Saturday, 24 January 2015 11:58

የመገናኛ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በርካታ ሠራተኞች በየጊዜው እየለቀቁብኝ ነው አለ

Written by 
Rate this item
(7 votes)

ተደጋጋሚ የቅጥር ማስታወቂያ ባወጣም ሠራተኛ ማግኘት አልቻልኩም ብሏል
በአመራር ደረጃ ላይ ያሉ ሠራተኞች የአመለካከትና የአቅም ችግር እንዳለባቸውም ገልጿል

   የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በያዝነው አመት ካጋጠሙት ችግሮች ሁሉ እጅግ የከፋው በርካታ ሠራተኞች በየጊዜው ከሥራ መልቀቃቸው መሆኑንን በመጠቆም ይህም በሚፈልገው መጠን ለመሥራት እንዳይችል እንቅፋት እንደሆነበት ተገለፀ፡፡ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል፤ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከትናንት በስቲያ ባቀረቡት የስድስት ወራት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ እንደገለፁት፤ በበጀት ዓመቱ የተለያዩ ችግሮች የገጠሙአቸው ቢሆንም በጐላ መልኩ የሚጠቀሰው ግን በርካታ ሠራተኞች በየጊዜው መልቀቃቸው እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ከሥራቸው በለቀቁ ሠራተኞች ምትክ ለመቅጠርና ክፍት የሥራ ቦታዎች ለማሟላት የቅጥር ማስታወቂያ በተደጋጋሚ ቢወጣም በሚፈለገው መጠንና ጊዜ የሰው ኃይል ከገበያው ለማግኘት አለመቻሉን ገልፀዋል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ከፍተኛ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሩ፤ ተደጋጋሚ የሥራ ማስታወቂያዎችን ማውጣትና ያሉት ሰራተኞች በተቻለ መጠን ስራዎችን በማካካስ እንዲሰሩ ማድረግ እየተወሰዱ ካሉት እርምጃዎች ተጠቃሽ እንደሆኑም ገልፀዋል፡፡ የሥራ ተቋራጮች
በውላችን መሰረት የግንባታውን ሥራ በተቀመጠው ጊዜ ያለማስኬድ ችግር አለባቸው ያሉት ሚኒስትሩ፤ የስራ ተቋራጮቹ በገቡት ውል መሰረት ስራዎቹን እንዲያከናውኑ ኃላፊነት እንዳለባቸው የማስገንዘብ ስራ እየሰሩ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ሚኒስቴር መ/ቤቱ በዋናነት ከኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች አፈፃፀም መጓተት ጋር በተያያዘ የተመደበለትን በጀት በተሟላ መልኩ መጠቀም አለመቻሉን ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው ላይ ገልፀዋል፡፡

Read 3201 times