Saturday, 07 February 2015 12:26

የ500ሺ ብር ናፍጣ ሸጦ ቦቴ መኪናውን ያቃጠለ ሾፌር ተፈረደበት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

     ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ 36 ሺህ ሊትር ናፍጣ ከሸጠ በኋላ እንዳይታወቅበት የነዳጅ መላለሻ መኪናውን በእሳት አጋይቷል ተብሎ የተከሰሰ ሾፌር ሰሞኑን በፍ/ቤት ጥፋተኛ ተባለ፡፡ ተከሳሹ ከጅቡቲ 44ሺህ ሊትር ናፍጣ የጫነ መኪና ወደ ጅማ ማድረስ እንደነበረበት የገለፀው አቃቤ ህግ፤ በመሃል የቦቴ መኪናውን እሽግ በመፍታት ከ36 ሺህ በላይ ሊትር በድብቅ ሸጧል ብሏል፡፡ ተከሳሹ ሹፌር ነዳጅ መስረቁና መሸጡ እንዳይታወቅበት፤ የተፈታውን እሽግ መልሶ በማያያዝ መኪናውን በእሳት አቃጥሎታል ብሏል - የፀረ ሙስና አቃቤ ህግ፡፡ በጂማ ስኮሩ ወረዳ አካባቢ ነሐሴ 12 ቀን 2005 ዓ.ም ማለዳ መኪናውን ከነተሳቢው ያቃጠለው በድንገተኛ አደጋ ቃጠሎ የደረሰበት ለማስመሰል ነው ሲልም ክሱን አስረድቷል፡፡ ሹፌሩ ሀዱሽ ገብረክርስቶስ በአቃቤ ህግ የተጠቀሰበትን ወንጀል እንዳልፈፀመ በመግለፅ፤ የተከራከረ ሲሆን፤ አቃቤ ህግ ግን ተከሳሽ መኪናውን ሲያቃጥል ታይቷል በማለት ምስክሮችን አቅርቧል፡፡ የተሸጠውና የተቃጠለው ነዳጅ ከ600 ሺ ብር በላይ እንደሚያወጣ አቃቤ ህግ ገልፆ፤ ከመኪናው ዋጋ ጋር የ2 ሚሊዮን ብር ንብረት ወድሟል ብሏል፡፡
ጉዳዩን የተመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት፣ ሰሞኑን ተከሳሽ
ጥፋተኛ ነው በማለት ፍርድ የሰጠ ሲሆን፤ የቅጣት ውሳኔ ከማስተላለፉ በፊት የቅጣት አስተያየት
ለማድመጥ ለየካቲት 11 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

Read 2256 times