Saturday, 24 January 2015 13:29

የብሩክታዊት ፉጨቶች በ“ጾመኛ ፍቅር!”

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)

ኢ.ኤ ግሩንግ ላምቦርን፤ ግጥምን በዜማ የተነከረ ስዕል አድርገው ያዩታል፤ ነፍስ በሙዚቃው ዳንስ ሰክራ ካልተንገዳገደች፣ በስሜት ደም ቀልማ ካልተዥጎረጎረች ግጥም ህያው አይደለም ብለው ያስባሉ፡፡ እናም የብዙዎቻችን ችግር ግጥም ከሙዚቃ መወለዱን መዘንጋታችን ነው፤ ይላሉ፡፡
ይሁንና በገጣሚያን መካል የዘዬ፣ የፍልስፍናና የአተያይ ጥልቀት ልዩነት እንዳለ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ በተለይ ሒሊየር እንደሚሉት፤ ግጥም እንደ ወንድ ዘር ፍሬ ቀድሞ አእምሮ ላይ ዋኝቶና ደንሶ ሲያበቃ ነው ዕንቁላል ሰብሮ ነፍስ የሚዘራው፡፡
ሰሞኑን በካፒታል ሆቴል የተመረቀው የብሩክታዊት ጎሳዬ “ፆመኛ ፍቅር” የግጥም መድበል ነው ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ፡፡ ግጥሞቿን ሳነበው፣ ይህቺ ከሀገር ውጭ የምትኖር ገጣሚ፣ ስደትን እንዴት እንዲህ አየችው? ማለቴ አልቀረም፡፡ ስደት ላይ ያተኮርኩት ሰባት ያህል ግጥሞቿ፣ ለዚያውም ረዘም ረዘም ያሉት እዚያ ላይ በማነጣጠራቸው ነው፡፡ እርግጥ ነው በአብዛኛው የጥበብ ሰው ትኩረት ሁሌ ከሕይወቱ ይነሳል፤ ደግሞም የአካባቢውን ቀለም ያጠቅሳል፡፡ ለዚህ ደግሞ የእነ ሔሚንግዌይ፣ ቶልስቶይ፣ ዩዶራ ዌልቲንና ሌሎች ሥራዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከገጣሚያንም እነ ጆን ሚልተን አሉ፡፡ ሚልተን ስለ ዕድሜ ድንገት መብረር፤ ኋላም ስለ ዓይኑ ብርሃን መጥፋት የነገረን በግጥሞቹ ነው፡፡
ብሩክታዊትም ይህንኑ የእውነት ምህዋር ተከትላ ነው የሄደችው፡፡ ሕይወት አበባ የተነሰነሰባት ሳትሆን እሾህ የተነጠፈባትም ሸለቆ እንደሆነች ነው የምታሳየው፡፡ ለምሳሌ እንደ ማዕበል ሰይፍ ስሜቷ በስደት ዘመኗ ከፍ እያለ፣ እንደገና መሬት የነካበትን ሌሊት በተራኪዋ  አንደበት በዜማ ትነግረናለች፡፡
“ማንነት” የሚለው ግጥሟ እንዲህ ይላል፡-
ሲነጋ -- ከቆመ እድሜዬ ላይ አንድ ቀን ሲሸረፍ
ልቤ በትዝታ ወዳገሬ ሲከንፍ
“ከነድህነቴ ከነመከበሬ
ምነው እግሬን ሰብሮ ባኖረኝ ሀገሬ እልና--”
በእነዚህ  ስንኞች ውስጥ በሀገሯ ያላትን ክብር፤ … ከሺህ ቀን ባርነት ያንድ ቀን ነፃነት በሚል ዓይነት ታስበውና ከሀገሯ የወጣችበትን ቀን ትረግማለች፡፡ ሁሉም በአገር ያምራል ብላ፡፡ ይህንን ያሰበችው ማታ ነው፡፡ (ገፀ ባህሪዋ ወይም ገፀ ባህሪው)
ሲነጋ ደግሞ ወፎች
ሲነጋ … ወፎች ሲንጫጩ
ደርሶ ሲንፎለፎል … የተስፋዬ ምንጩ
ሀገሬን ኮንኜ - ሳሞግስ ስደቴን
ሳበሸቃቅጠው ያምና ድህነቴን
“ሳልኖር እሞት ነበር …” እልና በዕለቱ
ሊቀር በማግስቱ …
ስሜቷ ሲቀየር ተስፋ አፍንጫዋ ሥር መጥቶ ሽቶውን ሲረጭባት፣ የተሻለ ኑሮ፣ የተሻለ ሕይወት፣ የተሻለ ትራንስፖርት፣ የኮረንቲ አለመጥፋት፣ ከወያላ ስድብ ማምለጧ ትዝ ሲላት፣ እንኳን መጣሁ --- እዚያ አንገፍጋፊ ድህነት ውስጥ ልሞት ነበር ትላለች፡፡ ሁለት ማንነት!
ይሄኔ - ስንኞች እየተሳሳሙ በዜማ ባህር ላይ ሲደንሱ፣ የፌሽታ ጅራፍ ይጮሃል! … የገደል ማሚቶው ድምፁን ያስተጋባል፡፡ ርዝቅና ክብር - ነፃነትና የሰው ሀገር ስርፀት - ይጋጫሉ፡፡ ይህ ሁሉ ግን የግጥም ድንኳን ድምቀት ነው፡፡ ሳቅ ብቻ ግጥምን አያደምቃትም፣ ለቅሶም ውበት አይሆናትም፡፡ ሁለቱንም አቅፋ፣ ሁለት ጡቶቿን ታጠባለች፡፡
ከብሩክታዊት ግጥሞች  በርከት ያሉት ፍቅርና ሀገር ላይ ያጠነጥናሉ፡፡ ለምሳሌ “ቅብጥብጥ ፍቅር”፡-  
ኤቨረስት እንውጣ ነፋስ እንቀበል
በጨረቃዋ ፍም ድንቻችን ይብሰል
ከዐባይ ፏፏቴ ዋና ተፎካክረን
ከሳይቤሪያ ላይ እንረፍ ተቃቅፈን
እንዳሻን እንሁን አሁን አሁኑኑ
የመፋቀር ዘመን አጭር በመሆኑ፡፡
ፍቅርም ግጥምም ዕብደት የሚሆነው ይሄኔ ነው፡፡ ላፈቀረ ሰው ኤቨረስት መውጣት ቀላል ነው፡፡ በጨረቃ ብርሃን ድንች መቀቀልም ይቻላል፡፡ በተለይ የሳይቤሪያን ቅዝቃዜ የሚያሸንፍ ፍም ያለው ፍቅር ነው፡፡ ግነቱ ጣዕም ያለው ነው፡፡ ለመዘርዘር ገፁ አይፈቅድምና ልተወው፡፡
“ህልም ምኞት” የሚለው ግጥምም ዜማውና ምቱ የልብ ትርታን መስመር ባይከተልም ሃሳቡ ጠለቅ ያለ ይመስላል፡፡
እጥፍ ብለህ
ሀረግ መስለህ
  አይሃለሁ
ልደግፍህ እመኛለሁ
ግን ሃሜታን እፈራለሁ፤
እንደኪኒን መዋጥ ብችል
ውስጥህ በቆምኩ ቀጥ እንድትል፡፡
ራስን ለፍቅር የመስጠትን ብርታት የሚያሳይ ምትሀት ነው፡፡ ተራኪዋ ሴት ትመስላለች፡፡ ወንዱ ገፀ ባህሪ እንደ ሀረግ እጥፍ ያለ ነው፤ አጥንት የለውም፣ … አጥንት የምለው ምናልባት ሌላ ጉድለት፣ አንገት የሚያስደፋ ነገር ይሆናል - ድህነትንም ልንጠረጥር እንችላለን፡፡ ልትደግፈው አስባ ሃሜታው ግን መከራ ሆኖባታል፡፡ ስለዚህም ከሰውነት ተራ ወርዳ፣ ለርሱ ስትል ኪኒን መሆን ተመኘች፡፡ እርሱ እርሷን ውጦ፤ ቀጥ ብሎ እንዲኖር ጓጓች፡፡  ሕልውናዋን አጥታ ህልውናው ሙሉ እንዲሆን! … ይህ ነው የፍቅር ጣት! ይህ ነው የፍቅር ሰማይ!
ገፅ 39 ላይ “የተከለከለ” የሚል በቁጭት ጥርስ የሚያስነክስ ግጥም አለ፡፡
“መማር ነው” እያሉ ይሸነግሉናል
“መጣር ነው” እያሉ ያንከራትቱናል
    ሲገባን ሀሰት ነው
በልጦ ለመገኘት ሌላ መንገድ አለ
ላልበቃን ላልነቃን የተከለከለ፡፡
እዚህ ግጥም ውስጥ ተራኪዎቹ መማርንም መጣርንም ሞክረውታል፤ ግን በልጦ ለመገኘት፣ ጅራት ሳይሆን ራስ ለመሆን ሌላ መንገድ እንዳለ ተረድተዋል፡፡ የሚያሳዝነው ግን ያንን እንዲያውቁ አልተፈቀደላቸውም፡፡ ተከልክለዋል፡፡ በምን መስፈርት እንደሆነ ባይታወቅም ይህን መንገድ የሚጠቀሙበት ሌሎች ናቸው…. ስለዚህ ግጥሟ በቁጭት ቁንጥጫ እርር ያለ ልብ የወረወራት ማስታወሻ ናት፡፡
“ጾመኛ ፍቅር” ውስጥ በርካታ ግጥሞች በተቃርኖ የተሞሉ ናቸው፡፡ ውስጣቸው ግብግብ አለ፡፡ እንደ “አፍና ልብ”፤ “ወይ ጉድ”፣ “አለፈ”፣ “እምነት አልባ ፍቅር” ወዘተ… የመሳሰሉት፡፡
ገፅ 13 ላይ “ሁለት ቅጠሎች” የሚለው ግጥም ደግሞ ተምሳሌታዊ መልዕክት ያለው ይመስላል፡፡ እዚህ ግጥም ላይ የምናደምጠው ከአንድ ትልቅ ዛፍ ስር ያለች ጥገኛ ዛፍ ቅጠል፣ ለትልቁ ዛፍ ቅጠል - የምትለውን  ነው፡፡ እንዲህ፡-
እኔ ተነቃይ ነኝ አንቺ አብሮ ነዋሪ
አንቺ ሁሌ ቁጡ እኔ ሁሌ ፈሪ፡፡
--- ትላለች የትንሹ ዛፍ ቅጠል፡፡ ሸምቃቃ ናት፡፡ ፈሪ ናት፡፡ እንባ ያነቃትም ትመስላለች፡፡ ግን ደግሞ ወደ ቀጣዩ ቀን የምታየው ተስፋ፣ የምትጠረጥረው ነገር አለ፡፡ ቅጠልን ለመጣል ንፋስ ይመጣልና ማን ያውቃል? ዓይነት!  
ግን እኮ ታውቂያለሽ?
አንዳንድ ነፋስ አለ
ለለውጥ የሚነፍስ
ወፍ ዘራሿን ትቶ
ከትልቁ ዛፍ ላይ ቅጠል የሚበጥስ …
የተወሰኑትን ስንኞች ስናይ የምናገኘው ጠቅላላ ሀሳብ፣ ማንም የቆመ ቢመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ! የሚለውን የወንጌል ቃል ነው፡፡ አንቺ “ተደላድያለሁ” ብለሽ እኔን ከዚህችም ኑሮዬ ለመንቀል ሙከራ ታደርጊያለሽ፣ ትሳደቢያለሽ፣ ትቆጫለሽ፣ ግን ደግሞ እንዳይመስልሽ አንዳንዴ‘ኮ እንዳንቺ በትዕቢት  በተወጠሩት ላይ የሚነፍስ አለ፤ ያ - ንፋስ ድንገት ከላይ በጥሶ መሬት ላይ ይጥላል ነው የምትላት፡፡ ይህ በብዙ አቅጣጫ ሊመነዘር ይችላል፡፡ አዳዲስ ሃሳቦች፣ ልዩ ልዩ የሀሳብ ጌጦች እንደፈርጥ ሊያበሩበት መንገዱን ከፍቷል፡፡
“አፍሪካዊ” የሚለው ግጥምም ውስጥን የሚነካ ትልቅ ሃሳብ ያለው ነው፡፡
ረሃብ ካልሆነ … ጦርነት ይሆናል
ጦርነት ከጠፋ … እብድ ፖለቲካ
ገርፎ ያስወጣዋል
ሰበብ የሌለውን …. እውቀት ይጠራዋል
ሃገሩ ቢወለድ … በሃገሩ አያድግም
ሃገሩ ላይ ቢያድግ … ሃገሩ አያረጅም
አፍሪካዊ ማለት ሲሰራ ከጥንቱ
ተበይኖበታል እንዳይገናኙ
እንጀራና ቤቱ፡፡
የምናውቀው እውነት ቢሆንም እንደገና ነፍሳችንን በቁንጥጫ ያሳርራታል፡፡ በተለይ የእንጀራና የቤት መራራቅ፡፡ በስደት ምክንያት ከእናት አባት፣ ከወንድም እህት መለየት፣ በሰርግና በለቅሶ ያለመገኘት፡፡ ለቅሶን እንኳ መንገድ ላይ መጨረስ … ጉዳችን ብዙ ነው፡፡
የብሩክታዊት “ጾመኛ ፍቅር” የዜማ ስብራት፣ የአጨራረስ ችግርም ይታይበታል፡፡ ግን ደግሞ ሞገስ ያላቸው ደማቅ ዜማና ምት ይዘዋል፡፡ ስደቱ ያላዳፈነው የጥበብ እሳት ወደፊት የተሻለ እየፈካ እንደሚሄድ እጠብቃለሁ፡፡ መሻሻል ያለባቸውን ጉድለቶች ተረጋግቶ ላጣጣመ፣ መቼም ቢሆን ለጥበብ የተፈጠረ ሰው እያደገ እየጎለበተ መሄዱ የሚጠበቅ ነው፡፡ ሌሎች እህቶቻችንም የእሷን ዱካ ተከትለው ብቅ ቢሉ ደስታችን ነው፡፡

Read 2526 times