Tuesday, 03 March 2015 14:33

ሁለተኛው የጉማ ፊልም ሽልማት “ከተስፋ ጋር መሸለም ትልቅ ነገር ነው”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

የ“ረቡኒ” እና “ኒሻን” ዳይሬክተሮች እኩል አሸንፈዋል

  • የዘሪቱ ከበደ ፊልም በ4 ዘርፎች አሸንፏል
  • ኮሜዲያን ፍልፍሉ ታዳሚውን ሲያሳቅቅ አምሽቷል

   ሁለተኛው የጉማ ፊልም ሽልማት ከፊልም ምዝገባው እስከ ማጣሪያው እንዲሁም የሽልማት ስነስርዓቱ ድረስ ብዙ ወራትን ፈጅቷል፡፡ 67 ፊልሞች ለውድድር ተመዝግበው 27 የታጩ ሲሆን ፊልሞቹን ለመዳኘት 102 ዳኞችና ተመልካቾች ተሳትፈውበታል፡፡ በ17 ዘርፎች ሲካሄድ የቆየው የጉማ ፊልም ሽልማት ውድድር ባለፈው ሰኞ አሸናፊዎቹን በመሸለም ተጠናቋል፡፡
አርፍዶ መጀመር ዘግይቶ መጨረስ
የሽልማቱ ስነ-ስርዓት በብሄራዊ ቴአትር አዳራሽ ከቀኑ 10፡30 ጀምሮ እንደሚካሄድ በመጥሪያው ካርዱ ላይ ተገልጿል፡፡ ፕሮግራሙ የተጀመረው ግን እንደተለመደው በጣም ዘግይቶ ነው፡፡ ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት እንኳ አልተጀመረም ነበር፡፡ ታዳሚው ትዕግስቱ መሟጠጡን በፉጨት፣ በጭብጨባና በጩኸት ሲገልፅ ቆይቶ፣ 1፡10 ላይ ምላሽ አገኘ፡፡ የማስታወቂያ ባለሙያው አርቲስት ሽመልስ በቀለ ወደ መድረኩ ብቅ ብሎ ፕሮግራሙ በሰዓቱ ባለመጀመሩ ይቅርታ ከጠየቀ በኋላ መድረኩን መምራት ጀመረ፡፡ የመድረክ አጋፋሪው እሱ ነበር፡፡  
የዕለቱ የክብር እንግዳ የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ አማካሪና በአሁኑ ወቅት በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የጽ/ቤት ኃላፊና የሚኒስትሩ ልዩ ተወካይ  አቶ አሰፋ ከሲቶ፤ የመክፈቺያ ንግግር አድርገዋል፡፡ የተለያዩ ዲፕሎማቶች፣ አምባሳደሮች፣ በርካታ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የውድድሩ ተሳታፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች አዳራሹን ሞልተውት ነበር፡፡
ከሚኒስትሩ ተወካይ ንግግር በኋላ ቀጥታ ወደ ሽልማት ስነ-ስርዓቱ የተገባ ሲሆን ብቸኛው  የህይወት ዘመን ተሸላሚ ከያኒው ደበበ እሸቱ ለሽልማት ወደ መድረክ ተጠራ፡፡ ታዳሚው በሙሉ ከመቀመጫው ተነስቶ በጭብጨባና በፉጨት ለአንጋፋው የጥበብ ሰው ያለውን አክብሮትና አድናቆት ገለፀ፡፡ አርቲስቱ መድረክ ላይ እንደወጣ በወርቀ ዘቦ ጥልፍ የተንቆጠቆጠ ካባ ተደረበለት፡፡ ከአገር ውስጥ እስከ ሌሎች አለማት የሰራቸው የኪነ ጥበብ ስራዎች ታወሱ፡፡ አሁንም የታዳሚው አድናቆት አልቀነሰም፡፡ ደበበ ከአርቲስት ብርሃኑ ሽብሩ እጅ ዋንጫ ከተሸለመ በኋላ አጠር ያለች አዝናኝ ንግግር አድርጓል፤ “ወደዚህ አዳራሽ ስገባ አንድ ጋዜጠኛ ይዞኝ ‘አሁን መድረክ ላይ የምታደርገው ንግግር ምንድን ነው?’ ብሎ ጠየቀኝ፡፡ #ምንም አልተዘጋጀሁም መድረኩ ላይ ከወጣሁ በኋላ ልቤና አዕምሮዬ ተመካክረው የወሰኑትን እናገራለሁ” ብዬው ነበር” በማለት ነው ንግግር የጀመረው፡፡ “ዛሬ ከምነግራችሁ በላይ ደስ ብሎኛል፤ ሰዎች ዳር ሆነው ይሄ ፊልም ጥሩ ነው፣ ይሄኛው መጥፎ ነው ሲሉ እሰማለሁ፤ ለእኔ ግን ፊልም መስራት መጀመሩ ነው ትልቁ ነገር” ብሏል፡፡
እያደገ ስለመጣው የፊልም ኢንዱስትሪ የተናገረው የእድሜ ዘመን ተሸላሚው፤ በአንድ ወቅት አርቲስት ንጋቷ ከልካይ አንድ እርግማን ተራግመው እንደነበር ሲገልጽ ሁሉም እርግማኑን ለመስማት ጆሮውን ከፈተ፡፡ “…አርቲስቷ በመሬት ጉዳይ ሙግት ጀምረው መረታት ሳይኖርባቸው ተረቱና ኢትዮጵያ ልጆችሽ ሁሉ አዝማሪ  ይሁኑ አሉ” ሲል አዳራሹ በሳቅ ተናጋ፡፡
“ታዲያ ስለ አርቲስቷ ህይወት ለማወቅ በአንድ ወቅት ኢንተርቪው ሳደርግ “እትዬ ንጋቷ እርግማንሽ ደረሰ ወይስ አልደረሰም?” ብዬ ጠየቅኋት፤ አርቲስቷም “እንዴት አልደረሰም፤ ደረሰ እንጂ የደጅ አዝማች ሰብስቤ ልጅ ኩኩ ሰብስቤ እንኳን ዘፋኝ ስትሆን” አለችኝ፤ ሲል ሌላ የሳቅ ሁካታ በአዳራሹ ነገሰ፡፡ ከዚያም አርቲስቱ ላለፉት 44 ዓመታት እንደ እህትም እንደ ጓደኛም እንደ ጠበቃም እንደ ሚስትም ሆና ከጎኑ ሳትለይ አራት ልጆችና ሰባት የልጅ ልጆች እንዲያይ ላደረገችው ውድ ባለቤቱ ምስጋና አቀረበ፡፡ “እግዜር የጥበብ ሙያን በላያችሁ ይዝራባችሁ” ሲልም መረቀ፡፡ “የህይወት ዘመን ተሸላሚ ሆኗል ይበቃዋል ብላችሁ ካሰባችሁ ሲያምራችሁ ይቅር፤ ገና ብዙ እሰራለሁ” በማለትም ንግግሩን አጠናቆ ከመድረክ ወርዷል፡፡
ሽልማቱ ግን ቀጠለ፡፡ በምርጥ የተማሪ አጭር ፊልም ዘርፍ “ሃጢያት የሌለበት” በተሰኘው ፊልም አቤል ዳዊት አሸናፊ ሲሆን በምርጥ ድምፅ በ “ኒሻን” ፊልም ከዴንማርክ የመጣችው ኦሪያላ ዊንተር አሸንፋ ዳይሬክተሩ ይድነቃቸው ሹመቴ ሽልማቱን ተቀብሎላታል፡፡ በምርጥ ሙዚቃ በ “ቀሚስ የለበስኩለት” ፊልም እውቁ የሙዚቃ አቀናባሪ አበጋዝ ክብረወርቅና ድምፃዊት ዘሪቱ ከበደ ያሸነፉ ሲሆን አበጋዝ ባይገኝም ሽልማቱን ዘሪቱ ተቀብላለች፡
በምርጥ ስኮር አሁንም በ “ቀሚስ የለበስኩለት” አበጋዝ ክብረወርቅ አሸንፎ ሽልማቱን ዘሪቱ ከበደ ከሙዚቃው ሃያሲው ሰርፀ - ፍሬ ስብሃት እጅ ተቀብላለታለች፡፡ በምርጥ የምስለ ገፅ ቅብ (ሜክአፕ) ዘርፍ “በጭስ ተደብቄ” ፊልም ዳዊት አለማየሁ አሸናፊ ሆኗል፡፡
በምርጥ ስክሪፕት የ “ረቡኒ” ፊልም ደራሲ ቅድስተ ይልማ ስታሸንፍ፣ በምርጥ ሲኒማቶግራፊ ዘርፍ ደግሞ በ “ቀሚስ የለበስኩለት” ፊልም ታሪኩ ደስአለኝ አሸንፎ፣ ከእውቁ ፎቶግራፈር ታደሰ ደምሴ እጅ ዋንጫውን ተቀብሏል፡፡ ታሪኩ ከሽልማቱ በኋላ ባደረገው ንግግርም፤ “ይህ ዋንጫ መታሰቢያነቱ ዝዋይ ማረሚያ ቤት በእስር ላይ ለሚገኘው ለብርቱው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ይሁንልኝ” ብሏል፡፡ ታዳሚውም በጭብጨባና በፉጨት አጅቦታል፡፡
በምርጥ ተስፋ የተጣለባት ተዋናይት ዘርፍ “በቀሚስ የለበስኩ’ለት” ፊልም ድምፃዊት ዘሪቱ  ከበደ አሸንፋ ዋንጫ የወሰደች ሲሆን ደጋግሞ ወደ መድረክ በመውጣትና በመውረድ ብዛት በምሽቱ የተወዳደራት አልተገኘም፡፡ ሽልማቱን ከወሰደች በኋላ የተሰማትን ስትናገርም፤ “ከተስፋ ጋር መሸለም ትልቅ ነገር ስለሆነ ደስታዬ ከፍተኛ ነው” ብላለች፡፡
በምርጥ ተስፋ የተጣለበት ወንድ ተዋናይ በ“ያልታሰበው” ፊልም ህፃን ኢዮብ ዳዊት አሸናፊ ሆኗል፡፡ በምርጥ ሴት ረዳት ተዋናይት ዘርፍ አሸናፊ የሆነችው እውቋ ተዋናይት አዚዛ አህመድ ስትሆን “በጭስ ተደብቄ” ፊልም ላይ ባሳየችው ብቃት ተሸልማለች፡፡ በምርጥ ረዳት ወንድ ተዋናይ “ኒሻን” ፊልም ላይ ብቃቱን ያሳየው አርቲስት አለባቸው መኮንን ያሸነፈ ሲሆን ከኮሜዲያን ደረጄ ሃይሌ እጅ ሽልማቱን ወስዷል፡፡ ደረጄ “ረዳት ለመሆን ምን አነሳሳህ?” ሲል ለተሸላሚው ያቀረበው ድንገተኛ ጥያቄ ታዳሚውን አስፈግጐታል፡፡
በምርጥ መሪ ሴት ተዋናይት “ረቡኒ” ፊልም ላይ የተመልካችን ቀልብ የማረከችው ሩታ መንግስተአብ አሸንፋ፣ ከአምናው የጉማ ፊልም ሽልማት ምርጥ ሴት መሪ ተዋናይት አሸናፊ ኤልሳቤት መላኩ እጅ ሽልማቷን ስትወስድ፣ በምርጥ ወንድ መሪ ተዋናይ “በጭስ ተደብቄ” ፊልም ላይ ተመልካችን ያስደመመው ዕውቁ አርቲስት ግሩም ኤርሚያስ አሸናፊ ሆኖ ከአንጋፋው አርቲስት አብራር አብዶ እጅ ሽልማቱን ተቀብሏል፡፡
በበደሌ ስፔሻል ምርጥ የተመልካች ምርጫ ፊልም “ረቡኒ” አሸናፊ ሲሆን ደራሲዋ ቅድስት ይልማ ከሄኒከን ማርኬቲንግ ማኔጀር ከወይዘሪት ሪታ ፀሐይ እጅ  ሽልማቷን ወስዳለች፡፡
በምርጥ ዳይሬክተር ዘርፍ የ “ረቡኒ” ፊልም ዳይሬክተር ቅድስት ይልማ እና የ “ኒሻን” ዳይሬክተር ይድነቃቸው ሹመቴ የተመረጡ ሲሆን ሁለቱ ባለሙያዎች እንዴት እኩል አንደኛ ይወጣሉ የሚለው መነጋገሪያ ሆኖ አምሽቷል፡፡
በመጨረሻም በምርጥ ፊልም ዘርፍ “ኒሻን” አሸንፏል፡፡ ቀደም ብሎ በመድረኩ ላይ እንደተገለፀው፤ “ ኒሻን” በ11 ዘርፍ፣ “ረቡኒ” በ10 ዘርፍ፣ “ቀሚስ የለበስኩለት” በ10 ዘርፍ፣ “ያልታሰበው” በዘጠኝ ዘርፍ፣ “በጭስ ተደብቄ” በሰባት ዘርፍ፣ “400 ፍቅር” በአምስት ዘርፍ ታጭተው ነበር፡፡
በመቀጠል የተከናወነው በኪነ ጥበቡ ዘርፍ የረዥም ዘመን አገልግሎት ሰጥተው ያለፉ አንጋፋ አርቲስቶችን የማመስገንና የማስታወስ ፕሮግራም ሲሆን ከስድስት ወር በፊት ያለፉት የፊልም ባለሙያ ሚሼል ፓፓታኪስ፣ ረዳት ፕሮፌሰር ሃይማኖት አለሙ፣ የመጀመሪያዋ ሴት ተዋናይት ሰላማዊት ገ/ሥላሴ፣ አርቲስት ሙናዬ መንበሩ፣ አርቲስት በላይነሽ አመዴ (ኩንዬ)፣ አብርሃም አስመላሽ፣ እንግዳዘር ነጋ፣ ዓለሙ ገ/አብ፣ ሲራክ ታደሰ እና አርቲስት ሙሉጌታ ባልቻ ፎቶአቸው በስክሪን እየታየ የታወሱ ሲሆን “በስራችሁ ህያው ናችሁ፤ እናመሰግናለን” ተብለዋል፡፡ በደሌ ቢራም ለእውቁ የኪነ ጥበብ ሰው ሚሼል ፓፓታኪስ መጠኑ ያልተገለፀ ገንዘብ በስጦታ አበርክቷል፡፡
ኮሜዲያን ፍልፍሉ ሲያሳቅቅ አመሸ
በሽልማት ሥነስርዓቱ ላይ የፕሮግራሙን ታዳሚዎች ለማዝናናት ሁለት ኮሜዲያን ተገኝተው ነበር፡፡ አንደኛው ኮሜዲያን የዓለም አቀፍ መሪዎችንና የአገራችንን ዕውቅ ሰዎች፣ ድምፅ በአማርኛና በእንግሊዝኛ በማስመሰል ደረጃቸውን በጠበቁ ቀልዶቹ ሲያዝናና ያመሸ ሲሆን ኮሜዲያን በረከት በቀለ (ፍልፍሉ) ግን ህዝቡን ያስቃል ተብሎ ቢጠበቅም ሲያሳቅቅ አምሽቷል፡፡
ኮሜዲያኑ ምን እንደነካው ባይታወቅም ከኢትዮጵያዊ ጨዋነት የራቀ፣ ፕሮግራሙን የታደሙትን ህፃናትና አዛውንት ከግምት ውስጥ ያላስገባ ችኮ ቀልድ በማቅረብ ተመልካቹን አበሳጭቷል፡፡
አንድ የሽልማት ሥነስርዓቱን የታደሙ አዛውንት በሰጡት አስተያየት፤ “በአሁኑ ሰዓት የኮሜዲ ስራ የተከበረ ትልቅ ሙያ ቢሆንም እንደዚህ ዓይነት ቀልዶች ሙያውን እንዳያረክሱት እሰጋለሁ” ብለዋል፡፡  “የጉማ ፊልም ሽልማት አዘጋጆች፤ በፍልፍሉ ሲዘለፉና ሲቀለድባቸው ያመሹትን ታዳሚዎች በይፋ ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው” ያሉት ደግሞ በእንግድነት ተጋብዘው የተገኙ አንድ  የግል ዩኒቨርሲቲ መምህር ናቸው፡፡
ከተባለበት ሰዓት እጅጉን ዘግይቶ የተጀመረው የሽልማት ሥነስርዓት ፕሮግራሙ ከምሽቱ 4፡20 ላይ የተጠናቀቀ ሲሆን አብዛኛው ታዳሚ (የትራንስፖርት እጥረትን በመፍራት) ከ3፡30 ጀምሮ አዳራሹን እየለቀቀ ወጥቷል፡፡

Read 4725 times