Saturday, 21 February 2015 13:07

ራያ ቢራ እየተከፋፈለ ነው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(6 votes)

    ራያ ቢራ አክሲዮን ማኅበር ህብረተሰቡ የሚጠብቀውን ዓይነት ጥራቱን የጠበቀ፣ ተመራጭ ቢራ ለገበያ እንደሚያቀርብ አስታወቀ፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት ትልቅ ራዕይ ይዘው የተነሱ 58 ግለሰቦች እያንዳንዳቸው ባወጡት 50ሺህ ብርና ባስመዘገቡት ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል የተመሰረተው ራያ ቢራ አክሲዮን ማኅበር፤ በአሁኑ ወቅት 2441 አባላት ሲኖሩት ባለፈው እሁድ በማይጨው ከተማ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በተገኙበት በይፋ ተመርቋል፡፡
የራያ ቢራ አክሲዮን ማህበር የቦርድ ሊቀመንበር ሌተናል ጀኔራል ገብረፃድቃን ገ/ትንሳኤ ለ6ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ባቀረቡት ሪፖርት፤ ከባለ አክሲዮኖች 600 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን፣ ከአክሲዮን ሽያጭ (ፕሪሚየም) 32.59 ሚሊዮን ብር መገኘቱን፣ በባንክ ከተቀመጠ ገንዘብ ወለድ 14.8 ሚሊዮን፣ ከባንክ ብድር 974 ሚሊዮን ብር በብድር  እንደተገኘ፣ ለፋብሪካው ግንባታና ለማሽነሪዎች ግዢና ተከላ 1.558 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ገልፀዋል። እንዲሁም ለ4 ወራት ለምርት ግብአትና ለስራ ማስኬጃ የሚወጣውንና ወደፊት ለማድረግ የታሰበውን ማስፋፊያ ጨምሮ በአጠቃላይ 1.7678 ቢሊዮን ብር እንደሚፈጅ ተናግረዋል፡፡
የተለያዩ ግለሰቦች፣ ማኅበራት፣ የልማት ተቋም ሰራተኞች እንዲሁም አቻ የቢራ ፋብሪካዎች በጤናማና ቅን የመረዳዳት ስሜት ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ በመግዛትና ልምዳቸውን በማካፈል፣ ለፋብሪካው እውን መሆንና ስኬት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን የጠቀሱት የቦርድ ሊቀመንበሩ፤ ዛሬ ብቻ ሳይሆን በመጪው ጊዜም ስለራያ ቢራ ሲወሳ፣ ራሳቸውን፣ ወገንንና ሀገርን ለመጥቀም ያደረጉትን መረባረብ ታሪክ የማይረሳው በመሆኑ ሁሉንም አካላት አመሰግናለሁ ብለዋል፡፡
ወቅቱ የደረሰበትን የቴክኖሎጂ የብቃት ደረጃ ያሟላ ፋብሪካ ማቋቋማቸውን የጠቀሱት ሌተናል ጀኔራል ገብረፃድቃን፤ ሶስት ዓይነት ቢራ አዘጋጅተው በአገሪቷ አሉ የተባሉ ቀማሾች የትኛው ተመራጭ እንደሆነ በሰጧቸው ሐሳብ ላይ ተመስርተው ጥራቱን የጠበቀ ተወዳጅ ቢራ ለህብረተሰቡ እንዳቀረቡ በእርግጠኝነት ተናግረዋል፡
የተለያዩ ግብአቶችን ወደ ፋብሪካው የሚያመጣ፣ በተለያዩ አካባቢዎች የምርት እጥረት እንዳይከሰትና በተፈለገው ጊዜ ቢራውን ለህብረተሰቡ የሚያደርስ ትራንስፖርት የግድ አስፈላጊ በመሆኑ መስራች ባለአክሲዮኖች በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤት ፈርመው “ራዝ ትራንስፖርት አ/ማ” የተባለ የትራንስፖርት ኩባንያ መቋቋሙን ጠቅሰው ዝቅተኛው የአንድ አክሲዮን ዋጋ 50 ሺህ ብር፣ ከፍተኛው ደግሞ ከ1.5 ሚሊዮን ብር እንዳይበልጥ መገደቡንና የራያ ቢራ አ/ማ እና የራዝ ትራንስፖርት አ/ማ ራሳቸውን የቻሉ ሁለት የተለያዩ ተቋማት መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
ጉባኤተኞቹ፣ በግለሰብ ደረጃ በ150 ሚሊዮን ብር 25 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ በመግዛት ለራያ ቢራ ፋብሪካው እውን መሆን ከፍተኛ ሚና ለተጫወቱትና ለራያ ቢራ የቦርድ ዳይሬክተር አባል ለአቶ ዳዊት ገ/እግዚአብሔር ከመቀመጫቸው ተነስተው በማጨብጨብ አክብሮትና ምስጋናቸውን ገልጸውላቸዋል፡፡ ቢጂአይ - ኢትዮጵያ (ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ) ከራያ ቢራ ፋብሪካ 42 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ በመግዛት አብሮ በመስራት ላይ ነው። ቢጂአይ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ሀዋሳ፣ በኦሮሚያ - በዝዋይ ካስቴል ወይን ጠጅ፣ በአማራ - በኮምቦልቻና በአዲስ አበባ ቢራ ፋብሪካ እየሰራ መሆኑን የጠቀሱት የቢጂአይ ኢትዮጵያ ማርኬቲንግ ማናጀርና የራያ ቢራ አ.ማ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል አቶ ኢሳያስ አደራ፤ በመላ ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ለመሳተፍ የቀራቸው ትግራይ ክልል እንደነበር ጠቁመው፣ በራያ ቢራ የመሳተፍ ዕድል ስላገኙ፣ 42 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ በመግዛትና አብሮ በመስራት እውቀትና ልምዳቸውን እያካፈሉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡  
በዚሁ የምረቃ ስነ - ስርዓት ላይ የኢሕዴሪ ፕሬዚዳንት ክቡር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ባደረጉት ንግግር፤ በእያንዳንዱ ግለሰብ፣ ቤተሰብና ድርጅት ተበታትኖ የነበረውን ሀብት በማሰባሰብ ግዙፍ ኢኮኖሚያዊ አቅም መፍጠር እንደሚቻል ጠቅሰው፣ ራያ ቢራ አክሲዮን ማህበር ኢኮኖሚያዊ ትስስር ሊፈጥር የሚችል የኢንዱስትሪ ፕሮጀክት እውን እንዲሆን ያደረገው ጥረት በእለቱ ለፍሬ በመብቃቱ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
የአክሲዮን ማህበራት ሀብትን አሰባስበው ወደ ልማት በማስገባት ትልቅ የኢኮኖሚ አቅም በመፍጠር በርካቶችን የድርጅት ባለቤት ከማድረጋቸውም በላይ ለዜጎች የሚፈጥሩት የስራ እድል በእጅጉ የጎላ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የራያ ቢራ አክሲዮን ማህበር በፋብሪካው ግንባታ ወቅት ለአካባቢው ወጣቶች ከፈጠረው የስራ ዕድል ባሻገር ወደ ምርት በሚገባበት ወቅት ተጨማሪ ሰራተኞችን በቋሚነት ቀጥሮ ማሰራቱ የፋብሪካውን ፋይዳ ከፍተኛ ያደርገዋል ሲሉ ገልፀዋል፡
የግሉ ዘርፍ ከውጭ ከሚመጣው ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ጋር በሽርክና ከመስራት አልፎ ያለውን ጥቂት ሀብት አስተባብሮ በአክሲዮን በመደራጀት ሀገሩን ለማልማት ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል ያሉት ፕሬዚዳንት ሙላቱ፣ መንግስት የግሉን ዘርፍ የሚያጠናክሩ በርካታ ፖሊሲዎችን ከማውጣት ባሻገር የሀገር ውስጥ ባለሀብት ራሱን አጠንክሮ ኢኮኖሚውን በግንባር ቀደምትነት መምራት እንዲችል የተለያዩ ማበረታቻዎችን ቀይሶ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የራያ ቢራ ፋብሪካ ዓመታዊ የማምረት አቅሙ 600 ሺህ ሄክቶ ሊትር ወይም 180ሺህ ጠርሙስ ቢራ እንደሆነ የጠቀሱት የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ አቶ አታክልቲ ሀጎስ፤ አሁን ፋብሪካው የተገጠመለት የማሽን ዓይነት በቀላል ወጪ በማሻሻያ ፕሮጀክት በመቶ ሺዎች ሄክቶሊትር ማምረት እንዲችል እንደሚደረግና አጠቃላይ ወጪው ከ1.7 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡
ፋብሪካው እጅግ ዘመናዊ የንፁህ ውሃና ቆሻሻ ውሃ ማጣሪያ፣ የመጥመቂያና ማሸጊያ ማሽኖች የተገጠሙለት ስለሆነ ከማንኛውም ብክለት የፀዳ መሆኑን ገልፀው፣ ቢራውም ከባህር ወለል በላይ 2450 ሜትር ከፍታ ካለው የማይጨው ተራራ ከሚገኝ የምንጭ ውሃ መጠመቁ ቢራውን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ በፋብሪካው ግንባታ፣ በመሳሪያ ተከላና ጠመቃ የተለያዩ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን በግንባታው ዳዩ የተባለው የቼኮዝሎቫኪያ ኮንትራክተርና ክሮነስ የተባለው የጀርመን ኩባንያ እንደተሳተፉ፣ ፒፒኤስ፣ ኤምጂኤምና ወለባ ድርጅቶች በአማካሪነት እንደሰሩ፣ አሁን ያለው የቢራ ገበያ ጠንካራ ውድድር የሚታይበት ስለሆነ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመዝለቅ በተለያዩ የቢራ ፋብሪካዎች የሰራና ከፍተኛ ልምድ ያለው የውጭ አገር ቢራ ጠማቂ መቅጠራቸውንና ከ483 በላይ ለሆኑ ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል።

Read 3835 times