Saturday, 31 January 2015 12:42

ባራክ ኦባማ - አዛሪያስ ረዳ - የአሜሪካ ፖለቲካ

Written by  ዩሃንስ ሰ.
Rate this item
(8 votes)

ባራክ ኦባማ - አዛሪያስ ረዳ - የአሜሪካ ፖለቲካ
አዛሪያስ ረዳ ማን ነው?
“ከ12 የዘመናችን ወጣት ጥቁር አሜሪካዊያን መሪዎች አንዱ” -  (ታይም መፅሔት፣ የዚህ ሳምንት የጥር 18 እትም)
“በፖለቲካና በህግ ዘርፍ ብቅ ካሉ 30 አዳዲስ መሪዎች አንዱ” -  (ፎርብስ መፅሔት፣ ከሳምንት በፊት የጥር 11 እትም)
“እውቀት ኃይል ነው የሚል የኢትዮጵያ ተወላጅ አሜሪካዊ” - (ዎል ስትሪት ጆርናል፣ ዘንድሮ የመስከረም 10 ዘገባ)
“የአሜሪካን ፕሬዚዳንት ለማስመረጥ እንዲረዳ በሪፐብሊካኖች የተጠየቀ” - (ብሉምበርግ፣ አምና የመጋቢት 29 ዘገባ)


   የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች፣ ባለፈው ሳምንት ባራክ ኦባማ እንዳደረጉት፣ የፓርላማ አባላት ዘንድ በመቅረብ “ስቴት ኦፍ ዘ ዩኒዬን” የተሰኘ ንግግር በማሰማት ነው የአመቱን ስራ በይፋ የሚጀምሩት። ታክስ ለመጨመር ወይም ለመቀነስ፣ የንግድ ማዕቀብ ለመጣል ወይም ነፃ ንግድ ለማስፋት፣ የቢዝነስ ማደናቀፊያ ቁጥጥሮችን ለመፈልፈል ወይም ለመሻር፣ ጦርነት ለማወጅ ወይም ሰላም ለማውረድ ... በተለምዶ አንድ ሰዓት ገደማ በሚፈጀው ንግግር ዋና ዋና የአመት እቅዶችን ይዘረዝራሉ። እስቲ ከኦባማ ንግግር ጥቂቱን ልጥቀስላችሁ - ከፓርላማ (ከኮንግረስና ከሰኔት) አባላት ካገኙት ምላሽ ጋር።
አንዳንድ የታክስ ጭማሪዎችን በመተግበር ለምሳሌ በቋሚ ንብረት ላይ ታክስ በመጫን) ድሆችን መደጎም እንደሚፈልጉ የተናገሩት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ የባንኮችን አሰራር ለመቆጣጠር የወጡ ሕጎች በኮንግረስና በሰኔት ሊሻሩ አይገባም ብለዋል። የፓርቲያቸው (የዲሞክራቲክ ፓርቲ) ተመራጮች ከወንበራቸው ተነስተው ሲያጨበጭቡ፣ በአመዛኙ ለታክስ እና ለድጎማ ፍቅር የሌላቸው የሪፐብሊካን ፓርቲ ተመራጮች ከወንበራቸው ንቅንቅ አላሉም።
ከኩባ ጋር ለግማሽ ምዕተዓመት የዘለቀውን ጠላትነት ማብረድ ይኖርብናል በማለታቸው ከብዙዎቹ ዲሞክራቶች የድጋፍ ጭብጨባ የተቸራቸው ኦባማ፤ በሶሪያና በኢራቅ ሰዎችን እየፈጀ የሚገኘው አይሲስ የተሰኘውን አሸባሪ ቡድን ለማጥቃት ኮንግረስ ጦርነት ማወጅ እንዳለበት በመጠቆምና የአሜሪካን ጦር ሠራዊት በማሞገስ ሪፐብሊካኖችም እንዲያጨበጭቡ አድርገዋል።
ዩክሬንን በወረረው የራሽያ መንግስት ላይ የተጣለው የኢኮኖሚ ማዕቀብ የቭላድሚር ፑቲንን እብሪት ማብረክረክ እንደጀመረና ወደፊትም እንደሚገፉበት ኦባማ ጠቅሰው፤ ከኤሺያ አገራት ጋር ነፃ ንግድ ለማስፋፋት የኮንግረስንና የሰኔትን ድጋፍ ጠይቀዋል። ይሄኔ፣ የጭብጨባው አቅጣጫ ተቀየረ። ከራሳቸው ፓርቲ ይልቅ ከተቃዋሚያቸው ፓርቲ ነው ከፍተኛ ድጋፍ ያገኙት። የሪፐብሊካን ፓርቲ ተመራጮች ከወንበራቸው ተነስተው አዳራሹን በጭብጨባ አደመቁት - በአብዛኛው የነፃ ንግድ ደጋፊዎች በመሆናቸው። ኦባማ የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባል ቢሆኑም፣ አብዛኞቹ የፓርቲው ተመራጮች ከወንበራቸው ሊነሱ ይቅርና፣ ለወጉ እንኳ አላጨበጨቡም። ለምን ቢባል፤ ዲሞክራቶች በአመዛኙ በሌሎች አገሮች እንደተለመደው ያፈጠጠና ያገጠጠ የነፃ ንግድ ጠላትነት ባይጠናወታቸውም፤ የነፃ ንግድ ፍቅርም አይታይባቸውም። እናም፤ ከተወሰኑት በስተቀር አብዛኞቹ ዲሞክራቶች ድጋፋቸውን አልገለፁም። በአጭሩ ከፓርቲ ትዕዛዝ እየተቀበሉ የሚያጨበጭቡ ወይም የሚቃወሙ አይደሉም፡፡ የአሜሪካዊያን ነፃነት እንዲህ ነው!
በእርግጥ ባራክ ኦባማ  ከኤሽያ አገራት ጋር የነፃ ንግድ ስምምነት ለመፈራረም ያቀዱት የነፃ ንግድ ደጋፊ ስለሆኑ አይደለም። እንደ አብዛኞቹ ዲሞክራቶች፣ ለነፃ ንግድ ብዙም ፍቅር የላቸውም። ነገር ግን፤ ከሌሎቹ ዲሞክራቶች የተለየ ሃላፊነት አለባቸው፤ ፕሬዚዳንት ናቸው። ከነፃ ንግድ የሸሸ አገር፤ ወደ ኋላ እየተንሸራተተ እንደሚቀር እያወቁ፣ የነፃ ንግድ ስምምነት ላለመፈረም ቢወስኑ፤ የኋላ ኋላ ፓርቲያቸው ሳይሆን ራሳቸው በግል ተወቃሽ ይሆናሉ። ለዚህም ነው፤ ከፓርቲያቸው ተመራጮች ድጋፍ ባያገኙም፤ የነፃ ንግድ ስምምነት ለመፈረም ያቀዱት።
በዚያ ላይ፣ ከዚህ ስምምነት ውጭ ሌሎቹ የኦባማ እቅዶች ከእቅድነት ያለፈ እጣፈንታ አይኖራቸውም። ለምን? የዲሞክራቲክ ፓርቲው ባራክ ኦባማ በቀሪው የስልጣን ዘመናቸው፣ አንዳች ቁምነገር መስራት የሚችሉት ከሪፐብሊካን ፓርቲ ተመራጮች ድጋፍ ካገኙ ብቻ ነው። ለምን? በኮንግረስና በሰኔት አብላጫውን ወንበር የያዙት ሪፐብሊካኖች ናቸዋ። ፕሬዚዳንቱ ያረቀቁት ህግ፣ ኮንግረስና ሰኔት ካላፀደቁት ዋጋ አይኖረውም። በኮንግረስ የፀደቀ ህግም እንዲሁ በሰኔት ወይም በፕሬዚዳንቱ ተቀባይነት ካላገኘ፣ መክኖ ይቀራል። እንዲህ አይነቱን አሰራር፣ check and balance ይሉታል።  ብልሆቹ የአሜሪካ መስራቾች፣ ሆን ብለው የፈጠሩት አሰራር ነው - መንግስት መረን ከተለቀቀ፣ እዚህም እዚያም እጁን እያስገባ አገሪቱን የሚያቃውስ፣ ዜጎችን የሚያሰቃይ አቻ የማይገኝለት አደገኛ የወንጀል ተቋም እንደሚሆን በመገንዘብ። በተለይ፣ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች የኋይት ሃውስ፣ የኮንግረስና የሰኔት ስልጣን ሲቆጣጠሩ፣ እርስ በርስ ተቆላልፈው አንዱ ሌላውን አስሮ ይይዛል። ልክ አሁን እንደሚታየው ማለት ነው።
የዛሬን አያድርገውና (የዛሬን ያድርገውና)፤ ባራክ ኦባማ የዛሬ ስድስት ዓመት በመላው ዓለም “ጉድ” በተባለለት የምርጫ ዘመቻ አሸንፈው የታላቋ የነፃነት አገር የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የሆኑ ጊዜ፤ ደስታቸው እጥፍ ድርብ ነበር። እሳቸው ኋይት ሃውስ ሲገቡ፣ ፓርቲያቸው በኮንግረስና በሰኔት አብላጫ ወንበሮችን አሸንፎ ነበር - ከ100 የሰኔት ወንበሮች 57ቱን፤ እንዲሁም ከ435 የኮንግረስ ወንበሮች 257ቱን። በእርግጥ፣ ከላይ እንደገለፅኩት፤ ሁሉም የሪፐብሊካን ፓርቲ ተመራጮች፤ በሁሉም ጉዳይ ላይ ሁልጊዜ ፕሬዚዳንቱን ይቃወማሉ ማለት አይደለም። የዚያኑ ያህል፣ ሁሉም የዲሞክራቲክ ፓርቲ ተመራጮች ፕሬዚዳንቱን ሁልጊዜ ይደግፋሉ ተብሎ መታሰብ የለበትም። ስለዚህ ፓርቲያቸው በኮንግረስና በሰኔት አብላጫ ወንበር ቢይዝም፤ ሁሉም ነገር አልጋ ባልጋ ይሆንላቸዋል ማለት አይደለም። እንዲያም ሆኖ፤ የትኛውም ፕሬዚዳንት ከዚህ የተሻለ እድል ሊመኝ አይችልም። እናም፣ ለባራክ ኦባማ ትልቅ ፌሽታ ነበር - የዛሬ ስድስት አመት።
ዛሬ ግን፣ ነገሮች ተለውጠዋል። የሪፐብሊካን ፓርቲ ተመራጮች በኮንግረስ እና በሰኔት አብላጫ ወንበር ይዘዋል። እንዲያውም፣ በዘንድሮው የኮንግረስና የሰኔት ምርጫ ላይ ሪፐብሊካን ፓርቲ ያገኘው ድል፣ ባለፉት 85 ዓመታት ያልታየ ትልቅ ድል ነው ተብሎለታል። ነገሮችን እንዲህ የሚለውጥ ምን አዲስ ነገር ተፈጠረ?
ምን አዲስ ነገር ተፈጠረ?
በቀውስ የተመታው የአሜሪካ ኢኮኖሚ፤ ከአውሮፓና ከጃፓን በተሻለ ሁኔታ ቢያገግምም በፍጥነት ለማንሰራራት አለመቻሉ፣ ኦባማንና ዲሞክራቶችን የሚያሳጣ ትልቁ ችግር ነው። የመንግስት ጣልቃ ገብነት እየተስፋፋ፣ ሃብትን የሚያባክኑ የድጎማ አይነቶች መበራከታቸው፣ በዚያው ልክ የመንግስት ወጪ እያበጠ የታክስ ጫናዎች መክበዳቸው፣ እንዲሁም የቢዝነስ ሥራን የሚያደናቅፉ አላስፈላጊ ቁጥጥሮች እንደ አሸን መፍላታቸው ለብዙ አሜሪካዊያን እጅጉን አሳሳቢ እየሆኑ መምጣታቸውም ሌላው ለውጥ ነው። መንግስት በየአመቱ የሚያብጠውን ወጪ በታክስ መሸፈን ሲያቅተው፣ በየአመቱ በቦንድ ሽያጭ ብድር እየሰበሰበ የእዳ ክምር እየገነነ መምጣቱም እንዲሁ ብዙዎችን እያሳሰበ ኦባማንና ዲሞክራቶችን እንዲቃወሙ አድርጓቸዋል፡፡
የዛሬ 35 ዓመት ከአንድ ትሪሊዮን በታች የነበረው የመንግስት እዳ፣ በአስር አመት ውስጥ ወደ ሦስት ትሪሊዮን፣ እንደገና በአስር ዓመት ወደ አምስት ትሪሊዮን መጨመሩን ስትመለከቱ፣ በሽታው አዲስ እንዳልሆነ ያመለክታል። ነገር ግን፣ እንደ ካንሰር ፍጥነቱን እየጨመረ መጥቷል። ባራክ ኦባማ ስልጣን በያዙበት አመት፣ የመንግስት እዳ አስር ትሪሊዮን ደርሶ ነበር። ባለፉት ስድስት ዓመታት ደግሞ፣ በየአመቱ ከአንድ ትሪሊዮን ዶላር በላይ እየተበደረ፣ የእዳው ቁልል ወደ 18 ትሪሊዮን አድርሶታል። ይህ አልበቃ ብሎ፤ እንደገና የመንግስትን ጣልቃ ገብነትን የሚያስፋፋና የመንግስትን ወጪ የሚያባብስ የጤና ኢንሹራንስ ህግ ፀድቆ ተግባራዊ ሆኗል። ከዚህ ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ መንግስት መረን ተለቋል የሚል ፀረ ኦባማ ተቃውሞ፣ “ቲ ፓርቲ” በተሰኘ የነፃ ገበያ እንቅስቃሴ መፈጠሩ ሌላ ለውጥ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ፣ እንደ ቴድ ክሩዝ፣ ራንድ ፖል እና ማርኮ ሩቢዮ የመሳሰሉ የታዋቂዋ ደራሲና ፈላስፋ አየን ራንድ አድናቂ አዳዲስ ሪፖብሊካን ሴናተሮች መበራከታቸውን መጥቀስ ይቻላል።
ባለፉት ስድስት ዓመታት ከተፈጠሩት ከእነዚህ ለውጦች በተጨማሪ፣ኦባማንና ዲሞክራቶችን የሚያሳጣ  ምን አዲስ ነገር ተከሰተ?
አዛሪያስ ረዳ አሜሪካ ውስጥ ተከሰተ
በኢትዮጵያ ደሴ ተወልዶ ያደገው አዛሪያስ፤ አሜሪካ የገባው የዛሬ 12 ዓመት ነው። በእነዚህ 12 ዓመታት ግን፤ ስንት ነገር ሰርቷል! እዚህ ያቋረጠውን የዩኒቨርስቲ ትምህርት ማጠናቀቅ የመጀመሪያው ስራ ነው - አራት ዓመት ተኩል ፈጅቶበታል። ግን ለአንድ ዲግሪ ብቻ አይደለም። በኮምፒዩተር ሳይንስ፣ በሂሳብ እና በቢዝነስ አስተዳደር ... በአንድ የምረቃ ስነስርዓት ሶስት ጊዜ ስሙ እየተጠራ ሶስት ዲግሪ ይዞ ከወጣ በኋላ፤ ለግማሽ ዓመት ያህል፣ ሥራ ተቀጥሮ በሶፍትዌር ዝግጅት ሰርቷል። ወደ ትምህርት ተመልሶ የማስተርስ ጥናት መከታተል ከመጀመሩ በፊት ማለት ነው። በዚያውም የፒኤችዲ ጥናት። ሦስት ዓመት አልፈጀበትም - ዶ/ር አዛሪያስ ረዳ ለመሆን።
እግረመንገዱን፤ ኢትዮጵያ መጥቶ የቴክኖሎጂ ፋኩልቲ ውስጥ ለግማሽ አመት አስተምሯል፤ ህንድ ሄዶም ለተወሰነ ጊዜ ለማይክሮሶፍት ማዕከል ጥናት ሰርቷል። አሜሪካ ተመልሶ፣ ከፌስቡክና ከቲውተር ጋር አብሮ ስሙ የሚነሳ LinkedIn በተሰኘው የኢንተርኔት ኩባንያ ውስጥም በሶፍትዌር ዝግጅት የራሱን አሻራ አሳርፏል። ከዚህ በኋላ ነው የራሱን የኢንተርኔት ኩባንያ ለመመስረት ወጥሮ መስራት የጀመረው።
በዚህ መሃል ግን፤ ሕይወትን የሚቀይር ነገር ተፈጠረ - በአጭር ጊዜ በአሜሪካ ታላላቅ የሚዲያ ተቋማት አፍ ውስጥ እንዲገባ ከሚያደርግ የሥራ ሃላፊነት ጋር ተገናኘ። ቀላል ነገር አይደለም።
በአንድ በኩል መልክ እየያዘ የነበረ የራሱ ኩባንያ እና ጅምር ሥራ አለ። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ሌላ አዲስ ትልቅ ሥራ! ከባድ ምርጫ ነው። ቡልምበርግ እንደዘገበው፤ አዛሪያስ ከኦስቲን ቴክሳስ ዘመድ ጥየቃ ወደ ዋሽንግተን ጎራ ሲል ያነጋገሩት ሰዎች፣ ጊዜ አላባከኑም። እቅጩን ነው የነገሩት። ጊዜው አምና ህዳር ወር ገደማ ነው። ሰዎቹ የሪፐብሊካን ፓርቲ ተወካዮች ናቸው - “በጀመርከው መንገድ ምርጥ የኢንተርኔት ፕሮግራም ወይም ዌብሳይት መፍጠር ትችላለህ፤ ወይም ቀጣዩን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለመምረጥ ልትረዳን ትችላለህ” አሉት። ታይም መጽሔት ሰሞኑን እንደገለፀው የቀረበለት የሃላፊነት ቦታ የዋዛ አይደለም፡፡
በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ ቁልፍ ተዋናይ ለመሆን የሚያስችል ሃላፊነት ነው፡፡ አዛሪያስ ከራሱ ኩባንያ እና ከሪፖብሊካን ፓርቲ አንዱን መምረጥ ነበረባት፡፡ የፓርቲውን እንቅስቃሴ በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚያስተባብረው ብሔራዊ ሪፐብሊካን ኮሚቴ መሪዎች ጋር ተነጋገረ። እናም፤ በ2016ቱ ምርጫ ሪፐብሊካን ፓርቲ እንዲያሸንፍ ለመርዳት... ዶ/ር አዛሪያስ ረዳ፣ የዛሬ አመት ጥር ወር ሃላፊነቱን ተቀብሎ አዲሱን ስራ ጀመረ - የፓርቲው ቺፍ ዳታ ኦፊሰር በሚል ስያሜ። ዎል ስትሪት ጆርናል እና ብሉምበርግ እንደዘገቡት፤ ይህ የሪፐብሊካን ፓርቲ እና አዛሪያስ ረዳ ውሳኔ በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ለውጥ የሚያመጣ ውሳኔ ነው፡፡
በ2008 ከዚያም በ2012 የዘመኑን የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ፣ የመረጃ አሰባሰብና ትንታኔ፣ የኢንተርኔትና የሞባይል ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ተጠቅመው የምርጫ ዘመቻ ባካሄዱት ባራክ ኦባማ ክፉኛ የተሸነፉት ሪፐብሊካኖች፣ በአንድ አስተማማኝ እመርታ ብልጫ ለማግኘት ታጥቀው ለመነሳት መወሰናቸው አይገርምም። ወደ ተግባር ለመግባት ጊዜ አልፈጀባቸውም። በዲጂታል ሚዲያ (በኢንተርኔትና በሞባይል) የፓርቲውን የምርጫ ዘመቻ የሚያስተባብር የኮሙኒኬሽን ባለሙያ ቀጥረዋል - በጆርጅ ቡሽ የምርጫ ዘመቻ የዲጂታል ሚዲያ ዋና መሪ የነበረ ባለሙያ። የቴክኖሎጂ መረጣ የሚመራ ሌላ ባለሙያም መርጠዋል - የፌስቡክ ኢንጂነር የነበረ። ከዚህ በኋላ የሚያስፈልገው፣ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም እልፍ አእላፍ ጥሬ መረጃዎችን የሚሰበስብና የሚተነትን፣ በወግ በወጉ የሚያደራጅና ለሚዲያ አመቻችቶ የሚያቀርብ ምርጥ የዳታ ባለሙያ ነው - አዛሪያስ ረዳ።
በጭፍንና በግምት ሳይሆን በመረጃ ላይ የተመሰረተ አስተማማኝ የምርጫ ዘመቻ ለማካሄድ፣ ትልቁን ቁልፍ የሃላፊነት ቦታ የተረከበው አዛሪያስ፣ በየአመቱ ከሚገሰግሰው የኮምፒዩተርና የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ጋር የሚራመድ ዘመናዊ ስራ ለማከናወን ከፈለገ ወጣት ባለሙያዎችን መቅጠርና ማደራጀት ነበረበት። እናም በኮምፒዩተር ሳይንስና በሂሳብ ትምህርት ስመጥር ዩኒቨርሲቲዎችን አሰሰ፡፡ በኮምፒዩተርና በኢንተርኔት ማዕከልነቱ በሚታወቀው የካሊፎርኒያው ሲልከንቫሊ ምርጥ ምርጦችን ለመመልመል ዞረ። ከዚያ በኋላ ለቁጥር የሚያስቸግሩ የጥሬ መረጃ ክምሮችን በወጉ ማበጃጀት፣ ተጨማሪ መረጃዎችን መሰብሰብ፣ በየእለቱና በየደቂቃው አዳዲስ መረጃዎችን እየተከታተለ ለማካተት የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት... ከዚህ ስፍር ቁጥር የሌለው መረጃ ውስጥ ቁምነገርና ፍሬነገር አጣርቶ ለማውጣት ሌት ተቀን የሚሰሩ የትንታኔ ዘዴዎችን መፍጠር፣ በዚህም ለፓርቲውና ለምርጫ ተፎካካሪዎች የገንዘብና የድምፅ ድጋፍ ሊያስገኙ የሚችሉ መንገዶችን እየመረጠ ማቅረብ... እንዴት መሰላችሁ?
የፌስቡክ ደንበኛ ስትሆኑና ድረገፅ ስትከፍቱ፣ ያደጋችሁበትን ከተማ ወይም የተማራችሁበትን ዩኒቨርስቲ ትመዘግቡ የለ? ፌስቡክ የበርካታ ሚሊዮን ሰዎችን መረጃ በማሰስና በመተንተን፣ እገሌና እገሊትም እዚህ ዩኒቨርስቲ ተምረዋል፣ እነ እንትና እዚህ ከተማ የሚኖሩ ናቸው፤ ታውቃቸው ይሆን? ብሎ በርካታ ስሞችን ያቀርብላችኋል። አማዞን ዌብሳይት ገብታችሁ አንድ የመፅሐፍ ርዕስ ስትፈልጉ፣ የዚህ መፅሐፍ ደራሲ’ኮ ሌሎች መፅሐፍት አሳትሟል ብሎ ይዘረዝርላችኋል፤ “ይሄን መፅሐፍ የወደዱ ሰዎች ይሄንንና ያንንም መፅሃፍ አንብበው ተደስተዋል፤ እስቲ አንቺም ተመልከቻቸው” ብሎ ያቀርብላችኋል። በመረጃ ላይ የተመሰረተና ለእያንዳንዱ ሰው ታልሞና ተለክቶ የተዘጋጀ ማስታወቂያ ልንለው እንችላለን።
የፖለቲካ የምርጫ ዘመቻም እንዲህ፣ በመረጃ ላይ ተመስርቶ፤ ለእያንዳንዱ መራጭ እና ለለጋሾች በተመቸ ሁኔታ መቅረብ ይችላል። ለምሳሌ፣ የምርጫው እለት ሳይደርስ ከቀናት በፊት ድምፅ መስጠት የሚቻልበት አሰራር እየተስፋፋ ከመምጣቱ የተነሳ፣ ዛሬ ዛሬ ሩብ ያህሎቹ መራጮች ከምርጫው እለት በፊት ነው ድምፅ የሚሰጡት። እንግዲህ በምርጫው እለት ስልክ እየደወሉ፣ ኢሜይል እየላኩ፣ በፌስቡክ እየፃፉ ወይም በየቤቱ እየዞሩ መራጮች ድምፅ እንዲሰጡ የሚቀሰቅሱ ደጋፊዎችን አስቧቸው። ከወዲሁ ድምፅ የሰጡ መራጮች ላይ ጊዜያቸውን ማባከን የለባቸውም። ለተቀናቃኝ ፓርቲ ድምፅ የሚሰጡ ሰዎችን ለመቀስቀስ ጊዜ ማባከን ደግሞ ድርብ ኪሳራ ነው። ስለዚህ ባለፉት ምርጫዎች በተደጋጋሚ የሰጡትን ድምፅ ማወቅ ቢቻል፤ በምርጫ ዘመቻው ወቅት በቤት ለቤት ቅስቀሳ የእያንዳንዱን መራጭ አዝማሚያ ወዴት እንደሚያዘነብል ማወቅ ቢቻል፣ ከምርጫው እለት በፊት ድምፅ መስጠት አለመስጠቱን ማወቅ ቢቻል... የት ላይ ማተኮር እንዳለብህ አወቅክ ማለት ነው፤ የምርጫ ዘመቻው ይበልጥ ውጤታማ ይሆናል። ይሄን ይሄን እና ተመሳሳይ ቁልፍ ጉዳዮችን በማወቅ የዘመቻ አቅጣጫ ለፓርቲው ማሳየት የአዛሪያስ ረዳ ስራ ነው፡፡
ድንቅ ነው፡፡ ግን ይሄው የአዛሪያስ ረዳ ሃላፊነት ከሃሳብነት አልፎ በእውን ውጤት ያመጣ ይሆን? ሪፓብሊካኖች በ2016 ዓ.ም የፕሬዚዳንት ምርጫውን እንዲያሸንፉ ይረዳቸው ይሆን? አዛሪያስ አጭር ምላሽ አለው፡፡
ስራውን ከጀመረ አመት ባይሞላውም፤ ገና ከወዲሁ ውጤት እንደምናስገኝ በዘንድሮው የኮንግረስና የሰኔት ምርጫ ታያላችሁ ብሎ ነበር - መስከረም ወር ላይ፡፡ የምርጫው ቀን ደረሰ፡፡ ህዳር ወር ምርጫው ሲካሄድ…እውነትም አዛሪያስ እንደተነበየው ሪፐብሊካኖች ለ85 ዓመት ያላዩት ትልቅ ድል ተቀዳጁ፡፡

Read 3729 times