Monday, 16 March 2015 09:20

መስተንግዶና ውጤት የሰመረለት 12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው ሰሞን በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ለአራት ቀናት የተካሄደው 12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና አገሪቱ ወደፊት አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮችን ለማዘጋጀት የምትችልበትን አቅምና ብቃት ማሳየቱ ተገለፀ፡፡ በሻምፒዮናው አስተናጋጇ ኢትዮጵያ በውድድር መስተንግዶ ብቃት ከመደነቋም በላይ፤ በአዲስ አበባ የነበረው የስፖርት አፍቃሪ ለሻምፒዮናው በሰጠው ማራኪ ድባብ ከተለያዩ አካላት ምስጋና ቀርቧል፡፡ የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን በሰጠው መግለጫ ሻምፒዮና ስኬታማ እንደነበር አስታውቆ በሻምፒዮናው ታሪክም ኢትዮጵያ ከፍተኛውን የተመልካች ቁጥር ያስተናገደች አገር እንደሆነች አመልክቷል፡፡
ሻምፒዮናው የምንግዜም ምርጥ ለምን ተባለ
ሻምፒዮናው በተመልካች ብዛት፤ በዝግጅት እና በመስተንግዶ፤ በደማቅ ፉክክር እና በቴሌቭዥን ስርጭት በታሪክ የምንግዜም ምርጥ እንደነበር የተናገሩት የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ማሀመድ ካልካባ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ አህጉራዊ የአትሌቲክስ ሻምፒዮናውን ያለአንዳች ችግር በማስተናገዷ ወደፊት ሌሎች ውድድሮችን የምታስተናግድበትን እድል እንደሚያሰፋውም ገልፀዋል፡፡በአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑትና በ12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና የውድድር ዝግጅትና የቴክኒክ ኮሚቴዎችን የመሩት ሞሪሲሽያዊ እና የኬንያ አትሌቲክስ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ዴቪድ ኦኮዩም የኢትዮጵያ ዝግጅትና መስተንግዶ እንዳስደነቃቸው ተናግረው ከመስተንግዶ ባሻገር በማራኪ ድጋፍ እና የተሳትፎ ውጤት የታጀበ መስተንግዶ መታደማቸው አርክቶናል ብለዋል፡፡ ሁለቱ የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን አመራሮች ከደቡብ አፍሪካ ከኬንያና ከምራብ ባሻገር ወደፊት በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ መደረግ ያለባቸውን ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች እንደ ዓለም ሻምፒዮና እና ኦሎምፒክ ለማስተናገድ ኢትዮጵያም እጩ የምትሆንበት አቅም እንዳላት መስክረዋል፡፡
የአትሌቶች ማናጀር የሆነውና በግሎባል ስፖርት ኮምኒኬሽን ስር የበርካታ ታላላቅ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ዲያሬክተር እና በሻምፒዮናው የውድድር ዲያሬክተር የነበሩት አቶ ዱቤ ጅሎ ደግሞ ኢትዮጵያ ከ6 ዓመት በፊት ካስተናገደችው 16ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በተሻለ 12ኛውን የአፍሪካ የወጣቶች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና በተሟላ ብቃትና ስኬት ማስተናገዷን ገልፀዋል፡፡ የወጣቶች ሻምፒዮናውን ስኬታማ ለማድረግ የአትሌቲክስ ፌደሬሽን ከመንግስትና ከአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የስፖርት ተቋማት በቅንጅት መስራቱን የጠቀሱት አቶ ዱቤ ጅሎ ፤ ወደፊት መሠል የአፍሪካ አትሌቲክስ ውድድሮችን ለማዘጋጀት ከፍተኛ መነቃቃት ተፈጥሯልና ይላሉ፡፡  በወጣቶች ሻምፒዮናው ኢትዮጵያ በነበራት ተሳትፎ በተለይ በሜዳ ላይ የስፖርት ውድድሮችና በአጭር ርቀት የአትሌቲክስ ውድድሮች ጠንካራ እና በሜዳልያ ውጤት የታጀበ ተሳትፎ ማድረጓ በአገሪቱ በማካሄዱ አካዳሚዎች፣ የአትሌቲክስ ፕሮጀክቶች መልካም ተግባራት መከናወናቸውን እንደሚያመለክትም አቶ ዱቤ ገልፀዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ኤጀንት ሆኖ የሚሠራው ጌታሁን ተሰማ በበኩሉ፤  የወጣቶች ሻምፒዮናው በአዲስ አበባ በድምቀት መካሄዱን አድንቆ፣ የወደፊት የኦሎምፒክና የዓለም ሻምፒዮኖች የሚወጡበት መድረክ በመሆኑ የተሳትፎ አቅም ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ምክር ሰጥቷል፡  የናይጀሪያ የወጣቶች የአትሌቲክስ ቡድን የአጭር ርቀት ሯጮች አሰልጣኝ ኩስሊ ሞናልዬ በሰጡት አስተያየት ናይጀሪያ ወጣትና ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት በስፋት እንደምትሠራ ጠቅሰው፣ በመላው አገሪቱ በመንግስት ስር ያሉ አካዳሚዎችና በግል የሚከፈቱ ማሰልጠኛዎች ውጤታማ እንዳደረጋቸው አስገንዝበዋል፡፡ በናይጀሪያ አትሌቲክስ ለወጣቶች ላይ ትኩረት በመስጠት ይሠራል ያሉት አሰልጣኙ በአካዳሚዎች አሠራር ሁለት ደረጃዎችን እንደሚከተሉ ጠቅሰዋል፡፡ የመጀመሪያው ዕድሜያቸው ከ13-15 የሚሆኑ ታዳጊዎች ከ2-4 ዓመት የሚሠለጥኑበት ሲሆን ሁለተኛው ደረጃ ደግሞ ዕድሜያቸው ከ16-19 የሚሆናቸው ወጣቶች ለ2ና 3 ዓመታት ሠርተው ለፕሮፌሽናል ደረጃ የሚደርሱበት ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካው አሰልጣኝ በበኩላቸው ወጣት አትሌቶችን ለማሠራት የአገራቸው የከፍተኛ የስፖርት ብቃት ማሰልጠኛ ተቋማት በመላው የአገሪቱ ክልሎች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡ በእነዚሁ አካዳሚዎች ከ3ሺ በላይ ወጣቶች በሁሉም የአትሌቲክስ የሜዳና የትራክ ስፖርቶች ከፍተኛ ስልጠና ይሰጣቸዋል ብለዋል፡፡  በደቡብ አፍሪካ በት/ቤቶችና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚደረጉ ዓመታዊ ውድድሮችንም ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት ምቹ መድረኮች እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡
የሜዳልያው ሰንጠረዥና የኢትዮጵያ ማራኪ ተሳትፎ
በሻምፒዮናው ኢትዮጵያ በሜዳሊያ ብዛት ቀዳሚ ሆና ብታጠናቅቅም በከፍተኛ የወርቅ ሜዳልያ ብዛት አንደኛ ደረጃ ለማግኘት የቻለችው ናይጄሪያ በ12 ወርቅ፣ በ8 ብርና በ7 ነሐስ ሜዳልያዎች ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ በ9 ወርቅ፣ በ7 ብርና በ7 የነሐሰ ሜዳሊያ ሁለተኛ ስትሆን ኢትዮጵያ በ6 ወርቅ፣ በ12 ብርና በ10 የነሐስ ሜዳሊያ ሦስተኛ ደረጃ አግኝታለች፡፡ናይጄርያ  የሜዳልያ ሰንጠረዡን በአንደኛነት በመምራት ለሁለተኛ ተከታታይ ሻምፒዮና ክብሯን አስጠብቃለች፡ ሁለቱ አትሌቶች የአጭር ርቀት ሯጩ ዲቫይን ኦዱዱሩ በወንዶች እንዲሁም በዝላይ ውድድሮች እና በ100 ሜትር ሩጯ ኤሴ ብሩሜ በሴቶች ሶስት የወርቅ ሜዳልያዎችን በማግኘት ስኬታማ ነበሩ፡፡ የናይጄርያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በሻምፒዮናው በተገኘ መነቃቃት ወደፊት በረጅም ርቀት የአትሌቲክስ ውድድሮች አትሌቶችን ለማፍራት ለስፖንሰሮች ድጋፍ ጥሪ እንዳቀረበ ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቶች ፍፁም የበላይነት ካደረጉባቸው የመካከለኛ እና የረጅም ርቀት ውድድሮች በተጨማሪ በሜዳ ላይ ስፖርቶች እና በአጭር ርቀት ጠንካራ ተሳትፎ ማድረግ ችለዋል፡፡ በ12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በተካፈሉት 39 አገራት 550 ተወዳዳሪዎች የተሳተፉ  በሻምፒዮናው ከቀረቡት 127 ሜዳልያዎች  (43 የወርቅ 43 የብርና 41 የነሐስ)   19 አገራት የየድርሻቸውን አግኝተዋል፡፡በወንዶች ምድብ 209 በሴቶች ምድብ 145 አትሌቶች የተካፈሉ ሲሆን በሻምፒዮናው ዳኝነት፤ አመራር እና ማስተናበር ከ172 በላይ የስፖርት ባለሙያዎች ነበሩ፡፡
ግብፅ በ13 ሜዳልያዎች (5 ወርቅ 3፣ ብርና 5 ነሐስ) ፤ ኬንያ በ12 ሜዳልያዎች (4 ወርቅ ፣  5 ብርና 3 ነሐስ) ፤ አልጄርያ በ5 ሜዳልያዎች (2 ወርቅ ፣ 1 ብርና 2 ነሐስ)  ፤ ቦትስዋና በ3 ሜዳልያዎች  (2 ወርቅና 1 ብር)  ፤ ሞሮኮ በ5 ሜዳልያዎች (1 ወርቅ ፣ 1 ብርና 3 ነሐስ)  ፤ ኡጋንዳ በ3 ሜዳልያዎች (1 ወርቅና 2 ነሐስ)  ፤ ቱኒዚያ በ2 ሜዳልያዎች (1ወርቅና 1 ነሐስ)  ፤ ዚምባቡዌ፣ ኮትዲቯርና እና ናሚቢያ እያንዳንዳቸው 1 የብር ሜዳልያ እንዲሁም ዛምቢያ፣ ኮንጎና ማዳጋስካር እያንዳንዳቸው 1 የነሐስ ሜዳልያ በማግኘት ከ4 እስከ 14 ያለውን ደረጃ አከታትለው አግኝተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በ12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ካሰለፈቻቸው አትሌቶች መካከል 2 አትሌቶች ከሜዳልያና ከዲፕሎማ ውጪ ሲሆኑ 2 አትሌቶች ከውድድር ውጪ መሆናቸውን ያስታወቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክሰ ፌደሬሽን 76 አትሌቶች ከወርቅ /ከ1ኛ/ እስከ ዲፕሎማ /7ኛ/ ያለውን ደረጃ በመያዝ ውድድራቸውን እንዳጠናቀቁ በማመልከት ሁኔታውይህ የተተኪዎችን የነገ ተስፋ አመላካች ውጤት በማለት አድንቆታል፡፡
በሻምፒዮናው ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ 28 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ የበላይ ነበረች፡፡ ከሰበሰበቻቸው 6 የወርቅ ሜዳሊያዎች 5ቱ በሴቶች የተገኙ ናቸው፡፡ ዮሚፍ ቀጀልቻ በወንዶች 5 ሺህ ሜትር ለሀገሩ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳልያ ሲወስድ፤ ሌሎቹ 5 የወርቅ ሜዳልያዎች በዘውዴ ማሞ 3 ሺህ ሜትር መሰናክል ሴቶች፤ በእታገኝ ማሞ 5ሺህ ሜትር ሴቶች፤ በኋላየ በለጠ 5ሺህ ሴቶች የዕርምጃ ውድድር ፤ በንጉሴ ብረስ በ3ሺህ ሜትር ሴቶች እንዲሁም በዳዊት ስዩም 1ሺህ 5 መቶ ሜትር ሴቶች አማካኝነት የተገኙ ናቸው፡፡
አስደናቂው የቲቪ ቀጥታ ስርጭት እና ቲቪ ሚዲያ ስፖርት
ለሻምፒዮናው የ4 ቀናት ውድድሮች በ22 የአፍሪካ አገራት የቀጥታ ስርጭት ሽፋን በመስጠት ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር የሰራው ተቀማጭነቱን በፈረንሳይ ያደረገው ቲቪ ሚዲያ ስፖርት ነበር፡፡ በዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮች አዘጋጅነት፤ የስርጭት ሽፋን፤ የማርኬቲንግ እና የመረጃ ስራዎችን በመስራት በአጭር ጊዜ ስኬታማ የሆነው የብሮድካስት ኩባንያው፤ ከበርካታ አገራት የስፖርት ፌደሬሽኖች ጋር በመስራት በተለይ ለአፍሪካ ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ እየተሳካለት መጥቷል፡፡
በ12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ 14 ካሜራዎች ለውድድሩ የቀጥታ ስርጭት ተግባር ላይ የነበሩ ሲሆን ከቲቪ ሚዲያ ስፖርት 45 ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ከ100 በላይ ባለሙያዎች በቅንጅት ሰርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በሻምፒዮናው የቀጥታ ስርጭት ከፍተኛ እገዛ ማድረጉን የሚገልፁት የቲቪ ሚዲያ ስፖርት መስራች ሄይዲ ሃመል፤ ኮርፖሬሽኑ ያሉት ካሜራዎች እና የድምፅ መሳርያዎች ከፍተኛ ደረጃ እና ብቃት ያላቸው መሆኑ እንዳስደነቃቸው ለስፖርት አድማስ ተናግረዋል፡፡ የፎቶ ፊኒሽ፤ የመረጃ እና የሰዓት አያያዝን ለማከናወን ተግባር ላይ የዋሉ መሳርያዎች የወቅቱን ቴክኖሎጂ በብቃት ያሳዩ መሆናቸውንም ገልፀዋል፡፡ የውድድሩ ስርጭት በአፍሪካ ብቻ አለመወሰኑን  የገለፁት ሄይዲ ሃመል፤  በአፍሪካ የወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በሳተላይት በመጠቀም በአንዳንድ አውሮፓ አገራት ሽፋን ለመስጠት ተችሏል ብለዋል፡፡
በሞስኮ የተካሄደውን 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፤ በዚያው በራሽያ የተደረገውን የሶቺ የክረምት ኦሎምፒክ እንዲሁም በሞሮኮ የተደረገውን የዓለም ክለቦች ዋንጫን ያስተላለፈው ቲቪ ሚዲያ ስፖርት በስፖርቱ ዙርያ ሲሰራ ከ11 ዓመት በላይ ሲሆነው በአውሮፓ እግር ኳስ፤ በዓለም አትሌቲክስ ከፍተኛ የስራ ድርሻ ያለው ሲሆን በተለይ በአፍሪካ የስፖርት እንቅስቃሴ የቲቪ ስርጭትን ለማሳደግ በከፍተኛ ዓላማ በመያዝ እንደሚንቀሳቀስ ይገልፃል፡፡ ቲቪ ሚዲያ ስፖርት በ2016 በብራዚል ሪዮዲጄነሮ የሚደረገውን 21ኛው ኦሎምፒያድ፤ ከ2014 ጀምሮ እስከ 2017 ሁሉንም የአይኤኤፍ ውድድሮች፤ ከ2004 ጀምሮ የአውሮፓዎቹን ታላላቅ ሊጎች የጣሊያኑን ሴሪኤ እና የጀርመኑን ቦንደስ ሊጋ በ43 አገራት በቲቪ የማሰራጨት ሙሉ መብቱን ይዟል፡፡

Read 1991 times