Saturday, 24 January 2015 13:22

የአማርኛ ግጥሞች ትንታኔ በተለያዩ ምሁራን

Written by  ዮሐንስ ሰ.
Rate this item
(35 votes)

እንደ ማስተማሪያ የሚቆጠሩት የአምስቱ ምሁራን አስተሳሰቦች ምን ያህል እርስ በርስ የማይጣጣሙና የቱን ያህል ዝብርቅርቅ ሃሳቦችን እንደሚፈጥሩ ማሳየት ነው የፈለግሁት። ከዚህ ጋር አብሮ የሚመጣው ሌላው ጥያቄ፣ “በዩኒቨርስቲ የቋንቋና የስነፅሁፍ ተማሪዎች በስነግጥም ዙሪያ ዝብርቅር ሃሳቦችን እየተጋቱ እንዴት ቅጥ ያለው እውቀት ሊገበዩ ይችላሉ?” የሚል ነው።

እዮሐ አበባዬ የሚለውን የአዲስ አመት ዘፍን የምታውቁት ይመስለኛል። የዘፈኑ ግጥም፣ ባለ አስር ቀለም እንደሆነ መንግስቱ ለማ ይገልፃሉ። “እዮሐ አበባዬ ቤት” በሚል የሚታወቀው ይሄው የግጥም ስልት፣ ሌሎች መሰረታዊ የግጥም ስልቶችን በማደባለቅ የሚፈጠር መሆኑን መንግስቱ ለማ ሲገልፁ፤ የሰንጎ መገን ቤት፣  የቡሄ በሉ ቤት እና የወል ቤት ድብልቅ ነው ይላሉ። ምሳሌ ሲጠቅሱም፣ “አይዞሽ ነፍሴ/ ደረሰልሽ ገብሴ” የሚሉ ቃላትን በአንድ ስንኝ አያይዘው ካቀረቡ በኋላ፣ የስንኙ የመጀመሪያ ሐረግ ባለ አራት ቀለም እንደሆነ አመልክተዋል፤ [አይ’ዞሽ’ - ነፍ’ሴ’]። ይህን ሐረግ ከመሃል ለሁለት የሚከፍል ሰረዝ የተጠቀሙት፣ ቃላትን ለመለየት እንዳልሆነ ልብ በሉ። ቀለማቱን በሁለት በሁለት ማቧደናቸው ነው። ለዚህ ማስረጃ ሁለተኛው ሐረግ ባለ ስድስት ቀለም መሆኑን በመግለፅ ቀለማቱን እንዴት እንዳቧደኗቸው ተመልከቱ፡ [ደ’ረ’ - ሰ’ልሽ’ - ገብ’ሴ’]። “የአማርኛ ግጥም፤ ዓይነቱ፣ ሥሪቱ፣ ሥርዓቱ” በሚል እ.ኤ.አ 1963 በኢትዮጵያ ጥናቶች ጆርናል በገፅ 148 – 149 ካሰፈሩት ትንታኔ የተወሰደ ነው።
ከመንግስቱ ለማ በፊት አለማዮህ ሞገስ በ1954 ዓ.ም ባሳተሙት “ያማርኛ ግጥምና ቅኔ ማስተማሪያ” ደግሞ ሌላ ገለፃ እናገኛለን። “እዮሐ አበባዬ ቤት” ተብሎ ለሚታወቀው የግጥም አይነት እንደ መንግስቱ ለማ ተመሳሳይ ምሳሌ የጠቀሱት አለማዮህ ሞገስ፤ በአንድ ስንኝ ሳይሆን በሁለት ስንኝ አድርገው አቅርበውታል፤ በየስንኙ ስድስት ቀለማት እንደተካተቱም ገልፀዋል።
አይዞሽ ነፍሴ
ደረሰልሽ ገብሴ
“አይዞሽ ነፍሴ” የሚሉት ቃላት፣ ባለ አራት ቀለም የስንኝ ክፋይ ናቸው በማለት መንግስቱ ለማ ሲገልፁ፣ አለማዮህ ሞገስ በበኩላቸው ባለ ስድስት ቀለም ሙሉ ስንኝ ናቸው ይላሉ። ሦስት መሰረታዊ የግጥም አይነቶችን ያደባለቀ የግጥም ስልት መሆኑን መንግስቱ ለማ ሲጠቅሱ፣ አለማዮህ ሞገስ በበኩላቸው ከወል ቤት ግጥም ጋር ያመሳስሉታል - የወል ቤት ግማሽ ያህል እንደሚሆን በመጠቆም።
ከመንግስቱና ከአለማዮህ በፊት ብላታ መርስዔኀዘን ወልደቂርቆስ በበኩላቸው፤ በ1948 ዓ.ም ባሳተሙት “ያማርኛ ሰዋስው” መፅሐፍ ውስጥ የ“እዮሐ አበባዬ ቤት” ግጥም ከስንት ቀለማት እንደሚዋቀር ሳይጠቅሱ፣ በደፈናው ሐረጉና ስንኙ አጫጭር ነው ብለዋል - “አይዞሽ ነፍሴ/ ደረሰልሽ ነፍሴ” የሚለውን በምሳሌነት በማካተት። ነገር ግን እንደ አንድ ስንኝ አልያም እንደ ሁለት ስንኝ ሊቀርብ ሊታይ ይችላል ብለዋል።
ተሾመ ይመር በ1989 ዓ.ም በኢትዮጵያ ጥናቶች ጆርናል፤ “የአማርኛ ግጥም አይነቶች” በሚል ባቀረቡት ፅሁፍ ደግሞ፣ “እዮሐ አበባዬ ቤት” በመርስዔኀዘን፣ በመንግስቱና በአለማዮህ የግጥም ዓይነቶች ዝርዝር ውስጥ በስም እንደተጠቀሰ ገልፀዋል። ነገር ግን፣ የግጥም አይነቶችን በአዲስ መልክ በመዘርዘር ሲያቀርቡ፣ “እዮሐ አበባዬ” ከየትኛው ምድብ እንደሚካተት አላስረዱም። ብርሃኑ ገበየሁ በ1993 ዓ.ም “ምጣኔ በአማርኛ ስነግጥም” በሚል በኢትዮጵያ ጥናቶች ጆርናል ባቀረቡት ፅሁፍ እንዲሁም በ1999 ዓ.ም የአማርኛ ሥነግጥም በሚል ባሳተሙት መፅሐፍ ውስጥ፣ ስለ ግጥም የምጣኔ አይነቶች ብዙ ቢናገሩም፣ “እዮሐ አበባዬ” የሚል አንድም ቦታ ሳይጠቅሱ አልፈዋል።
በአማርኛ የግጥም አይነቶች ዙሪያ በብዛት የሚጠቀሱት ሰዎች በአንድ የግጥም አይነት ላይ እርስ በርስ የማይጣጣም አስተያየት መስጠታቸውና ከፊሎቹም ከግጥም አይነት ዝርዝር ውስጥ ሳያስገቡት መቅረታቸው ወይም እስከነጭራሹ በስም ሳያነሱት ማለፋቸውን አይተናል። ይህም ብቻ አይደለም። ሌሎች የተለመዱ የግጥም አይነቶችም ላይ የተዘበራረቀ አስተያየት ታገኛላችሁ። “ቡሄ በሉ”፣ “ሆያ ሆዬ” እና “አበባዬ ሆይ” የተሰኙትን ግጥሞች ወይም የግጥም አይነቶችን ተመልከቱ።
መርስዔኀዘን፣ ከስምንቱ የግጥም አይነቶች አንዱ፣ “ቡሄ በሉ ቤት” መሆኑን ጠቅሰው፣ ስንኙ አጫጭር እንደሆነና ሕፃናት ለቡሄ እንደሚጨፍሩበት ገልፀዋል።   
እዚያ ማዶ ጭስ ይጨሳል
አጋፋሪ ይደግሳል
ያንን ድግስ ውጨ ውጨ
በድንክ አልጋ ተገልብጨ...
ሌላኛው የግጥም አይነት “ሆያሆዬ ቤት” እንደሚባል መርስዔኀዘን ጠቅሰው፣ “አበባዬ ሆይ” የተሰኘው የሴቶች ዘፈንም ከዚሁ ቤት እንደሚመደብና አንዳንድ ጊዜ ከ“ሰንጎ መገን ቤት” ጋር እንደሚገጥም አውስተዋል።
አለማዮህ ሞገስ ግን፣ “ሆያሆዬ” እና “አበባዬ ሆይ” ከሰንጎ መገን ቤት ጋር አንድ ናቸው በማለት እዚያው ቤት መድበዋቸዋል። የ“ቡሄ በሉ ቤት” ግን በአለማዮህ ከተዘረዘሩት 14 የግጥም አይነቶች ውስጥ አልተካተተም። መንግስቱ ለማ፣ በአንድ በኩል ከአለማዮህ ጋር ይስማማሉ - ሆያሆዬ እና አበባዬ ሆይ በባህሪያቸው በሰንጎ መገን ቤት ውስጥ የሚመደቡ ናቸው በማለት። እንደ ሌሎች የሰንጎ መገን ግጥሞች ሁሉ፣ ሆያሆዬ እና አበባዬ ሆይ ባለ አስር ቀለም ስንኞችን የያዙ፣ እያንዳንዱ ስንኝም ሁለት ሐረጋትን ያቀፈ፣ በየሐረጉ የሚገኙ አምስት ቀለማትም “ነ-ነነ-ነነ” ወይም “ነነነ-ነነ” በሚል ስልት የተቀናበሩ (የተቧደኑ) ናቸው ሲሉ መንግስቱ ለማ ያስረዳሉ።
[የ’-ኔ’ማ’ - ጌ’ታ’/ የ’-ሰ’ጠኝ’ - ሙ’ክት’]
[በ’-ለ’ጭ’ - ማ’ነው’/ ባ’- ለ’ም’-ል’ክት’]
አበባዬ ሆይ የሚለውንም  ግጥም እንደ ሆያሆዬ በተመሳሳይ የ(ነ-ነነ-ነነ) ስልት ቢያቀርቡትም፣ በ[ነነነ-ነነ] ስልት ቢሆን ይመረጣል።
[ባ’ልን’ጀ’-ሮ’ቼ’/ ቁ’ሙ’በ’-ተ’ራ’]
[እን’ጨት’ሰ’-ብ’ሬ’/ ቤት’እስ’ት’-ሠ’ራ’]   
የመንግስቱ ለማ ትንታኔ ከሌሎቹ ለየት የሚለው፣ ከቀለማት ብዛት ባሻገር የቀለማት አወቃቀር (ቀለማት በቡድን የተደራጁበት ስልት) ላይ ማተኮራቸው ነው። በዚሁ አቅጣጫ፣ መሰረታዊዎቹ የግጥም አይነቶች ሦስት ናቸው የሚል መደምደሚያ ላይ የደረሱት መንግስቱ ለማ፣ ከእነዚህም መካከል “ነነነ-ነነ” የሚለው የሰንጎ መገን ስልት አንዱ መሆኑን ያብራራሉ። በእርግጥ፣ “የሰንጎ መገን ስልት” ከሚለው ትክክለኛ አገላለፅ በተጨማሪ፣ አንዳንዴ “የሰንጎ መገን ስንኝ”፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ “የሰንጎ መገን ቤት” የሚሉ አገላለፆችን በዘፈቀደ እያቀያየሩ መጠቀማቸው ለስህተት የሚዳርግ ነው። የሰንጎ መገን ስልት “ነነነ-ነነ” ሲሆን፣ ስንኙ ግን ስልትንና ምጣኔን በማካተት “ነነነ-ነነ/ ነነነ-ነነ” የሚል ይሆናል። የሰንጎ መገን ቤት ሲባል ደግሞ፣ ከእንደዚህ አይነት የስንኝ አወቃቀር የተበጁ ግጥሞችን የሚወክል የአይነት ስያሜ ነው። እነዚህን ልዩነቶች ማምታታት ስህተት ቢሆንም፣ መንግስቱ ለማ ከሌሎቹ ምሁራን በተለየ ሁኔታ ከቀለማት ብዛት ባሻገር፣ የቀለማት አወቃቀር (ስልት) ላይ ያተኮረ ትንታኔ ማቅረባቸው፣ በአገራችን የሥነግጥም ዘርፍ ከሁሉም የላቀ ከፍ ያለ ቦታ ሊያሰጣቸው ይገባልም። ምክንያቱም፣ ከግጥም ዋና ባሕርያት መካከል አንዱ የሆነውን ምት (ሪዝም)፣ በቀለማት ብዛት ሳይሆን በቀለማት ስልት ላይ የተመሰረተ ነው። ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህንም ይህንን የግጥም ባህርይ በተመሳሳይ መንገድ ነበር የሚገነዘቡት። አሳዛኙ ነገር፣ መንግስቱና ፀጋዬ ወደፊት ያራመዱት የግጥም ስልትና የምት ትንታኔ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተረሳ፣ በተለይ ደግሞ በብርሃኑ ገበየሁ ጨርሶ ትርጉም አልባ እንዲሆን ተደርጓል ማለት ይቻላል - ምት የተመሳሳይ ድምፆች ድግግሞሽ ነው ብለዋል (የአማርኛ ስነግጥም ገፅ 206)። በአንድ ስንኝ ውስጥ ‘ሮ’ እና ‘ሎ’ የሚሉ ሳብዕ ድምፆች መኖራቸው እንደ ዋና የምት ምሳሌ ማቅረባቸው፣ የምትን እሳቤ እጅጉን በሩቁ እንደሳቱት ያረጋግጣል። በሚገባ አንጥረው ባያወጡትም፣ “ስልት” ላይ ያተኮረው የመንግስቱ ለማ ትንታኔ፣ በንፅፅር ሲታይ የቱን ያህል የቀደመ እንደሆነ በዚሁ አጋጣሚ መረዳት ይቻላል።
ወደ ጀመርነው ውጥን ስንመለስ፣ ቡሄ በሉ ቤት በአለማዮህ ሞገስ የግጥም አይነቶች ባይካተትም፣ መንግስቱ ለማ ግን፣ ከሰንጎ መገን በተጨማሪ፣ ከዋና ዋናዎቹ ሦስት መሰረታዊ የግጥም ስልቶች መካከል አንዱ፣ የቡሄ በሉ ስልት እንደሆነ ይገልፃሉ። በባለ 8 ቀለም ስንኞችንና በየስንኙም ሁለት ሐረጋትን የያዘው የቡሄ በሉ ቤት ግጥም፣ በየሐረጉ በሁለት በሁለት የተቧደኑ ቀለማት እንዳሉ መንግስቱ ለማ ሲያስረዱ፣ “የስንኙ ስልት፣ ነነ-ነነ/ ነነ-ነነ የሚል ነው” ብለዋል።
[እ’ዚያ’ - ማ’ዶ’/ ጭስ’ ይ’-ጨ’ሳል’]
[አ’ጋ’ - ፋ’ሪ’/ ይ’ደ’-ግ’ሣል’]
ተሾመ ይመር በበኩላቸው፤ ግጥም ተመጥኖ የሚያልቀውና የግጥሙ ምትና ዜማ የሚዋቀረው በሐረግ ውስጥ እንደሆነ ገልፀው፤ የግጥም ዓይነቶችን መለየት የሚቻለው በስንኝ ስልት ሳይሆን በሐረግ ስልት ነው ይላሉ። በእርግጥ መንግስቱ ለማ፣ የስንኝ ስልት፣ የቤት ስልት፣ የሐረግ ስልት የሚሉ አገላለፆችን አላግባብ በማደበላለቅ ቢጠቀሙም፣ የግጥም ዓይነቶችን ለመፈረጅ የተጠቀሙት የሐረግ ስልትን ነው። ለምሳሌ፣ የቡሄበሉ ስንኝ ስልት ከነምጣኔው “ነነ-ነነ/ ነነ-ነነ” የሚል ባለ 8 ቀለም ቢሆንም፣ የቡሄበሉ ስንኝ ስልት “ነነ-ነነ” የሚል ነው ብለዋል - የአንድ ሐረግን ብቻ በማሳየት። እንግዲህ ተሾመ ይመርም በስንኝ ላይ ሳይሆን በሐረግ ላይ ማተኮር አለብን ስለሚሉ፣ አካሄዳቸው ከመንግስቱ ለማ ጋር ተመሳሳይ እንደሚሆን ልንጠብቅ እንችላለን። ነገር ግን ይለያያል። እንዴት? የግጥም ዓይነቶችን የምንፈርጀው፣ “በሐረግ ውስጥ ያለውን የቀለማት ብዛት መሰረት አድርገን” ነው ይላሉ ተሾመ ይመር። እናም “እዚያ ማዶ/ ጭስ ይጨሳል” የሚለው ባለ 8 ቀለም ስንኝ፣ ከባለ አራት ቀለም ሃረጋት የተዋቀረ መሆኑን ይጠቅሳሉ (ገፅ 109)። መንግስቱ ለማ ግን፣ ከቀለም ብዛት ባሻገር ቀለማቱ የተቧደኑበትንም ስልት ያጣመረ ነው - አራት ቀለማት ያሉት የቡሄበሉ ሐረግ “ነነ-ነነ” በሚል ስልት የተዋቀረ ነው ይላሉ።
ብርሃኑ ገበየሁ ደግሞ፣ የሐረግ ቀለማት ብዛትም ሆነ የሐረግ ቀለማት ስልትን አይቀበሉም። በስንኝ የቀለማት ብዛት ነው ግጥሞችን የሚፈርጁት አቶ ብርሃኑ፤ ቡሄበሉ ቤት በአንድ ስንኝ ከሶስት እስከ አምስት ቀለማት ይይዛል ብለዋል - “እዚያ ማዶ” ባለ አራት ቀለም ስንኝ መሆኑን፣ እንዴት አድርገው እንዳነበቡት ባይታወቅም “ጭስ ይጨሳል” የሚለው ደግሞ ባለ አምስት ቀለም ስንኝ እንደሆነ ገልፀዋል (ገፅ 239)። ብርሃኑ ገበየሁ፣ የምት እሳቤን ብቻ ሳይሆን ከመነሻው የቀለም ምንነት ላይ ከዚያም የስንኝ ምንነት ላይ ከፍተኛ የግንዛቤ ችግር እንዳለባቸው መፅሐፋቸው ውስጥ በተደጋጋሚ ይታያል። በእርግጥ፣ የዚህ ፅሁፍ ትኩረት፣ ከሌሎቹ ተጠቃሽ ምሁራን በተለየ ሁኔታ በአይነትና በብዛት ገንነው የሚታዩ የብርሃኑ ገበየሁ ስህተቶችን ለመዘርዘር አይደለም። ይልቅስ፣ እንደ ማስተማሪያ የሚቆጠሩት የአምስቱ ምሁራን አስተሳሰቦች ምን ያህል እርስ በርስ የማይጣጣሙና የቱን ያህል ዝብርቅርቅ ሃሳቦችን እንደሚፈጥሩ ማሳየት ነው የፈለግሁት። ከዚህ ጋር አብሮ የሚመጣው ሌላው ጥያቄ፣ “በዩኒቨርስቲ የቋንቋና የስነፅሁፍ ተማሪዎች በስነግጥም ዙሪያ ዝብርቅር ሃሳቦችን እየተጋቱ እንዴት ቅጥ ያለው እውቀት ሊገበዩ ይችላሉ?” የሚል ነው።
ከላይ እንደጠቀስኩት፣ ከባለ 8 ቀለም ስንኞች የሚዋቀር የ“ቡሄበሉ” ግጥም፣ ራሱን የቻለ መሰረታዊ የስንኝ ስልትን እንደሚከተል የገለፁት መንግስቱ ለማ፣ ከባለ 10 ቀለም ስንኞች የሚዋቀሩ የሆያሆዬ እና የአበባዬ ሆይ ግጥሞች ደግሞ፣ በሌላኛው መሰረታዊ የስንኝ ስልት በሰንጎ መገን ውስጥ እንደሚመደቡ ጠቅሰዋል። የስንኝ እና የቀለም ምንነት ላይ የግንዛቤ ጉድለት የሚታይባቸው ብርሃኑ ገበየሁ በበኩላቸው፣ አንዱን ስንኝ እንደ ሁለት ስንኝ እየቆጠሩ ስለሚከትፉት፤ የቡሄበሉ፣ የሆያሆዬ እና የአበባዬ ሆይ ግጥሞች፣ በአንድ ስንኝ ውስጥ ከአምስት በላይ ቀለም እንደሌላቸው ይገልፃሉ - በጋራ “ቡሄ በሉ ቤት” በማለት ይጠሯቸዋል። ተሾመ ይመር፣ የስንኝ እና የቀለም ምንነትን ባይስቱም፣ ከቀለም ብዛት ባሻገር የስልት ልዩነትን ለማካተት ባለመቻላቸው፣ ቡሄበሉ፣ ሆያሆዬ እና አበባዬ ሆይ የተሰኙትን ግጥሞች በአንድነት የህፃናት ግጥም በሚል ፈርጀዋቸዋል።    
ሁሉም በጋራ እንደ የግጥም አይነት ወይም እንደ ስልት የሚጠቅሱት አለ - የወል ቤት የተሰኘ።
ፀጋዬ ገብረመድህን በድምፅ ባስቀረፁት የግጥም ንባብ እና ማብራሪያ፣ ስለ ግጥም የምጣኔና የስልት አይነት ተናግረዋል። አንድ ግጥም በወል ቤት እንዲሁም አራት ግጥሞች የፀጋዬ ቤት እንደተቀናበሩ ጠቅሰው፤ የሁለቱ ልዩነት በአጭሩ፣ የወል ቤት ስንኝ ባለ 6 ምት፣ የፀጋዬ ቤት ስንኝ ባለ 8 ምት መሆናቸው ብቻ ነው። የወል ቤትን ምጣኔ ከነስልቱ ለማስረዳት፣ [ተ’ተ’ተ’ - ተ’ተ’ተ’ - ተ’ተ’ተ’ - ተ’ተ’ተ’] በማለት በድምፅ ካሰሙ በኋላ፣ በተጨባጭ ምን እንደሚመስል ለማሳየትም፣ ከከበደ ሚካኤል ግጥም አንድ ስንኝ በመምዘዝ በምሳሌነት አቅርበዋል፤ [አ’ቻም’ና’ - ቅ’ዳ’ሜ’ - በ’ክእ’ረምት’ - ወ’ራ’ትእ’]። (እዚህ ላይ፣ “በክረምት” የሚለውን ቃል ስንናገር፣ “ክ” ራሱን የቻለ ቀለም ሆኖ ተረግጦ የሚወጣ ድምፅ መሆኑን ለማመልከት “እ” የሚል አናባቢ ተጨምሮበታል። ወራት የሚለው ቃል፣ በትክክለኛው አነጋገር፣ ባለ ሁለት ቀለም ነው - ወ’ ራት’። “ት” ለብቻው ሳይሆን የ“ራ” ቅጥያ ሆኖ የሚወጣ ድምፅ በማድረግ። ነገር ግን፣ የግጥሙን የምት ስልትና ምጣኔ ላለማጓደል፣ “ት” ራሱን የቻለ ቀለም እንዲሆን ይረገጣል - “እ” የሚል አናባቢ ይጨመርበታል ማለት ነው። በነገራችን ላይ፣ “ይረገጣል” ማለት ሌላ ትርጉም የለውም “እ” የሚል አናባቢ አለው ማለት ነው። “ይጠብቃል” ወይም “ጠብቆ ይነገራል” ማለት ግን፣ ቀለም ከመሆንና ካለመሆን ጋር ግንኙነት የለውም። በእንግሊዝኛው ጀሚኔሽን የሚባለው ነው። በተደጋጋሚ ከሚጠቀሱ ምሳሌዎች ማየት ይቻላል። ተናገረ በሚል ትርጉም “አለ” ስንል ለ አይጠብቅም። መኖርን ለማሳየት “አለ” ስንል ግን ይጠብቃል - “አልለ” የማለት ያህል ነው።)
ለወል ቤት ያቀረቡት ምሳሌ፣ ምጣኔውን ከነስልቱ የሚያሳይ ነው። ምጣኔውን ለማሳየት ሙሉ ስንኙን ማየት ያስፈልጋል። ስልቱን ለማሳየት ግን የስንኙን የተወሰነ ክፍል ብቻ ማሳየት በቂ ነው። “ተተተ - ተተተ... እያለ የሚቀጥል ወይም ራሱን የሚደግም ነው” ብሎ አሳጥሮ እንደ መግለፅ ቁጠሩት። ለዚህ ነው የወል ቤት ባለስድስት ነው ብለው የገለፁት። ግን በዚህ አያቆሙም፣ ስድስቱ አንድ ላይ የታጀሉ አይደሉም - በሶስት በሶስት የተሰደሩ መሆናቸውን በግልፅ አስገንዝበዋል። ይህንንም “ሁለት ባለ ሦስት” ሲሉ ይጠሩታል።         

Read 15837 times