Monday, 16 March 2015 09:32

የአትሌቶቻችን ህንፃዎች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(11 votes)

በሩጫው የተሳካላቸው አትሌቶች የዕውቁን አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴን አርአያነት በመከተል ጥሪታቸውን በኢንቨስትመንት ላይ እያፈሰሱ ይገኛሉ፡፡ አብዛኞቹም በሪል ስቴት ኢንቨስትመንት ላይ በማተኮር ትላልቅ ህንፃዎችን ገንብተዋል፡፡ አትሌቶች በስፖርት እና በኢንቨስትመንት በተያያዘ ያላቸው ካፒታል ከ7 እስከ 10 ቢሊዮን ብር እንደሚገመት መረጃዎች ይገልፃሉ። ኃይሌና ዓለም ኢንተርናሽናል እንዲሁም ማራቶን ኢንጅነሪንግ ባለፈው ዓመት ብቻ  እስከ 28 ሚሊዮን ብር የገቢ ቀረጥ መክፈላቸውን ያመለከቱ መረጃዎችን በመንተራስ ለመገንዘብ የሚቻለው በሁሉም አትሌቶች እየተንቀሳቀሱ ያሉ ኢንቨስትመንቶች ለመንግስት በሚያስገቡት የቀረጥ ገቢ ምን ያህል ሚና እንዳላቸው ነው፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት በኦሎምፒክ እና በዓለም ሻምፒዮና የአትሌቲክስ የውድድር መድረኮች  በወርቅ ሜዳሊያዎች ኢትዮጵያን ሲያኮሩ የቆዩት  አትሌቶች ካለፉት 10 ዓመታት  ወዲህ ደግሞ በኢንቨስትመንት ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ አገራቸውን  የሚያለሙ ባለውለተኞች ሆነዋል።  አትሌቶች የተሠማሩባቸው የኢንቨስትመንት መስኮች በሪል ስቴት፣ በወጭና ገቢ ንግድ፣ በሆቴል፣ በስፖርትና በግብርና፣ በአውቶሞቲቭ፤ በእርሻ ያተኮሩ ናቸው፡፡ ኢንቨስትመንቶቻቸው እስከ ሶስት ሺ ለሚደርሱ ኢትዮጵያውያንም የስራ እድል ፈጥረዋል፡፡ አትሌቶቹ ለህንፃዎቻቸው ግንባታ በተለይ መገናኛና ቦሌን የመረጡ ይመስላሉ፡፡
በመገናኛ እስካሁን አምስት የአትሌቶች ህንፃዎች እየተገነቡና ስራ እየጀመሩ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የአትሌት ጥሩነሽ ዲባባና ስለሺ ስህን ንብረት የሆነው “ስለሺ ስህን ቢዝነስ ሴንተር” ተጠቃሽ ነው፡፡ ይሄ ህንፃ አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን ጥንዶቹ አትሌቶች በቀድሞው ካራማራ ሆቴል አካባቢ ባለ18 ፎቅ ህንፃ አራት ኮከብ ሆቴል ለመገንባት እቅድ ይዘዋል፡፡ እዚያው መገናኛ ላይ አትሌት ደራርቱ ቱሉ ከሁሉም አትሌቶች በትልቅነቱ ግንባር ቀደም የሆነ ባለ 15 ፎቅ ህንፃ እየገነባች ነው፡፡ በሪል እስቴት ዘርፍ የተሰማራችው ደራርቱ በአሰላና አዳማም ህንፃዎችን ገንብታለች፡፡  በመገናኛ አካባቢ በግንባታ ላይ ካሉት ህንፃዎች አንዱ የገዛሐኝ አበራ ነው፡፡ በሃዋሳ ከ342 ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት  ሪዞርት ያስገነባው ገዛሐኝ አበራ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሆቴሌቹን የሚገነባ እና በሪል ስቴት እና በእርሻ ለመስራት የሚንቀሳቀስ ሆኗል፡፡ ሌላዋ መገናኛ አካባቢ ህንፃ እያስገነባች ያለችው አትሌት ደግሞ መሰረት ደፋር ናት፡፡
ቦሌ አካባቢ ህንፃ በመገንባት ፈርቀዳጅ የሆነው አትሌት ኃይሌ ሲሆን ፤ በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ከ10 በላይ ህንፃዎች አሉት፡፡ ኃይሌ በመጀመርያ ያስገነባው ዓለም ሲኒማ ያለበትን ሃይሌ ዓለም ህንፃ ነው፡፡ በዚያው በቦሌ አካባቢ በመድሃኒያለም ቤተክርስትያን አቅራቢያም አትሌቶች በርካታ ህንፃዎችን ገንብተው ስራ ጀምረዋል፤ እየገነቡም  ናቸው፡፡የአትሌት ቀነኒሳ ሆቴል ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ነው፡፡የቀነኒሳ ሆቴል ባለአራት ኮከብ ሲሆን በኢጣሊያዊ አርክቴክት ዲዛይኑ ተሰርቶ በ200 ሚሊዮን ብር ወጭ የተገነባ ነው፡፡ ከአትሌት ኃይሌ በመቀጠል ከፍተኛ ገንዘብ ኢንቨስት በማድረግ የሚታወቀው አትሌት ቀነኒሳ፤ እስካሁን 500 ሚሊዮን ብር ኢንቨስት አድርጓል፡፡ አትሌቱ ከ”ቀነኒሳ” ሆቴል ባሻገር በሱልልታ የአትሌቲክስ ማእከልና ሆቴል  ከማስገንባቱም በላይ በአሰላና በትውልድ ከተማው በቆጂም ህንፃዎችን ሰርቷል፡፡ በሩጫ ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማቶች በመሰብሰብ ከዓለም ሴት አትሌቶች በ6ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው አትሌት ብርሃኔ አደሬም ቦሌ መድሃኒያለም አካባቢ ከሌሎቹ ገዝፎ የሚታይ እና “ብርሃን አፍሪካ” የተባለ ባለ 8 ፎቅ ህንፃ አስገንብታ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ እዚያው አካባቢ በግንባታ ላይ የሚገኘው ሌላው ባለ 10 ፎቅ ህንፃ የአትሌት ገብረእግዚአብሄር ነው፡ አትሌት ገብረእግዚአብሄርና ባለቤቱ ወርቅነሽ ኪዳኔ ሌሎች ሁለት ህንፃዎችን በከተማዋ የተለያዩ ክፍሎች እያስገነቡም ይገኛሉ፡፡ ጌጤ ዋሚ በትውልድ ስፍራዋ ደብረብርሃን ሆቴል የምታስተዳድር ሲሆን አንጋፋው አትሌት ወርቁ ቢቂላ በዱከም ካለው መለስተኛ ሆቴል በተጨማሪ በምስራቅ አፍሪካ በውሃ ጉድጓድ ቁፋሮዎች በርካታ ፕሮጀክት የሚያቀሳቅስ ኩባንያን ከሆላንድ አጋሮቹ ጋር እያከናወነ ይገኛል፡፡ ሌላው አትሌት  በላይ ወላሼ  በቡና ኢንቨስትመንት የሚንቀሳቀስ ሲሆን  ሌሎች እውቅ  እና ወጣት አትሌቶችም በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እና የንግድ ስራዎች መሰማራታቸው ይገለፃል፡፡ ዜግነታቸውን ለውጠው ለውጭ አገራት የሚሮጡ አትሌቶችም መገናኛ አካባቢ ህንፃ ገንብተዋል፡፡ ለባህሬን የምትሮጠው ማርያም ዩሱፍ ጀማል፤ የካ ጋራ ላይ በ200 ሚሊዮን ብር “ቤልቪው” የተባለ ሆቴል ገንብታለች፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቶች በስፖርቱ ኢንቨስትመንት መስክም ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ሱሉልታ የሚገኘው “ያያ ቪሌጅ” በአንድ የቀድሞ አትሌትና በኃይሌ ገብረስላሴ ሽርክና የተገነባ ነው፡፡ እዚያው ሱልልታ የቀነኒሳ የአትሌቲክስ ማእከልና መዝናኛም ይገኛል፡፡ በሱልልታ የተገነባው የቀነኒሳ የስፖርት ማእከል የመሮጫ ትራክ፤ የጎልፍ ሜዳ፤ የቅርጫት ኳስ እና የእጅ ኳስ ሜዳዎች ያሉትና የተለያዩ የመዝናኛ አገልግሎቶች በመስጠት እስከ 120 ሰዎች የሚያስተናግድ ሆኖ በ350 ሚሊዮን ብር የተገነባ ነው፡፡ አትሌቶች የሩጫ ውድድሮችን በማስተናገድ ዘርፍም ኢንቨስት እያደረጉ ነው፡፡ በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሰው ከ14 ዓመታት በላይ ያስቆጠረውና ከ100 ውድድሮች በላይ ያዘጋጀው የኃይሌ ገብረስላሴ “ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ” ነው፡፡ በቅርቡ ደግሞ አትሌት ገብረስላሴ “የተራራ ላይ ሩጫ” በሚል ተመሳሳይ ኢንቨስትመንት ውስጥ ገብቷል፡፡

Read 7867 times