Saturday, 07 February 2015 13:01

30ኛዋ የአፍሪካ ዋንጫ ዝሆኖቹን ከጥቋቁር ክዋክብት ታፋጥጣለች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

30ኛው አፍሪካ ዋንጫ ዛሬና ነገ ለደረጃ እና ለዋንጫ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይፈፀማል፡፡ ዛሬ በደረጃ ጨዋታ አዘጋጇ አገር ኢኳቶርያል ጊኒ ከዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ ሲጫወቱ ነገ ደግሞ ኮትዲቯርና ጋና በዋንጫ ፍልሚያ ይፋጠጣሉ፡፡ የምእራብ አፍሪካ ጎረቤታሞች የሆኑት ኮትዲቯርና ጋና  በአፍሪካ ዋንጫ የፍፃሜ  ጨዋታ ሲገናኙ  ሁለተኛቸው ሲሆን በሁሉም ውድድሮች ደግሞ ለ40ኛ ጊዜ መጋጠማቸው ነው፡፡ ሁለቱ የምእራብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች በፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ሙሉ በሙሉ መገንባታቸው፤ በአፍሪካ ዋንጫ እና በዓለም አቀፍ ውድድሮች ባላቸው ከፈትኛ ልምድ እና የውጤት ታሪክ ተመጣጣኝ በሚባል አቋም ላይ ናቸው፡፡ ኮትዲቯርና ጋና  በሁሉም ዓለም አቀፍ ውድድሮች 39 ጊዜ ተገናኝተው፤ 14 እኩል ሲሸናነፉ በ11 አቻ ተለያይተዋል፡፡ በ1992 እኤአ ኮትዲቯር እና ጋና በአፍሪካ ዋንጫ ለፍፃሜ በተገናኙበት ወቅት አሸናፊው የተለየው በመለያ ምቶች ነበረ፡፡ ኮትዲቯር ብቸኛውን የአፍሪካ ሻምፒዮናነት ክብር ተቀዳጅታበታለች፡፡ በነገራችን ላይ ኮትዲቯር በአፍሪካ ሁለት ሌሎች የዋንጫ ጨዋታዎች አሳዛኝ ተሸናፊ ነበረች፡፡ በ2002 እኤአ በግብፅ እንዲሁም በ2006 እኤአ በዛምቢያ በመለያ ምቶች ተሸንፋ ሁለት ዋንጫዎችን ተነጥቃለች፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ የ56 ዓመታት ታሪክ በተካሄዱት 29 የፍፃሜ ጨዋታዎች አራቱ አሸናፊዎች በተጨማሪ ሰዓት ሲታወቁ፤ 7 የዋንጫ ፍልሚያዎች ደግሞ በመለያ ምቶች ሻምፒዮኖቹ ተለይተዋል፡፡ከዛሬው የደረጃ እና ከነገው የዋንጫ ጨዋታዎች በፊት በ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እስከ ግማሽ ፍፃሜ 30 ግጥሚያዎች ተካሂደው 72 ጎሎች ከመረብ ተዋህደዋል፡፡ እስከ ሩብ ፍፃሜ በመጓዝ ባስመዘገቡት ውጤት ደግሞ ከ5 እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ ኮንጎ ፤አልጄርያ፤ ቱኒዚያ፤ ጊኒ ፤ሴኔጋል ፤ማሊ ፤ኬፕቨርዴ ጋቦን ፤ካሜሮን ፤ዛምቢያ ፤ደቡብ አፍሪካና ቡርኪናፋሶ ያገኛሉ፡፡በ30 የአፍሪካ ዋንጫዎች  ሻምፒዮንነት  በ5 ዞኖች ሲከፋፈል  ሰሜን አፍሪካ በ10 ዋንጫዎች (7 የግብፅ እንዲሁም እያንዳንዳቸው አንድ ቱኒዚያ፤ አልጄርያ እና ሞሮኮ ) በማግኘት ይመራል፡፡ የምእራብ አፍሪካ ዞን ከ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጋር በ9 ዋንጫዎች  (የጋና 4 ወይም 5 ፤ የናይጄርያ 3 እንዲሁም የኮትዲቯር 1 ወይም 2) ፤ መካከለኛው አፍሪካ በ7 ዋንጫዎች (4 የካሜሮን፤ 2 የዲ ሪ ኮንጎ 1 የኮንጎ ኪንሻሳ)፤ ምስራቅ አፍሪካ በ2 ዋንጫዎች  (የኢትዮጵያ እና የሱዳን) እና ደቡብ አፍሪካ በ2 ዋንጫዎች  (የደቡብ አፍሪካ እና የዛምቢያ) ተከታታይ ደረጃ ያገኛሉ፡፡የኢኳቶርያል ጊኒ ብሄራዊ መብረቅብሄራዊ መብረቅ በሚል ቅፅል ስም የምትጠራው ኢኳቶርያል ጊኒ  2ኛዋን የአፍሪካ ዋንጫን መሳተፏ ነበር፡፡ ሁለቱንም ደግሞ በአዘጋጅነት ነው፡፡ በ2012 እኤአ 28ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ከጋቦን ጋር በጣምራ አዘጋጅነት  ለመጀመርያ ጊዜ በመካፈል ሩብ ፍፃሜ ደረሰች፡፡ 30ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ደግሞ በምትክ አዘጋጅነት  ተረክባ በ64 ቀናት በማዘጋጀት በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ግማሽ ፍፃሜ ደርሳለች፡፡

  • የጋና ጥቋቁር ክዋክብት
  • አማካይ እድሜ 24.9 ዓመት
  • የአንድ ተጨዋች አማካይ ዋጋ እስከ  4 ሚሊዮን ዶላር
  • የእግር ኳስ ደረጃ በዓለም 37 በአፍሪካ 4
  • የቡድን ዋጋ ግምት $150,743,365

ጋና በ19 የአፍሪካ ዋንጫዎች ስትሳተፍ  4 ጊዜ ሻምፒዮን (1963, 1965, 1978, 1982)፤ 4 ጊዜ ሁለተኛ ደረጃ(1968, 1970, 1992, 2010)፤ 1 ጊዜ ሶስተኛ ደረጃን (2008) እንዲሁም ለሶስት ጊዜያት በአራተኛ ደረጃ (1996, 2012, 2013) ጨርሳለች፡፡ በእነዚህ አፍሪካ ዋንጫዎች ባስመዘገበችው 154 ነጥብ በምንግዜም የውጤት ደረጃ ሶስትኛ ናት፡፡
የኮትዲቯር ዝሆኖቹ

  • አማካይ እድሜ 26.4 ዓመት
  • የአንድ ተጨዋች አማካይ ዋጋ እስከ 8 ሚሊዮን ዶላር
  • የእግር ኳስ ደረጃ በዓለም 28 በአፍሪካ 3
  • አጠቃላይ የቡድን ዋጋ ግምት $207,628,902

ኮትዲቯር በ20 የአፍሪካ ዋንጫዎች የተሳትፎ ታሪኳ 1 ጊዜ ሻምፒዮን(1992)፤ ሁለት ጊዜ ሁለተኛ ረጃ(2006, 2012)፤ 4 ጊዜ ሶስተኛ ደረጃ (1965, 1968, 1986, 1994) እንዲሁም 2 ጊዜ አራተኛ ደረጃ (1970, 2008)ነበራት፡፡ በምንግዜም የአፍሪካ ዋንጫ የውጤት ደረጃ አምስትኛ ናት፡፡ያያ ቱሬ ከአገሩ ጋር ትልቅ ዋንጫ ይፈልጋልየኮትዲቯር አምበል ያያ ቱሬ በ10 ዓመቱ ታኬታ ተሰጥቶት በአቢጃን ጎዳናዎች ስሙ የገነነ ታዳጊ ተጨዋች  ነበር፡፡ ታላቅ ወንድሙን ኮሎ ቱሬን በመከተል በአዜክ ሚሞሳ አካዳሚ ሰለጠነና አውሮፓ ገባ፡፡ በግሪክ፤ በስፔንና በእንግሊዝ ክለቦች በመጫወት የየአገራቱ ሊጎች ሻምፒዮን ሆኗል፡፡ በተለይ በስፔኑ ክለብ ባርሴሎና 5 ትልልቅ ዋንጫዎችን በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ፤
በዓለም ክለቦች ዋንጫ፤ በኮፓ ዴላ ሬይ እና በሌሎች ውድድሮች ወስዷል፡፡ በእንግሊዙ ክለብ ማንችስተር ሲቲ የፕሪሚዬር ሊግ ዋንጫ ብቻ ሳይሆን የኤፍኤ ካፕ ዋንጫን አግኝቷል፡፡ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮከብ ተጨዋች ሆኖ ለአራተኛ ጊዜ በመመረጥ ባለክብረወሰን ነው፡፡ ዘንድሮ በአፍሪካ ዋንጫ የተሳተፈው ለ5ኛ ጊዜ ሲሆን በ3 ዓለም ዋንጫዎችም  ወርቃማ ትውልድ ከሚባለው የኮትዲቯር ቡድን ጋር በመካፈል የረባ ውጤት አላስመዘገበም፡፡አሳሞሃ ጂያን የጋናን የ33 ዓመታት የዋንጫ ረሃብ መታደግ ይፈልጋልየጋናው አምበል አሳሞሃ ጂያን ደቡብ አፍሪካ ባዘጋጀችው 19ኛው የዓለም ዋንጫ አፍሪካዊ ቡድን ለመጀመርያ ጊዜ ግማሽ ፍፃሜ የሚገባበትን እድል ኢሊጎሬ በመሳቱ ያበላሸ እና በዚያ ታሪክ ዝነኛ የሆነ አጥቂ ነው፡፡ በዓለም ዋንጫ የተሳትፎ ታሪኩ አምስት ጎሎች በማግባት የአፍሪካ ኮከብ ግብ አግቢ የሆነው ጂያን 4ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ መሳተፉ ነው፡፡ የጋና ብሄራዊ ቡድን ከአፍሪካ ዋንጫ ለ33 ዓመታት የራቀበትን ሁኔታ መቀየር ይፈልጋል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት የነበረበትን የእንግሊዝ ክለብ ሰንደርላንድ በመልቀቅ ለዩናይትድ አረብ ኢምሬትሱ ክለብ አል አሊን አወዛጋቢ ዝውውር ፈፅሞ እየተጫወተ ይገኛል፡፡  ፈረንሳዊ ሄርቬ ሬናርድ ከእስራኤላዊ አቭራም ግራንትለ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለፍፃሜ የደረሱት ሁለቱ አሰልጣኞች ሄርቬ ሬናርድና አቭራም ግራንት ከአፍሪካ ውጭ የመጡ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ 46 ዓመታቸው የሆኑት ፈረንሳዊው ሄርቬ ሬናርድ በኮትዲቯር ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ለመስራት  የሁለት ዓመት ኮንትራት ተሰጥቷቸዋል፡፡ በ2012 እኤአ ላይ የዛምቢያን ብሄራዊ ቡድን ለሻምፒዮናነት ያበቁበት ታሪክ ትልቁ ስኬታቸው  ነው፡፡ ከ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ በፊት ሬናርድ ስለኮትዲቯር ቡድን ተጠይቀው ለያያ ቱሬ ያላቸውን አድናቆት ከገለፁ በኋላ ‹‹በምሰሶዎቹ ግንባታ ላይ ያለ ብሄራዊ ቡድን ነው፡፡  ወደ አቢጃን ዋንጫውን ይዘን ለመመለስ ተስፋ አድርገናል፡፡›› ብለዋል፡፡
አቭራም ግራንት 60 ዓመታቸውን ሊደፍኑ ሲሆን በጋና ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት የሁለት ዓመት ውል አላቸው፡፡ የእስራኤል ብቻ ሳይሆን የፖላንድ ዜግነት ያላቸው አቭራም ግራንት ጋና በአገር ደረጃ ለማሰልጠን ሃላፊነት ያገኙበት የመጀመርያው ብሄራዊ ቡድናቸው ነው፡፡ ከዚሁ ሃላፊነት በፊት በአውሮፓ እግር ኳስ ያካበቱት ልምድ አለ፡፡ በእንግሊዙ ክለብ ቼልሲ በዲያሬክተርነት ተቀጥረው ከዚያም በአሰልጣኝነት ሰርተዋል፡፡ በ2008 እኤአ በማንችስተር ዩናይትድ የተነጠቁት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ የማይረሳ ታሪካቸው ነው፡፡ ከቼልሲ በኋላ የፖርትስማውዝ፤ የዌስትሃምና የፓርቴዝያን ቤልግሬድ አሰልጣኝ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በገና ብሄራዊ ቡድን ዙርያ አቭራም ግራንት አስተያየት ተጠይቀው ‹‹በየጨዋታው ከፍተኛ መሻሻል አሳይተናል፡፡ ጋናውያን ከፈቀዱ ዋንጫውን ባሸንፍም ባላሸንፍም በሃላፊነት ብቆይ ደስ ይለኛል፡፡›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡በ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ከተሳተፉት 16 ቡድኖች ሶስቱ ብቻ በአፍሪካውያን አሰልጣኝ የተመሩ መሆናቸው የአህጉሪቱ እግር ኳስ አንድ ተዳካመ ሁኔታን የሚያመለክት ሆኗል፡፡ አንዳንድ ዘገባዎች ይህ የአፍሪካውያን አሰልጣኞች ዝቅተኛ ተሳትፎ ከ1996 እኤአ በኋላ የወረደ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ከ3ቱ የአፍሪካ አሰልጣኞች እስከ ግማሽ ፍፃሜ በመድረስ ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገቡት የዲሪ ኮንጎው ፍሎረን ኦቤንጊ ናቸው፡፡ ሌሎቹ ሁለት አፍሪካዊ አሰልጣኞች በምድብ ማጣርያ ከእነ ብሄራዊ ቡድናቸው የተሰናበቱት የደቡብ አፍሪካው ኤፍሪዬም ሼክስ ማሻባ ከደቡብ አፍሪካ እና ሆን ጃንዛ ከዛምቢያ ናቸው፡፡ በ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከተሳተፉ 16 ብሄራዊ ቡድኖች አራት ፈረንሳዊ አሰልጣኞች መወከላቸው ከፍተኛው ነው፡፡ የአልጄርያው ክርስትያን ጉርኩፍ፤ የኮትዲቯሩ ሄርቬ ሬናርድ፤ የኮንጎው ክላውድ ዲለሮይና የሴኔጋሉ ኤቴን ግሬሲ ናቸው፡፡ ሁለት ፖርቱጋላዊያን ጆርጌ ኮስታ በጋቦንና ራውል አኑዋስ በኬፕ ቬርዴ ሁለት ቤልጅማውያን ፖል ፑት በቡርኪናፋሶና ጆርጅ ዚኮንስ በቱኒዚያ የሰሩ አሰልጣኞች ናቸው፡፡ ካሜሮን በጀርመናዊው ቮልከር ፊንኬ፤ ጋና በእስራኤላዊው አቭራም ግራንት፤ ኢኳቶርያል ጊኒ በአርጀንቲናዊው ኤስቴበን ቤከር እንዲሁም ማሊ
በፖላንዳዊው ሄነሪክ ካስፐርዣክ አሰልጣኝነት የአፍሪካ ዋንጫውን ተሳትፈዋል፡፡ባለፉት 29 የአፍሪካ ዋንጫዎች አሸናፊ አሰልጣኞች 18 ከአፍሪካ ውጭ ካሉ አገራት የተገኙ ሲሆን ሻምፒዮን መሆን የቻሉት 11 አፍሪካውያን አሰልጣኞች ናቸው፡፡ ከውጭ አገር አሰልጣኞቹ 5 ፈረንሳውያን፤ 4 ዩጎስላቪያውያን፤ እንዲሁም አራት ሃንጋራዊያን ሲሆኑ 6 ሻምፒዮንአሰልጣኞች ከብራዚል፤ ከቼክ፤ ከሆላንድ ከሮማንያ፤ከጀርመንና ከዌልስ ከእያንዳንዳቸው የተገኙ ናቸው፡፡ ከነገው የ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ በኋላ ሻምፒዮን ለመሆን የተሳካላቸው የውጭ አገር አሰልጣኞች ብዛት 19 ይደርሳል፡፡
ቦነስና ሽልማትበ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የኢኳቶርያል ጊኒ ተጨዋቾች በተከፈላቸው የውጤት ቦነስ የሚስተካከላቸው አልነበረም፡፡ ሩብ ፍፃሜ በመድረሳቸው ለእያንዳንዳቸው 30 ሺ ዶላር ነበር የተከፈላቸው፡፡ ጋናን አሽንፈው ለፍፃሜ ቢደርሱ 50 ሺ ዋንጫውን ከወሰዱ ደግሞ አስከ 150ሺ ዶላር  ቦነስ እንደሚሰጣቸው ቃል ተገብቶ ነበር፡፡ በዓለም ዋንጫ እና በአፍሪካ ዋንጫ በየጊዜው በቦነስ ክፍያ የሚጨቃጨቁት የጋና ብሄራዊ ቡድን ጥቋቁር ክዋክብቶች በአንድ ጨዋታ በአማካይ 5ሺ ዶላር የውጤት ቦነስ እንዲታሰብላቸው ተደራድረዋል፡፡ ዋንጫውን ካሸነፉ ለእያንዳንዳቸው 60ሺህ ዶላር እንደሚከፍል ፌደሬሽኑ ቃል ገብቷል፡፡  የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ለአፍሪካ ዋንጫው በድምሩ 10 ሚሊዮን ዶላር ለሽልማት አቅርቧል፡፡ ሻምፒዮኑ 1.5 ሚሊዮን ዶላር ሲሸለም፤ ሁለተኛ ደረጃ የሚያገኘው 1 ሚሊዮን ዶላር
እንዲሁም ለደረጃ የሚጫወቱት ሁለት ቡድኖች እያንዳንዳቸው 750ሺ ዶላር ይበረከትላቸዋል፡፡
በሩብ ፍፃሜ የቀሩት አራት ቡድኖች እያንዳንዳቸው 600ሺ ዶላር በነፍስ ወከፍ ሲያገኙ፤ በምድብ
ማጣርያ ሶስተኛ ደረጃ የሚያገኙት አራት ቡድኖች እያንዳንዳቸው 500ሺ ዶላር እንዲሁም
በየምድባቸው የመጨረሻ ደረጃ የሚያገኙት እያንዳንዳቸው 400ሺ ዶላር ይታሰብላቸዋል፡፡


Read 2851 times