Saturday, 21 February 2015 13:18

በረከት መቀበል ማን ይጠላል?

Written by  በደረጀ ይመር
Rate this item
(1 Vote)

      ጋዜጠኛ ሔኖክ ስዩም፤ በ150 ገጾች የተቀነበበውን የጥበብ ሥራውን በመንገድ በረከት ስም ተይቦ፣ እንካችሁ እያለ በግብዣ ያግደረድረናል። ወደ ግብዣው ለመዝለቅ ስንዳዳ፣ እንደ እልፍኝ አስከልካይ ከፊት ለፊታችን የተደነቀረው የቀላ ሰማይ - አድማስ - የሽፋን ስዕል ነው፡፡ በእርግጥም ጉዞው ፍዝ አይደለም። የተሳፈርንበት የምናብ ታንኳ ከፍ ዝቅ እያደረገን፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያን በወፍ በረር ያስቃኘንና አፍታም ሳይፈጅበት ወደ ሰሜን ሰማይ ጠቀስ ተራሮች አናት ላይ ሊሰቅለን ክፉኛ ይጣደፋል፡፡ በጉዞው ላይ በግኡዝ ውበት ብቻ ተደምሞ ተሰብስቦ መቀመጥ አያስችልም፡፡ ለሚታየውም ለማይታየውም ቀልብን መስጠት ግድ ይላል፡፡
አስጎብኚው ብዕረኛ፣ የእርካታችን ጣሪያ በታሪካዊ ቅርሶቻችን ላይ ብቻ ተሸብቦ እንዳይቀር በማሰብ  ወደ ስነልቦናው ጎራ እንድንዘልቅ ብዙ ምልከታዎችን ያለ ስስት ያቀብለናል፡፡ ይህንንም የሚያደርገው በሆደሰፊነት ነው፡፡ በታሪኩ ላይ ለተሰለፉት ዘማዊያን ብሽቀት፣ ምሬትና ብሶት ጆሮ አይነፍጋቸውም፡፡ ምሬታቸውን፣ ምልከታቸውን እንደ ግኡዝ ቅርስ ዓይን አዋጅ ሊያደርግብን በብርቱ ይውተረተራል፡፡
የደራሲው ምናባዊ የማውጠንጠን ደረጃን አንጀት አርስነት ለመመስከር ገና የመጀመሪያ ገጾች አፋፍ ላይ ቆመን መጣደፋችንን እንጀምራለን፡፡ በገጽ 7 ላይ ጅማን ሲያስተዋውቀን እንዲህ ብሎ ይጀምራል፡
“ይህቺ ያደላት ሀገር ተኝታለች፣ስንቶቹ የእሷ እኩዮች ጨንቋቸው እንቅልፍ ካጡ ስንት ዓመታቸው?....እውነት የምታንቀላፋ….ስትተኛ መላ አካሏ ይተኛል…ከመላ አካሏ ላይ እንደምንም እንነሳለን፤ጎህ ስለቀደደ ሳይሆን፣ ወፎቹ ስለጮኹ ሳይሆን፣ ወፎቹ አላስተኛ ስላሉን…….ግን ወፎቹ ማን እንደሚያስጮኻቸው ሳስብ፣ ሳስብ…..የላካቸውን እደርስበታለሁ። አሜሪካ፣ካናዳ፣ኢጣሊያ፣….እነዚያ..ብዙ..ሀገራት.ስማቸው..የበዛ…ወሬያቸው.የበዛ--.የሚናፈቁ--.ከነአኖች--.እነሱ ሀገር ያሉ ወፎች ሥራ የኔን ሀገር ሰው በጠዋት መቀስቀስ ነው፡፡”
እዚህ ጋር የጅማን ፍዝነት፣ ማንጎላዠት አስታኮ ስለ ወል ድብታችን አብዝቶ የሚደሰኩር ይመስላል፡፡ በጸጉረ ልውጡ ዓለም መሽቶ እስኪነጋ ብክነት፣ወከባና  ሩጫ ነው፡፡ እዚህ ምንም እንዳልተፈጠረ ለሽ ብሎ ማሸለብ የአዘቦት ልማድ ነው፡፡ በጅማ የተመሰለን ግብር፣ ተከናንቦ የወደቀ ሰብዕናን ለመቀስቀስ ይህን አይነቱን የስላቅ ፍላፃ ሳያሰለስ ያስወነጭፋል፡፡
በምናባዊ ሽርሽሩ ቅርሶች ብቻ አይደሉም አይን እንዲይዙ የተፈቀደላቸው፡፡ ዥንጉርጉሩ ስነልቦናም እይታችንን ሊያጥበረብረን አብዝቶ ይተጋል፡፡ ከገጽ ወደ ገጽ በተራመድን ቁጥር የመታደስ ጥምን ከመቁረጥ የሚያደነቃቅፉን ጉሽ ስነልቦናዎች ከፊት ለፊታችን ይበዛሉ። ሰላም አየለ የምትባል ዘማዊት ደግሞ ጉሹን ልታስጎነጨን የኮማሪነትን ዘውድ ደፍታ ወዲህ ወዲያ ትላለች።  ኮረዳዋ በደራሲው የቴፕ  ቆይታ ላይ እንደ ሀገር ተነጥፋ ለዓውደ ርዕይ የምትቀርብ፣ እድሜዋን በብዙ ርቀት ያስከነዳች ትንግርት ናት። አካባቢዋን፣ገዢዎቿን ባላት አቅም ትሞግታለች፤
“አንድ ጊዜ በዓል ላይ ሀረር ሄድኩ፣ የመጨረሻዋ እህቴ ስለ ኢትዮጰያዊነት ወላ ሃንቲ የምታውቀው ነገር የለም፡፡ በኦሮሚኛ ስለ ኦሮሚያ ውበት ትዘምራለች። ውቢቷን ኢትዮጲያ እንዳታወድስ የምትማረው ነገር አጥሯታል፡፡ በቋንቋዋ ስለ አባይ ብትዘምርስ?ጎጃሜው ለሶፍ ዑመር ቢቀኝ?እርስ በእርስ የነበረንን ትስስር በጥሳችሁታል፡፡በማይመች መንገድ ተጉዘን ያፀናነውን አንድነት መንገድ ሰርታችሁ አፍርሳችሁታል፡፡በእርግጥ ተስርቷል፤ብትመጣበት ግን ከየት መጣህ የሚለው ጥያቄ ምላሽ የመጣህበት ስፍራ ያንተ እንዳልሆነ ይነግርሃል፡፡ ” ገጽ 38
ከመሬት ከፍ ያላለችው አንዲት ፍሬ ልጅ እንዲህ ያለውን ቋጥኝ እውነት ስታቀብለን ግርምታችን ይጋነንብናል፡፡ ኮሌጅ መበጠስ ድሮ ቀረ ብለን እንዳንቆጭ፣ ሰላም አየለ በእዚህኛውና በወዲያኛው ትውልድ መኻከል እንደ ድንበር ቆማ ትከላከለናለች። ይኽቺ ለአቅመ-ብስለት ተጣድፋ የደረሰች ኮረዳ፣ የምትነፍሰው አውነት ትንታግ ነው፡፡ ከመንፈስ ሸለቆ ዘልቆ የሚገባ ውስጥን የሚበሳ አረር፡፡
ተጓዡ  ብዕረኛ ከስነልቦናው ዓውደ ርዕይ ለጊዜው ገሸሽ አድርጎን ከእናት ተፈጥሮ ጋር በተፈጥሮ ቋንቋ አንድ ሁለት እንድንባባል ወደ ምድረ ገነቱ የሸካ ጫካ እንደ በትር እየመራን ያስገባናል፡፡ የሀገራችን ከያኒያን የዘነጓቸው የውበት ፈርጦች - የሻካ ጫካዎች- እዚህ አስተዋሽ አግኝተው፣ አብዝተው ሲፈግጉ ከአይናችን ይገባሉ። በእርግጥም እነኚህ የውበት ዋርካዎች እንደ አልባሌ ቸል መባላቸው፣ጥበብ መወደሷን መነፈጓ ከፉኛ ይከነክናል፡፡ ምንአልባትም ከያኒያኖቻችን የቸኩ/cliché/ ስንኞችን እየደረደሩ ከሚያታክቱን ለእንደነዚህ ላሉ ድንግል የውበት ፈርጦች  ፊት መስጠትን ቢያውቁበት ምንኛ መንፈሳችን ከፍታ ላይ ባንጠላጠሉት ብለን እንቆጫለን፡፡ ገጽ 68 ላይ በሰፈረው በደራሲው ግርምት እንደመማለን፣
“እግር ጉረኛ ነው፡፡ ፎቅ ሲመለከት ባለመብረክረኩ ጀግና ይመስላል፤ግን ውሸታም ነው፡፡ ሸካ ደን መሃል ሲርበተበት ብታዩት?ቆንጆ ሴት ብቻ የምታፈዝ ይመስለኝ ነበር፡፡ ሺ አመንዘራ ቢሆኑ ተፈጥሮ እንዲህ ተኳኩላ ከወጣች ትበልጣለች፡፡ ለነገሩ ጉደኛም ሰው አለ…..ይህን መሳይ ደን ቢያሳዩት ለአስገድዶ መድፈር እንደምን ይመቻል ብሎ የሚያስብ ሰው፤ከዚህ ዓይነቱም ሰው ግን የሚበልጠው ጉድ የሸካ ተፈጥሮ ነው፡፡”
እንዲህ በሸካ ደን የውበት ድባብ አቅላችንን ጥለን ሳንጨረስ እያዋከበ ወደ ሌላ ቆፈን ውስጥ ይጨምረናል፡፡ ከምቾት አቀበት ላይ እያዳፋ ወደ ትካዜ ተዳፋት ውስጥ ያንደረድረናል፡፡ በቁዘማው ተዳፋት ላይ ደግሞ ሀብታሙ ከሚባል ሰው ጋር እንተዋወቃለን፡፡ ይህን ባለ ስል አእምሮ ኮበሌ፣ ደራሲው ጉዞውን ከደቡብ ምዕራብ ጠቅሎ ወደ ሰሜን ሲጓዝ ደብረብርሃን ከተማ ላይ ያገኘው የመንገድ ሲሳይ ነው፡፡ ሀብታሙ ስለ ባህላችን፣ ስለ እምነታችን ፣ስለ ዕውቀት ልምዳችን ተቆጭቶ ተቆጭቶ ከአንጀቱ አልጠጋ ይለዋል፡፡ በገጽ 100 ላይ እንዲህ አድርጎ ይናደፋል፡
 “ከሰለሞን ቤት የተቀዳው ጥበብ እኛ ሀገር የሞት ፍርድ ተፈርዶበት እንኳን እየኖረ ነው፡፡ በረዶ ከሰማይ የሚበትን እልፍ ደብተራ መደብ ላይ እያደረ በረሃብ ሲመታ፣የግብርና ቴክኖሎጂ ብላ የማታውቀውን ሙጥኝ ብላ አሳሯን የምታይ ሀገር “
ከቆፈኑ ተዳፋት አሁንም አልወጣንም፤ ሀገር ቸል ስላላቸው ባለ ገድለ ብዙ ጀግኖቻችን ከንፈራችንን ለመምጠጥ ሰሜን ሸዋ አንጎለላ ኪዳነ ምህረት ላይ ሀዘን እንቀመጣለን፡፡ እዚህ ስፍራ ላይ የአደዋው አድባር የፊታአውራሪ ገበየሁ አስክሬን እንደ አልባሌ ተጥሏል፡፡ ገጽ 104-105 ከሰፈረው በጥቂቱ፡
“ ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ
 መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ
 የተባለላቸው ፊታውራሪ ገበየሁ፤ አይረሴ የአድዋ ጌጥና የጥቁር ሕዝቦች ሰማዕት ናቸው፡፡ አሁን ከፊቱ የቆምኩት የአድዋው የጦር ሳይንሳት አጽም ዘንድ ነው፡፡ ምቹ ባልሆነ ኹኔታ አንጎለላ ኪዳነ ምህረት ተቀምጦ ለጎብኚ ይታያል፡፡”
ለጀግኖቻችንን የምንሰጠው ክብር ምን ያህል እንደሆነ የጀግናው ገበየሁ አጽም ዋቢ ምስክር ነው:፡ ታሪክ የሞሸሩትን፣ ታሪክ የቀለሱትን ኹነኛ ሰዎችን እንዲህ እንደ አልባሌ ከጉድባ ውስጥ ሸሽገናቸው ስለ ታሪክ ሀብታምነታችን ብንለፍፍ ትርፉ ጉንጭ ማልፋት ይሆናል፡፡  
ብዕረኛው አስጎብኚያችን በጀግኖቻችን አመድ አፋሽነት የተሰማንን የስሜት ማሽቆልቆል ያጤነ ይመስል የመንፈስ ከፍታን በቦታ ከፍታ ሊያድስ ወደ ሰማይ ባልንጀሮቹ የሰሜን ተራሮች እንደ መንኮራኮር ይዞን ሽቅብ ይመነደጋል፡፡ በእርግጥም እዚህ ጋ በጉዞው ማሳረጊያችን ላይ ሆነን ትንሽ አየር መሰብሰብ እንጀምራለን፡፡
 አስጎብኚያችን ተራሮቹን ሲያስተዋውቀን አንዳንድ ቱባ እውነታዎችን እንደ ዋዛ ያነሳና በኩርማን አንቀጽ  አኮስምኖ ያልፋቸዋል። ሰሜን ተራራዎች ላይ የደራሲውን ንፉግነት በደንብ እናስተውልበታለን፡፡ ካራ ምሽግ ላይ ያሳየውን ስስት በየዳ ላይ ይደግመዋል፡፡ በተለያዩ መንግሥታት ከባድ የትጥቅ ትግል ስላስተናገደ ስፍራ ከስም የዘለለ ምንም አይነት መረጃ አላስጨበጠንም፡፡ ስፍራዎቹ ከትጥቅ ትግል ጋር ያላቸው ታሪካዊ ትስስር ወጋ ወጋ ተደርጎ፣ በስም ብቻ ተጠቅሶ ማለፉ የአንባቢን ስሜት ያቆረፍዳል። ቢያንስ የማሻዋን ሜሪ እና የቴፒዋን ሰላም አየለ ያህል ትኩረት ሊሰጣቸው በተገባ ነበር። ታሪካዊ ቅርሶቹ ብዙ ሊወራባቸው የሚችሉ፣ ቢቆሰቆሱ ትልቅ የፖለቲካ ዓውድን የሚከፍቱ ዓይን ማረፊያዎች እንደሆኑ እየታወቀ እንደ ዋዛ ዳምጧቸው ማለፉ እንደ አንድ ድክመት ሊቆጠር ይችላል፡፡
ሌላው የደራሲው ድክመት አንዳንድ መረጃዎችን ሲሰጠን የሚያሳየው ዝንጉነት ነው። ለምሳሌ በአፋር ስለሚገኘው እሾሃማ ዛፍ ሲያስተዋውቀን፣ ሀገሬው “ወያኔ” ዛፍ እያለ እንደሚጠራው ይነግረናል፡፡ ዛፉ በእሾሃማነቱ የተነሳ በኣካባቢው ኅብረተሰብ ላይ ሁለንተናዊ ኪሳራ ያደረሰ ነው፡፡ የቀዬውን ከብት በየጊዜው ጭዳ እያደረገ ሀገሬውን ከማራቆትም አልፎ  የአካባቢውን በረሃማነት በማባባስ  የነዋሪው ራስምታት ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡
ዛፉ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር የተዋወቀው በኃይለስላሴ ዘመነ መንግሥት ሆኖ ሳለ፣ ግብሩ ከመጠሪያው ጋር ያለውን ዝምድና ከመነሻው አንስቶ ጫን ብሎ ሊያስተዋውቀን አለመድፈሩን ስናስብ በሰጠን መረጃ ተአማኒነት ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርብን ያደርገናል፡፡ ቴፒ ላይ ደራሲው በሚያሳየን ክልክ ያለፈ እርጋታ ትዕግስታችን ሊከዳን ይፈታተነናል፡፡ አንዳንዴ እንደውም ጉዞውን ከእነካቴው የዘነጋው እስኪመስልን ድረስ “ቀዥቃዣነቱን” ለመቃረም አብዝተን እንባትታለን፡፡ ስለ አካባቢው ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ከሚነገርን በገገነ መልኩ ከሴተኛ አዳሪዎች ጋር ስለነበረው ቅርርብ ከልክ በላይ በመዘርዘር ጊዜውን ያጠፋል፡፡ ለታሪክ ፍሰትና ማራኪነት ሲባል በአካባቢው ልንተዋወቃቸው የሚገቡ ታሪካዊ ስፍራዎች  ቸል ተብለዋል ፡፡
 በተረፈ ጋዜጠኛ ሔኖክ ስዩም፣ ጅምሩና የሔደበት ርቀት ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ወደፊት ሁሉንም የሀገራችንን ስፍራዎች ያካለለ የጉዞ ማስታወሻን ዳጎስ ባለ የመጽሐፍ ቁመና  እንደሚያስተዋውቀን እምነቴ ነው፡፡       

Read 1627 times