Saturday, 17 January 2015 10:44

መቐለ ህዝብ በሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች ሲጋራ እንዳይጨስ አገደች

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ያጨሰ 1 ሺህ ብር፣ ያስጨሰ 3 ሺህ ብር ይቀጣል

የመቐለ ከተማ አስተዳደር በመዝናኛ ስፍራዎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በሆስፒታሎችና በመሳሰሉት ህዝብ የሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች ሲጋራ እንዳይጨስ የሚከለክል ህግ ተግባራዊ ማድረጉ ተገለፀ፡፡በመዝናኛ ስፍራዎች ሲጋራ ሲያጨሱ የተገኙ ግለሰቦች ከ1 ሺህ ብር በላይ፣ ሲጋራ እንዲጨስ የፈቀዱ የመዝናኛ ስፍራዎች ባለቤቶች ደግሞ ከ3ሺህ ብር በላይ ቅጣት እንደሚጣልባቸው የጠቆመው የአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ሊደረግ የታቀደውን ይህን ህግ በስራ ላይ በማዋል መቐለ የመጀመሪያዋ ከተማ መሆኗንም አስታውቋል፡፡ህጉ ከዚህ በተጨማሪም በስታዲየሞችና ሃይማኖታዊ ዝግጅቶች በሚከናወኑባቸው ስፍራዎች ሲጋራ እንዳይጨስ እንደሚከለክል ታውቋል፡፡በወጣትነት የእድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን አንድ አስረኛ ያህሉ የሲጋራ ሱስ ተጠቂ እንደሆኑ የአለም የጤና ድርጅት መረጃ ይጠቁማል፡፡የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ ህዝብ በሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች ሲጋራ እንዳይጨስ የሚከለክልና በሲጋራ ሽያጭ ላይ ገደብ የሚጥል  አዋጅ ማጽደቁ ይታወሳል፡፡

Read 3934 times