Monday, 16 March 2015 09:16

ኢሕአዴግኣዊ ዴሞክራሲ እና ሊብራሊዝም

Written by  ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ
Rate this item
(8 votes)

ካለፈው የቀጠለ
ባለፈው እትም የጽሑፌ ክፍል፣ ዴሞክራሲ እና ነጻነት ለመጎናጸፍ ይበጃሉ የሚባሉት ተቋማትን ገዥው ግንባር ኢሕአዴግ እንደምን መንፈሳቸውን ቀይሮ የራሱ የፖለቲካ መገልገያ እንዳደረጋቸው፤ የምርጫ ሥርዐቱን በምሳሌነት በማንሣት ለማብራራት ሞክሬአለኹ፡፡ እንደ ፓርላማ፣ የፍትሕና የሚዲያ፣ የመድበለ ፓርቲና የምርጫ ሥርዐት ማስፈጸሚያ ተቋማት በአገዛዙ የታለመላቸውን ዓላማ ለማሳካት አወቃቀራቸው ብቻ ሳይኾን ኦሆ ባይ አንቀሳቃሾቻቸውም/yes men/ ያስፈልጓቸዋል። ያለ ኦሆ ባይ አንቀሳቃሾች መዋቅሮቹ እንደማይሠሩ ብረዳም በምሳሌነት በአነሣኹት የነጻ እና ፍትሓዊ ምርጫ አወዳዳሪ ተቋም አግባብ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ እና ለሰብሳቢው ፕሮፌሰር መርጋ በቃና የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለማቅረብ እወዳለኹ፡፡
በ‹‹አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ›› አመራር መካከል ተፈጠረ ለተባለው ውዝግብ፣ የሚመሩት ተቋም በተለይም እርስዎ ጉዳዩን ተቀብለው በዐደባባይ ለማሸማገል መሞከርዎ አስገርሞኛል፡፡ ምርጫን ለማስተዳደር የተመሠረተ ተቋም ጉዳዩን በዐደባባይ በቴሌቪዥን ሽምግልና ለመፍታት መሞከሩ በየትኛው ሕጋዊ፣ ሞራላዊና ልማዳዊ አሠራር ነው ተቀባይነት የሚኖረው?
እርስዎ በ‹‹ታዛዥነቱ›› የፈረዱለትን የፓርቲውን አንድ ቡድን የሚመራው አቶ ትዕግሥቱ አወሉ፣ በፓርቲው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ወቅት በአባሉ ዘንድ የነበረው የተቀባይነት ኹኔታ ለራሱ ከሰጠው ድምፅ በቀር በድምፅ አልባነት የተገለጸ ነበር፡፡ ይህን ከራሱ ውጭ አንዳችም የድጋፍ ካርድ ያላገኘበትን መድረክ እና ብያኔውን ችላ ብሎ ሌላ ስብስብ ፈጥሮ በአቋቋመው መድረክ አካሔድኹት ያለውን የምርጫ ውጤት ቦርዱ እንደምን ተቀበለው?
በአቶ አበባው መሐሪ የሚመራው የመኢአድ ቡድንና የኢንጅነር ግዛቸው ሺፈራው ‹‹የአንድነት ለዴሞክራሲና ፍትሕ ፓርቲ›› ሊዋሐዱ ቅድመ ዝግጅቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ጽ/ቤትዎ፣ ‹‹የአቶ አበባው መኢአድ ያላሟላው ጉዳይ አለ፤›› በሚል ምክንያት አመራሩ ሕጋዊ እንዳልኾነና መዋሐዱም ተቀባይነት እንደማይኖረው ገልጸው ነበር፡፡ ይህን ታላቅ የኅብረ ብሔራዊ አንድነት ኃይል መዋሐድ አክሽፈው ሲያበቁ፣ በመኢአድ አመራሮች መካከል ልዩነት ሲፈጠር ደግሞ ትላንት ሕጋዊ አይደለም ያሉትን የአቶ አበባው መሐሪ አመራር ዕውቅና የመስጠትዎ የፖሊቲካ ዥዋዥዌ በእጅጉ አስገርሞኛል፤ አሳዝኖኛልም፡፡    
፫. ዐውደ ፍትሕ
በዚኽ ሦስተኛው የመጣጥፉ ክፍል በጣም አሳሳቢ በኾነው የፍትሕ ጉዳይ ላይ አንዳንድ ሐሳቦችን አቀርባለኹ። ፍትሕን በሚመለከት፣ በአገራችን ካለፈው ሥርዐት በተለየ የተወሰኑ መሻሻሎችና መስተካከሎች ቢታዩም፣ አኹንም ቢኾን ትልቅ የፍትሕ ክፍተት አለ የሚል እምነት አለኝ።
በፍትሕ ኀልዮት ታሪክ ውስጥ ወሳኝ ድርሳናት የጻፉ ሰዎች እንደሚያቀርቡት፣ ‘ፍትሕ’ በጥቅሉ ኹለት ዐበይት መደቦችን የያዘ ፅንሰ ሐሳብ ነው፤ እኒኽም ‘ሰብስታንቲቭ ጀስቲስ’ (ፍሬ-ነገራዊ ፍትሕ) እና ‘ፕሮሲጀራል ጀስቲስ’ (ወጋዊ ፍትሕ) ይባላሉ። ከኹለቱ የፍትሕ አመለካከቶች በመነሣት በአገራችን ውስጥ የሚታዩትን ችግሮች ለማሳየት እሞክራለሁ።
ስለ ‘ሰብስታንቲቭ ጀስቲስ’ በምናወራበት ጊዜ፣ በርእሰ ነገሩ ላይ ወሳኝ ድርሳን የጻፉትንና ለብዙ ዓመታት በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ያስተማሩትን ጆን ሮውልስን ሳንጠቀስ አናልፍም። ‘የፍትሕ ንድፈ ሐሳብ’ (A Theory of Justice) በተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ ጆን ሮውልስ ፍትሕን በተመለከተ ባስቀመጡት አስተምህሮ፣ አንድን ሥርዐት ፍትሐዊ ነው የምንለው÷ ዜጎች በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ኹሉም ተቋማት ውስጥ ገብተው ሥራ ለመያዝ ወይም ለመገልገል (በጨረታም ኾነ በሌላ መልኩ ለመሳተፍ) በፆታ፣ በብሔር እና በመደብ ሳይኾን እንደየችሎታቸው ብቻ ተመርጠው ለመሳተፍ ሲችሉ ነው። የአገራችን ብሂል “ከዕንጨት መርጦ ለታቦት፣ ከሰው መርጦ ለሹመት” ይለዋል፤ የጆን ሮውልስን ሐሳብ። በአኹኑ ሥርዐት ግን ያ ተቀልብሶ “ከዕንጨት መርጦ ለታቦት፣ ከብሔር መርጦ ለሹመት” ኾኗል።
በኹለተኛ ደረጃ፣ ፍትሕን በሚመለከት ማይክል ቫልዘር የተባለው ዕውቅ አሜሪካዊ ምሁር ‘Spheres of Justice’ በሚለው መጽሐፉ ውስጥ ያሰፈረውን እንመልከት። ቫልዘር ያቀረበው ሐሳብ ጥንት አፍላጦን ስለ ‘ፍትሐዊት ከተማ’ ካቀረበው የፍትሐዊነት ሐሳብ ጋር ትስስር አለው። አፍላጦን የሰው ልጅን በሦስት መደቦች ይከፍላል፤ አንደኛ፣ ኅሊናዊነት ያመዘነባቸው፤ ኹለተኛ፣ ልባምነት ያመዘነባቸው፤ እና ሦስተኛ፣ አምሮታዊነት ያመዘነባቸው ናቸው። አፍላጦን፣ እኒኽን መደቦች ከለየ በኋላ፣ አንዲት አገር ፍትሐዊነትዋ የሚሠምረው ሦስቱ መደቦች በአገሪቱ ውስጥ ልከኛ ቦታዎቻቸውን ሲይዙ መኾኑን ይናገራል፡፡ ይኸውም ኅሊናውያኑ ሀገር መሪ፣ ልባውያኑ ሀገር ጠባቂ፣ እና አምሮታውያኑ አምራች ሲኾኑ ነው፣ ይላል።
ቫልዘርም በበኩሉ፣ በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ፍትሕ የሚዋቀርባቸው ልዩ ልዩ ዐውዶች አሉ፤ የእኒኽም ሥምረትና ኅብር ለማኅበረሰቡ የፍትሕን መልካም ጽዋ ያስጎነጫሉ፤ ነገር ግን ከዐውዶቹ መካከል አንዱ እንኳ ያለቦታውና ያለግብሩ ከዋለ ፍትሕ ትዛባለች። ለምሳሌ፣ ገንዘብ አንድ የራሱ ተገቢ ዐውድ ማለትም የሚንቀሳቀስበት የራሱ ተገቢ ምሕዋር አለው፡፡ ከዚኽ ዐውድ ወጥቶ ወደ ሌላ ዐውድ ውስጥ ጥልቅ ቢል ግን፣ ያኔ ፍትሕ አጉል ትኾናለች። ገንዘብ ከመገበያያነት ዐውድ ወጥቶ ለፖለቲካዊ ተጽዕኖ ማሳረፊያነት ከዋለ፣ ኀጢአት ማስተስረያ ከኾነ፣ የዳኝነት ውሳኔን ካስለወጠ… ወዘተ የአንዲት አገር የፍትሐዊነት ዐውዶች መስመሮቻቸው ይዘበራረቃሉ።
ዛሬ በአገራችን ‘ብሔር’ እና ‘ልማት’ ዐውዳቸውን ስተው ያለግብራቸው ውለዋል። በመጀመሪያ ‘ብሔር’ የሚለውን ብንወስድ፣ የብሔር እኩልነትና ተዋፅኦ በሚል ፈሊጥ፣ የግለሰቦችን የብሔር አባልነት ብቻ በማየት ዐቅማቸው ከሚፈቅደው በላይ ሓላፊነት እንዲሸከሙ ኾነዋል። ይህ ደግሞ በሹመትና በሥራ ውጤት መሀል ትልቅ ክፍተት ይፈጥራል። እዚህ ላይ፣ የብሔር እኩልነት የሚለው ጥሪ በጎ ቢኾንም፣ አኹን ግን ከገደቡ ወጥቶ፣ ጥንት ሰዎች ሹመትን በሐረገ ትውልድ/ውልደት/ መስፈርት ከሚያገኙበት ባላባታዊው ሥርዐት ጋራ ተመሳስሏል።
ከአንዲት አገር የፍትሕ ዐውዶች መካከል አንዱ ፖለቲካ ነው፤ ፍትሐዊ ይኾንም ዘንድ በውስጡ ሌሎች ዐውዶች ሊጥሱት አይገባም። በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ግን የፖለቲካ ምሕዋሩ በሌሎች ዐውዶች እየተጣሰ ነው። ብሔር ያለቦታው፣ ያለግብሩ ለፖለቲካዊ ሹመት በመስፈርትነት ውሏል፤ በዚኽም የፖለቲካ ዐውድ ተጥሷል፤ ይህም በጥቅሉ የአገሪቱ ‘ዐውደ ፍትሕ’ ላይ ተጽዕኖውን አሳርፏል። ለፖለቲካዊ ሹመት መስፈርቱ ፖለቲካዊ አስተዳደርን መቻል እንጂ፣ የዚኽኛው ወይም የዚያኛው ብሔር አባል መኾን የለበትም።
በሌላም በኩል እንዲኹ፣ ኢሕአዴግ በተደጋጋሚ “አመርቂ ግስጋሤ እያስመዘገብኹ ነው” የሚልበት የልማት ዐውድ የራሱን ምሕዋር ጥሶ ብቸኛ የፖለቲካዊ ቅቡልነት አለኝታ ተደርጎ እየቀረበ ነው፡፡ አንዳንዴ ከዚኽም አልፎ፣ ለዴሞክራሲ ዕጦት ሐዘናችን እንደ መጽናኛ ለመቅረብም ይዳዳዋል። ኢኮኖሚያዊ ልማትን የነገሮች ኹሉ ፍጻሜና ማማ አድርጎ ማቅረብ አንዳንዴ በግላጭ፣አንዳንዴም በደፈናው የጊዜያችን ዜማ ኾኗል።
ብሔርም ኾነ ልማት በራሳቸው ዐውድ ውስጥ እስከቆዩ ድረስ መልካም ናቸው፤ ችግሩ ግን ከላይ እንዳልነው፣ የራሳቸው አልበቃ ብሏቸውና ከምሕዋራቸው ወጥተው ሌላውን መጣስና መዋጥ ሲጀምሩ ነው። በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ነገሮችን ኹሉ ከአንድ ነጠላ ዐውድ አንጻር መገንዘብ ተገቢ አይደለም። ለምሳሌ÷ ዐርበኛነትንም ሥነ-ጥበባትንም ባህላዊ እሴቶችንም ጤና ጥበቃንም… ወዘተ ከልማት አጋርነት አንጻር ብቻ መመልከቱ ተገቢ አይኾንም። በምንም ዐይነት ድንጋጌ ዐርበኛነት እና ልማት አንድ አይደሉም። ዐርበኛነት የራሱ ዐውድ አለው፤ ልማትም እንዲኹ። ስለ ዐርበኛነት ሲነሣ የመድፉ ባለሟል ሻቃ በቀለ ወያ ከዐርበኞች መሀል ትዝ ሊሉን ይችላሉ፤ እንዲኹም ስለልማት ሲነሣ አቶ በቀለ ሞላ ትዝ ሊሉን ይችላሉ። ለኹለቱም በየዐውዳቸው ትልቅ ቦታ ሊሰጣቸው ይችላል። ኾኖም የነጻነት ፋኖው በጀግንነቱ፣ የልማት ታታሪውም በታታሪነቱ መወሳት አለባቸው እንጂ ልማትን አውራ እሴት በማድረግ ዐርበኛነትን የልማት ገላጭ ማድረግ የለብንም።
ባለፈው ሥርዐት ዐብዮትን ብቻ የኹሉ ነገር ማማ በማድረግ ጣታችንን ተቃጥለን ነበር። አኹን ደግሞ ብሔር እና ልማት የሚሉ ነጠላ ፅንሰ ሐሳቦችን ብቻ ይዘን፣ እኒኽንም ከኹሉ ነገር በላይ በመስቀላችን፣ በአንድ አገር ውስጥ ሊኖሩ የሚገባቸውን ሌሎች በጎ ነገሮችን እየደፈጠጥን ነው። ኹልጊዜ አንድ ነጠላ ነገርን መርጦ የበላይ ማድረግ፣ የብዙ ዐውዶች ሕብር ልትኾን የሚገባትን ፍትሐዊት አገር ያሳጣናል።
ልማትን በተመለከተ ያለኝ ተጨማሪ ትዝብት፣ አገሪቱ ካለፈው ጊዜ የተሻለ ደረጃ ላይ ናት ሲባል፣ የኢሕአዴግ አቀራረብ የሕዝቡን ታታሪነትና ሥራ ወዳድነት ወደ ጎን በመተው ኹሉን ነገር በራሱ ብቻ እንዳስገኘው አድርጎ ለማሳየት መጣጣሩ ተገቢ አይደለም፡፡ በልማታዊነቱም ቢኾን ከብክነት፣ ከጥራትና ከአድልዎ አኳያ በሦስተኛና ገለልተኛ ወገን ለመፈተሽ ዕድሉ ሳይሰጥ ‹ሠሪው ፈጣሪው እኔ ነኝ› በሚል ፈሊጥ ምንጊዜም የፖሊቲካ ሽልማቱን ለመውሰድ ይሽቀዳድማል፡፡  
‘ፕሮሲጀራል ጀስቲስ’ን በተመለከተ፣ ዕውቅ አስተምህሮ የጻፈው ፕሮፌሰር ስቱዋርት ሃምሻየር (Stuart Hampshire) “ፍትሕ ግጭት ነው” (Justice is Conflict) በተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ እንደሚሉት፣ የሰው ልጅ ከጭቅጭቆችና ከግጭቶች ነጻ ባይኾንም፣ ፍትሕ ርትዕ ይሰፍን ዘንድ ኹሉም ወገኖች የሚደመጡበትና ሐሳባቸውን የሚያቀርቡበት መድረክ ሲኖር ነው፤ ካሉ በኋላ፣ የጥንት ሮማውያንን አባባል፣ “የሌላውንም ወገን ድምፅ ስማ” (Audi alteram partam) የሚለውን ምክር ይለግሳሉ።
ለማጠቃለል፣ የዴሞክራሲ መሠረታዊ ግብ የሚሠምረው፣ በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የተለያዩ ሠናያት እና ግቦች ባሏቸው ግልጋሎቶችና እሴቶች በሕዝቡ ተመዝነው ነገሮቹ እርስ በርስ በኩታ ገጠምነት መሔድ የሚችሉበትን ምርጡን መንገድ በነጻነት መምረጥ ሲቻል ነው። ምርጫው በጫና የመጣ ሳይኾን በሕዝቡ ነጻ ፈቃድ የተመረጠ መኾን አለበት፡፡ ይህም የልዩ ልዩ ሐሳቦች ተዋፅኦና ነጻ የአመለካከቶች መንሸራሸርን የግድ ይላል፡፡ ይህን መገደብ ዴሞክራሲንም መገደብ ነው።
በአኹኑ ወቅት በኢሕአዴግ በኩል ሲባል የምንሰማው፣እኛ የምናወጣቸው ፖሊሲዎችና የምናስፈጽማቸው ተግባራት ‘ትክክለኛውን አቅጣጫ’ የተከተሉ ስለመኾናቸው እርግጠኞች ነን፤ የሚል የፍጹማዊነት መርሕ ነው። ይህም በመኾኑ ለተለያዩ አመለካከቶች መንሸራሸር ቦታ ተነፍጓል፤ ለዴሞክራሲ ማበብም ትልቅ መሰናክል ፈጥሯል። ፍጹም እርግጠኛነት የተለያዩ አመለካከቶች መንሸራሸርን የሚገድብ ብቻ ሳይኾን ለዴሞክራሲም ቀንደኛ ጠላት ነው።
በመግቢያው ውስጥ እንደጠቀስኩት ጽሑፌን የማጠቃልለው ለአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በአጭሩ በማቀርበው ‘ግልጽ ደብዳቤ’ ነው።
ይድረስ ለተከበሩ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር፤
በቅድሚያ ሰላምታዬ ይድረስዎ እያልኹ በአክብሮት ማስታወሻዬን እጀምራለኹ። እንደ እውነቱ ከኾነ፣ ማስታወሻም ኾነ ደብዳቤ ለእርስዎ ለመጻፍ ሐሳብ አልነበረኝም፡፡ የመጀመሪያ ዕቅዴ ለፕሮፌሰር መርጋ በቃና ትችታዊ ደብዳቤ መጻፍ ነበር። የትችቱም ይዘት በዋናነት የሚያተኩረው፣ በአንድነት ፓርቲ ውስጥ ተነሣ ለተባለው “መከፋፈል” እርሳቸው ከማሸማገል ጀምረው እስከ ውሳኔ አሰጣጥ ድረስ የሔዱበትን መንገድ የተመለከተ ነበር። ኾኖም ግን፣ እርስዎ በፓርላማ ቀርበው ስለዚኹ ጉዳይ በተጠየቁ ጊዜ ፕሮፌሰር መርጋ በቃናን እና ምርጫ ቦርዱን መሔስና መተቸት በሕግ ሊያስጠይቅ ይችላል፤ ብለው ስላሉ፣ ፕሮፌሰር መርጋ በቃናን ተችቼ በሕግ ከመጠየቅ፣ አንድ ፊቱን፣ እንደ አንድ ዜጋ፣ ትችቴን ወደ እርስዎ አቅርቤ፣ ሕግ ፊት የሚያስቀርበኝም እንደኾነ፣ በእርሳቸው ሳይኾን በእርስዎ ስም ለመቅረብ መርጬአለኹ።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ በዴሞክራሲ ሥርዐት ውስጥ፣ “ዐለቀ፣ ፍጻሜውንም አገኘ” ተብሎ የሚዘጋ አንዳችም ፖለቲካዊ ሐሳብና አመለካከት የለም። ኹሉም ፖለቲካዊ እይታዎች ለውይይት፣ ለጥያቄ፣ ለትችትና ለተደጋጋሚ ፍተሻ ኹሌም ክፍት መኾን አለባቸው። ለዚኽ ማሳያ ይኾን ዘንድ፣ አኹን በቅርቡ ከዐርባ ዓመታት በላይ የአሜሪካ የፖለቲካዊ ሳይንስ ክፍል ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድረዋል ከሚባሉ ጥቂት ምሁራን መካከል አንዱ የኾኑት ፕሮፌሰር ሮበርት ዳል (Robert Dahl) ስለ የአሜሪካ ሕገ መንግሥት የጻፉትን ትንሽ እጠቅስ ዘንድ ይፈቀድልኝ።
ፕሮፌሰሩ፣ ‘’የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ምን ያኽል ዴሞክራሲያዊ ነው?’’ (How Democratic is the American Constitution?) በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ የሚከተሉትን ወሳኝ ጥያቄዎች አቅርበዋል።
አንደኛ፣ ዐሥራ አንድ ስቴቶች እና ሠላሳ ዘጠኝ እንደራሴዎች ብቻ ከዛሬ ኹለት መቶ ዓመታት በፊት ያረቀቁትንና የፈረሙትን ሕገ መንግሥት ዛሬ ለምን እንቀበላለን? እውን፣ አብዛኞቹ አሜሪካውያን እንደሚሉት፣ ሕገ መንግሥቱን የምንከተለው የዜጎችን ኹሉ ቅቡልነት ስላገኘ ነውን? ብለው ይጠይቁና ምላሹን ለማግኘት ሌላ ጥረት ሳያስፈልጋቸው፣ ግን እስኪ፣ ይህን መጽሐፍ ከምታነቡ ዜጎች መካከል ምን ያኽላችሁ ለሕገ መንግሥቱ ቅቡልነትን ትሰጡ ዘንድ ተጠይቃችኹ ሰጥታችኋል? ሲሉ ይሞግታሉ።
ኹለተኛ፣ አንዳንድ አሜሪካውያን፣ የምንከተለው ሕገ መንግሥት ከዓለም ምርጡ ነው፤ ብለው እንደሚናገሩ ፕሮፌሰሩ ያወሱና ይህ አባባል እውነት ከኾነ፣ ለምን ኻያ ሦስት የዓለም ታላላቅ ዴሞክራሲዎች የአሜሪካን ሕገ መንግሥት ነጥብ በነጥብ አልገለበጡም? ሲሉም ይጠይቃሉ። የፕሮፌሰር ሮበርት ዳል ዋነኛ ዓላማ፣ የአሜሪካ ሕገ መንግሥትን ማስቀየር ሳይኾን፣ ሕዝቡ ስለ ሕገ መንግሥቱ ያለውን ዶግማዊ አመለካከት ሽሮ ዳግም ወደ ውይይትና ፍተሻ ይገባ ዘንድ ለመጎትጎት ነው። ኹለት መቶ ዓመታት የሞላውና በዓለም ላይ አድናቆትን ያተረፈው የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ጥያቄና ትችት የሚቀርብበት ኾኖ ሳለ፣ ኻያ ዓመታት ብቻ ያስቆጠረው የአገራችን ሕገ መንግሥት ላይ ጥያቄ በሚነሣ ጊዜ፣ ሕገ መንግሥቱን “ለማፍረስ (ለመናድ)” በሚል ፈሊጥ ዜጎች ዴሞክራሲያዊ ውይይት የሚያደርጉባቸው መንገዶች መዘጋት የለባቸውም።
ከላይ ፕሮሲጀራል ጀስቲስን በተመለከተ እንደጠቀስነው፣ እንደ እርስዎ በከፍተኛ የአገር መሪነት ቦታ ላይ የተቀመጠ ሰው የአንድ ወገንን ድምፅ ብቻ ሳይኾን፣ የሌላውንም ወገን አመለካከትና ስሞታ ማድመጥ እንደሚኖርበት ያውቃሉ የሚል እምነት ቢኖረኝም፣ አንድነት ፓርቲን በተመለከተ በፓርላማ ቀርበው የሰጡት አስተያየት ይህንኑ በተግባር አላሳየኝም። ይህም የኾነው በአንድ በኩል፣ ትክክለኛ መረጃ ስላልደረስዎ ሊኾን ይችላል፤ በሌላ በኩል ደግሞ፣ የሌላውን ወገን ስሞታ ለመስማት ተገቢውን አትኩሮት ስላልሰጡ ሊኾን ይችላልና እንደ አንድ ዜጋ ቅሬታ አድሮብኛል።
በአንድ አገር ውስጥ ኅብረተሰባዊ ሒስ ከተከለከለና መንግሥት ነጠላ አመለካከትን አንግሦ ሌላ ተፃራሪ ሐሳቦችን ሳያስተናግድ ከሔደ፣ የዴሞክራሲ ጎዳና ተብሎ የተሰየመው በስም ብቻ ኾኖ ፍሬ ሳያፈራ ይመክናል። ከእርስዎና ከአመራሩ ክፍል፣ አገሪቱ በሕዳሴ ጎዳና ላይ እንደምትገኝ በተደጋጋሚ ተነግሮናል። ኾኖም ግን፣ እኔ እስከማውቀው ድረስ፣ ከዚኽ ቀደም የሠመረ ሕዳሴ ያካሔዱ አገሮች በሙሉ ሕዳሴንና ትችትን በመነጣጠል ሳይኾን በአንድነት ይዘው የዘለቁ ናቸው። ይህም የሚኾንበት ምክንያት፣ የሕዳሴ ፅንሰ ሐሳብ በራሱ ትችትን አካትቶ የያዘ ፅንሰ ሐሳብ ነው።
ለማጠቃለል፣ እርስዎ ጠቅላይ ሚኒስትር በኾኑ ጊዜ በኹለት ጉዳዮች የተነሣ ብዙ ኢትዮጵያውያን ደስ ብሏቸዋል፡፡ ይኸውም አንደኛ፣ እርስዎ የተገኙበት የፖለቲካ ምኅዳር ኢትዮጵያን በሚመለከት “ሐምሌታዊ ጭቅጭቅ” (የመኾን አለመኾን አተካራና ውልውል) ከሌለበት ክፍል በመኾኑ፤ ኹለተኛ፣ እርስዎ ጠመንጃ ታጥቀው ወደ ሥልጣን የመጡ ባለመኾኑ፣ አገሪቱ ልታደርግ ለሚገባት የሲቪል አስተዳደር ሽግግር መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ተብሎ በመታሰቡ ነው። ኾኖም ግን፣ ሕዝብ በእርስዎ ላይ ያሳደረው ይህ በጎ አመለካከት እንዳይመክን ተጠሪነትዎ ለአንድ ፓርቲ ሳይኾን፣ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትርነትዎ ለመላው የአገሪቱ ሕዝብ መኾኑን ምንጊዜም ባይዘነጉ የሚል ማዘከርያ(ማስታወሻ) አለኝ።
ክቡርነትዎ መዘንጋት የሌለበት፣ ከዚኽ ቀደም በዐድዋ፣ በማይጨው እና በባድመ ከወራሪ ጠላት ጋር ተናንቆ ሉዓላዊነቱን ያስከበረው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፤ በሌላ በየትኛውም ክፍል ቢኾን የተዋደቀውም አገሬ ተደፈረች በማለት እንጂ ውለታ ለማስቆጠር አልነበረም፡፡ ካለፈው ሥርዐትም ጋር ቢኾን መገዳደሉ ከእርስ በርስ ጦርነት የተነሣ እንጂ አንዱ የኢትዮጵያ ክፍል ከሌላው ኢትዮጵያዊ ካሳ የሚጠይቅበት ጉዳይ ኾኖ አይደለም፡፡ በሌላው ዓለም በቅርቡ የተካሔዱት የእርስ በርስ እልቂቶች (ከአሜሪካ እስከ ስፔን) የሚያረጋግጡትም ለጉዳቱ የጋራ መፍትሔ ማበጀትን እንጂ የአንዱ ከሌላው የበደል ካሳ መጠየቅን አይደለም፡፡
ክቡር አቶ ኃይለ ማርያም፣ ያለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ‹‹ኢትዮጵያዊ›› እንዲኾኑ የብዙ ሰው ጸሎትና ተማጥኖ ነበር፡፡ እርስዎ ደግሞ እውነተኛ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር›› እንዲኾኑ ምኞታችን ነው፡፡ በመኾኑም ክቡርነትዎ ምልዓተ ሕዝቡ የሚፈልገውን እንዳይኾኑ መሰናክሎች ቢበዛብዎትም ጫናውን ተቋቁመው የብዙኃኑ ተምኔት ይደርስ ይፈጸም ዘንድ እመኛለኹ፡፡
ከፍ ካለ አክብሮትና ምስጋና ጋር

Read 3738 times