Saturday, 10 January 2015 10:19

የገና ራሥ ኮከበ ፅባህ፤ (የንጋት ኮከብ)

Written by  ከበደ ደበሌ ሮቢ
Rate this item
(1 Vote)

ባለፈው ረቡዕ የኢየሱሥ ክርስቶስ ልደት (ገና) በኢትዮጵያውያን ክርሥቲያን ምዕመናንና  በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተከብሮ አልፎአል፡፡
ገና፡- የጌታ ልደት ነው፤ የጌታ ኢየሡሥ ክርሥቶሥ ልደት፡፡ የገና ራሥ ደግሞ ለክርሥትና ሃይማኖት መከሠትና እውን መሆን ምክንያት የሆነው በክርሥትና የመለኮት ሊቃውንት የቤተ ክርሥቲያን ራሥ የሚሠኘው ኢየሡሥ ክርሥቶሥ ነው፡፡ ኢየሱሥ ክርሥቶስ፡- አዳኝ ጌታ ብርሀን የንጋት ኮከብ…መሆኑን በእምነትም በእውቀትም መናገር ይቻላል፡፡ እርሡ ራሡ መፅሐፍ ቅዱስ ላይ፡- እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ…ይላል፡፡ በሌላ ሥፍራ ደግሞ፡- እኔ መንገድ እውነትና ህይወት ነኝ…ብሎ ራሡን ይገልፃል፡፡
ከአንድ መቶ ዘጠና ሥምንት ዓመታት በፊት በእኛ በ1809 በጥንታዊቱ ፋርሥ ወይ ፐርሺያ በአሁኒቱ ኢራን ሺራዝ ከተማ አቅራቢያ የተወለደውን በኋላ ላይ ለእግዚአብሄር መልዕክተኝነት የእግዚአብሔር ክብር በእርሡ ላይ የሚመጣውን ሁሴን ዓሊ ሚርዛ (ን)፤ ሙሥጠፋ የሚባል ባህታዊ እመንገድ ላይ አግኝቶት፡…አንተ የእውነት ብርሀን ነህ፤ አንተ የመመሪያ ፀሀይ ነህ፤ ራሥህን ለሌሎች ግለፅ…ነው ያለው፡፡
በዚህ በዛሬው ዘመን በዓለማችን ላይ ካሉ ሃይማኖቶች ሁሉ ብዙ ተከታዮች ያሉት ክርሥትና ነው፡፡ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብቻ እንኳን ከአንድ ቢሊዮን በላይ ክርሥቲያን ምዕመናን እንዳሏት ከሚያረጋግጡት ጥናታዊ መረጃዎች፡- Man Kind’s Search For God (የሠው ልጅ እግዚአብሔርን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ) በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ እና በሌሎች ሰላሳ ሶስት ቋንቋዎች የተፃፈው መፅሀፍ አንዱ ነው፡፡ የክርሥትና ሃይማኖት በተከታይ ምዕመናን ብዛት እዚህ አሀዝ ላይ ለመድረሥ ሁለት ሺህ ዓመታት ተጉዙአል፡፡ ይሄ ገለፃ:- ኢየሡሥ ክርስቶስ የተወለደው ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት መሆኑን ያሣያል፡፡ ኢየሡሥ ክርሥቶስ ሲሰቀል በምድር ላይ መቶ ክርስቲያኖች እንኳን አልነበሩም፡፡ ደቀ መዛሙርቱና ጥቁት ሴቶች ብቻ ናቸው አብረውት የነበሩት፡፡ አሁን ከአንድ ቢሊዮን በላይ ተከታይ ምዕመናን አሉት፡፡
መሰረታዊ የሆኑ የክርስትና ሃይማኖት አውደ ዓመቶች ሁሉ የኢየሱስ ክርስቶስን ህይወት ህያው ክንዋኔዎች መነሻና መድረሻ (መሰረት) ያደረጉ ናቸው፡፡ ገና፡- ልደቱ ነው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሄም በከብቶች በረት ውስጥ የተወለደበት እለት፡፡ ስቅለት፡- ስቅለቱ ነው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በጎለጎታ ጌተሰማኒ ቀራንዮ መስቀል ላይ የተሰቀለበት ዕለት፡፡ ጥምቀት፡- ጥምቀቱ ነው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ዕድሜው ሰላሳ ዓመት በሆነ ጊዜ በዮርዳኖስ ወንዝ በመጥምቁ ዮሐንስ አጥማቂነት የተጠመቀመበት፡፡ ፋሲካ፡- ትንሳኤው ነው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ከተሰቀለ ከተቀበረና ሶስት ቀናት በመቃብር ውስጥ ካደረ በኋላ ሞትን ድል አድርጎ የተነሳበት ዕለት፡፡ መሥቀል፡- ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት እውነተኛው መስቀል ያለበት ስፍራ የት እንደሆነ ፍንጭ የተገኘበት ወይም ምልክት የታየበት ዕለት ነው፡፡ ይኸውም እንዲህ ነው፡- ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ከሶስት መቶ ዓመታት በላይ ቆሻሻ ሲከመርበት ከኖረ በኋላ ንግስት እሌኒ መስቀሉን ከተቀበረበት የቆሻሻ ክምር ውስጥ ለማውጣት በችቦ ብርሃን ታግዛ በትክክል፤ መስቀሉ ያለበትን ስፍራ ለማወቅ ፍለጋዋን ጀመረች፡፡ መስከረም አስራ ሰባት ቀን የችቦው ጭስ ሽቅብ ወደ ሰማይ ወጣ፤ ከዚያም ቁልቁል ወደ ምድር ከተመለሰ በኋላ ሰገደ፡፡ ንግስቲቱ ጭሱ የሰገደበትን ስፍራ ማስቆፈር ጀምራ አንድ መቶ ሰባ ሁለት ቀናት ከፈጀ ቁፋሮ በኋላ መጋቢት አስር ቀን መስቀሉ ተገኘ፡፡
ከክርስቶስ ልደት በፊት ታህሳስ ሃያ ዘጠኝ ቀን የተወለዱ አዱኒስን ወይንም አዱንያስን የመሳሰሉ ሌሎች ኃያላት መኖራቸውን ዳቪንቺ ኮድ የተሰኘው መፅሀፍ በገፆቹ አስፍሮአል፡፡ እንዲሁም ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከዘጠኝ መቶ ዓመታት በፊት የኖረውና ከአንድ ድንጋይ ከአስራ አንድ ያላነሱ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ያነፀው ኢትዮጵያዊው ቅዱስ ንጉሥ ጠቢብ ላሊበላ የተወለደው በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የልደትቀን ነው፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ፡- ፍፁም ሰው፤ ፍፁም አምላክ ነው … ይላል ክርስቲያናዊ የመለኮት እውቀት፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በኖረባቸው ዓመታት መለኮታዊ ክብሩን፤ አምላካዊ ባህሪውን የሚገልፁ በርካታ ተግባራት አከናውኖአል፡፡ አጋንንትን ማውጣት የሞተውን ማስነሳት ፈውስ ተአምራት … እነዚህና የመሳሰሉት የመለኮታዊ ክብሩ ሰብዕና ገላጮች ናቸው፡፡ በጎነት ፍቅር፣ እውነት፣ ርህራሄ፣ ደግነት፣ ቅንነት፤ ግልፅነት፣ ቀጥተኝነት፣ ቅድስና፣ ንፅህና … እነዚህና የመሳሰሉት ደግሞ የአምላካዊ ባህሪው ነፀብራቆች ናቸው፡፡ ክርስቲያኖች እግዚአብሄር ሰውን በአምሳሉ ፈጠረው … ሲሉ፤ ከባህሪው አጋራው ማለታቸው ነው፡፡ ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ ሁለት ቁጥር ሰባት ላይ፡- እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ከጭቃ አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የህይወትን እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ህያው ነፍስ ያለው ሆነ … ይላል፡፡ ከእግዚአብሔር የወጣው ወደ ሰው ገባ ማለት ነው፡፡ እርሱም የእግዚአብሔር ባህሪ ነው፡- ህያውነት፣ እውነት፣ እውቀት፣ በጎነት፣ ደግነት፣ ርህራሄ፣ አዛኝነት እና የመሳሰሉት፡፡ ትንቢተ ኤርሚያስ ምዕራፍ አንድ ቁጥር አምስት ላይ፡- በሆድ ሳልሰራህ አውቄሃለሁ፤ በማህፀን ሳለህ ቀድሼሃለሁ፤ በህዝብ ላይ ነቢይ አድርጌ ሾሜሃለሁ … ሲል፡- በዚህ ማህፀን ውስጥ ከመፀነስህ በፊት በእኔ ውስጥ ህያው ሆነህ ነበርክ ማለቱ ነው፡፡
*          *          *
ዘኬዎስ ቁመቱ በጣም አጭር የሆነ ቀራፂ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን ለማየት ፈልጎ ቁመቱ አጭር ከመሆኑ የተነሳ መሲሁን የሚከተሉት ብዙ ህዝቦች እንዳይጋርዱት ኢየሱስን ለማየት ይቻለው ዘንድ ዛፍ ላይ ወጣ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በዚያ ሲያልፍ፡- ዘኬዎስ ብሎ ጠራው፡፡ ና ከዚያ ዛፍ ላይ ውረድ፤ እኔ ዛሬ በአንተ ቤት ምሳ እበላለሁ … አለው፡፡ ዘኬዎስ እንደዚያን ቀን ተደስቶ አያውቅም፡፡ እርሱ የፈለገው፡- ኢየሱስን ለማየት ነው፤ ኢየሱስ ግን ዛሬ ከአንተ ጋራ እሆናለሁ … አለው፡፡ ዘኬዎስ እንደ ህንቦቃቅላ ህፃን እየፈነደቀ፡- ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል … አለ፤ የተበደርኩት እንኳ ቢኖር አራት እጥፍ አድርጌ እከፍላለሁ ….፡፡ የዘኬዎስ መሻት፡- ኢየሱስን ማየት ሆኖ ሳለ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ምሳውን ከዘኬዎስ ጋር በዘኬዎስ ቤት ለመብላት ፈቀደ፡፡ ዘኬዎስን አከበረ፡፡ እናም ወደ ዘኬዎስ ቤት ገባ፡፡ የዘኬዎስን የልብ መሻት አይቶ እርሱ ደግሞ ይበልጡን አብዝቶ አከበረው፡፡ በዚህም ለዘኬዎስና ለቤቱ መዳን ሆነለት፡፡
በዚህን ጊዜ አንዲት ሴት ተንደርድራ ወደ ዘኬዎስ ቤት ገባችና በብልቃጥ የተሞላውን አልባጦሮስ ሽቶ ብልቃጡን ሰብራ ኢየሱስ ክርስቶስ እግር ላይ አፈሰሰችው፡፡ መጫሚያውን ደስ የሚልሽቶ ቀባችው፡፡ እግሮቹ ላይ ተደፍታ እንደ ጥቁር ወርቅ በሚንተገተግ ውብ ፀጉሯ እግሮቹን አበሰች …፡፡ የዚህችን ሴት ሁለንተናዊ አድራጎት የተቃወመውን አንድ ሰው፤ ኢየሱስ፡- ተው! … አለው፡፡ አንተ ለእግሬ ውኃ አልሰጠኸኝም፤ እርሷ ግን እግሮቼን በሚያውድ ሽቶ አበሰች…
ብዙ ሺህ አጋንንት ሰፍረውበት በመቃብር ቤት ውስጥ ጠላት ዲያቢሎስ እያጎሳቆለው የሚኖር ሰው አለ፡፡ ልክ ኢየሱስን እንዳየው በላዩ ላይ የሰፈሩት ሺህ አጋንንት መታወክ እና መንጫጫት ጀመሩ፡፡ ወደ ገደል እንዳትከተን ሲሉ … ኢየሱስን ለመኑት፡፡ ከኢየሱስ ክርስቶስ ሁለንተና እና ከዓይኖቹ ውስጥ የሚወጣው ኃይል ወደ ሰውዬው በገባ ጊዜ፤ ከሰውዬው ውስጥ አጋንንት መውጣትጀመሩ፡፡ ሂዱ ከዚህ ሰው ውጡና ወደነዚያ አሳሞች ግቡ … ብሎ ኢየሱስ ክርስቶስ በኃይል ገሰፃቸው፡፡ አጋንንቱ ሰውዬውን በለቀቁት ጊዜ ፊቱ በደስታ ነደደ፤ ተፍለቅልቆ በራ ….፡፡ የዓሳማው መንጋ በአጋንንቱ ታመሰ፡፡
አንድ፤ ልጅ የታመመበት መቶ አለቃ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መጣና፡- ልጄ ታሞአል፤ አንተ ብቻ ቃልህን ልቀቅ፤ ልጄ ይድናል! … አለው፡፡ ኢየሱስም፡- በሰላም ወደ ቤትህ ሂድ፤ ልጅህን ድኖ ታገኘዋለህ፤ እምነትህ አድኖሀል … ሲል መለሰለት፡፡ የመቶ አለቃው ቤቱ ሲደርስ ልጁ ከደዌው ተፈውሶ እንደ እንቦሳ ጥጃ ሲፈነጭ አገኘው፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ከስፍራ ስፍራ በብዙ አጀብ ሲንቀሳቀስ አንዲት አስራ ስምንት ዓመት ሙሉ ባለማቋረጥ ደም ሲፈስሳት የኖረች ሴት በአጀቡ መሃከል ተጋፍታ ጨርቁን ነካች፡፡ ሲፈስሳት የኖረው ደም ወዲያውኑ ቀጥ አለ፡፡ መፍሰሱን አቆመ፡፡ የአሥራ ስምንት ዓመት ደዌ በቅፅበት ተመታ፡፡ ቀጥ፡፡ በዚህን ጊዜ ኢየሱስ ማነው የነካኝ … አለ፡፡ ማንም አልነካህም … አሉት፡፡ ኃይል ከእኔ ወጥቷል … የነካኝ ሰው አለ፤ አላቸው፡፡
ኢየሡሥ ክርሥቶስ በቤተመቅደስ በማስተማር ላይ እያለ፤ አይሁድ፡- ጋለሞታ ናት…ያሏትን ሴት ትልልቅ ጓል ይዘው ሢያሣድዷት ሴትዮይቱ እየሸሸች ወደ ቤተመቅደሡ ገባች፡፡ ጓል ይዘው የሚያሣድዷትም ሠዎች ተከትለዋት ገቡ፡፡ ኢየሡሥ ክርስቶስ የሆነውን ሁኔታ ሁሉ አጢኖ ጐንበሥ ብሎ ምድር ላይ ፃፈና ሴትዮይቱን ወደ ተከተሉት ጓል የያዙ አሣዳጆች እያየ፣ ከናንተ መሃከል ንፁህ የሆነው ሠው በዚህች ሴት ላይ የመጀመሪያውን ጓል ይወርውር…አላቸው፡፡
በዚህን ጊዜ አሣዳጆቹ ከኋለኞች እስከ ፊተኞች ፊታቸውን አዙረው መሠሥ ብለው ከቤተመቅደሱ እየወጡ ሄዱ፡፡ ሴትዮይቱ ብቻዋን ቆማለች፡፡ ኢየሡሥ፡- አንቺ ሴት እምነትሽ አድኖሻል፤ ደግመሽ እንዳታጠፊ፤ በሰላም ወደ ቤትሽ ሂጂ…ብሎ አሠናበታት፡፡
እነዚህ እስከዚህ የቀረቡት መወሣቶች የሚገልፁት ከኢየሡሥ ክርስቶስ መለኮታዊ ክብሮችና አምላካዊ ባህሪያት መገለጫ የሠብዕና ክፍሎች ጥቂት ሠበዞች የመምዘዝ ያህል ነው፡፡
*        *       *
ለአገሬ ለኢትዮጵያ ክርስቲያን ምዕመናን፤ ለመላው ኢትዮጵያውያን እና ለመላው ዓለም ክርስቲያኖች ያለኝን የሚደነቅ ፍቅር በተጌጠ ክብር ለመግለፅ፤ እንኳን ለዘንድሮው የገና በዓል በሠላም አደረሰን ለማለት፡፡ ለብርሃን ክብር፤ ለኢየሡሥ ክብር፤ ለክርሥትና ክብር፤ ለአምላክ ክብር፤ ለኢትዮጵያ ክብር፣  ለህዝቦች ክብር፤ ይህ ተፃፈ፡፡ እነሆ፡- የገና ራሥ፡፡
ሠላምዎ ይብዛ! በፍቅር!
Soli Deo! Gloria!  
 

Read 2368 times