Saturday, 14 February 2015 14:58

በ100 ሚ. ብር የተገነባው “አዲሲኒያን” ሆቴል ሥራ ጀመረ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

ከሶስት ዓመት በፊት ግንባታው ተጀምሮ በቅርቡ የተጠናቀቀውና 100 ሚሊዮን ብር የወጣበት “አዲሲኒያን” ዓለም አቀፍ ሆቴል ባለፈው ረቡዕ ተመርቆ ሥራ ጀመረ፡፡ ባለ አራት ኮከብ ደረጃ እንዳለው የተነገረለት ዘመናዊው ሆቴል፤ሁለት ትላልቅ ሬስቶራንቶች፣ የተለያየ ደረጃ ያላቸው 60 የመኝታ ክፍሎች፣ ጂም ሃውስ ስፓ እና ሌሎች አገልግሎቶች እንደተሟሉለት የሆቴሉ ባለቤትና ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ አዲስ ገ/ማሪያም ገልፀዋል፡፡
ሃያ ሁለት ማዞሪያ ቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል አካባቢ የሚገኘው ባለ 10 ፎቅ  ሆቴል፤ ለ85 ሰዎች የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን በሙሉ አቅሙ ስራ ሲጀምር የሰራተኛውን ቁጥር ወደ 120 እንደሚያሳድግ ተጠቁሟል፡፡ ከወጣትነት እድሜያቸው አንስቶ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች እንደኖሩ የተናገሩት ወ/ሮ አዲስ፤ ገና ልጅ ሳሉ ጀምሮ ነጋዴ የመሆን ጥልቅ ፍቅር ነበራቸው፡፡ መጀመሪያ በትራንስፖርት ዘርፍ ውስጥ  ተሰማርተው ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን በመቀጠልም ከአሁኑ ሆቴል ጎን የሚገኘውን “አዲስ የእንግዳ ማረፊያ” በመክፈት እየሰሩ ባጠራቀሙት ገንዘብ እንዲሁም ከአዋሽ ባንክ በተገኘ ብድር “አዲሲኒያ”ን መገንባት እንደቻሉ አስረድተዋል፡፡  
ሆቴሉ ግሎቲን ከተባለው አለርጂ አምጪ ንጥረ ነገር ነፃ የሆኑ ኬኮችን ከጤፍ በመሥራት እያከፋፈለ እንደሆነ የጠቆሙት የ“አዲሲኒያ” ኤክስኪዩቲቭ ሼፍ ሲራክ፤ ይህም በአገራችን እምብዛም የተለመደ እንዳልሆነና ሆቴሉን ከሌሎች ለየት እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡ በሆቴሉ ከኬኮች በተጨማሪ ሌሎች ጣፋጭ ምግቦችና ላዛኛ  ከጤፍ  እንደሚሰሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡  

Read 1628 times