Saturday, 10 January 2015 10:12

“እየሄዱ መጠበቅ” በወፍ በረር

Written by  ሱለይ አዳም
Rate this item
(3 votes)

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጦርነቱን መግለጽ የሚችል የሥነ-ግጥም ውድድር ተካሂዶ ነበር፡፡ አያሌ ገጣምያንም በቋንቋ ውበት የተራቀቁበትን አያሌ ቅኔያት ዘረፉ፡፡ ብዙ ሺ ታዳሚያን በተሰበሰቡበትም ዳኞች ተሰይመው… ግጥሞችን መፈተሽ ያዙ፡፡ ገጣሚ “ያሸንፍልኛል” ያለውን ግጥም እየያዘ መድረኩን ነገሰበት፡፡ ሶስት አሸናፊዎች እኩል በመውጣታቸው እነሱን መለየት ግድ ሆነ፡፡ ስለዚህ ተጨማሪ ግጥሞች እንዲያቀርቡ ተደረገ፡፡ ቅፅበታዊ በነበረው የመለያ ውድድር አንዱ ባለቅኔ አሸነፈ፡፡ ግን እንዴት?
አንደኛው ተወዳዳሪ ያቀረበው ግጥም ከሌሎቹ የተለየ ነበር፡፡ ማይክራፎኑን ይዞ የመድረኩ መሀል ላይ ዝም ብሎ ቆመ፤ ትንፋሹ እንኳን አይሰማም፡፡ ይኼኔ ታዳሚው መበሳጨት ጀመረ … “ምን እንደ ጅብራ ይገትረዋል… ግጥሙን አያነብም?!” አለ፡፡ እሱ ግን አሁንም ዝም እንዳለ ነው … ጉርምርምታዎች ሲበዙ … ከዳር እስከ ዳር የከባድ መሳሪያና መብረቅ ቅልቅል የሚመስል ድምጽ በማይክራፎኑ ለቀቀበት … “ዷ! ዷ! ዷ!” የታዳሚዎቹ ቀልብ ተገፈፈ … ደነገጡ፡፡ ለጆሮ ታምቡር የከበደ ጩኸት ነበር፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ከመጀመሪያው ባነሰ ሰዓትና ድምፅ ሁነቱን ደገመው፡፡ ከዚያም ለሶስተኛ ጊዜ ባነሰ ድምፅ ደገመውና መድረኩን ለቀቀ፡፡ አሸናፊ ሆኖም ሽልማቱን ታቀፈ፡፡
አንድ ገጣሚ ከሌላው የሚለየው በፈጠራ ክህሎቱ፣ በሐሳብ ልቀቱ፣ በቋንቋ እርቀቱና አርቅቆቱ ነው፡፡ ገጣሚ በላይ በቀለ ወያ “እየሄዱ መጠበቅ” በተሰኘው የግጥም መድበሉ መግቢያ ላይ የግጥምን ምንነት በተመለከተ ምርጫዎች ይሰጠናል፡፡ ሁሉም ምርጫዎች ግን “ግጥም በቃ ግጥም ነው!” የሚል አንደምታ ያላቸው ናቸው… ይህ የእሱ አተያይ ነው፡፡
የአይናችንን ሥርዓተ እርግብግቢት … የልባችንን ሥርዓተ ምት… ብናስተውል፣ ረቂቅና ቅንብሩም ከጥበብ በላይ የሆነ ኃይል ያለው ነው፡፡ ጥበብ ከመጋረጃ ጀርባ ያለን የተደበቀን ምሥጢር ፈልፍሎ የሚያወጣ… የተሰወረን አዚም ማርከሻ የሚቆፍር .. የጠፋን መንገድ የሚጠቁም … ሁሌም የሚኖር ሕያው ጉልበት ነው፡፡ ጎበዙ ገጣሚ ቴዎድሮስ ፀጋዬ፤ በ“ነፍሰጡር ስንኞች” የግጥም መድበሉ  “ባለፀጋው” በሚል የከተባት ግጥም እንዲህ ታትታለች …
ባለጸጋው
ትንሽ ሰጥቶ
ብዙ አትራፊ
ነጋዴ እኮ ነው ገጣሚ፣
ለሚጭረው ጥቂት ስንኝ
ቢሊዮን አይነት ፍቺ የሚሰጥ ስላለው እልፍ ተርጓሚ፡፡
ለአንዲት ግጥም አንባቢያን እልፍ ትርጓሜ ሊሰጧት እንደሚችሉ ሲነግረን ነው፡፡ ባለቅኔና ጸሐፌ ተውኔት ጋሼ መንግስቱ ለማ ደግሞ፤ “ሸጋ ግጥም ጥሩንባ አያሻውም፤ ባይሆን ትሬንታ-ኳትሮ እንጅ!” ብለው ኳኳቴ በበዛበት ቦታም ጥሩ ግጥም ጆሮ ጎትቶ ስሙኝ እንደሚል አስረግጠዋል፡፡
ወደ ድግሳችን ስናመራ፣ በግጥም መድበሉ ላይ የማቀርበው የግል ምልከታዬን እንደሆነ ከወዲሁ  ለመግለፅ እሻለሁ፡፡ “እየሄዱ መጠበቅ” ከሚለው  ርዕስ እንጀምር፡፡ “እየሄዱ መጠበቅ” ማንን? ለምን? የት ድረስ? ምን ያህል ጊዜ? ገደቡስ? እኒህን ጥያቄዎች ይዤ የሽፋኑን ምስል ስመለከት በግራ በኩል ተጠቅልሎ የተኛ ድርብ ቀለም ያለው እባብ የሚመስል የጫማ ገመድ፣ መሃል ላይ ደግሞ እግሩን አንቧትሮ እርምጃ የሚቆጥብ ሰው የመሰለ የተጠላለፈ የጫማ ገመድ አስተዋልኩ፡፡ ሆኖም “እየሄዱ መጠበቅ”ን የሚያህል ሀሳብ በዚህ ምስል ተገልጧል አልልም፡፡ ለወደፊቱ ስዕሉ ቢቀየር የሚል ሃሳብ አለኝ፡፡
46 ግጥሞች የያዘችው “እየሄዱ መጠበቅ”፤ በ65 ገጾች ትጠናቀቃለች፡፡ “ማነው?” ባዩ የመጀመሪያው ግጥም ሲሆን “ማነው ደግሞ ዛሬ ጀምበር ከጠለቀች ከደጃፌ ቆሞ በሬን የሚመታ/ትሆን እንደሆነ፣ የፀባዎት ጌታ” በማለት ይጀምራል፡፡ የበሩ መንኳኳት “ርቦኝ ቤትህ መጥቼ አላበላኸኝም… ጠምቶኝ ቤትህ መጥቼ አላጠጣኸኝም” ከሚለው የእምነት ሃሳብ ጋር የተቆራኘ ይመስለኛል፡፡
“ደግሞስ እስኪ አስበው፤ ሎሌ ሆነው ሳሉ፣
ምን ይሉት ድፍረት ነው፤ በሻገተ እንጀራ ጌታን መቀበሉ፣” …
ሁለተኛዋ ግጥም ከማጠሯ መጐጠሯ…ዓይነት ናት… “የኋላው ባይኖርም … ” ትሰኛለች፡፡ በፈጣሪ ቁጣ የምትጠፋን ሀገር
እየዞሩ ማየት ጥፋት እንደነበር
 ሲነገር የሰማ ቤተሰቡን ይዞ
እንደሎጥ ያለ ሰው ከጥፋት ይድናል የኋላውን ሳያይ
ወደፊት ተጉዞ (ገፅ 10…)
ለማምለጥ ወደፊት መራመድን ጮሃ የምትጣራ ውድ ግጥም ናት!!
ሶስተኛዋ መንቶ ግጥም “እሱ እየሻከረ…” ትላለች፡፡ ይህ ደግሞ ሞረድ ወትሮስ ለስላሳ ነበርን? ብዬ እንድጠይቅ አስገድዶኛል … ባይሆን ሌሎችን ለመሳል ሲል አካሉ እየተሸራረፈ እየለሰለሰ ሊሄድ ይችላል፡፡ የተወጠረበት ሃሳብ ቢስተካከል (በእኔ እይታ) ብዙ ግጥም ነች!
“የአንዱ ሰው ህይወት ሞረድን ይመስላል
እሱ እየሻከረ ሌላውን ይስላል … ትላለች፡፡
“ተረትና ምሳሌ” (ገጽ 17) የምትለዋ ግጥም ምርጥ ናት፡፡ እንዲህ ያለግጥም ሺህ ቢገጠም ማንስ ይጠላና!
ሞኝና ወረቀት
የያዘውን አይለቅ ለሚባለው ተረት
ምሳሌው እኔ ነኝ
አንቺን ብቻ ይዤ የያዘኝን ሁሉ የማልመለከት፡፡
ቀጣዩዋ ግጥም የመጽሐፉ የጀርባ ሽፋን ላይ የሰፈረች ስትሆን ብቻዋን መጽሐፍ የመሆን አቅም ያላት ናት፡፡ “ፍጥነትና ነጻነት” ትላለች፡፡
አልጋ ባልጋ ሆኖ የጥንቸሎች ፍጥነት፤
ፍጥነት ከተባለ፣
በዔሊዎች ጫንቃ፤ ራሱን ያልቻለ፤
ግዙፍ ድንጋይ አለ…
(ስርዐተ ነጥብ ከራሴ) ራሱን መቻል ያቃተው ድንጋይ ምንድነው? ኤሊን ተጭኖ ምን አምጪ እያላት ይሆን? እነጥንቸል፤ እንደ ኤሊ ድንጋይ ቢጫናቸው ምን ይገጥማቸው ነበር? በሳል … ፍልስፍናው ተፈልፍሎ የማያልቅ ግጥም  ነው፡፡ የዘመን ፍዳ ትከሻውን ያጎበጠው ሰውን ምስል ይከስታል፡፡
“የወረኞች ወሬ” የምትለዋ ግጥም ጭራሽ ባትካተት ጥሩ ነበር … እንደነ “አበሻ ቀጠሮ”ን፣ “እንቅልፍና ንጉሥ”ን መከተብ የቻለ ብዕር፤ “የወረኞች ወሬ”ን መፃፉ “የባለቅኔ ብዕር ዥንጉርጉር” ያሰኛል፡፡ “እንቅልፍና ንጉስ” የሚለውን ግጥሙን እንየው፡-
የደቀ መዛምርቱ መሪ በታንኳ ላይ ሳለ
ክርስቶስ ላፍታ ተኝቶ
አልቀው ነበር ባይቀሰቅሱት
ሞገድ
ማዕበል ተነስቶ
ለካስ ላፍታ ያህል ንጉስ ካንቀላፋው
ቀስቃሽ ሰው ከሌለ ህዝብ ነው ‘ሚጠፋው፡፡
የመጨረሻው ገጽ ላይ ያለችዋ “የሐበሻ ቀጠሮ” የተሰኘች ግጥምም ጥልቅና ድንቅ ናት፡፡
ከዚህ ውጭ ያለውን እንግዲህ እናንተው ተወጡት፤ በግጥሞቹ ተብሰልሰሉበት፡፡
(አዘጋጁ፡- ከዚህ በላይ የቀረበው የግጥም መፅሃፍ ቅኝት፣ በማህበራዊ ድረገፅ ላይ በወጣ ውድድር በአንደኝነት አሸንፎ የተሸለመ መሆኑን ጠቅሰው አዘጋጆቹ የላኩልን ነው፡፡ ፅሁፉ በዝግጅት ክፍሉ የአርትኦት ስራ ተደርጎለት የወጣ ነው)

Read 2995 times