Saturday, 07 February 2015 13:23

“24 አመት ሙሉ የዲሞክራቲክ ተቋማት መጠናከር አልቻሉም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

*ኢዴፓ በእነ አንድነት ጉዳይ ላይ የተሰጠውን ውሳኔ ተችቷል    

ከምርጫ 97 በኋላ የተከሰተውን የፖለቲካ ቀውስ ተከትሎ “ሦስተኛ አማራጭ” በሚል የትግል ስልት ብቅ ያለው ኢዴፓ፤ በግንቦቱ አገራዊ ምርጫ ከሚወዳደሩ 60 ፓርቲዎች አንዱ ነው፡፡ የፓርቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ፤ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ ዶ/ር ጫኔ ከበደ የማስተርስ ዲግሪያቸውን በዴቨሎፕመንታል ኢኮኖሚክስ፣ ዶክትሬታቸውን ደግሞ በዴቨሎፕመንት ስተዲስ ያገኙ ሲሆን በአማካሪነት በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡  

በቅርቡ ምርጫ ቦርድ በአንድነትና በመኢአድ ላይ የወሰነው ውሣኔ “ከተፈቀደለት የህግ አግባብ ውጪ የፈፀመው ጣልቃ ገብነት ነው” የሚሉ ወገኖች አሉ፤ ኢዴፓ አቋሙ ምንድን ነው? ውሳኔውንስ እንዴት አየው?  
በእውነት የሆነው ነገር በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ በሁለቱም በኩል ያለውን ክፍተት አይተናል፡፡ ምርጫ ቦርድ አጣብቂኝ ውስጥ የገባበት አሠራር ላይ ነው የደረሰው፡፡ ምርጫ ቦርዱ ህጉን መሠረት አድርጐ ያወጣቸውን ህጐች መከተል ያለበት፡፡ ከዚያም በላይ ህገ-መንግስቱ የሠጣቸውን መብት መጠቀም መቻላቸውን ማረጋገጥ አለበት፡፡ እንዲህ አይነት ችግሮች ሲፈጠሩ የማስተካከል፣ እርምት የመውሰድ፣ የማሠልጠን ግዴታ አለበት - ቦርዱ፡፡ መጀመሪያ ላይ ቦርዱ፣ አንድነትና መኢአድ ሊዋሃዱ ሲሉ የአቶ አበባው መሃሪን አመራር አላውቅም ብሎ ነበር፡፡ የሁለቱ ውህደት እንዳይፈፀም የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ከዚያ በኋላ አንድነት ውስጥ በተፈጠረው ችግር በእነ ኢ/ር ግዛቸው በኩል የነበረውን ሂደት ውስጣዊ መተዳደሪያ ደንባችሁን ተግባራዊ አላደረጋችሁም፣ እውቅና አልሠጣችሁም --- ብሎ ምን ያህል ሲያስቸግር እንደነበር ይታወቃል፡፡ በኋላም የእነ አቶ በላይ ቡድን ሲመጣ፣ ለእነሱም እውቅና ላለመስጠት ይሄኛው ህግ አልተከበረም፣ያኛው አልተከበረም ሲል ታዝበነዋል፡፡ ቦርዱ ሃላፊነቱን ለመወጣት ያኔ ነው  መሸምገል የነበረበት፡፡
አሁን ለመኢአድ አቶ አበባውን አጽድቆ፣መኢአድን ማስቀጠል የሚለው በኛ በኩል አያስኬድም፤ ተቀባይነትም የለውም፤ የአንድነትም ቢሆን አንዱን ጥሎ ለሌላኛው ቡድን መስጠት ለአባላቶቹ ፌዝ ነው፡፡ ስለዚህ ቦርዱ መጀመሪያ በአግባቡ ሃላፊነቱን አልተወጣም፡፡ ይህ ባለመሆኑም ቦርዱ የወሰነው ውሣኔ ገለልተኝነቱን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ሆኖ ቁጭ አለ፡፡ የፓርቲዎቹን ስናይ ደግሞ ለአሉባልታና ለሌላ ነገር በራቸውን ክፍት አድርገው የሰጡት ራሳቸው ናቸው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ አወቃቀር ከድሮዎቹ ፓርቲዎች አስተሳሰብና ከኢሠፓ አመለካከት ያልተላቀቀ ነው፡፡ ከዚያም ባሻገር ኢህአዴግ ከሚከተለው ፅንፍ ያልተላቀቀ አስተሳሰብ ያላቸው ግለሰቦች ፓርቲው ውስጥ ተሠግስገው በራቸውን ከፍተው ሰጡ፡፡ እድሉን ከፍተው የሠጡት ፓርቲዎቹ ራሣቸው ናቸው፡፡ መግቢያ በር የለም ቢሉ ኖሮ ማንም አይደፍራቸውም ነበር፡፡ የአንድ ግለሰብ አስተሳሰብ ተጽዕኖ እንደሚፈጥርም አልተገነዘቡም፡፡ ስለዚህ በምርጫ ቦርድ ብቻ ማሳበብ ሳይሆን እነሱም ሃላፊነቱን ይወስዳሉ፡፡
የቦርዱ ውሣኔ ተገቢ ነው  ወይስ አይደለም?
ቦርዱ ችግሮች ሲፈጠሩ የመፍታት ሃላፊነት አለበት፡፡ ካግባባቸውና ካነጋገራቸው በኋላ የአብላጫውን ድምጽ ይዞ ውሣኔ መስጠት ይችላል፡፡ አሁን ችግሩ የተፈጠረው ያንን ባለመስራቱ ነው፡፡ እኛ እንጠብቀው የነበረው ቦርዱ ከወሰነው በተቃራኒ ነው፡፡ ሁለቱ ቡድኖች አንድ ሆነው ተጠናክረው እስኪመጡ ድረስ ጊዜ አራዝሞ እድል ይሰጣቸዋል ብለን ነበር፡፡ ምናልባት የሚያጡት ይሄን የምርጫ ጊዜ ይሆናል፡፡ ከዚያ ውጪ ግን ተግባብተው የሚመጡበትን እድል ይሰጣቸዋል ብለን ነበር የጠበቅነው፡፡ አሁን የወሰነው ውሣኔ ገለልተኝነቱንም ጥያቄ ውስጥ ያስገባው ከዚህ አንፃር ነው፡፡
ኢዴፓ ቅንጅት ለመፍረሱ ምክንያት ነበር የሚሉ ወገኖች አሁንም ኢህአዴግን ለማሸነፍ ወይም ለመግራት የሚደረገውን ትግል ፓርቲው እያኮላሸው ነው እያሉ ይወቅሳሉ---
ኢዴፓ ከምርጫ 97 በፊት በጣም ጠንካራ የነበረ ፓርቲ ነው፡፡ በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ፅ/ቤቶችን ከፍቶ ብዙ አባላትን ያደራጀና አስተሳሰቡን ወደ ህብረተሰቡ እያሰረፀ የነበረ ፓርቲ ነው፡፡ ያንን መሰረት አድርጐ ቅንጅት በመፈጠሩ ምክንያት ያየነው ውጤት ተከተለ፡፡ ከዚያ በኋላ በነበረው ሂደት የተከሰተው የግለሰቦች አለመግባባት ግን ሁሉንም ፓርቲዎች አደጋ ላይ ጥሎ ነው ያለፈው፡፡ የግለሰቦች አለመግባባት ፓርቲዎችን አደጋ ላይ ሲጥል ህብረተሰቡንም አሳዝኖ አልፏል፡፡ ነገር ግን ፓርቲዎች እንደ ፓርቲ መቀጠል ስላለባቸው ኢዴፓም የራሱን ህልውና ለማስጠበቅ ከቅንጅት ተለይቶ የራሱን ስራ መስራት ጀመረ፡፡
እኔም በሂደቱ ስለነበርኩ መጀመሪያውኑ ውህደት እንዴት ይፈፀም የሚለው አለመግባባት ፈጥሮ ነበር፡፡ ያ ሁኔታ ፓርቲዎቹን እንዲበታተኑ ሲያደርጋቸው፣ ኢዴፓ ጠቅላላ ጉባኤውን ጠርቶ ሌላ ሥራ አስፈፃሚ መርጦ፣ አዲስ የማዕከላዊ ም/ቤት በማቋቋም እንደ አዲስ ስራው እንዲሠራ ተደርጓል፡፡ ከዚያ በኋላ  “የቅንጅት መንፈስ የኔ ነው” እየተባባሉ እርስ በእርሣቸው ሲሻኮቱ፣ “ቅንጅት ከተወሰደብኝማ አንድነትን አቋቁማለሁ” ተባለ፡፡ “አንድነት” ተቋቋመ፡፡ “አንድነትም” መሃል ላይ “መርህ ይከበር” በሚል ለሁለት ተሰንጥቆ “ሠማያዊ ፓርቲ” ተፈጠረ፡፡ አሁንም እያየነው፣ አንድነት ለሁለት ተሠነጠቀ፡፡ መኢአድም  ውስጣዊ ችግሩ አልፈታ ብሎ ሲንከባለል ቆይቶ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ደረሰ፡፡ ኢዴፓ ግን በተረጋጋ መንፈስ፣ ንቁ ተሣታፊ በሆኑ አባሎቹ፣ በቁርጠኛ የሠላማዊ ትግል መንፈስ፣ ዛሬ ሣይሆን ነገ ይደርሣል ብሎ ስለተነሣ ብቻ፣ ውስጠ ዲሞክራሲውን አጠናክሮ፣ አሁን ላይ ደርሷል፡፡
በፖለቲካ አሠራር የአንድም ግለሰብ አስተሳሰብ ተፅዕኖ ይፈጥራል የሚል መርህ አለን፡፡ ስለዚህ ውስጠ ዲሞክራሲያችን መጠናከር አለበት የሚል እምነት አለን፡፡ በዚህ ምክንያት አሁን ያለው የኢዲፓ ስራ አስፈፃሚ ሣይሸረሸር፣ በፍላጐት በቁርጠኝነት፣ፓርቲውን ወደ አንድ ምዕራፍ ለማሸጋገር እየሠራ ነው ያለው፡፡
ከዚህ አንፃር ኢዴፓ በትግል ስልቱ ገዥው ፓርቲ እየተጠናከረ እንዲሄድ እድል እየከፈተ ነው የሚለው አያስኬድም፡፡ እንደውም እኛ መንግስትን ልንገዳደር እንደምንችል ብቻ ሣይሆን በሠላማዊ የስልጣን ሽግግር ተሣትፎ ለማድረግ የምንችል ብቃት ያለን ፓርቲ ነን ብለን ነው የምናስበው፡፡ በተቃራኒው ገዥው ፓርቲ ቆሞ እንዲሄድ እድል እየከፈቱ ያሉት አሁን እየፈራረሱ ያሉ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ በር ከፍተው እየሠጡ ሲፈራርሱ እያየን ነው፡፡ ይሄ ሁሉ የመጣው የትግል ስልታቸውን ባለመፈተሻቸውና ባለማስተካከላቸው ነው፡፡ መከባበር ባለማሣየታቸውና የግለሰብ አስተሳሰብ ተፅዕኖ ያመጣል ብለው ባለማሰባቸው ነው፡፡ እኛ ቆም ብለን እየገመገምናቸው ነው የምንጓዘው፡፡ ስለዚህ ገዥው ፓርቲ ቆሞ እንዲሄድ እድል የሠጡት እነዚህ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ ገዥው ፓርቲ የኛን አካሄድ የሚያከብረውን ያህል የኛን አሠራር በጥንቃቄ የሚያየው መሆኑን በእርግጠኝነት እናገራለሁ፡፡ ሂደቱ ጩኸት እየበዛበት የሚሄድ ከሆነ፣ ህብረተሰቡንም እያሳዘነ ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ይወስደዋል፡፡
የፓርቲው የአባላት ቁጥር ስንት ደረሰ?
ሪፖርቱ ስላልተጠናከረ በቁጥር መግለጽ ባይቻልም በጣም በርካታ አባላት ናቸው ያሉት፡፡ አሁን ለምርጫ በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ላይ እጩዎችን አስመዝግበናል፡፡ እስካሁን ድረስ (ቃለ ምልልሱ የተደረገው ረቡዕ ነው) ወደ 270 የሚደርሱ እጩዎችን አስመዝግበናል፡፡ እቅዳችን እስከ 450 ለማስመዝገብ ነው፡፡ እቅዳችንን አሁን በተጨመረው ጊዜ ውስጥ እናሣካለን፡፡
ኢዴፓ “3ኛ አማራጭ” በሚል የጀመረው የትግል ስልት አዋጥቶታል ይላሉ?
የሊበራል አስተሳሰብ የሚገዛን እንደመሆኑ፣ በምክንያት መደገፍ፣ በምክንያት መቃወም የሚለውን አቅጣጫ ነው የምንከተለው፡፡ ገዥው ፓርቲ ፈጽሟል የምንለውን ስህተት በምክንያት አስደግፈን እንቃወማለን፣ጥሩ ሠርቷል የምንለውንም እንደዚያው፡፡ ገዥው ፓርቲ ያልሠራባቸውንና ህዝብ እየበደለባቸው ያሉትን በመረጃ ላይ መሠረት አድርገን እንቃወማለን፡፡
በምክንያት ከምትቃወሟቸውና ከምትደግፏቸው የገዥው ፓርቲ ተግባራት መካከል ቢጠቅሱልን?
በምክንያት የምንቃወማቸው… ገዥው ፓርቲ መንግስት እንደመሆኑ መጠን የሚሠራቸው ስራዎች አሉ፡፡ ለምሣሌ የኢኮኖሚ ፖሊሲውን እንቃወማለን፡፡ ሊያሠራ የሚችል ፖሊሲ አይደለም፡፡ ስለዚህ መንግስት ፖሊሲውን ሊያሻሽል ይገባል ብለን እናስባለን፡፡ መንግስት ይሄን ማድረግ ካልቻለ ወደ ሊበራል ኢኮኖሚ ዘዴ በመግባት፣አጠቃላይ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ይሆናል እንላለን፡፡ መንግስት የፖሊሲ ሣይሆን የአፈፃፀም ችግር አለብኝ ነው የሚለው፤ 24 አመት ሙሉ የአፈፃፀም ችግር ሊኖር አይችልም፡፡ ሌሎችም የዲሞክራሲ ተቋማት በብቃትና በቴክኖሎጂ እየተደራጁ አይደለም፡፡ ክፍተት እየተፈጠረ ነው፡፡ በመንግስት የተዋቀሩ ቢሆንም ከገዥው ፓርቲ ነፃ እየሆኑና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉ አይደለም፡፡ ህብረተሰቡም በዚህ ምክንያት መብቱን ማስከበር አልቻለም፡፡ 24 አመት ሙሉ የዲሞክራቲክ ተቋማት መጠናከር አልቻሉም፡፡ በአጠቃላይ ቢሮክራሲው ችግር አለበት፡፡ ከዚያም ባሻገር ችግሩ ወደ ሙስና ሄዷል፡፡ እያንዳንዱ የመንግስት ስራ የሚሰራው በእጅ መንሻ ሆነ፤ ግልጽነት ጠፋ፣ አሠራሩም አልተዘረጋም፤ የፍትህ አካሉ በትክክል እየሠራ አይደለም፡፡ የፍ/ቤቶች ነፃነት ጥያቄ ላይ ነው ያለው፡፡ እነዚህን የመሳሰሉትን እየተቃወምን፣ የፖሊሲ ለውጦች እንዲመጡ መታገል አለብን ብለን እናምናለን፡፡ ህብረተሰቡ ደግሞ በድምጽ እውቅና ከሰጠን፣ መንግስት ሆነን መፍትሔ እናመጣለን ብለን እናስባለን፡፡
በመረጃ ተንተርሰን የምንደግፋቸው ደግሞ አሉ፡፡ አሁን ያሉት የመንግስት መዋቅሮች ትክክል ናቸው፡፡ እኛም መንግስት ብንሆን ይሄን መዋቅር ነው የምንከተለው፡፡ እነዚህን ተቋማት በሰው ሃይልና በሎጀስቲክስ ማጠናከር ከተቻለ የሚፈለገውን አገልግሎት መስጠት ይችላሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህን ተቋማት እውቅና ሰጥተን እንጓዛለን፡፡ ነገር ግን የተቋማቱን ችግሮች ነቅሰን አውጥተን እንዲሻሻሉ እናሳስባለን፡፡ በዚህ ዙሪያ መንግስትን እንደግፋለን፡፡ በልማት እና በመሠረተ ልማት ዙሪያ የሚከናወኑ ሜጋ ፕሮጀክቶችን እንደግፋለን፡፡ እኛም መንግስት ብንሆን የምናደርገው ነው፡፡ ውጤቱ ለህብረተሰቡ ይጠቅማል ብለን ስለምንገምት የአባይ ግድብ መሠራቱን፣ የመንገድ መሠረተ ልማቱን እንደግፋለን፡፡ ወረዳ ከወረዳ እየተገናኘ ነው፤ በአሁን ሰአት መንገድ ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ዋስትና ነው፡፡ የባቡር ፕሮጀክቱ ከጅቡቲ አዲስ አበባ የሚገባው ትልቅ መዋቅር ነው፡፡ አሠራሮቹ በሙሉ ከሙስና የፀዳ መሆኑን ግን እንከታተላለን፣ ከፖለቲካ ገለልተኛ መሆኑን ማረጋገጥ እንፈልጋለን፡፡ መንግስት እንደመንግስት ብቻ የሚሠራቸው መሆኑን ማረጋገጥ እንሻለን፡፡ ገዥው ፓርቲ የኔ ሃብቶች ናቸው፣ የኔ ውጤቶች ናቸው… እያለ የሚሰብከውን ግን እንቃወማለን፤ የህዝብ ተቋሞች መሆናቸውን እንዲያረጋግጥ እንፈልጋለን፡፡
ኢዴፓ ለግንቦቱ ምርጫ ምን ዝግጅት እያደረገ ነው? ከምርጫው የሚጠብቀው ውጤትስ ምንድን ነው?
የምርጫ ቦርድን የጊዜ ሠሌዳ መሠረት አድርገን እቅድ አውጥተን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ እጩዎችን በመመልመል በርካታ ስራ ሠርተናል፡፡ በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች፤ በትግራይ፣ አማራ፣ ቤኒሻንጉል፣ ኦሮሚያ፣ አዲስ አበባ፣ አፋር፣ ሱማሌ፣ በጋምቤላ…  እጩዎችን አስመዝግበናል፡፡ በምርጫው አብላጫ ድምጽ በማግኘት ሠላማዊ የስልጣን ሽግግር ወይም በገዥው ፓርቲ ላይ ተፅዕኖ እንፈጥራለን ብለን ነው የምናስበው፡፡
እስከመጨረሻው ያለው የምርጫ ሂደት ሠላማዊ እንዲሆን ለፓርቲዎች ጥሪ አስተላልፋለሁ፡፡ ህዝቡም ለሠላማዊ ትግሉ የማይመጥኑና ወደ ጥርጣሬ የሚወስዱትን ሂደቶች በጥንቃቄ እንዲገመግም ጥሪ አቀርባለሁ፡፡ ገዥው ፓርቲ መንግስት እንደመሆኑ መጠን የዲሞክራሲ ተቋማት ነፃና ገለልተኛ ሆነው ምርጫውን የሚታዘቡበትን ሁኔታ መዘርጋትና መከታተል ይጠበቅበታል፡፡ አሁን ገለልተኛ አይደሉም የሚባሉትን ተቋማት፣ ገለልተኛነት ማስመስከር አለበት፤ ካልሆነ ግን የኢትዮጵያን ህዝብ እየበደለና እያሳዘነ የሚሄድበት እድል ሠፊ ነው፡፡ ሌላ የትግል አማራጭ የመፈለግ አዝማሚያም እየታየ ስለሆነ፣ ያንን የሚዘጋበትን እድል ማመቻቸት ይጠበቅበታል፡፡  

Read 2757 times