አጥረት ነው።  ሪል እስቴት ግዙፍ ኢንቨስትመንት በመሆኑ ከፍተኛ መዋዕለንዋይ ይጠይቃል። ኩባንያዎች ከደንበኞች ከሚሰበስቡት የቅድሚያ ክፍያ ውጪ ሌላ የፋይናንስ ምንጭ የላቸውም። በሃገራችን እንደሌላው ዓለም ሞርጌጅ ባንኮች  ባለመኖራቸው ለሪልእስቴት ብድር የሚሰጥ ባንክ የለም። በዚህ ሳቢያ ዘርፉ ተለዋዋጩን የገበያ ዋጋ ለመቅደምና ጊዜውን ለመጠቀም የሚያስችለው የፋይናንስ አቅም የለውም። ከዚህ በተጨማሪም ሪልእስቴቶች ለግንባታ መሬት በሚረከቡበት የከተማ ማስፋፊያ አካባቢዎች እንደ መንገድ፣መብራት እና ውሃ ያሉ መሰረተልማቶች በጊዜ ባለመሟላታቸው በግንባታ ስራው ላይ ብቻ ሳይሆን በሚገነቡት ቤቶች ዋጋ ላይ ጭምር ከባድ አሉታዊ ተጽዕኖ ፈጥሯል። እነዚህ እንግዲህ ውጫዊ ከሆኑት ምክንያቶች ጥቂቶቹ ናቸው።
ውስጣዊ ምክንያቶችን ስንመለከት ደግሞ የልምድ እጥረት መኖር፣የስራ ባህልና የስራ ላይ ስነምግባር አለመዳበር፣የዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እጥረትና በዘርፉ ብቃት ያለውና የሰለጠነ ባለሙያ በገበያው ውስጥ እንደተፈለገው አለመገኘት ተጠቃሽ ምክንያቶች  ተደርገው መወሰድ ይችላሉ።
  አብዛኞቹ የሪል እስቴት ደንበኞች በውለታቸው መሰረት ቤታቸው በጊዜ ተጠናቆ መረከብ አለመቻላቸውን በተመለከተ ተደጋጋሚ ቅሬታ ያነሳሉ። ምክንያቱ ምንድነው ይላሉ?
ከላይ ለመዘርዘር የሞከርኳቸው ውጫዊና ውስጣዊ  ችግሮች ለዘርፉ እድገት ማነቆ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ለደንበኞች ቅሬታ መነሳትም ምክንያት ሆነዋል። በርግጥ እያንዳንዱን ኩባንያ ወክዬ  ከደንበኞቻቸው ለቀረቡት ቅሬታዎች መልሱ ይህ ነው ማለት አልችልም። ግን የጋራ የሆኑና በኢንደስትሪው ላይ ተደጋግመው የሚታዩ ችግሮች ለደንበኞች ቅሬታ መከሰት ገዢ ምክንያት ሆነው ሲወጡ ይስተዋላል። ያም ቢሆን ግን በግሌ ውስጣዊም ይሁን ውጫዊ ምክንያት ማቅረብ የደንበኞችን ቅሬታ ለመሸፋፈን  እንደ ምክንያት  (Excuse factor) ሊቀርብ አይገባም ባይ ነኝ።
ደንበኛ ሁልጊዜም ትክክል ነው በሚለው መርህ አምናለሁ። ደንበኛው ከኩባንያው ጋር ውል ከገባና ተገቢውን ክፍያ ከፈጸመ በኋላ የሚፈልገው በየትኛውም መንገድ ይሁን በውሉ መሰረት ቤቱን መረከብ ነው። ነገር ግን ሪል እስቴት አልሚዎች ለደንበኞቻቸው የሚገነቧቸውን ቤቶች ዋጋ አውጥተውና ከዚያም ላይ ትርፋቸውን አስልተው ስራ ሲጀምሩ እጥረት የሚከሰትበትና በየጊዜው የሚያሻቅበው የኮንስትራክሽን ግብዓት ዋጋ እጃቸውን የሚያስርበት ሁኔታ አለ፡፡ ባስቀመጡት የጊዜ ገደብ እንዳይንቀሳቀሱ ምክንያት ይሆናል። ያ ብቻ ሳይሆን የግብዓት ዋጋው እየጨመረ ሲመጣ የግንባታ ዋጋም የዚያኑ ያህል ከፍ ስለሚል  ዞሮ ዞሮ ውሉ በኮንትራት ጊዜ ውስጥ ለሚፈጠረው የግብዓቶች ዋጋ ንረት ደንበኛው ልዩነቱን እንዲከፍል ያስገድደዋል። ይህን ጊዜ ጫናው በሁለቱም ላይ ይወድቃል። የተገልጋይ እርካታም ይጠፋል። በዚህ ሳቢያ ግንባታዎች ለሁለትና ሶስት ዓመታት ሊጓተቱ ይችላሉ። ይህ የቢዝነሱን ባህሪ ኢ-ተዓማኒ የማድረግ አደጋ ስለሚጋርጥ ለኩባንያዎቹ ከባድ ፈተና ነው። እዚህ ላይ ደንበኞች ለችግሩ አስተዋጽዖ ስለሌላቸው የሚወቀሱበት ምክንያት የለም። ጫናው ሃገር አቀፍና የሁሉም ሪልእስቴት አልሚ ችግር ስለሆነ ልዩ ልዩ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በመቀየስ  የደንበኛውን ፍላጎት ለማሳካት መስራት ግድ ይሆናል።
   በሌላ በኩል ዘርፉ ከዋጋው አንጻር ከፍተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ብቻ ዒላማ ያደረገ በመሆኑ የብዙሃኑን የቤት ፍላጎት ከማሟላት አንጻር ያበረከተው አስተዋጽዖ አናሳ ነው የሚል ትችትም ይቀርብበታል። ይህን እርስዎ እንዴት ያዩታል?
ይህ ጥያቄ ታሳቢ ማድረግ  ያለበትን ዋና ነገር የዘነጋ ይመስለኛል። የመኖሪያ ቤት  (መጠለያ) በየትኛውም የኑሮ ደረጃ ላይ ያለ ዜጋ እንዲሟላለት ከሚፈልጋቸው መሰረታዊ ፍላጎቶች አንዱ ነው። መጠለያ የማግኘት ጉዳይ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን መብትም ጭምር ነው። በእርግጥ ፍላጎት በአቅም ላይ  የተወሰነ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህ ከተስማማን መንግስት በስፋት የሚያካሂደው የጋራ መኖሪያ ህንጻዎች ግንባታ ታሳቢ ያደረገው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ነው። መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ደግሞ በአብዛኛው በማህበር በመደራጀት ወይም በተናጥል መሬት በመግዛት መኖሪያ ቤታቸውን ራሳቸው ይገነባሉ። በሌላ በኩል አቅም ያላቸውና ገንዘብ አውጥተው የተገነቡ ቤቶችን ለመግዛት የሚችሉ ዜጎችን ፍላጎት ለማሟላት ደግሞ ብዙዎቹ የሪልእስቴት ኩባንያዎች በንጽጽር ከፍ ያለ ዋጋ የሚያወጡ መኖሪያ ቤቶችን ይገነባሉ። በዚህ መሰረት የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት በየደረጃው ለማሟላት የሚሰሩ  አንቀሳቃሾች (Actors) ድምር ስራ በሃገሪቱ ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ማቃለል ያስችላል ማለት ነው። ጉዳዩን በዚህ መልክ መረዳት ይቻላል።
  የውጭ ሪልእስቴት ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ መግባት ለሃገር ውስጥ አልሚዎች ስጋት ነው ብለው ያምናሉ?
በቅርቡ ወደ ገበያው የተቀላቀሉትንና ለመግባት ፍላጎታቸውን ያሳዩትን የውጭ ሃገር ሪልእስቴት አልሚዎች ‘ስጋት’ ከማለት ይልቅ ‘ከባድ ተወዳዳሪ’ በሚል ብገልጻቸው ይስማማኛል። ይህንን የምለው ሁላችንም ማለት በሚያስችል መልኩ የሃገር ውስጥ ሪልእስቴት አልሚዎች ያለብንን የጋራ ችግር መሰረት አድርጌ ነው።
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ገና በጨቅላ እድሜ ላይ ያለና ከልምድም ይሁን ከሰለጠነ የሰው ሃይል እንዲሁም ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም አንጻር ብዙ የሚቀረው ዘርፍ ነው። በተለይ በመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ላይ ያለን ልምድ ብዙ የሚያግደረድር አይደለም። እነዚህ የውጭ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ በሃገራቸው ባንኮች ፋይናንስ ስለሚደረጉ የገንዘብ እጥረት የለባቸውም። እንደ ሃገር ውስጥ ኩባንያዎች፣ ከደንበኞች በሰበሰቡት ገንዘብ ሳይሆን በራሳቸው አቅም ቤቱን ገንብተው በቀጥታ ወደ ሽያጭ ነው የሚሄዱት። ወዲያው ከፍሎ ወዲያው ቤቱን ለመረከብ ለሚፈልግ ሰው አማራጭ ይዘው መጥተዋል ማለት ነው። የግንባታ ጊዜያቸው ባጠረ ቁጥር የኮንስትራክሽን ግብዓት ዋጋ መናር ሊያስከትልባቸው የሚችለውን ግሽበት ያመልጡታል ማለት ነው። ስለዚህ አትራፊ ይሆናሉ። በሁለተኛ ደረጃ በዘርፉ የካበተ ልምድ ስላላቸውና ለግንባታ ቁልፍ የሆነውን የሰለጠነ የሰው ሃይል ይዘው ስለሚመጡ እኛን የሚገጥመን አይነት ችግር አይገጥማቸውም። ሶስተኛው ምክንያት ደግሞ በግንባታው ዘርፍ ወቅታዊ ነው የሚባለውን ቴክኖሎጂና ማሽን  ሁሉ መጠቀማቸው ነው። ይህም በአነስተኛ ወጪ፣በፈጣን ጊዜና በቀላል አሰራር ግንባታ እንዲያካሂዱ እድል ይፈጥርላቸዋል። በእነዚህ ብቃቶቻቸው ሳቢያ እንደ እኛ ባሉ በዘርፉ የተሰማሩ የሃገር ውስጥ ኩባንያዎች ላይ ከባድ ተወዳዳሪ ይሆናሉ ማለት ነው። የኩባንያዎቹን ወደ ኢትዮጵያ ገበያ መግባት በመልካም አጋጣሚው ስናየው ደግሞ የቤት ፍላጎት ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ገበያው ገና አልተነካምና ሜዳው ሁላችንንም ሊያጫውት የሚችል ነው። ሃገሪቱ ሰፊ ናት። ሪል እስቴቱ እስካሁን በአብዛኛው አዲስ አበባ ከተማ ላይ ተወስኖ የቆየ ነው። ስለዚህ የመጫወቻ ሜዳውን ወደ ክልል ከተሞችም ማስፋት ይገባናል። ከዚህ በተጨማሪ እነዚህ የውጭ ኩባንያዎች ይዘው የመጡትን ቴክኖሎጂና እውቀት በጊዜ ሂደት ከኛ ጋር ለማዋሃድ እድሉ አለን። ሁላችንም እነሱ ወደደረሱበት ደረጃ ለመድረስ እየጣርን  የአቅማችንን በመስራትና ለደንበኞች የምንሰጠውን አማራጭ በማስፋት በዘርፉ ውስጥ ተወዳዳሪ ሆነን ለመቀጠል የሚያስችሉን ብዙ እድሎች አሉ። በጊዜ ሂደት ዘርፉ እንዲያድግ ለማስቻል የነዚህ ኩባንያዎች መምጣት በጎ አስተዋጽዖ አለው ብዬ አምናለሁ። በርግጥ ቀላል ፉክክር እንደማይገጥመን ብረዳም ከወዲሁ ስትራተጂ ቀይሶ በገበያው ውስጥ ለመቀጠል ከተነሳን ግን  የተሻሉ አቅጣጫዎችን መቀየስ እንችላለን ብዬ አምናለሁ። የሪል እስቴቱ ዘርፍ ፈተናዎች ቢበዙበትም ሊጠቀምባቸው የሚገባ መልካም አጋጣሚዎች እንዳሉትም መዘንጋት የለብንም።
በመጨረሻ ቀረ የሚሉት ሃሳብ ካለ ----
በዚህ አጋጣሚ መንግስት ለዘርፉ እስካሁን እያደረገ ላለው እገዛና እየገጠሙን ላሉት ችግሮች መፍትሄ ለማበጀት ለሚያደርገው ጥረት ምስጋና  ማቅረብ እወዳለሁ። ይህ እንዳለ ሆኖ የሃገሪቱን የስራ አጥ ቁጥር በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ቀጣሪ በመሆን በኢኮኖሚው ውስጥ ጉልህ ሚና የሚጫወተውን የግል ግንባታ ዘርፍ አሁን ካለው በበለጠ መልኩ ትኩረት ሰጥቶ ሊደግፈው፣ በመልካም አስተደደርና በሌሎችም ዘርፎች የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለመፍታትም የጋራ መድረኮችን በማዘጋጀት ድጋፍና ክትትል ሊያደርግለት ይገባል የሚል መልዕክት ማስተላለፍ እወዳለሁ።

Read 4388 times