Monday, 09 March 2015 11:34

ገብሩ አስራት - ከህወሐት እስከ አረና

Written by 
Rate this item
(14 votes)

     በቅርቡ “ሉአላዊነትና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ባወጡት መፅሐፍ የመጀመርያዎቹ አራት ምዕራፎች ላይ ራስዎንም ጭምር እየተቹ ፅፈዋል፡፡ የ1993 ክፍፍልና ከዚያ በኋላ ያለውን በሚተርከው ክፍል ላይ ግን ብዙ የተድበሰበሱ ጉዳዮች እንዳሉ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ….
እኔ ይሄን መጽሐፍ በሁለት አላማዎች ነው የፃፍኩት። አንዱ አላማ በኢትዮጵያ የሉአላዊነት ጉዳይ ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ ማስገንዘብ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ሂደት በ40 አመት ውስጥ ከየት ወዴት እንደደረሰ ለማሳየት ነው፡፡ ስለዚህ ሰዎች ይሄን ግንዛቤ እንዲይዙ ከራሴ ልምድና ከነበርኩበት ድርጅት አጠቃላይ እንቅስቃሴ በመነሳት የተቻለኝን ሁሉ አስቀምጫለሁ የሚል አስተያየት አለኝ፡፡
እኔ መጽሐፉ ከወጣ በኋላ ከደረሱኝ አስተያየቶች ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ነገሮችን በግልጽ ማስቀመጤን የሚጠቁ ሲሆን እንዲያውም አንዳንዱ ከሚጠበቀው በላይም ተገልጿል የሚል ነው፡፡ በህወሐቶች ዘንድ ደግሞ አላስፈላጊ የሆኑ ሚስጥሮች አውጥቷል ተብሎ እንደሚታሰብ ተገንዝቤአለሁ፡፡ እኔ ግን ህሊናዬና አቅሜ በሚፈቅደው የተቻለኝን ያህል እውነታውን ገልጨዋለሁ፡
በግልፅ አልተብራራም ከተባሉት መካከል በ1993 ክፍፍል ወቅት እርስዎን ጨምሮ አቶ ስዬ፣ አለም ሠገድ፣ አባይ ፀሐዬ… በአቶ መለስ ቦናፓርቲዝም ዙሪያ ያቀረባችሁት ጽሑፍ በሚገባ አልተጠቀሰም የሚለው ይገኝበታል፡፡ ምን አይነት ጽሑፎች ነበሩ የቀረቡት?
በኔ በኩል ስለ መለስ ቦናፓርቲዝም በመጽሐፉ ውስጥ በዝርዝር አስቀምጫቸዋለሁ፡፡ የመለስ አቋም፤ በኢትዮጵያ አመራር ውስጥ ቦናፓርቲዝም በግልፅ ተከስቷል የሚል ነበር፡፡ የቦናፓርቲዝም ዋናው ጉዳይ ደግሞ ሙስናና ፀረ ዲሞክራሲያዊነት ነው ብሏል፡፡ የኛ ጽሑፎች ከዚህ የተለዩ ናቸው፡፡
የቦናፓርቲዝም ንድፈ ሃሳብ መለስ ከአስቀመጠው የተለየ ትርጉም ነው ያለው፡፡ የቦናፓርቲዝም ዋናው ቁምነገር ሁለት ሃይሎች/መደቦች ለመጠፋፋት ከጅለው፣ ይሄን መጠፋፋት አስታርቆ የሚመጣ መካከለኛ መንግስት ማለት ነው፡፡ በመለስ አገላለጽ ግን ቦናፓርቲዝም ሙስናና ፀረ ዲሞክራሲ ስርአትን ለማንገስ የመጣ ስርአት ነው፡፡ ከዚያ በላይ በእኛ ፅሁፎች በስፋት የተገለፀው መለስ በወቅቱ የነበረውን የኢትዮጵያን ችግር በስፋት አላቀረበም የሚል ሃሳብ ነው፡፡ በወቅቱ ከነበረው ትልቅ ችግር ለመሸሽ የተዘጋጀ ጽሑፍ ነው የሚል አቋም ነው የያዝነው፡፡ ምክንያቱም የወቅቱ ትልቁ የኢትዮጵያ ችግር የሉአላዊነት መደፈር ነው፡፡ በተለይ በኤርትራ መንግስት የተቃጣብን ወረራ በልማታችን ላይ ያስከተለውን ችግር ሣይናገር፣ ሌላ ጉዳይ አንስቶ ከዋናው አጀንዳ አፈግፍጓል ብለን ነው በጽሑፋችን ያስቀመጥነው፡፡ ሉአላዊነት ሲባል የድንበር ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ በሀገራችን፣ በህዝባችን፣ በመንግስታችን ላይ የተቃጣ መሆኑም ጭምር ነው። መለስና ጓደኞቹ ለውጭ ጫና ተንበርክከው፣ በወቅቱ ከእውነታው ሸሽተዋል የሚል ነው የጽሑፋችን ጭብጥ፡፡ እሱ ደግሞ ዋናው ጉዳይ የሙስናና የዲሞክራሲያዊነት ነው፤ የሉአላዊነት ጉዳይ ውጫዊ ጉዳይ ነው ብሎ ነው ያቀረበው፡፡ በአጠቃላይ አቶ መለስ ያቀረበው ጽሑፍ ከሉአላዊነት አጀንዳ የመሸሽ ነው፡፡
ከእናንተ ጋር አብረው አቶ መለስን ሲቃወሙ የነበሩት አቶ አባይ ፀሐዬ እንዴት ወደ አቶ መለስ ቡድን ተመለሱ?
ይሄን መመለስ ያለበት አባይ ራሱ ነው፡፡ እኔ እስከማውቀው ግን አቶ አባይ የመለስን አቋም ይቃወም ነበር፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በተለይ ወረራውን በተመለከተ አቶ መለስ የወሰደው አቋም የተሣሣተ ነው በሚል ይቃወም ነበር፡፡ የእነ አቶ መለስ ቦናፓርቲዝም አስተሳሰብ ከሃገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የወጣና ያፈነገጠ ጉዳይ ነው ብሎ አጥብቆ ተከራክሯል፡፡ እንግዲህ የክፍፍላችን ሁኔታ የተጠናቀቀው በፖለቲካዊ ውይይት አይደለም፡፡ አቶ መለስ የሠራዊቱንና የደህንነቱን ጣልቃ ገብነት ተጠቅሞ ነው ያሸነፈው እንጂ በውይይት አላሸነፈም፡፡ አስቀድሞ ሠዎችን በመግዛት በማስፈራራት ነው ያሸነፈው፡፡ አባይም ምናልባት ይሄን ጫና መቋቋም አቅቶት ይሆናል እንጂ እስከመጨረሻው ያለውን ሃቅ ያውቀዋል፡፡
እስከመጨረሻው የክፍፍሉ ሰአት ድምፅም ሠጥቷል፡፡ ከታገዱት 12 ሰዎች ውስጥም አንዱ እሱ ነበር፡፡ የመለስን አቋም እቀበላለሁ ብሎ መግባቱ የመለስን ጫና መቋቋም አቅቶት ሊሆን ይችላል፡፡ በወቅቱ ውስጥ ገብቶ መታገል ነው የሚያዋጣው ብሎ ነበር፤ ከገባ በኋላ ግን እንዳለው አልታገለም፡፡ የህወሓት ችግር እየባሰበት ሄደ እንጂ የለወጠው ነገር የለም፡፡ ዋናው መልስ መስጠት ያለበት እሱ ቢሆንም የኔ መላምት በአቋሙ መዝለቅ ያቃተው ጫና በዝቶበት ሊሆን ይችላል የሚል ነው፡፡
ግብርናን ኮሜርሻላይዝድ ለማድረግና ሜጋ ፕሮጀክቶችን በሀገሪቱ እንዴት መተግበር እንደሚቻል የሚያመላክት የስትራቴጂ እቅድ ነድፈው ለአቶ አዲሱ ለገሠ ሰጥተው ነበር፡፡ ከዚያ እቅድ ውስጥ ኢህአዴግ እስካሁን ተግባራዊ ያደረገው አለ?
ብዙም አይመስለኝም፡፡ ያኔ አቶ መለስ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ይቃወም ነበር፡፡ እኛ ደግሞ ኢንዱስትሪው መምራት አለበት፣ ትላልቅ የመስኖ ስራዎች መተግበር አለባቸው፡፡ እርሻም መሠረቱን በሚለውጥ መንገድ መሄድ አለበት እንል ነበር፡፡ ከተሞችም በተጠና መንገድ ማደግ ነው ያለባቸው፡፡ ግብርና መር እያሉ እዚያው መንከባለል ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ አያመጣም… የሚል አስተያየት ነበር ያቀረብኩት፡፡
በቅርቡ የ5 አመት እቅድ ብለው በነደፉት ላይ ኢንዱስትሪ መር እናደርጋለን ብለዋል፡፡ ሁኔታው አስገድዷቸው ሊሆን ይችላል፡፡ የሄዱበት መንገድ ለውጥ አለማምጣቱን ተረድተው ይሆናል፡፡ ሆኖም መሠረታዊ መዋቅራዊ ለውጥ እስካሁን ድረስ አልመጣም፡፡ ያኔ እነሱ የሚያዳምጥ ልቦና አልነበራቸውም፡፡ አሁንም የገቡበት ስትራቴጂ በተጠና መንገድ ስለመሆኑ ያሳብበኛል። የሆነ ሆኖ ያኔ የቀረቡት ሃሣቦች አሁንም አንዳንድ አሉ። እኔን ይበልጥ የሚያስገርመኝ ትግራይ ክልል ላይ እኛን ሲቃወሙን የነበረውን አሁን በእጥፍ እየተገበሩት መሆናቸው ነው፡፡ መለስ እኛን ለመምታት ሲል “ብክነት አለበት” ብሎ ያልተቀበላቸው የመስኖ ስራዎች፣ የመንገድ ስራዎች፣ የግድብ ስራ፣ የሪፈራል ሆስፒታል ስራ፣ የሠማዕታት ሃውልት ግንባታ… እነዚህን ሁሉ አሁን ትክክል ናቸው ብለው ተቀብለዋል፡፡ ይሄን ሲያደርጉ ደግሞ ያኔ ትክክል አይደሉም ላሉት ይቅርታ ሳይጠይቁ ነው፡፡ ለነገሩ እነሱ ከሠውም ወስደናል አይሉም፤ ይቅርታም አይጠይቁም፡፡ በኤርትራ ጉዳይ ብዙ ጥፋት ተሠርቶ ይቅርታ ያሉት ነገር የለም፡፡
ያኔ እናንተ “ሻዕቢያን ማንበርከክ…” ብላችሁ ያቀረባችሁት ሃሣብ ሊሳካ ይችል ነበር ይላሉ?
በነገራችን ላይ አቶ መለስ ወደፊት ገፍቶ የሻዕቢያን ሠራዊት ማንበርከክና መደምሰስ አይቻልም የሚል ሃሳብ ነው ያቀረቡት፡፡ ኋላ ላይ የመጡ መረጃዎች ግን ማንበርከክ ይቻል እንደነበርና… ያለቀለት ጉዳይ እንደነበረ ይጠቁማሉ የኤርትራ ባለስልጣናትም እየተናገሩት ነው። ለምሣሌ ሃይልይሮ የተባለውና አሁን በእስር ላይ የሚገኘው፤ ባለስልጣን፤ “በቃ ወያኔ አጥለቅልቆናል፤ በሚገባ አሸንፎናል” ብሎ ነበር፡፡ ሌላ አድሃኖም የሚባል የእነሱ አመራር፣ የሻዕቢያ ሠራዊት ከአሰብ ወደ ምጽዋ ማፈግፈግ ጀምሮ እንደነበር ጠቅሶ ከአስመራም ለማፈግፈግ ተቃርቦ ነበር ብሏል፡፡ ገፍተን ብንሄድ ኖሮ አሁን በአካባቢው የተፈጠረው ትርምስ ባልኖረ ነበር፡፡ ኢትዮጵያን ለ14 አመት ችግር ውስጥ ነው የከተታት የጉዳዩ እልባት አለማግኘት ነው፡፡ ሁሌም በተጠንቀቅ እንድትቆም ነው ያደረጋት፡፡ ከዚያም በላይ ሻዕቢያ የሚደግፋቸው ሃይሎች በኢትዮጵያ ውስጥ ትርምስ ለመፍጠር ሲሞክሩ እያስተዋልን ነው፡፡ ሻዕቢያን ማስወገድ ቢቻል ኖሮ ለኤርትራ ህዝብም ሆነ ለኢትዮጵያ በጐ ነገር በተፈጠረ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ረጅም እፎይታ ያገኝ ነበር፡፡
አሁን እርስዎ የሚከተሉት ርዕዮተ ዓለም ምንድን ነው?
እኔ በአጠቃላይ እውነተኛውን፣ መሠረቱን ሊብራል ያደረገ ዲሞክራሲን መከተል በሚለው ነው የማምነው። ሊበራል ውስጥ ብዙ አይነት ክፍሎች አሉ፡፡ በአሁን ወቅት በኢትዮጵያ ሶሻሊዝም ማርክሲዝምን ተግባራዊ ማድረግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ማርክሲዝም ረሃብና ጭቆናን ለማስወገድ ጠቃሚ ነው፡፡ በደርግም በንጉሡ ስርአትም አሁንም ዲሞክራሲ በተግባር ስራ ላይ አልዋለም፡ ባለንበት እየረገጥን ነው፡፡ ዲሞክራሲ ያለ ነፃ የሲቪል ማህበረሰብ፣ ያለ ነፃ ፕሬስ አይታሰብም፡፡ ህብረተሰቡ በነፃነት ሣይንቀሳቀስ በየ5 አመቱ ምርጫ ማካሄድ ዲሞክራሲ አይደለም፡፡ መድብለ ፓርቲ በሌለበት ዲሞክራሲ የለም፡፡ በኢትዮጵያ እነዚህ ነገሮች እንኳ ብንተገብር ለውጥ ይመጣ ነበር፡፡ መጀመሪያ የዲሞክራሲ መሠረትን መገንባት ነበር የሚያስፈልገው፤ ከዚያ በኋላ ማርክሲስቱም፣ ሊበራሉም፣ ሌላውም የፈለገውን ሃሳብ ማራመድ ይችላል፡፡ እኔ አሁንም የፀና እምነቴ እውነተኛውን ዲሞክራሲ መተግበር በሚለው ስለሆነ የምታገለውም ለዚሁ ነው፡፡
ከ1993 የህወኃት ክፍፍል በኋላ ከድርጅቱ የወጣችሁ ፖለቲከኞች አንድ ላይ መሠባሰብ አልቻላችሁም፤ ሁላችሁም በየፊናችሁ ነው የተበታተናችሁት? አንዳንድ ወገኖች ከድርጅቱ የወጣችሁትግለሰብ ላይ ባላችሁ ጥላቻ እንደሆነ ይናገራሉ…
እኛ አቶ መለስን የተቃወምነው በሉአላዊነት ጉዳይ ነው፡፡ ከዚያ ጋር በተያያዘም በአብዮታዊ ዲሞክራሲ የተቃኘው ዲሞክራሲ ትክክል አይደለም የሚል ነበር። መለስም አቸንፌያለሁ ብሎ አንዳንዱን እስር ቤት ወርውሮታል፣ አንዳንዱን የቁም እስረኛ አድርጐታል፤ አንዳንዱን እንደገና ጫና ፈጥሮ እንዲመለስ አድርጐታል። ህወሐት የወጣን ሰዎች የጋራ ፕሮግራም አልነበረንም። በሁለቱ ጉዳዮች የጋራ መግባባት ነበረን እንጂ የጋራ ፕሮግራም አልነበረንም፡፡ መታወቅ ያለበት ግን አቋም ዋጋ ያስከፍላል፡፡ እኛ ህይወት የሚያስከፍል አቋም ነው ወሰድነው፡፡
ከክፍሉ በኋላ አቶ መለስ አለማቀፍ ሰብዕና ያላቸው ሰው ሆነዋል፣ “የምጡቅ አስተሳሰብ ባለቤት” እየተባሉ ተሞካሽተዋል፡፡ በተቃራኒው የእናንተ ቡድን ደግሞ “ራሱን አላደሰም” ተብሎ ይወቀሳል፡፡ አስተሳሰባችሁን አንጥራችሁ ማውጣት አልቻላችሁም ተብላችሁ ትወቀሳላችሁ…
እኔና በአረና ፓርቲ ውስጥ ያለን ግለሰቦች መሰረታዊ ለውጥ አድርገናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ፕሮግራማችንን ማየት ይቻላል፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ምናምን የሚል ማጭበርበር የሌለበት ፕሮግራም እንዲነደፍ አድርገናል። በባህር በር ጉዳይም ኢትዮጵያ የባህር በር ይገባታል ብለናል፣ መሬት የመንግስት መሆን የለበትም፣ የህዝብ ነው የሚል አቋም ወስደናል፡፡ በኢትዮጵያ አንድነት ዙሪያም መሰረታዊ አቋም በመውሰድ መገንጠል የሚባል ነገር መኖር የለበትም ብለናል፡፡ ኢህአዴግ ግን ባለበት አቋሙ ነው የፀናው፡፡ መለስ መች የአይዲኦሎጂ ለውጥ አመጣ? የተለየ አይዲኦሎጂ አምጥቶ ቢሆን ኖሮ እንደተባለው እኛ ባለንበት ቆመናል በሚል ተብለን ልንወቀስ እንችላለን፡፡ አንድ ነገር ግን ለውጥ መጥቷል፡፡ እኛ ስንቶቻቸው የነበሩ ነገሮችን አቶ መለስ በተግባር አውሎታል፡፡ የአለማቀፍ ድርጅቶችና ሃብታም ሃገሮችን ተላላኪነትን በስራ ላይ አውሎታል፡፡ መለስ ይኑርም አይኑርም ኢህአዴግ አለማቀፍ ተቀባይነት ያገኘው ወደ ሱማሌ ግባ ሲባል በመግባቱና የተላላኪነት ሚና በመወጣቱ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ሚና የሚወጣላቸውን አካል ደግሞ እነዚህ ሃገሮች ተክለ ሰውነቱን ይገነቡታል፡፡ ዲፕሎማሲ የጥቅም ጉዳይ ስለሆነ እነዚህ ሃገሮች የደገፋቸው ወይም የታዘዘላቸው መሪ ካገኙ ሰብዕናውን ይገነቡታል እንጂ አቶ መለስ ኢህአዴግ ይከተለው ከነበረው ርዕዮተ አለም የመጠቀ አስተሳሰብ ስለተከተለ አይመስለኝም፡፡
በመፅሀፉ ከትግሉ ጀምሮ እስከ ህወሐት ክፍፍል ድረስ ስህተት ያሏቸውን ጉዳዮች በግልፅ አስቀምጠዋል፤ እርስዎ እነዚያን ስህተቶች ተሸክመው እንዴት እስከ ክፍፍሉ ድረስ ዘለቁ? ለምን በወቅቱ እርምጃ አልወሰዱም?
በወቅቱ ድርጅቱ የሚገመግማቸው ስህተቶች ነበሩ። ይኖራሉም፡፡ ግን ሁልጊዜ በሂደት ይታረማሉ የሚል ሃሳብ ነበረኝ፡፡ መሰረታዊ ቢሆን እንኳ ተወያይተን የምናርማቸው ጉዳዮች ነው የሚሆኑት ብለን እናስብ ነበር፡፡ በክፍፍሉ ወቅት ግን እነዚያ ችግሮች መታረም አይችሉም ብለን አቋም ወሰድን፡፡ አንዳንድ ስህተቶች ደግሞ ከምንከተለው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም ነበር የሚመነጩት፡፡ ያን ያየሁት ከወጣን በኋላ ነው፡፡ ስንከፋፈል እንኳ ሁለታችንም የነበረን ርዕዮተ ዓለም አብዮታዊ ዲሞክራሲ ነው፡፡ ከወጡት አሁንም አብዮታዊ ዲሞክራሲን የሚከተሉ ይኖሩ ይሆናል፡፡ እኔ ማርክሲዝምን በማምንበት ጊዜ፣ ዲሞክራሲ ለወዳጅ እንጂ ለጠላት መሰጠት የለበትም የሚል አቋም ነበረኝ። ግን ዲሞክራሲ ለሁሉም ዜጋ እኩል መድረስ ያለበት መሆኑን አምኛለሁ፡፡
በትግል ህይወትዎ አሁን ሲያስቡት የሚያስቆጭዎ ወይም የሚፀፅትዎ ነገር አለ?
በመታገሌ ፈፅሞ አልቆጭም፡፡ በተለይ ለ17 ዓመታት ያደረግሁት ትግል ሌሎች አላማዎች ባይሳኩም በኢትዮጵያ ዲሞክራሲን አፍኖ የቆየው፣ ዜጎችን በግፍ ይገድል የነበረ ስርአት በመወገዱ እንደ ትልቅ ገድል አድርጌ እወስደዋለሁ፡፡
ያም ሆኖ አንዳንድ አቋሞቼ ይፀፅቱኛል፡፡ ለምሳሌ በኤርትራ ላይ በትግሉ ወቅት የወሰድነው አቋም ይፀፅተኛል፡፡ የኢትዮጵያን ጥቅም ሳናስከብር ቅኝ ግዛት ነው ብለን ኤርትራ ነፃ እንድትወጣ መወሰናችንና የዚያ ውሳኔ አካል መሆኔ ይፀፅተኛል፡፡ ኤርትራ ነፃ መውጣቷ በእርግጥ የግድ ነበር፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ ቅኝ ገዢ ስለሆነች የሚባለው ትልቅ ስህተት ነበር፤ ይሄ እስካሁን ድረስ ይፀፅተኛል፡፡ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅትም በመካከላችን የነበረውን ልዩነት ከጦርነቱ ቀድመን ማሳወቅ ነበረብን ወይ የሚለውም ያሳስበኛል። ከዚያ ውጪ ግን በአይዲኦሎጂ በተፈጠሩት ስህተቶች የጊዜውን ፋሽን ተከትሎ የሚለዋወጥ በመሆኑ አልፀፀትም፤ እታረማለሁ እንጂ፡፡ ከሁሉም የሚፀፅተኝ ኢትዮጵያን የባህር በር የነሳው ውሳኔ ነው፡፡ በጦርነቱም ወቅት በእንዝላልነት ያን ያህል ዋጋ መከፈል ሳያስፈልገው መከፈሉ ያሳዝነኛል፡፡ ቀደም ብሎ መደራጀት ቢቻል ኖሮ፣ ያሁሉ ሞትና መፈናቀል ባልተከሰተ ነበር፡፡
የሚያስደስትዎ ወሳኔስ?
ብዙ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ዋናው ግን ለመታገል መወሰኔ ያስደስተኛል፤ ችግሩ ሳይቀጥል በአንፃራዊነት ነፃ ሆኜ መኖሬም ትልቁ የሚያስደስተኝ ነገር ነው፡፡ አሁን አገሪቱ ውስጥ መሰረታዊ ችግሮች አሉ፡- የሙስና ችግር ስር የሰደደ ነው፣ ብልሹ አሰራሮችና የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች አሉ፤ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተበራክቷል፡፡ የ1997 ምርጫን ተከትሎ ከ190 በላይ ዜጎች ሲገደሉ የዚያ አካል አለመሆኔ ያስደስተኛል፡፡
ከአቶ መለስና ከአቶ ኃይለማርያም አመራር የትኛውን ይመርጣሉ?
በኢትዮጵያ ያለው ችግር የግለሰቦች አይደለም። በክፍፍሉ ከህውኃት የተለየነው ግለሰቦች መለስን አሸንፈን ስልጣን ብንይዝ ኖሮ እኛም አምባገነኖች እንሆን ነበር፡፡ ምናልባት በኤርትራና በሉአላዊነት ጉዳይ እንዲሁም በአንዳንድ ሃገራዊ ፖሊሲዎች ላይ የተሻለ ነገር የማምጣት እድል ሊኖረን ይችል ነበር፡፡ በተረፈ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ስለምንቀጥል አምባገነን ከመሆን የሚያግደን የለም፡፡ ይሄን ርዕዮተ ዓለም ተከትሎ የሄደ ሰው አምባገነን ነው የሚሆነው፡፡ መሰረቱ እዚያ ርዕዮተ ዓለም ውስጥ ነው ያለው፡፡ ርዕዮተ ዓለሙ ስልጣን አያከፋፍልም፣ በአንድ ሰው ላይ ነው የሚቆልለው፣ ተቃዋሚን አይፈቅድም፣ የሚቃወሙትን በጠላትነት ነው የሚያየው፡፡ ህዝቡ እንዳሻው እንዲንቀሳቀስ አይፈቅድም። ስለዚህ መለስም ይሁን ኃይለማርያም አምባገነን የሚያደርጋቸው የሚከተሉት ርዕዮተ ዓለም ነው፡፡
ኤፈርት በማን ሃብት ነው የተቋቋመው?
በህወሐት ሃብት ነው የተቋቋመው፡፡
የህወሐት የሃብት ምንጭ ምን ነበር?
በዚያን ወቅት ጠላት ከሚለው ደርግና፣ ከውጭ እርዳታ ያገኘው ሃብት ነበር፡፡ በንግድ በኩልም የተለያዩ መርከቦች ነበሩት፤ ይነግድ ነበር፡፡ መነሻ የሆነው ከዚህ የተገኘው ሃብት ነው፡፡ እኔ መነሳት ያለበት የሚመስለኝ፣ ሃብቱ ህዝብን እየጠቀመ ነው ወይ የሚለው ነው፡፡ ህዝቡስ ይሄን ሃብት መቆጣጠር ችሏል ወይ? የቦርዱ አባላትና ሊቀመንበሮች የፓርቲ አባላት ናቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ ስሙ ነው ኢንዶውመንት እንጂ የህወሐት ተብሎ ነው የሚታሰበው፡፡
እንደ ሌላው ተቋም ብዙ ሃብት ቢይዝም ግልፅነትና ተጠያቂነት የለውም፡፡ ህዝቡ ወጪና ገቢውን አያውቅም፡፡ እንደ መርህ አንድ ጥያቄ ማንሳት ይቻላል። ኢንዶውመንት ማቋቋም ህጋዊ ነው፡፡ ፓርቲ ነጋዴ ሲሆንስ? ይሄ ጥያቄ ነው መነሳት ያለበት፡፡ በኤፈርት ዙሪያ የሙስና፣. የባለቤትነት ጉዳዮች ይነሳሉ፡፡ ምናልባት የሰጠው ጥቅም የምለው በሚከፈቱት ድርጅቶች ህዝቡ የስራ እድል ማግኘቱ ነው፡፡
የህወሐት 40ኛ ዓመት አከባበርን እንዴት አዩት?
ትግል መዘከር አለበት፡፡ ፀረ-ዲሞክራሲያዊ ስርአትን ለመጣል የተሰዉትን መዘከር አግባብነት አለው፤ አስፈላጊም ነው፡፡ እንኳን ለዚህ ትግል ህይወታቸውን ለሰጡት በግለሰብ ደረጃም ይዘከራል፡፡ ግን የሚከበርበት መንገድ አግባብ አይደለም፡፡ “ለምንድነው ለዚህ ፕሮግራም 10 ሚሊዮን ብር የሚወጣው?” የሚለው የግድ መነሳት አለበት፡፡
ህወሐት ከተመሰረተ 40 ዓመት፣ ስልጣን ከያዘ 23 ዓመት ሆኖታል፡፡ በአሉን ሲያከብሩ በነዚህ ዓመታት የተጓዙበትን አቅጣጫ መገምገም ነበረባቸው፡፡ ግን በተቃራኒው ህዝቡና ተቃዋሚዎች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ለመደፍጠጥና ህዝቡን ወደ ኋላ ለመመለስ ሞክረዋል፡፡
ህውሐት ራሱም ወደ ፊት እንዳያይ ነው ያደረጉት፡፡ ህዝቡንም “ያሁኑን አታንሳ፤ ደደቢትን ተመልከት፤ የከፈልነውን መስዋዕትነት አስብ” ህወሐት በዚህ መልኩ ህዝቡን በስሜት ወደ ኋላ ጎትቶ በአሉን ማክበሩ ስህተት ይመስለኛል፡፡  

Read 9298 times