Saturday, 07 February 2015 13:40

የመምህሬ ወልደ ዩሃንስ ቀልዶችና አሽሙሮች - ክፍል 2

Written by  ከጉማራ ዙምራ zmtm1229@yahoo.com
Rate this item
(2 votes)

        አራት ገበሬዎች አክሱም ጽዮን ሊሳለሙ ሲመጡ ቀዬአቸው ላይ አንዲት ጠብታ ዝናብ እንኳን ሳይጥል አክሱም ግን ከባድ ዝናብ ጥሎ ይቆያቸዋል፡፡
ጠላ ቤት ገብተው ሲያወጉ አንደኛው “እንደው ይሄ መድኃኔዓለምስ !! እንዳ ማሪያም አክሱም ወተት የሆነ ዝናብ ጥሎ ሲያበቃ እኛ መሬት ላይ ጠብ የምትል ዝናብ ይከልክለን?” ብለው ሲያማርሩ ምህረይ ጆሮ ውስጥ ጨዋታው ይገባል፡፡ ምህረይ መለስ አድርገው “እና እንደ እናቱ እንዲያያችሁ ትፈልጋላችሁ እንዴ?” አሉ ይባላል፡፡
ባለፈው ሳምንት ጽሁፌ ማገባደጃ ላይ በቸር እንሰንብት ብለን እንደተለያየነው ይኸው በሰላም ቆይተን ለቀጣይ ክፍል ደርሰናልና ተመስገን ነው መቼስ ሌላ ምን ይባላል፡፡ የክፍል አንድ ጽሁፌ ላይ እንደገለጽኩላችሁ፣ የምህረይ ወልደ ዩሀንስ የህይወት ጉዞ እጅግ ፈታኝና መከራ የተቀላቀለበት፤ አሳዛኙ የህይወት እጣ ፈንታቸውን በጸጋ ተቀበለው ነገር ግን ከዚያ ክስተት በኋላ አብዛኛው ማህበረሰብ “እብደት” ብሎ የሚጠራው፣ የፍልስፍና ባለሙያዎች ደግሞ “ህሊናዊ ምጥቀትን ማረጋገጥ” የሚሉትን ዓለም መስርተው ለሶስት ዐስርት ዓመታት ዘልቀዋል፡፡
ህሊናዊ ምጥቀትን ማረጋገጥ ምን ማለት ነው? ቀላል የሚመስል ነገር ግን ጥልቅ የሆነ ሃሳብ ውስጥ ስዋኝ በአጋጣሚ ስለ ምህረይ ወልደዩሃንስ በተጻፈው መጽሀፍ ላይ የግል ምልከታውን በአጭሩ ያኖረ ሰው በግሌ አፈላልጌ አገኘሁት፡፡ አቶ ጎይቶም ገብሩ ይባላል፡፡ አክሱም ከተማ ተወልዶ ያደገ ሲሆን ምህረይ ወልደዩሃንስን ከልጅነት ጀምሮ ያውቃቸዋል። በፍልስፍና የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ አግኝቷል፡፡ “ፍልስፍና ዘ ካህሊል ጅብራን” የሚል መጽሀፍ በትግርኛ ተርጉሞ ለአንባቢያን እንዳደረሰ ነግሮኛል፡፡ ህሊናዊ ምጥቀትን ማረጋገጥ ምን ማለት ነው ? እንዴት ይረጋገጣል? ከፍልስፍና አንጻር እንዴት ይታያል? ከምህረይ ወልደዩሃንስ ህይወት ጋር የሚያገናኘው ነገር ይኖር ይሆን? የሚሉ እና ሌሎች ጥያቄዎችንም በቃለ መጠይቅ መልክ አቅርቤለት ነበር፡፡ የሰጠኝን ምላሽ ለጽሁፍ በሚመች መልክ አቅርቤዋለሁ፡፡
እብደት የተለያዩ መገለጫዎች ሊኖሩት ይችላሉ ይላሉ አቶ ጎይቶም፡፡ ከፍልስፍና አንጻር እብደት ማለት ምን ማለት ነው? ከምህረይ ወልደዩሀንስ የህይወት ታሪክ ጋር አያይዘው ቢያስረዱኝ? ብዬ ያቀረብኩላቸውን ጥያቄ ሲመልሱ፤ በመሰረቱ እብደትን በሁለት መንገድ ከፍለን ልናየው እንችላለን። አንደኛው የህሊናዊ ወይም የመስተሀለይ  ምጥቀት የምንለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከህሊናዊ ዝቅጠት ጋር ልናያይዘው እንችላለን፡፡ የተለያዩ ፈላስፎች  ስለ እብደት የተለያዩ ነገሮችን ብለዋል፡፡ ለምሳሌ ጀርመናዊው ፈላስፋ ፍሬድሪክ ኒቼ እንዲህ ይላል፡- “በመጀመሪያ እብደት ነበር። እብደትም ከዘላለማዊነት ጋር ነበር፡፡ እብደትም ዘላለማዊነት ነው፡፡” ስለዚህም እብደት ሁሌም ያለና ከእኛ ጋር የሚኖር እንደሆነ ነው የሚነግረን፡፡ በተጨማሪም ኒቼ  “በቡድን ማበድ ወይም በቡድን ተደራጅተህ ማበድ በጣም የተለመደ ነገር ቢሆንም ግለሰባዊ እብደት ግን ብዙም የተለመደ አይደለም” ይላል፡፡ በመሆኑም ይሄ ወደ ግለሰባዊ አስተሳሳብ ወይም Individual way of being ወደ ሚለው ሃሳብ ይወስደናል፡፡ ይሄን ጉዳይ ከምህረይ ጋር ስናያይዘው ሁለት ነገሮችን መውሰድ እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው እርሳቸው በህይወታቸው ላይ በደረሰው ከባድ ሀዘንና መከራ ምክንያት ህሊናዊ ምጥቀት ያረጋገጡ ሰው ስለሆኑ  ወይም ከተለመደው አስተሳሰብና አካሄድ ወጣ ስላሉ፣ ህብረተሰቡ እብድ ብሎ ይጥራቸው እንጂ ህሊናዊ ምጥቀታቸውን ያረጋገጡ ሰው ነበሩ ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ሁለተኛው ነገር ግላዊ ህይወት ስለመምራት ፈላስፋዎች የተለያዩ ነገሮች የሚነግሩን በመሆኑ ከፍልስፍናዊ እይታ ጋር እያሰናሰልን ብንሄድ ጥሩ ነው፡፡ ፈላስፋዎች ይሄ ግላዊ ህይወትን ከሰዎች መንጋ ዓለም ጋር በማነጻጸር ይነግሩናል፡፡ ለምሳሌ ብዙ ሰዎች ራሳቸውን ከመንጋ ውስጥ ማጣት የሚመርጡበት የራሳቸው ምክንያት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ለምሳሌ ኪርኪጋድ የተባለው ዴንማርካዊ ፈላስፋ ምን ይላል፤ “ሰዎች በቡድን ውስጥ ራሳቸውን ያጣሉ፡፡ ይህን የሚያደርጉበት ምክንያት ለምሳሌ አንዳንድ እንስሳት ራሳቸውን ለመከላከል ሲያስቡ አፈር ይቆፍሩና ራሳቸውን አፈሩ ውስጥ ለመደበቅ ይጥራሉ፡፡ ልክ እንደ እንስሳቱ የሰው ልጅም ከመንጋው ለመራቅ በሚፈልግ ጊዜ ራሱን አፈር ውስጥ ይደብቃል እንደማለት ነው” ይለናል ኪርኪጋድ፡፡ ይህም ማለት ሰዎች አንድን አመለካከት በቡድን ሲይዙት ምንም ችግር ላይኖረው ይችላል። ነገር ግን አንድን አመለካከት በግለሰብ ደረጃ ማራመድ ስትጀምር ችግር ይሆናል። ምክንያቱም በጋራ የሚታሰብ አመለካከት ካለ ለግላዊ ህይወት አስጊ አይሆንም፡፡ ነገር ግን ግላዊ ህይወት ከዚህ ወጣ ያለ አስተሳሰብ ስለሆነ ነው፡፡
ማርቲን ሀይድጋርድ የተባለው ጀርመናዊ ፈላስፋ እንደሚነግረን ከሆነ ደግሞ “የሰው ልጆች ግላዊ አስተሳሰብን መቀዳጀት ካልቻሉ፣ ሳያስቡት ወደ የሰዎች መንጋ ዓለም ይፈጠፈጣሉ ይላል፡፡ አንድን ነገር ሌሎች እንዳዩት ማየት ስንጀምር ነው ፍጥፈጣው የሚከሰተው፡፡ እናም በነዚህ የሰዎች መንጋ ዓለም ራሳቸውን በማጣት፣ እንደ አንድ ተግባራዊ ስራ እንደሚሰራ ቁስ አካል ይታያሉ” ይላል፡፡ በሰዎች መንጋ አለም ውስጥ ራሳቸውን ያጡና አንድን የጥበብ ስራ ወይም አካሄድ ሌሎች እንዳዩትና ሌሎች ሂስ እንደሰጡበት እይታ ያዩታል። ስለዚህ የመንጋው ደስታ የእነርሱ ደስታ ይሆናል፡፡ የመንጋውን ሀዘን የእነርሱም ሀዘን አድርገው ያዩታል ማለት ነው፡፡
ነገር ግን ግላዊ ህይወት ስንል ብዙ Existential Philosophers እንደ እነ ኒቼ፤ ኪርኪጋድ እና ከቅርቦቹም እንደ እነ ሀይድጋርድ እንደሚመርጡት “አንድ ሰው ግላዊ ህይወትን መምራት ካልቻለ በነጻነት ማሰብ ይሳነዋል” ብለው ስለሚያምኑ ነው። ሁለተኛው “የሰው ልጅ አንድ ነገር ከሌሎች ለየት ባለ መንገድ ለማየት ከፈለገ፣ ግላዊ ህይወቱን ነው መምረጥ ያለበት” ብለው ያምናሉ፡፡” ይህንን የፍልስፍና እይታ ወደ ምህረይ ስናመጣው ምን ፋይዳ ይኖረዋል? ነው ጥያቄው፡፡ የምህረይ የእብደት ደረጃዎች አሉ፡፡ እርሳቸውን የሚያውቁ ብዙ ሰዎች እንደሚናገሩት ከሆነ፣ መጀመሪያ ዝምተኛነት ያጠቃቸው ነበር -Silence የምንለው ማለት ነው። ከዚያም ብቸኝነት ያጠቃቸው ነበር - Solitude የምንለው ነው፡፡ ሶስተኛው ደግሞ መጮህ፤ በነገሮች መሳቅና ማፏጨት የመሳሰሉትን ያደርጉ ነበር። እነዚህን ነገሮች ስናያቸው ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል ለየት ብለው እንዲታዩ ያደረጓቸው መገለጫዎች ናቸው ማለት እንችላለን፡፡ እነዚህ ድርጊቶች የህይወት ስቃይን ተጋፍጦ በማለፍ፣ ህይወትን እንደ ተራ ጨዋታ ነገር ቆጥሮ ኑሮን መቀጠል መቻል ሊባል ይችላል፡፡
ሌላው ምህረይ ስለ ማህበራዊ፤ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ነጻና ግላዊ በሆነ መልኩ በሽሙጥና በአሽሙር መልክ ሂስ ይሰጡ ነበር። ክላውድ ሳምነር የተባሉ በኢትዮጵያ ፍልስፍና ላይ ሰፊ ምርምር ያካሄዱ ሰው “የቅኔ ትምህርት ለኢትዮጵያ ፍልስፍና መሰረት ነው” ብለው ያምናሉ። (ምህረይ የቤተክህነት ትምህርት ጎጃም ድረስ ሄደው እንደተማሩ-የባለፈው ጽሁፍ ላይ ተጠቅሷል፡፡) ለምን ቢባል “የቅኔ ትምህርት ተማሪዎች ነጻ በሆነና ግላዊ በሆነ መንገድ የማሰብና የመመራመር እድል ስለሚፈጥርላቸው፤ ቅኔ የፍልስፍና መነሻ ምንጭ ነው” ብለው ያምናሉ፡፡ እናም ምህረይ ከቅኔ ትምህርት ባገኙት እውቀት መነሻነት ግላዊ የሆነ አስተሳሰብ፤ እይታ እና ሂስ እንዲሰጡ አግዟቸዋል ሊባል ይችላል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ብዙ ፈላስፋዎች እንደሚስማሙበት፤ የሰው ልጅ ግላዊ የሆነ አስተሳሰብ ማበጀት ካልቻለ በስተቀር (የቡድንን አመለካከትና አስተሳሰብ የሚደግም ከሆነ) አስተሳሰቡ ፍልስፍናዊ ነው ሊባል አይችልም፡፡
ምህረይ ቀን እንደ እብድ ሲጮሁ ውለው ሌሊት ደግሞ ቤ/ክ ሲጸልዩ ያድሩ ነበር፤ ይሄን እንዴት ትመለከተዋለህ ወይም ከምን የመነጨ ነው? ብዬም ጠይቄው ነበር፡፡
እንግዲህ ምህረይ ሁለት የተለያዩ ሰብእናዎች/ dual personalities/ እንደነበራቸው ከልጅነቴ ጀምሮ ሳስተውለው የነበረ ነገር ነው፡፡ እናም ምህረይ በሶስት መንግስታት ስርአት ውስጥ ያለፉ በመሆናቸው ቀን ላይ በተለመደው አነጋገር እንደ እብድ ሆነው ህብረተሰቡን፤ ያለውን መንግስትን ሲወርፉ ውለው፣ ሌሊት ደግሞ ልክ እንደ ሌላው ካህን ሙሉ ሌሊት ቆመው የክህነት አገልግሎት ሲሰጡ ማደራቸው ሁለት የተለያዩ ሰብእናዎች ባለቤት እንደነበሩ አመላካች ነው፡፡
ምህረይ ሽሙጣቸው፤ ሂሳቸው ከባዶ የመነጨ አይደለም፡፡ በአስከፊው የአንበጣ ወረርሽኝ ምክንያት ቤተሰባቸው ለረሀብ በመጋለጡ፣ ቤተሰቤን አተርፋለሁ ብለው ስደትን መርጠው ወጥተው ነበር፡፡ ነገር ግን ሶስት ልጆቻቸውንና ባለቤታቸውን በአስከፊው የተስፋ ምድር ፍለጋ ጉዞ ምክንያት አጥተዋል፤ መሬታቸው ተዘርፏል፤ ተወስዷል፤ ፍርድ ቤት ሄደው መሬታቸውን ለማስመለስ ቢጠይቁም ምላሽ አላገኙም፡፡ እነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ተደራርበው በፈጠሩባቸው ጫና ምክንያት ዝምተኛነት፤ ብቸኝነትና ማፏጨትን ያዘወትሩ እንደነበረ ይነገራል፡፡ በዚህም ምክንያት ራሳቸውን ለማጥፋት “ማይ ሹም” በሚባል ሃይቅ ውስጥ እስከ መግባት  የደረሱበት ሁኔታ እንደነበር መጽሀፉ ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ከዚህ በተቃራኒም ህይወትን እየወረፉ፤ እየተቹ፤ እያሄሱና እየቀለዱ መኖር እንደሚቻል ባለሙሉ ተስፋ እንደነበሩ መረዳት እንችላለን፡፡ እዚህ ላይ ፍሬድሪክ ኒቼ ያለውን መጠቀስ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ “ህይወትን ተስፋ ከመቁረጥና ካለመቁረጥ ባሻገር ማየት መቻል አለብን” ባይ ነው፡፡ ይህን ማድረግ ከቻልን ብቁ ሰው ለመሆን አያዳግተንም ይላል፡፡ እናም ምህረይ ይህን ያረጋገጡ ሰው ነበሩ ለማለት እንደፍራለን፡፡ ነጻ ህሊናዊ አስተሳሰብ ለማረጋገጥ የቻሉ ነበሩ፡፡ ይህን ሁሉ መከራና ስቃይ ተቋቁመው ራሳቸውን ወይም ህይወታቸውን ማስቀጠል የቻሉ በጣም ቆራጥ ሰው እንደነበሩ ከህይወት ታሪካቸው ማረጋገጥ እንችላለን።
ሌላው መታለፍ የሌለበት ነገር ምህረይ ራሳቸውን እንደ አንድ ተራ ሰው ሳይሆን ልክ እንደ አንድ ታላቅ ንጉስ የሚመለከቱ ሰው ነበሩ፡፡ ራሳቸውን ሲጠሩ እንኳን  “ወልደዩሀንስ ንጉስ”  እያሉ ነበር፡፡ ለዚህም ይመስለኛል የአስተሳሰብ፤ የመናገርና የአመለካከት ነጻነት ብቻ ሳይሆን የቦታ ነጻነት (Freedom of Space) ይፈልጉ የነበረው፡፡
እኚህ ሰው የሰዎችን የነፍስ ፍላጎት በቀላሉ የማንበብ እና የመረዳት ችሎታ ነበራቸው፡፡ ለምሳሌ በፍጹም እንዲቀርቧቸው የማይፈልጓቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ ምናልባትም የሰው ልጅ ደመነፍሳዊ ፍላጎትን በቀላሉ ማንበብ የሚችሉ ሰው ስለነበሩ ይመስለኛል። ፈላስፎቹ “Beastly Man ብለው የሚጠሩትን ግማሽ ሰው ግማሽ አውሬ ሰብእናን እንደማለት ነው። እናም የሰው አውሬ ባህሪውን በቀላሉ መረዳት የሚችሉ ዓይነት ሰው ነበሩ፡፡
እርሳቸው ህሊናዊ ምጥቀትን ያረጋገጡ እንደመሆናቸው ሌሎች እብዶችን (ወደ ህሊናዊ ዝቅጠት የተፈጠፈጡትን) ይጠየፉና ይሸሹ ነበር። በተለይ ሴት እብዶችን ሲፈሩ አይጣል ነበር፡፡ በመጽሀፉ ላይ ሴት እብዶችን ለምን እንደሚፈሩ አንድ ሰው ሲጠይቃቸው፤ “ኧረ ተወኝ ወንድሜ፤ ሴቶች ሲያብዱ ደግሞ የምራቸውን ነው፡፡ እንደኛ ለስለስ ያለ አይደለም፡፡ ያከሩታል፡፡” ብለውታል፡፡ በአሽሙሮቻቸው እንሰነባበት፡፡
ካለነበባችሁን
ምህረይ ከአንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ጋር በምርጫ ሰሞን ያወጋሉ፡፡
ምህረይ፡ “እኛን ምረጡ እያላችሁ ለምንድነው የምታደርቁን? ለመሆኑ ከሌሎቹ እናንተ በምንድን ነው የምትሻሉት?”
የተቃዋሚው ፓርቲ አባል፡ “እኛ ምሁሮች ነን፡፡ ብዙ መጽሀፍቶችን አንብበናል፡፡”
ምህረይ፡ “ምን ዋጋ አለው ብዙ መጽሀፍ ማንበብ፡፡ በአግባቡ ካላነበባችሁን፡፡”
ሌላ እብድ
በአንድ ወቅት አክሱም ከተማ ውስጥ ድንጋይ የሚወራወር አዲስ እብድ መጣና ህዝበ አዳምን በድንጋይ ሲያራኩተው፣ ምህረይም እንደ ሌላው ሲሸሹ አንድ ሰው ያያቸውና፤ “ምህረይ እርስዎ እብድ ሆነው እንዴት እብድ ፈርተው ይሮጣሉ?” ብሎ ይጠይቃቸዋል።
ምህረይም ፈጠን ብለው“ ሁላችንም አብደን እንዳየነው እኛ ጨዋታ እንጂ ድንጋይስ አልወረወርንም ነበር፡፡ የዚህ ግን ለብቻው ነው ወንድሜ” ብለው ሩጫቸውን ቀጠሉ፡፡

Read 2496 times