Monday, 02 March 2015 08:48

ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች በኬንያ ፍ/ቤት ከፍተኛ ቅጣት ተጣለባቸው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

ፓስፖርትና ህጋዊ ሰነድ ሣይኖራቸው በህገ ወጥ መንገድ ኬንያ ውስጥ ተይዘዋል የተባሉት 101 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ፍ/ቤት ቀርበው እያንዳንዳቸው 50ሺህ የኬንያ ሽልንግ እንዲከፍሉ መክፈል ካልቻልኩ በአንድ አመት እስራት እንዲቀጡ ተፈረደባቸው፡፡
በኬንያ ታሲያ በተባለችው ግዛት ሰኞ እለት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ኢትዮጵያውያኑ በ3 ኬንያውያን ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ወደ ደቡብ አፍሪካ ለማቅናት ዝግጅት እያደረጉ ባሉበት ወቅት መሆኑን ኔሽን የተሠኘው የሀገሪቱ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
ስደተኞቹ ከትናንት በስቲያ ፍ/ቤት ቀርበው የዳኛውን የ50ሺህ ሽልንግ ቅጣት ሲሰሙና ይህን ካልከፈልኩም ለአንድ አመት በእስር ከቆዩ በኋላ ወደ ሃገራቸው ተመልሰው እንደሚላኩ በአስተርጓሚ ሲነገራቸው አምርረው ማልቀሣቸውንና አንዳንዶቹም መታመማቸውን ጋዜጣው ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያውያኑ ከፍርድ ውሣኔው በኋላ በምልክት ቋንቋ በፍ/ቤቱ አካባቢ የነበሩ ሰዎችን ምግብ ስጡን እያሉ ሲለምኑ እንደነበርም ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያውያኑን በህገ ወጥ መንገድ ሲያዘዋውሩ ነበር የተባሉት ሶስቱ ኬንያውያን ላይ ፍ/ቤቱ እያንዳንዳቸው ላይ 80ሺህ ሽልንግ ቅጣት ጥሎ ቅጣታቸውን ከፍለው ወዲያውኑ ተለቀዋል ተብሏል፡፡
በኬንያ የህገወጥ ስደተኞች መበራከት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ የተጠቆመ ሲሆን የኢትዮጵያውያን ቁጥር የላቀ ድርሻ አለው ተብሏል፡፡ በቅርቡም 11 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ህጋዊ የጉዞ ሰነዶችን ሳያሟሉ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመጓዝ ሲሉ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደዋሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ደቡብ አፍሪካ ለማቅናት በሚል በኬንያ አድርገው ሊጓዙ ሲሞክሩ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑንም ተጠቁሟል፡፡  

Read 1113 times