Saturday, 17 January 2015 11:25

የ “ዳሽን አርት አዋርድ” አሸናፊዎች ይሸለማሉ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

       ዳሽን ቢራ ለሀገራችን የኪነ-ጥበብ ዕድገት ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው የታመነባቸውን ሥነ - ጽሑፍ (ግጥም) እና ኪነ-ጥበብ (ሥዕልና ቅርፃ ቅርፅ) ለመደገፍ በየዓመቱ የሚካሄድ የ”ዳሽን አርት አዋርድ” ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡
ተወዳዳሪዎች ያሸልመኛል የሚሉትን ሥራቸውን ወሎ ሰፈር ሚና ሕንፃ፣ ሴንቸሪ ፕሮሞሽን ቢሮ እስከ ጥር 15 ድረስ ማቅረብ እንዳለባቸውና የሽልማት ሥነ - ሥርዓቱ ጥር 23  በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚከናወን የጠቀሱት የዳሽን ቢራ ፋብሪካ ም/ሥራ አስፈጻሚ አቶ መክብብ ዓለሙ ዘመንፈስ፤ የውድድርና ሽልማቱ ዓላማ ኪነ-ጥበቡን ለማሳደግና ለመደገፍ ስለሆነ፣ ተወዳዳሪዎች ዳሽን ቢራን ሳይጠቅሱ ነፃ ሆነው በፈለጉት ርዕስና ሥራ መወዳደር እንደሚችሉ አስታውቀዋል፡፡ ለአሸናፊ ግጥሞች ማሳተሚያም ድጋፍ እንደሚያደርጉ አክለው ገልፀዋል፡፡ ዳኞች ከደራስያንና ከሠዓሊያን ማኅበር እንዲሁም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሙያው ከፍተኛ ልምድና እውቀት ያላቸው እንደተመረጡ ጠቁመው፣ 1ኛ የግጥም አሸናፊ 33ሺ ብር፣ 2ኛ 22ሺ ብር፣ 3ኛ 11ሺህ ብር እንደሚሸለሙ፤ በሥዕልና ቅርፃ ቅርፅም ከ1ኛ እስከ 3ኛ ለወጡት አሸናፊዎች ተመሳሳይ ሽልማት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡ በዚህ ዘርፍ ከ4ኛ እስከ 10ኛ የሚወጡት ደግሞ 1.500 ብር ይሸለማሉ ብለዋል፡፡ ዳሽን ቢራ የኪነ-ጥበብ ሽልማቱን ያዘጋጀው ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት እንደሆነ የጠቀሱት ም/ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ካሁን ቀደምም በሕዝብ ተሳትፎ ት/ቤቶችና የጤና ተቋማት መሥራቱን፣ እስካሁን ማኅበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ማውጣቱን፣ ከዚህ ውጭ በስፖርት ዘርፍ ለባህርዳርና ለመቀሌ ስታዲየሞች የ26 ሚሊዮን ብር ድጋፍ፣ ለወልዲያ ስታዲየምም ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነና የኢትዮጵያን ስፖርት ለማሳደግ “ዳሽን ቢራ ስፖርት ክለብ” አቋቁመው በሁለቱም ፆታ እየተሳተፉ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ የእርሻና የኢንዱስትሪ ትስስርን ለማሳደግና የውጭ ምንዛሪን ለማዳን ከአርሶ አደር ጋር በመተባበር በቢራ ገብስ ላይ ለምርምር፣ ለምርጥ ዘርና ለሥልጠና በጀት መድበው እየሠሩ መሆኑን ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የገንዘብ አቅማቸው ደካማ (የድሃ ድሃ) ለሆኑ ሰዎች በጐንደር መኖሪያ ቤት መሥራት እንደጀመሩና በሌሎችም ስፍራ ተመሳሳይ ተግባር እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡

Read 1180 times