Saturday, 10 January 2015 09:50

ምርጫ ቦርድ፤ ሰማያዊ ፓርቲ ይቅርታ እንዲጠይቀው አሳሰበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

ፓርቲው ይቅርታ የሚያስጠይቅ ስህተት አልፈፀምኩም ብሏል
 
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፤ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫ በሚሰጥ የገንዘብ ድጋፍ ድልድል ዙሪያ ያዘጋጀሁትን የምክክር መድረክ ለመበተን ሙከራ አድርጓል ያለውን ሰማያዊ ፓርቲን ይቅርታ እንዲጠይቅ ያሳሰበ ሲሆን ፓርቲው በበኩሉ፤ ይቅርታ የሚያስጠይቅ ስህተት ስላልፈፀምኩ ይቅርታ አልጠይቅም ብሏል፡፡
ቦርዱ ታህሳስ 28 ቀን 2007 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ሰማያዊ ፓርቲ ቦርዱ ለፓርቲዎች በሚሰጥ ገንዘብ ላይ ለመመካከር የጠራቸውን ሁለት ስብሰባዎች ያለአግባብ ረግጦ መውጣቱ ስህተት እንደሆነ መገምገሙን አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም ፓርቲው የቦርዱን ስም የሚያጎድፍ ዘለፋና በሃሰት የመወንጀል ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን የጠቀሰው የቦርዱ መግለጫ፤ ከቦርዱ እውቅና ውጪ የሆነ “ትብብር” የሚባል አደረጃጀት መስርቻለሁ እያለ ህገወጥ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝም ጠቁሟል፡፡
ይህ መሰሉ የፓርቲው እንቅስቃሴ የነፃና ፍትሃዊ ምርጫ አካሄድን እንደሚጎዳ የጠቆመው ቦርዱ፤ ፓርቲው እስከ ፊታችን ሰኞ ድረስ በፅሁፍ ይቅርታ እንዲጠይቀው አሳስቧል፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡን የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ፤ ፓርቲው ስብሰባ ረግጦ ወጥቷል የተባለውን በተመለከተ ሲመልሱ፤ “ስብሰባ ረግጠን የወጣነው  አሳማኝ ምክንያት ይዘን ነው” ብለዋል፡፡ “ስብሰባ ረግጦ መውጣት ደግሞ በየትም ሃገር ያለ አካሄድ ነው፣ ያልተስማማንበትን ጉዳይ አስቀምጠን ወጥተናል፤ በዚህም የፈፀምነው ስህተት የለም” ብለዋል፡፡
ፓርቲው ዘለፋና የስም ማጥፋት ፈፅሟል በሚል በቦርዱ የቀረበበትን ውንጀላ እንደማይቀበሉት የተናገሩት አቶ ዮናታን፤ ፓርቲያቸው ነቀፋ እንጂ ዘለፋ ፈፅሞ እንደማያውቅ ጠቁመው መንቀፍ ደግሞ መብት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

Read 2227 times