Saturday, 14 February 2015 15:04

የአዳም መዝገበ (አዳዲስ) ቃላት

Written by  ዮሐንስ ገለታ
Rate this item
(15 votes)

     እንግሊዝኛ ቋንቋ ከስነጽሑፉ ዓለም ወስዶ እየተጠቀመባቸው ከሚገኙ በርካታ ቃላት መካከል ዲኬንዢየን (Dickensian: በቻርለስ ዲከንስ ልቦለዶች ውስጥ እንዳለው ዓይነት አስከፊ የድህነት ወለል፤ በተጨማሪም እንደ ዲከንስ ዓይነት የአፃፃፍ ስልት)፤ ኦርዌሊየን (Orwellian: በጆርጅ ኦርዌል ሥራዎች አንዱ በሆነው “1984” የተሰኘ መጽሐፍ ውስጥ እንደሚታየው ያለ አምባገነናዊ አገዛዝን ለማመልከት)፤ እንዲሁም Joycean, Kafkesque… እያልን መቀጠል እንችላለን፡፡  
ከላይ የተጠቀሱት ቃላት በደራሲያን ስሞች/ሥራዎች ሰበብ የተሠሩ ናቸው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ የተለያዩ ደራሲያን አዳዲስ ቃላትን ሲፈጥሩ ብቻ ሳይሆን እነኚሁ  ፍጥር ቃላት ቋንቋው ውስጥ ተካተው አገልግሎት ሲሰጡ ማየትም እንግዳ አይደለም፡፡   
በእርግጥ አዳዲስ ቃላትን መፍጠር ብዙ ዓይነት መልክ እንዳለው ይታወቃል፡፡ የመጀመሪያው ፍፁም አዲስ የሆኑ ቃላት ፈጠራ፤ ሁለተኛው ነባር ቃላትንና ቅጥያዎችን በማሻሻል ሲሆን ሦስተኛው ዓይነት የቃላት ፈጠራ ደግሞ ለነባር ቃላት ተጨማሪ ትርጉም እንዲይዙ ማድረግ ናቸው፡፡ ከእነኚህ ዘዴዎች አንዱን ወይም ከዚያ ከላይ በመጠቀም በልዩ ልዩ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ፀሐፍት ከተፈጠሩ ቃላት መካከል የኦ ሄንሪ Banana Republic (እ.ኤ.አ. በ1904 በወጣው Cabbages and Kings የተሰኘ የአጫጭር ልቦለድ ስብስብ)፤ የማርክ ትዌይን Hard-Boiled  (1886 as an adjective meaning “hardened”)፤ የሪቻርድ ቢ. ሼሪዳን Malapropism (The Rivals በተሰኘ የ1775 ቴአትር) እንዲሁም የዶናልድ ጎርደን Whodunit (1930) ይገኙበታል፡፡
ሼክስፒር፡ የፈረንጅ ‹‹አበው››
ሌሎች እንደ ጄምስ ጆይስ ያሉ ፀሐፊያንም በርካታ ቃላትን በመፍጠር የሚጠቀሱ ቢሆንም በእንግሊዝኛ ቋንቋና ስነጽሑፍ ውስጥ ብቻውን ብዙ ቃላትን በመፍጠር ሼክስፒርን የሚያክል አይገኝም፡፡ ሼክስፒር አሁን ድረስ በቋንቋው ተናጋሪዎች ግልጋሎት ላይ የሚውሉ ከ1700 በላይ ቃላትን ሊፈጥር ችሏል፡፡ ከእነኚህም መካከል bump, hurry, critical, እና road ይገኙበታል፡፡
ይህ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ባለውለታ የመፍጠር አቅሙ አዳዲስ ቃላት ላይ ብቻ ያተኮረ አልነበረም፡፡ የብዙዎቹ ፈሊጣዊ አነጋገሮችና አባባሎች ምንጭም ሼክስፒር ነው፡፡ The world’s my oyster፤ such stuff as dreams are made on እንዲሁም  much ado About nothingን ጨምሮ የሌሎች በርካታ አባባሎች ፈጣሪ ነው፡፡ በአማርኛ አንድን ምሳሌያዊ ንግግር ተከትሎ ‹‹…እንዲሉ አበው›› እንደሚባል ሁሉ በእንግሊዝኛም ‹‹…እንዲል ሼክስፒር›› ተብሎ ቢቋጭ የመሳሳት ዕድሉ በጣም ጠባብ ነው፡፡ በአጭሩ ሼክስፒር የፈረንጅ ‹‹አበው›› ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ (ሼክስፒር ከፈጠራቸው ሌሎች አባባሎችና ምሳሌያዊ ንግግሮች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡ Salad Days, Not slept one wink, Love is blind, Knock knock! Who’s there?, Laughing stock, Faint hearted, Break the ice, All that glitters is not gold) ወዘተ…
የአማርኛ ስነጽሑፍ ሼክስፒር
የበለጠ ወደሚመለከተን ቦታ መለስ ብለን ስንነጋር… የአማርኛ ስነጽሑፍን እናነሳለን፡፡ በስነጽሑፋችን አዳዲስ ቃላትን ፈጥሮ የመጠቀም ጉዳይ እምብዛም ነው፡፡ ስነጽሑፍ ብቻ ሳይሆን ከቋንቋ የሚወስደው፤ ቋንቋም ከስነጽሑፍ ሊወስድ እንደሚችል ለደራሲዎቻችን ተገልጦላቸው የሚያውቅ አይመስልም፡፡ ይባስ ብሎም የማሕበራችን አደረጃጀት በጽሑፍ ላይ ያልተመሠረተ በመሆኑ (Literary ባለመሆናችን) በስነጽሑፋችንና በዕለት ተዕለት የንግግር ቋንቋችን ያለው ድልድይ አልተገነባም፡፡ እንዲያ ባይሆን ኖሮ የአንድን ነገር መቋጫ ‹‹ኦሮማይ›› ወይም ደግሞ የከበርቴና የድሃ ቤተሰብ ልጆችን ጥንድ ‹‹ፍቅር እስከ መቃብራዊ›› ማለት በቻልን ነበር፡፡
ከደራሲዎችችን ስሞችና ሥራዎች ተራብተው የሚፈጠሩ አዳዲስ ቃላት ቢኖሩን እንኳ የፈጠራው ባለመብት ደራሲው ሳይሆን አባባሉን ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመው ግለሰብ (ምናልባት ሀያሲ) ወይም ተናጋሪው በደፈናው ነው፡፡ ፍጹም አዳዲስ ቃላትን በመፍጠር ረገድ ግን በዕውነታ እንጂ በእሳቤ ላይ ያተኮሩ ሥራዎች በብዛት አለመኖር ደራሲዎቻችን አዳዲስ ቃላትን ከመፍጠር እንዲቆጠቡ አድርጓቸው ሊሆን ይችላል፡፡  
በአማርኛ ስነጽሑፍ የአዳም ረታን ያክል አዳዲስ ቃላትን በመፍጠር የተካነ ደራሲ እስካሁን አላጋጠመኝም፡፡ ይህ ደራሲ እስካሁን ባሳተማቸው ስምንት መጽሐፍቱ ከአንድ መቶ በላይ አዳዲስ ቃላትን ለአማርኛ ቋንቋ አስተዋውቋል፡፡ በዚህ መልኩ አዳም የአማርኛ ስነጽሑፍ ሼክስፒር ነው ማለት ይቻላል፡፡
አዳም አዳዲስ ቃላትን ሲሠራ ሁሉንም ዓይነት የአዲስ ቃላት አፈጣጠር ይጠቀማል፡፡ የአዳዲስ ቃላት መዝገቡ ፍፁም አዳዲስ የሆኑ ቃላትን ከመፍጠር እስከ ድርብርብ ቃላት፤ ከውርስ ቃላት እስከ ምሕጻረ ቃል፤ ከድምፀ-ቀድ ቃላት እስከ አዳዲስ አባባሎች ያካልላል፡፡     
አዳም ለነባር ቃላት አዳዲስ ትርጓሜ ሲሰጥ በቋንቋ ውስጥ ከዚህ በፊት ጥቅም ላይ የዋሉ ቃላትን አካሄድ ተከትሎ ስለሆነ አዲሱ ትርጉም አይጎረብጠንም፡፡ ለአብነት ያክል በ‹‹ይወስዳል መንድ ያመጣል መንገድ›› (ይ.መ.ያ.መ.) ‹‹ክንፍ›› ሲል ‹‹ከመሀሉ ትልቅ ጥቁር የጆፌ አሞራ ምስል ያለበት ሰማያዊ የፕላስቲክ መታወቂያ ካርድ›› ለማለት ነው፡፡ ምሣሌ፡ ‹‹በጨዋታ፡ በቀልድ፡ የፀጋ ዘር መሆኑን እንዳምነው በዚያን ጊዜ የሚሰጠውን ክንፍ ከኮቱ ደረት ኪስ አውጥቶ አሳየኝ››፡፡ (ይ.መ.ያ.መ.) በተጨማሪም ‹‹ገበሬ›› ሲል አንድ ብር ለማለት ነው፡፡ ምሣሌ፡ ‹‹በኪሱ ቢያንስ አምስት ገበሬ አያጣም››፡፡ የዚህ ቃል አመጣጥ ‹‹የአንድ ብር ኖት ላይ ካለው አራሽ ገበሬ ምክንያት የተሰጠ ስያሜ›› እንደሆነ በ“አለንጋና ምስር” (አ.ም.) ውስጥ ከሚገኙት ታሪኮች በአንዱ ውስጥ ተጽፏል፡፡ (በእርግጥ በኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ይህ አባባል ጥቅም ላይ ይውል ነበር)፡፡
የአዳም ቃላት መለያ በቋንቋ ውስጥ ከዚህ በፊት ጥቅም ላይ የዋሉ ቃላትን ባሕሪ ተከትሎ መፈጠራቸው ብቻ ሳይሆን ዘመን ተሻግረው አሁን ያለንበትን ወቅት ነባራዊ ሁኔታ የሚገልፁ ሆነው ይገኛሉ፡፡ “እቴሜቴ ሎሚ ሽታ” (እ.ሎ.ሽ.) በተባለው ድርሰት ውስጥ “ገዳም አባተ” ተብሎ በአባቱ ስም ከመጠራት ይልቅ በሚስቱ ስም “ገዳም ማርታ” መባልን የመረጠ አንድ ደራሲ ይገኛል፡፡ ይህ ገጸባሕሪ የአባቱን ስም በሚስቱ ከመለወጡ በላይ የሚታወሰው ግን አዲስ በፈጠራት ጠቃሚ ቃል ነው፡ ‹‹ዝንደዳ››፡፡ ‹‹ዝንደዳ በጭራሹ አገርን መርሳት፣ ለአገር የሚችሉትን አለማድረግ፣ ግን የአገሪቷን ምግቦች እያሳደዱ በመብላት በዚያ ብቻ ዜግነትን ለማሳየት መጣር ማለት ነው›› ይላል ገዳም፡፡ “መዘንደድ ከሀዲ መሆን ነው” የሚለው ይህ ደራሲ፤ በ1978 ዓ.ም. በወጣው “የጨርቆስና የአገርሽ ዛንታ፡ ግልፅ ደብዳቤ ለአዲስ አበባ ጃሌዎች” በተሰኘ መጽሐፉ እንዲህ ይላል፡ “……የምናደርገው ነገር ቢኖር የልኳንዳ ስጋ በርካሽ ገዝተን እምብርታችን እስኪፈርስ እሱን በልተን በየአልጋችን መውደቅ ነው፡፡ የዚህ ድካም ሲያልፍ እሷና እኔ፣ እኔና እሷ ይቀጥላል፡፡ እሱና እሷ ይቀጥላል፡፡ ጠላት መጥቶ በር አንኳኩቶ አገራችንን ቢወስድ አንሰማም፡፡ ይሄንን ዝንደዳ እለዋለሁ”፡፡ (እ.ሎ.ሽ.)፡፡
ከፍፁም አዲስ እስከ ድርብርብ ቃላት
ከሚከተሉት ቃላት ውስጥ በመደበኛ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ውስጥ የሚገኘው ቃል የቱ ነው፤ ሞአብ፣ ተነካናኪ፣ ማላፍ፣ ማላፌሮ ወይስ ስርቀት? ለሚል ጥያቄ መልሱ ‹‹የትኛውም አይደለም›› ይሆናል፡፡ እነኚህ ቃላት (ሌሎች መሰሎቻቸውን ጨምሮ) አዳም ረታ የፈጠራቸው ፍፁም አዳዲስ ቃላት ናቸው፡፡ እነኚህ ቃላት ፍፁም አዲስ ቢሆኑም የእያንዳንዳቸውን ትርጉም ስንመለከት ወይም እንዲሁ ድምጻቸውን ስንሰማ ግን ከዚህ በፊት የምናውቃቸው እንደሆነ ይሰማናል፡፡ ለምሳሌ ‹‹ሞአብ›› የተሰኘውን ቃል እንውሰድ፡፡ ‹‹ሞአቦች በ2030 ዓ.ም. አካባቢ የመንገድ ላይ ሱቅ በደረቴዎች የሚጠሩበት ስም›› ነው (ይ.መ.ያ.መ.)፡፡ ሞአብ ፍፁም አዲስ ቃል ቢሆንም የቃሉን አመጣጥ ስናይ ግን ቃሉ አዲስ እንዳልሆነ ዓይነት ይሰማናል፡፡ የቃሉ አመጣጥ፡ ‹‹ቃሉን የፈጠረው ‘ሞአገለብ’ የተባለ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ነው፡፡›› (ዝኒ ከማሁ) በስሙ ሱቆች የተሰየሙለት አንድ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ትዝ አላለዎትም?
ሌላው ጠቃሚ የአዳም የፈጠራ ቃል ተነካናኪ ይሰኛል፡፡ የዚህ ቃል አወቃቀር እንደ ሁሉም የአዳም አዳዲስ ቃላት ሁሉ ለአማርኛ ስነ ድምፅ ባይተዋር ካለመሆኑም በላይ ሁለት ልዩ ልዩ ትርጉሞች ያሉት መሆኑ እንግዳነቱን ያስቀርለታል፡፡ በተጨማሪም በዕለት ተዕለት ንግግራችን ውስጥ አካተን ልንጠቀምበት ስለምንችል የሆነ ቋንቋ ክፍተትን ይሞላል፡፡ ተነካናኪ ማለት በመጀመሪያ ትርጉሙ ‹‹በምትችለው መጠን ለአገርህ መልካም ነገር ለመሥራት መሳተፍ፡፡ አገርህን በተመለከተ ስለ ሁሉ ነገር ለማወቅ መጣር›› ማለት ነው፡፡ ተነካናኪ በሁለተኛ ትርጉሙ ደግሞ ‹‹በአገራችን የባህል አሳሳል የበላይነት ቦታ ያላቸውን ዐይንና ፊትን በተለይ ዐይንን በሌሎች የስሜት ሕዋሳትና ብልቶች ቀስ በቀስ የመተካትና ቢቻል እኩል ለማድረግ የሚሞክር የሰዓሊ መስኮት ገረሱ አሳሳል ዘይቤ ነው›› (እ.ሎ.ሽ.)፡፡ ይህ ቃል በሦስተኛ ትርጉሙ የሌላ ቃል ተመሳሳይ ሆኖ ይመጣል፡ የቅርባዊነት፡፡ ተነካናኪ እዚህ ላይ ‹‹የሰዓሊ መስኮት ገረሱ የብሩሽ አጣጣል (የአሳሳል) ስልት ነው›› (እ.ሎ.ሽ.) (ብሩሽ መጣል ራሱ የፈጠራ ቃል ነው)፡፡
 አዳዲስ ቃላትን ማስተዋወቅ ሌላኛው ገጽ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ቃላትን የተወሰነ ክፍል ወስዶ በማጣመር አዲስ ቃል መፍጠር ነው፡፡ (A portmanteau word)፡፡ በዚህ መልኩ ከተሠሩ የአዳም ቃላት ውስጥ ውባል (ውሽማ + ባል)፣ መዲባ (መዲና + ባላገር፤ ይህ ቃል የእንግሊዝኛውን “suburb” የሚተካ ነው)፣ አፍገሬ (በአፉ አገሬ አገሬ የሚል) እንዲሁም አልተወረወረችውም (አልወረወረችውም + አልተወረወረችም) ሁለት ቃላትን በአንድ ላይ በማጣመር የተገኙ አዳዲስ ቃላት ናቸው፡፡
ከውርስ እስከ ምሕጻረ ቃል
እየጠፋ ካለ ወይም ደግሞ ጨርሶ ከሞተ ቋንቋ ላይ የሚወሰዱ ቃላትንም እንደ አዲስ ቃል ከወሰድናቸው በአዳም መዝገበ ቃላት ውስጥ ተጠቃሹ ቃል ‹‹ሐሲር›› ይሆናል፡፡ ደራሲው “መረቅ” በተሰኘው አዲሱ ሥራው ውስጥ ‹‹የተማራችሁትም ያልተማራችሁትም በሐሲር ጎዳና ሰከም ሰከም ስትሉ እንደ አንድ ዜጋ ወንድማችሁ ታዘብኳችሁ›› ይላል፡፡ “ሐሲር” ግዕዝ ሲሆን ትርጓሜውም ውድቀት ወይም የእንግሊዝኛውን decadence የሚተካ ነው፡፡
አዳዲስ ምሕጻረ ቃላትን በማስተዋወቅም ቢሆን ደራሲው አልቦዘነም፡፡ OMG (O, my God) የእንግሊዝኛ ተናጋሪዎች ለከሚያዘወትሯቸው አባባሎች አንዱ ነው፡፡ ይህንን በአማርኛ ለመተካት ይመስላል ‹‹ወይ እግዚአብሔር ሆይ››ን በምሕጻረ ቃል ወእሆ ብሎ “መረቅ” በተሰኘው መጽሐፉ ውስጥ ያስቀመጠልን፡፡ በእርግጥ ወእሆ ሁለተኛም ትርጉምም አለው፡ ወንድምና እህቶቼ ሆይ፡፡
ከድምፀ ቀድ ቃላት እስከ አዳዲስ አባባሎች
ድምፀ ቀድ ቃላት (Onomatopoeic words) አንድን ድርጊት ወይም ሁኔታ ከሚያወጣው ድምፅ በመነሳት የሚፈጠሩ ቃላት ሲሆኑ በስነጽሑፍ በተለይም ደግሞ በስነ ግጥም ውስጥ ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ በዚህ መልኩ ከተፈጠሩ የአዳም ቃላት ዋነኛው ‹‹መቸሻቸሽ›› ይሰኛል፡፡ ሆኖም የዚህ ቃል መፈጠር ከድምፀ ቀድነትም በላይ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ደራሲው ‹‹መቸሻቸሽ›› ሲል በአንድ ቃል ያስቀመጠው ሕዝቡ በፖለቲካ አቋም መለያየት ሰበብ ጎራ ለይቶ ደም የተፋሰሰበትን የያ ትውልድን ዘመን ሲሆን ቀጥተኛ ትርጉሙም ‹‹ወጣቶች በቡድን ተከፋፍለው በ “ቸ” እና በ “ሸ” ሆሄያት ልዩነት የፖለቲካ ፍትጊያ ሲያደርጉ›› ማለት ነው (እ.ሎ.ሽ.)፡፡ የቃሉ ፈጣሪ መስኮት ገረሱ የተባለው ገጸባሕሪ ሲሆን የቃሉ አመጣጥም “ቸ” እና “ሸ” በተባሉ ሆሄያት እንደመጋጨት ማለት ነው፡፡ መስኮት ‹‹በዚያን ጊዜ የሚሠራውን ፖለቲካ የሚጠራበት [ይህ መቸሻቸሽ የተሰኘ] ቃል ርቢው በራሱ አዲስ ቃል ነው፡ ትሹ (ለብዙ ቁጥር ‹‹ትሹዎች››)፡፡ ትርጓሜውም ‹‹አንድ ተመሳሳይ ሃሳብ አሰልፈው ግን እርስ በርስ የሚደባደቡ ቡድኖች›› ማለት ነው (ዝኒ ከማሁ)፡፡
ፍፁም አዲስ የሆኑ ቃላትን ከማስተዋወቅ ባሻገርም አዳም ፍፁም አዳዲስ አባባሎችን ለመፍጠር ችሏል፡፡ ከነዚህም ውስጥ “የሽግግር ሰቀቀን” አንዱ ሲሆን ሌላኛው “የረሻት ይሉኝታ” ነው፡፡ የሽግግር ሰቀቀን በሌላ አጠራር “የሽወዳ ሰቀቀን” የሚባል ሲሆን ‹‹ከመጋለጥ ለመሸሽ አርዕስት ለመለወጥ የሚዋሽ (ውሸት የተናገረ) ሰው አርዕስት ሲለውጥ በገፁ ይሁን በገላው የሚያሳየው መረበሽ›› ነው፡፡ ምሳሌ፡ ‹‹ይኼን የአርዕስት ልወጣ ስለተላመደው አይኖቹ ውስጥና ኩነቱ ላይ የሽወዳ ሰቀቀን ወይም የሽግግር ሰቀቀን አይታይም›› (እ.ሎ.ሽ.)፡፡ “መረቅ” በተባለው መጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሰው “የረሻት ይሉኝታ” የሚል አባባል ደግሞ ‹‹ወሲብ ላደረጉለት ሰው ማዳላት›› ማለት ነው፡፡ (ረሻት በግዕዝ የወንድ የዘር ፈሳሽ ማለት ነው)፡፡
አዳምና የቃላቱ እርምጃ
ለአንድ ቋንቋ ማደግ አስተዋፅዖ ከሚያደርጉ ነገሮች አንዱ በፍጥነት እያደገ የሚሄድ ቴክኖሎጂ ሲሆን ሌላኛው ጠንካራ የስነጽሑፍ ባሕል ነው፡፡ በሌላው ዓለም የቴክኖሎጂውን ዕድገት ተከትለው የተፈጠሩ በርካታ ቃላትን ማግኘት የተለመደ ሲሆን ከነዚህም መካከል ምስልና ድምፅን በአንድ ላይ የሚቀርፅ መሣሪያ- ‘ካምኮደር’፤ ግራማፎን ከሚባለው የሙዚቃ ማጫወቻ መሣሪያ ተራብቶ የተፈጠረው- ‘ግራሚ’ እንዲሁም በቅርቡ በኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት ውስጥ የተካተተችው ዝነኛ ቃል ‘ሰልፊ’ እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል፡፡  
ደግመን ወደ አገራችን ጉዳይ ስንመለስ… የቴክኖሎጂውን ነገር አያዛልቀንምና የስነጽሑፉን እናንሳ፡፡ አዳዲስ ቃላት ከስነ ጽሑፍ ከሚመነጩበት መንገዶች አንዱ የመጻሕፍት ርዕስን ወይም የደራሲዎችን ስም በመውሰድ እንደሆነ ከላይ ተጠቅሷል፡፡  በዚህ ስልት ከተፈጠሩ አባባሎች “አማኑኤል ደርሶ መልስ” (የአዕምሮ ጤና የማይሰማውን ሰው ለመግለፅ) አንድ ምሳሌ ነው፡፡ ይህ አባባል “በዚያ ጊዜ ተወዳጅ ከነበረው ከብርሃኑ ዘርይሁን ልቦለድ መጽሐፍ አርዕስት ከ‘አማኑኤል ደርሶ መልስ’ የተወሰደና በከተማ ትውፊት ውስጥ የተዋቀረ” መሆኑ ተጠቅሶ አጠቃቀሙም በተከታዩ ንግግር ውስጥ ተቀምጧል፡  “እዚ ጋ ስሙኝ--ነጋ የታሪክ አስተማሪያችን አማኑኤል ደርሶ መልስ ናት ሲባል ሰምተናል፡፡ የምትረብሹ ካላችሁ እብድ የሚሠራውን ስለማያውቅ……” (እ.ሎ.ሽ.)፡፡
ደራሲው አዳም ይህንን የብርሃኑ ዘርይሁን ርዕስ ወስዶ ተጨማሪ ትርጉም የሰጠው የዕለት ተዕለት ቋንቋችን ከስነጽሑፋችን መውረስ የሚችለው/የሚገባው ብዙ ነገር እንዳለ ሲጠቁመን ይሆናል፡፡ አዳዲስ ቃላትና አባባሎችን የሚፈጥረውም የድርሰቱን ድባብ ለማዋቀርና የተሟላ የፈጠራ ዓለም ለመገንባት ብቻ እንዳልሆነ ሲነግረን ይሆናል፡፡
ለነገሩ ብዙ ጊዜ ወደራሳችን መመልከት ስለሚያዳግተን እንጂ ስነጽሁፋችን ለቋንቋችን ዕድገት የሚያበረክተው አጥቶ አይመስለኝም፡፡ በአንድ ወቅት በ“አዲስ ነገር” ጋዜጣ ላይ በወጣ ፅሁፍ ውስጥ “የአኪሊስ እግር” የሚል አባባል ተካቶ ነበር፡፡ ይህ አባባል እንግሊዝኛ ከግሪክ አፈታሪክ ወስዶ የፈጠረው አዲስ አባባል ሲሆን በአማርኛ ሲባል ግን ባይተዋር ነው፡፡ ለዚህ እና ለሌሎች መሰል ቃላትና አባባሎች ስነጽሑፋችንን ብንፈትሽ አቻ የሚታጣለት አይሆንም፡፡ ለምሳሌ “ሲሲፊያን” የሚለውን ቃል ብንወስድ ከግሪክ ሚቶሎጂ ገጸባሕርዩ ከሲሲፈስ የተራባ ቃል ነው- ውጤት አልባ ከንቱ ድካምን ለማመልከት፡፡ ይሄንን በአማርኛ ጽሑፍም ሆነ ንግግር ውስጥ ለመጠቀም ብናስብ “ካሲያዊ” ልንለው እንችላለን፡፡ ካሲ ‹‹ከአላህ ጋር ላድርግልህ-አድርግልኝ ስምምነት ውስጥ ገብቶ በተደረገለት ችሮታ ምላሽ ወደ ወፍነት የተለወጠ፤ ሩቅ ቦታ ከሚገኝ ባሕር ኩምቢው ላይ በሚንጠለጠል ወንፊት ውሃ እየቀዳ ሽንቁር ማሰሮ እንዲሞላ የተፈረደበት›› “ሕማማትና በገና” በተሰኘው መጽሐፍ ውስጥ የሚገኝ የአዳም ረታ ገጸባሕሪ ነው፡፡
ይህ ደራሲ ከመቶ በላይ አዳዲስ ቃላትና አባባሎች እንደፈጠረ ከላይ ተጠቅሷል፡፡ እኛስ የባሕል አንዱ መገለጫ የሆነውን ቋንቋችንን ለማሳደግ እንዲህ ካልተጣጣርን አገር ወዳድነታችን አፋዊ ብቻ የሆነ ‹‹አፍገሬዎች›› ሆነን መቅረታችን አይደል?

Read 7812 times